(የመጨረሻ ክፍል – ከዓርብ እትም የቀጠለ)
በዚሁ ሳምንት በእለተ ሐሙስ እና ዓርብ እትሞች በተከታታይ ባስነበብኋቸው መጣጥፎች፤ ሰሞነኛውና አስደንጋጩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የጥናት ግኝት ላይ ተመርኩዤ ሕወሓት በዘር ማጥፋት ጥርሱን የነቀለ ወንጀለኛ የሽብር ቡድን ቢሆንም ይሄን ማንነቱን በልኩ ባለማጋለጣችንና ባለማሳወቃችን እውነትን ታቅፈን መቅረታችንና በዲፕሎማሲውም ሆነ በሚዲያው ብልጫ እንደተወሰደብን በቁጭት ገልጬ ነበር። በዛሬው የመጨረሻ ክፍል መጣጥፌም ካቆምሁበት የምቀጥል ሆኖ፤ ከዚያ በፊት ግን ሰሞኑን የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ድፍረት የተሞላበት፣ አስደንጋጭና ተስፋ መቁረጥ የተንጸባረቀበት ክስ አይሉት ፍረጃ ምዕራባውያን ላይ ደርቷል። ምዕራባውያን ለዩክሬን የሰጡትን ትኩረት ያህል ለትግራይ ያልሰጡት ዘረኞች ስለሆኑ ነው ማለቱን “ዘ-ጋርዲያን” ዘግቧል።
ምዕራባውያን ለቆዳቸውና ለስጋቸው እንደሚያደሉ ሳይታለም የተፈታ ጥሬ ሀቅ ነው። ዘረኝነትን በገዛ ዜጎቻቸው ሳይቀር እንደሚያራምዱ ጸሐይ የሞቀው የአደባባይ እውነት ነው። ይሄን ራሳቸውም ያምናሉ። ጆ ባይደን በዚያ ሰሞን ዘረኝነት በአሜሪካ ተቋማዊ መሆኑን ያለምንም ማቅማማት ተናግረዋል። እጁ በዘረኝነት ደም የጨቀየው ሕወሓት፣ ከሳሽ ሆኖ ሲመጣ ግን ጋዜጠኛ ሔርሜላ ሰሞኑን በቲዊተር ገጿ እንዳለችው ምጸት፣ ልግጫና ሾርኔ ይሆናል።
የጥቁሩ አፓርታይድ ሕወሓት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆነው ዶ/ር ቴዎድሮስ ግን ስለ ዘረኝነት የማውራት ምንም አይነት የቅስም ልዕልና የለውም። አገዛዝ ላይ ለመቆየት አገራችንን በዘር ከፋፍሎ ሲያባላ የኖረ፤ የማንነት፣ የጥላቻና የልዩነት ፖለቲካ ሲጎነቁል የኖረ፤ አንድን ብሔር በጠላትነት ፈርጆ ዘር ሲያጠፋና ሲያጸዳ የኖረ፤ እኩልነትን እንደ ሀጢያትና ወንጀል ቆጥሮ አገራችንን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ ያለ ዘረኛና ጠባብ ብሔርተኛ ፓርቲ አራጊ ፈጣሪ የሆነ ወንጀለኛ አይደለም ምዕራባውያንን ዲያብሎስን፣ ሒትለርንና ሞሶሎኒን በዘረኝነት የመክሰስ የሞራል ልዕልና የለውም።
ለዚህ ሁሉ ያበቃነው ግን እኛ ራሳችን ነን። በአገሪቱ ስምና ሀብት ለስልጣን አብቅተነው የአሸባሪው ሕወሓት “የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤” ሆኖ ሲያርፈው፤ ኃላፊነቱንና የድርጅቱን ሀብት ለሕወሓት ድጋፍ ማሰባሰቢያ ሲያደርገው፤ ስልጣኑን ሽፋን አድርጎ በሀሰተኛ ክስ ከምዕራባውያን ሚዲያዎችና ከእነ አመነስቲ ጋር አብሮ ቁምስቅላችንን ሲያሳየን ባላየ ባልሰማ አለፍነው። ሌላው ይቅርና ከሁለት ወይም ሶስት ወራት በፊት የጥቅም ግጭት ስላለበትና ገለልተኛም ስላልሆነ እንዲጣራ ለድርጅቱ ቦርድ ያቀረብነው መናኛ አቤቱታ እንኳ ከምን እንደደረሰ ተከታትለን አልጠየቅንም። ኢጋድንና የአፍሪካ ሕብረትን አስተባብረን ከእኩይ ተግባሩ እንዲታቀብ ግፊት ማድረግ፤ ከፍ ሲልም ከኃላፊነት እንዲነሳ አልቀሰቀስንም ። ለኤች.አር6600 እና ኤስ3199 የዳረገንም ይሄ እንዝህላልነትና ዳተኝነት ነው ።
