የሰው ልጅ ለሶስቱ ሕጎች እየተገዛ ሊኖር ግድ ይለዋል። ለሕገ-ልቦና፣ ለሕገ-እግዚአብሔር /ፈጣሪ/ እና ለሕገ-መንግሥት። ለሕገ-ልቦና/ለሕሊና ተገዢ መሆን ተፈጥሯዊ ጸጋ ነው። ሰው መጥፎ ነገር ከማድረግ ይልቅ ጥሩ ነገር በመሥራት ለህሊና ዳኝነት የሚገዛበትና የሞራል ልዕልናውን ከፍ የሚያደርግበት ውስጣዊ እሳቤ ነው። አባቶቻችን ‹‹ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፤ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም››የሚሉትም ለዚህ ነው።
ሕገ-እግዚአብሔር/ፈጣሪ የምንለው ደግሞ ሰው እንደየሃይማኖቱ አስትምህሮ የጽድቅ አክሊልን ለመቀዳጀት ሲል የፈጣሪን ትዕዛዝ ወይም ሕግ የሚያከብር መሆኑን የሚገልጽ ነው። ለምሳሌ፡- አትግደል፣ አትስረቅ አታመንዝር የሚለው የእግዚአብሔር ቃል ፈጣሪን በሚያመልክ ሰው ዘንድ ክቡር ነው።
ሕገ-መንግሥት የምንለው ደግሞ ሰዎች ማህበራዊ ሕይወትን ከመሰረቱ በኋላ አኗኗራቸውን ሥርዓት ለማስያዝ በስምምነት የሚጸድቁት የጋራ መተዳዳሪያ ደንብ ነው። በዚሁ መሰረት በህግ አርቃቂ፣ በሕግ ተርጓሚና በሕግ አስፈጻሚዎች ቅንጅታዊ አሠራር ተግባራዊ ይሆናል። ሕገ-መንግሥት በሕገ-ልቦና እና በሕገ-እግዚአብሔር መመለስ ያልቻሉ ሰዎችን ከሕገ- ወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያደርጋል፤ አደብ ያስገዛል።
አሁን በመዲናችን እየታየ ያለው ሕገ-ወጥነት ሶስቱንም የህግ እርከኖች ያለፉ ይመስላል። ሰዎች ሞራል አጥተዋል፤ ፈሪሃ እግዚብሔርም፣ ፈሪሃ መንግስትም አይታይባቸውም። በዛሬው ቅኝታችን ለመመልከት የምንሞክረው በጫኝና አውራጅ ስም እየተደራጁ ህገ- ወጥ ተግባራትን የሚፈጽሙ ሰዎችን ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ትኩረትን የሚስቡ ሕገ-ወጥ ተግባራት እያሉ እንዴት ጫኝና አውራጆች ላይ ይተኮራል እንዳትሉኝ። እርግጥ ነው ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ፣ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ የሚያደርጉ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች፣ መኪና ከነነፍሱ ሠርቀው የሚሰወሩ ሌቦች፣ በሙስናና በብልሹ አሠራር የተዘፈቁ የመንግሥት ባለስልጣናት እና ሌሎችም እንዳሉ ይታወቃል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፤ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና እግር ጥሏቸው ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን ካማረራቸው ጉዳይ አንዱ በየጎዳናውና በየመንደሩ እቃ ማውረድና መጫን የምንችለው እኛ ብቻ ነን በሚል በግለሰብ ንብረትና በግል ኪስ የሚያዙ ሕጋዊነትን ሽፋን አድርገው ሕዝብን ስለሚያሰቃዩ ግለሰቦችና ቡድኖች ስለመኖራቸው ለማንሳት ነው።
እቃ ማውረድና መጫን እንደ አንድ የሥራ ዘርፍ መታየቱ ባልከፋ። ድንገት መኪና ቆም ብሎ ተሳፋሪን ለማውረድ ሲሞክር ከእረዳቱ ቀድመው መኪና ላይ የሚንጠለጠሉ በየአካባቢው እየተበራከቱ መጥተዋል። ያለባለቤቱ ፈቃድ አስር ኪሎ ግራም የማትሞላ ቋጠሮ ወይም ሻንጣ ብጤ ሁለትና ሶስት ሰው ሆነው ተቀባብለው ካወረዱ በኋላ የሚጠይቁት ገንዘብ እቃው ቢሸጥ እንኳ የማያውጣው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በዚህ ላይ እራሴ አወርደዋለሁ ወይም እጭነዋለሁ ለሚል ሰው እድል አይሰጡም።
ቀደም ሲል መናኸሪያዎች አካባቢ የሚታየው እንዲህ አይነቱ ድርጊት አሁን በየጎዳናውና በየመንደሩ የሚታይና ሰዎችን ያማረረ ጉዳይ ሆኗል። በሕጋዊነት ስም ከለላ የተሰጣቸው እነዚህ ጫኝና አውራጆች የሚፈጽሙት ዘረፋ በራሱ ላይ ደርሶ ወይም በሌሎች ላይ ሲፈጸም አይቶ ከተማችን ወዴት እየሄደች ነው? ለምን ሕግ የሚያስከብር አካል ጠፋ? የማይል የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ይኖራል ተብሎ አይገመትም።