የዓለም የጤና ድርጅት በጤና ተቋማት ላይ የሚፈጸም ጥቃት የቅኝት ስርዓት/Surveillance system for attacks on health care /(SSA) አለው። ለዚሁ በተዘጋጀ መተግበሪያ እኤአ ከ2018 እስከ 2020 ዓ.ም በመላው ዓለም 2ሺህ 119 ጤና ተቋማት ጥቃት መሰንዘሩን ገልጿል። በዩክሬን በጤና ተቋማት ላይ ስለተፈጸመ ጥቃት በዚህ የመረጃ ቋቱ ከመመዝገብ አልፎ ተደጋጋሚ መግለጫ ሰጥቷል። የሚያሳዝነውና የሚገርመው ሕወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች በወረራ በቆየባቸው አምስት ወራት፤ በ110 ከተሞች ከ3ሺህ በላይ የጤና ተቋማት የወደሙና የተዘረፉ ቢሆንም አንዳቸውም በዚህ ድርጅት የመረጃ ቋት አልተመዘገቡም። ዛሬ ስለዩክሬን የሚንዘረዘረው ዋና ዳይሬክተር ተብዬም ትንፍሽ አላለም። ይህ ድርጅቱም ሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ገለልተኛ ላለመሆናቸው ጥሩ አብነት ነው። ይባስ ብሎ የድርጅቱን ሀብትና ያለውን ኃላፊነት ለአሸባሪው ሕወሓት የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ድጋፍ ማሰባሰቢያ አቋራጭ መንገድ እንዳደረገው በገሀድ እየታዘብን ነው።
የሽብር ኃይሉ በዘረፋቸውና ባወደማቸው የጤና ተቋማት የተነሳ የሚሊዮኖች ጤና ለአደጋ ሲጋለጥ፤ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ህጻናት፣ የኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ የስኳርና የሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ህሙማን መድኃኒት፣ ክትትልና ሕክምና ባለማግኘታቸው ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ ለከፋ የጤና ችግር ሲዳረጉና የእናቶችና የህጻናት ክትባት ሲስተጓጎል ትንፍሽ ያላለው ዋና ዳይሬክተር፤ ድርጅቱ ሕወሓት ላመጣው ቀውስ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያን መንግስት ተጠያቂ ሲያደርግና የአገሪቱን ገጽታ ጥላሸት ሲቀባ መንግስት እዚህ ግባ የሚባል ጠንካራ ተቃውሞ እንኳ ማሰማት አልቻለም። በተመሳሳይ ልሒቃን፣ የሲቭል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ አይደለም። የዩኒቨርሲቲ መምህራንና በቀጥታ የሚመለከታቸው የሙያ ማህበራት ሌላው ቢቀር እንኳ ነጠላ መጣጥፍ በውጭ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንኳ ሲጽፉ አናይም።
የአገር መሪዎች፣ ፖለቲከኞችና የአደባባይ ምሁራን በተለይ የምዕራባውያኑ አስተያየታቸውን፣ አቋማቸውን፣ ፖሊሲዎቻቸውንና የግል አመለካከታቸውን እንደ ማንኛውም ተራ ዜጋ እንደ ፋይናንሽያል ታይምስ፣ ዋሽንግተን ፓስት፣ ኒውዮርክ ታይምስ፣ ዎል ስትሬት ጆርናል፣ ደይሊ ቢስት፣ ዘ አትላንቲክ፣ ዘ ጋርዲያን ፣ ታይም፣ ዘ ኢኮኖሚስት፣ ኒውስዊክ፣ ወዘተረፈ ባሉ ዓለም አቀፍ ጋዜጦችና መፅሔቶች በመጻፍ በ(Op – ed ) ይገልጻሉ፡፡ Op-ed የopposite editorial ምህጻረ ቃል ሲሆን፤ የጋዜጣው ወይም የመፅሔቱ ተቀጣሪ ባልሆነ ተጋባዥ ወይም በራሳቸው ፍላጎት አስተያየታቸውንና አቋማቸውን የሚያንጸባርቁበት መጣጥፍ ነው ፡፡ ከምህጻረ ቃሉ እንደምንረዳው መጣጥፉ ከጋዜጣው ወይም ከመፅሔቱ ርዕሰ አንቀፅ ጋር ሊቃረን ይችላል፡፡ የጋዜጣው ወይም የመፅሔቱ አቋም ላይሆንም ይችላል፡፡
በአገራችን መሪዎችና ፖለቲከኞች ይቅርና በልሒቃኖቻችን ብዙ ባልተለመደ ሁኔታ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በዚያ ሰሞኑን በታዋቂው የቢዝነስና የኢኮኖሚክስ መሰናዘሪያ’ ብሉምበርግ ‘ የፖሊሲና የፖለቲካ አምድ ላይ በስማቸው ፣ “ What African Economies Need to Survive the Coronavirus? “/ “ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሮና ቫይረስን ለመቋቋም ምን ይፈልጋል? “ / በሚል ርዕስ ለንባብ አብቀተዋል፡፡ ካልዘነጋሁ ከዚህ በፊት ወይም በኋላ “ዋሽንግተን ፖስት” ላይ ይመስለኛል በኦፔድ ጽፈዋል። ሰሞኑን ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ በአንባቢዎቹ ዘንድ አንቱታን ባተረፈው” ዘ ኢኮኖሚስት “ መፅሔት ላይ “ Democracy in Africa “ በተሰኘ አምድ ላይ “ Threats to Ethiopia’s democratic transition “ በሚል ርዕስ ማለፊያ መጣጥፍ በግብዣ በመከተብ ሰልሰዋል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝም “ፎሪን ፖሊሲ” ላይ ጽፈው አንብቤያለሁ። ይህ ብዙ ያልተሄደበት የእሳቸው ፋና ወጊ መንገድና ዳና ይበል የሚያሰኝና ሊከተሉት የሚገባ ነው፡፡ እንደ ትህነጉ ዲጅታል ወያኔ፣ የሸኔ ደጋፊዎችና ግብፅ ያሉ ሀይሎች ሌት ተቀን በተናበበና በተመጋገበ ዘመቻ የሚነዙትን መርዝ ማርከስ የሚቻለው ዓለም አቀፍ ሚዲያውን በአግባቡ መጠቀም ሲቻል ነውና ልሒቃን፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንደ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር የተጣለባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል።
ወደ ቀደሙት መጣጥፎቼ መቋጫ ስመለስ፡- አሸባሪው ሕወሓት ይህን የሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም የተናጠል የተኩስ አቁም እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የአማራና የአፋር ክልሎች በሕዝባዊ ማዕበል በመውረር፤ በጭና ፣ በንፋስ መውጫ ፣ በጋሊኮማ፣ በአጋምሳና በወረራቸው ሌሎች አካባቢዎች ትህነግ በዘር ማጥፋት፣ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ በሚፈጸም ወንጀል እና በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቀውን ጅምላ ጭፍጨፋ ፈጽሟል። ህጻናትን ሴቶችን አረጋውያንን