አንድ መንገደኛ እቃ ይዞ ሲጓዝ ለማስጫኛና ለማውረጃ የሚበቃውን ገንዘብ ተምኖ መያዙ አይቀርም። ድንገት እቃውን ወርረው የያዙ ጫኝና አውራጅ ነን ባዬች ያልጠበቀውን ገንዘብ ሲጠይቁት ዝም ብሎ ሊሰጣቸው አይችልም። በዚህ የተነሳ አላስፈላጊ አምባ ጓሮ ይፈጠርና በገዛ ንብረቱ ስድብና መንጓጠጥ፤ እልፍ ሲልም ቡጢ ሊቀምስ ይችላል። ይህ ሁሉ የሚሆነው ደግሞ ደንብ አስከባሪዎችና ፖሊሶች በቅርብ ርቀት ላይ እያሉ ነው። አንዳንዶች አይተው እንዳላየ ሲሆኑ አንዳንዶቹም ሕገ-ወጥ ተግባር የፈጸመውን አካል ሥርዓት ማስያዝ ሲገባቸው ተስማሙ ብለው ሊያደራድሩ ይሞክራሉ። ይህ ሲታይ ሥርዓት አስከባሪዎቹ ከሕገ-ወጡ ቡድን ጋር የጥቅም ትስስር አላቸው እንዴ? ብለን እንድንጠራጠር ያደርገናል።
የቤት ኪራይ ዋጋ 500 ብር ሲጨምርባቸው በቅናሽ ዋጋ ቤት አግኝተው እቃ ጭነው የሚሄዱ ሰዎች የሚደርስባቸው ወከባና እንግልት ደግሞ ከዚህም የከፋ ነው። በማያውቁት መንደር በጎረምሶች ተከበው እስከ አምስት ሺህ ብር እንዲከፍሉ ሲጠየቁ ምነው ጭማሪውን ከፍዬ እዚያው በተቀመጥኩ የሚሉ ብዙዎች ናቸው።
ይህ ችግር እዚህ ድረስ የደረሰው በተቆጣጣሪ አካላት ድክመት፣ ወይስ ህዝብና መንግሥትን ለማገልገል ቃል የገቡት የጸጥታ ሃይሎች ለዘብተኝነት? ወይስ እነዚህና ሌሎችም ጉዳዩ ከአቅማቸው በላይ ስለሆነ ነው? ምንም ይሁን ምን ግን እንደዋዛ የሚታዩትና ትኩረት የሚነፈጋቸው ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እያደጉ ሄደው የከተሞችን ብሎም የአገርን ገጽታ እንዳያበላሹ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ሰዎች ወጥቶ መግባት ወይም ንብረትን ይዞ መንቀሳቀስ ሥጋት ሆኖባቸዋል። ኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባ እንደ ደቡብ አፍሪካ ሕገ-ወጦች የሚነግሱባት አገር ከሆነች የዲፕሎማት ከተማ ሆና የመቀጠሏ ነገር አጠያያቂ እንዳይሆን ከወዲሁ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
አንዳንድ ጊዜ ፖሊሶች፣ ደንብ አስከባሪዎችና የጸጥታ ኃይሎች ሕግ ለማስከበር እላፊ ሲሄዱ ይታያል። ለምሳሌ፣ የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ የሚካሄድ ከሆነ ስብሰባው ከማደረጉ በፊት ጎዳናዎች ሥነ ሥርዓት እንዲይዙ ይደረጋል። ሕገ-ወጥ የጎዳና ላይ ቤት፣ ሕገ-ወጥ ባለታክሲ፣ ሕገ-ወጥ ነጋዴ፣ የመኪና ሌባ፣ ሞባይል መንታፊ እንዲኖሩ አይፈለግም። ሌላው ቀርቶ ሊስትሮዎች፣ ቆሎ ነጋዴዎች፣ ሶፍትና ማስቲካ ሻጮች አስፋልት ዳር ዝር አይሏትም።
ከዚህ ውጭ ግን ጫኝና አውራጅን፣ የታክሲ ወረፋ አስያዥ ነን እያሉ ህብረተሰቡን የሚያሰቃዩ አደብ እንዲገዙ ሲደረጉ አይታይም። በተለይ በትራንስፖርቱ ዘርፍ የሚታየው ሕገ-ወጥነት ዓይን ያፈጠጠ ነው። የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ጉዳይም ከዚህ ተለይቶ የሚታይ አይደለም።
የአምስት ብር ታሪፍ የሚከፈልበትን መንገድ አስር እና አስራ አምስት ብር እያስከፈሉ ጥቅም የሚጋሩ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። በዚህም ላይ ሁለት ሰው የሚቀመጥበት ወንበር ሶስት ሰው እንዲይዝ ይደረጋል። ትንሽ መሸት ሲል ደግሞ ሁኔታዎቹ ከሚባለውም በላይ የከፉ ይሆናሉ። ታዲያ ሕግ የሚከበረው መች ነው? ታላላቅ እንግዶች ወደ አገራችን ሲመጡ ብቻ ነው? የፖለቲካ ጉዳዮች እየገነገኑ መጥተው ለአገር ስጋት እስከመሆን የሚደርሱት እንዲህ አይነት ማህበራዊ ችግሮች አስቀድመው ባለመፈታታቸው ነውና የሚመለከተው አካል የሕግ የበላይነት እንዲከበር በናፍቆት እየጠበቀ ላለው ህዝብ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ማሳሰብ እንፈልጋለን።
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11 /2014