መነኮሳትን በቤተሰባቸው ፊት በጠመንጃ በማስፈራራት በቡድን አስገድዶ ደፍሯል። ሌሎች ለመናገርም ሆነ ለማድመጥ የሚከብዱና እውነት ይህ ወራሪና የሽብር ኃይል ከትግራዋይ፣ ከኢትዮጵያውያን እና ከሰው ልጅ አብራክ የተገኘ ነው የሚል ጥያቄ የሚያስነሱ ነውሮችን ፈጽሟል። በመጀመሪያ በሰሜን ዕዝ በኋላ በማይካድራ የፈጸመውን የክህደትና የጦር ወንጀል እንዲሁም የዘር ማጥፋት ወንጀል በልኩ በተጠናና ሳይንሳዊ በሆነ አግባብ የተግባቦት የሕዝብ ግንኙነት ስራ ባለመስራታችን ብዙም ያልተጋለጠው ያልተጠየቀውና ያልተከሰሰው ከሀዲው ሕወሓት የልብ ልብ ስለተሰማው በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የማይካድራን ዘር ማጥፋት የሚያስንቅ የዘር ማጥፋት ሊፈጽም ችሏል።
ወደ 10ሺህ፤ የሚጠጉ የጤናና የትምህርት ተቋማት ተዘርፈዋል። ወድመዋል። የወሎ፣ የወልድያና የመቅደላ ዩኒቨርሲቲዎች እና የሰቆጣ የመምህራን ኮሌጅ ተዘርፈዋል። ወድመዋል። የሕዝቡ ሀብት ንብረት ተዘርፏል። በተረፈው እንዳይገለገል ሆን ተብሎ እንዲወድምበት ተደርጓል። አብያተ ክርስቲያናት እና መስጊዶች ረክሰዋል። ወታደራዊ ካምፕ፣ ምሽግና የከባድ ጦር መሳሪያ ማጥመጃ ሆነዋል። በከባድ መሳሪያ ተደብድበዋል። መጽሐፍ ቅዱሳት፣ ቅዱስ ቁራናትና ሌሎች መንፈሳዊ መጽሐፍት ሆን ተብሎ ተቃጥለዋል። የተረፉት እየተቀዳደዱ መጸዳጃ ሆነዋል። በአፋርና በአማራ ክልሎች በተለይ በኮምቦልቻና አካባቢው ከ40 በላይ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ተዘርፈዋል። ወድመዋል። በዚህ የተነሳ በ10ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ስራ አጥተዋል። ከተሞች መርፌ ሳይቀር ተዘርፈዋል። እርቃናቸውን ቀርተዋል። ለዚህ ነው ነዋሪዎች ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ወልድያና ሌሎች በወራሪው ስር የነበሩ ከተሞች ወደ መቐሌ ተጭነው ሔደዋል የሚሉት። የቀሩት እርቃናቸውን ነው ለማለት።
በሁለቱ ክልሎች የተዘረፈውና የወደመው ሀብት ወደ ግማሽ ትሪሊዮን ብር ይገመታል። ከተሞች 20 እና 30 አመታት ወደኋላ ተመልሰዋል። ለዘመናት በላቡና በደሙ ያፈራው የአርብቶና የአርሶ አደሩ ጥሪት ተዘርፏል። እንደ ልጆቹ የሚያያቸው እንስሳት ታርደው ተበልተዋል። የተረፉት በጥይት ተደብድበው ተገለዋል። የሚያሳዝነው ዛሬም ይህን ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ወንጀል ሰው ሰው የሚሸቱ ወቅታዊ መልዕክቶችን ቀርጸን፤ እንደ ታዳሚው ስብጥር የተቃኙ መረጃዎችን በፈጠራ አዋዝተን ማቅረብ አልቻልንም። በዚህ የተነሳም እውነትንና ፍትሕን ይዘን በሀሰተኛ መረጃ ብልጫ ተወስዶብናል። የአስገድዶ መድፈር ተጠቂዋ የሽዋሮቢቷ ኢክራም ለብቻዋ በራሷ ተነሳሽነት ወደ ሚዲያው በመምጣት የፈጠረችውን ተጽዕኖ ያህል እንኳ መፍጠር አልቻልንም ። ሰሞነኛውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስደንጋጭ ግኝት ዓለም አቀፍ አጀንዳ በማድረግ የሕወሓትን ምንደኞችና አለቅላቂዎች አንገት ማስደፋት ስንችል በመናኛ ዜና ብቻ አልፈነዋል። ሆኖም ዛሬም አልረፈደምና ስህተታችን ሊታረም ይገባል።
እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ኢክራምንና ዘሐራን ጨምሮ በየከተሞች የአስገድዶ መድፈር ፤ የግድያ፣ የሰብዓዊ መብት ጥቃትና ስቃይ ሰለባ የሆኑ ዜጎችን ሕመም እንዲያመን እንዲሰማን በማድረግ የማይናቅ ጥረት አድርጓል። በዚያ ሰሞን “ስለኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ያሰናዳው የፎቶግራፍ አውደ ርእይ ይህን የታሪክ ጠባሳ ሰዋዊ አድርጎ ለሕዝብ አቅርቧል። አሁንም ቢዘገይም አልረፈደምና ሚዲያዎቻችን፤ የመንግስት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሪፖርት ማንበብን ቀነስ አድርገው ፤ የደለበውንና በእጃቸው ያለውን የተግባቦት ግብዓት በጥበብ ሊጠቀሙበት ይገባል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጻናትና ሴቶች በቡድን ተደፍረው ፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ በግፍ ተገድለው ፤ የጅምላ መቃብራቸውን ታቅፈን ፤ ወደ 10ሺህ የሚጠጉ የጤናና የትምህርት ተቋማት ወድመው ፤ በሰሜን ዕዝ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ወደ ጦርነት ተገደን ገብተን፤ ወዘተረፈ እንዴት የሕወሓትን ሽብር፣ የጦር ወንጀል፣ የዘር ማጥፋት፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል፤ ወዘተረፈ ለዓለም ማጋለጥ ያቅተናል !?
የተግባቦት (ኮሙኒኬሽን)ስራዎቻችን ሶስት ዋና ዋና ልምሻዎች አሉባቸው። የመጀመሪያው በጥበብና በፈጠራ ስራዎች በማዋዛት መረጃዎች ሰው ሰው እንዲሸቱ የማድረግ ፤ ሁለተኛው ተደራሲዎችን(ኦዲየንስ) የመለየት ሲሆን፤ ሶስተኛው ደግሞ መልዕክቱን በአግባቡ የመቅረጽ ችግሮች ናቸው። በተለይ የቀውስና የጦርነት ጊዜ የተግባቦት ስራዎች ለሰው ልጅ ስሜት የቀረቡ ሆነው መቀረጽ አለባቸው። ወሰን ፣ ዘር ፣ ቀለም ፣ ጾታ ፣ እድሜ ፣ ሀይማኖት ፣ ርዕዮተ ዓለም ፣ መደብና ሌላ ልዩነት ሳይገድባቸው መላ የሰውን ልጅ ስሜት ገዝተው ለድርጊት የሚያነሳሱ መሆን አለባቸው። ከዚህ አንጻር ያለፉት ሶስት አመታትን በተለይ ደግሞ ያለፈውን አመት መለስ ብለን ስንገመግመው አፍን ሞልቶ ድክመቱን መናገር ይቻላል።
ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ/ሕወሓት ባለፈው አንድ ዓመት በሕዝቤ በአገሬና በሰሜን ዕዝ ከፈጸመው ኅልቆ መሳፍርት ከሌለው ለመስማት የሚሰቀጥጥ ለማየት ከሚዘገንን ሰቆቃ ፣ ግፍ ፣ ጭፍጨፋ ፣ ዘረፋ ፣ ውድመት ፣ ወዘተረፈ ባልተናነሰ ዛሬ ድረስ እንደ እግር እሳት የሚያንገበግበኝ አገሬ ሕዝቤ ሰራዊቴና መንግስቴ የክህደትና የጥቃት ሰለባ ሆነው እያለ ተወጋዥ፣ ተከሳሽና ተወቃሽ መሆናቸው ነው። እውነትንና ፍትሕን ታቅፈው ባዶ እጃቸውን አጨብጭበው መቅረታቸውን ሳስብ ጥርሴን እያፋጨሁ እቃትታለሁ። እቃጠላለሁ። እበግናለሁ። እናም እላለሁ፤ “ብዙኃን መገናኛዎቻችንና አምባሳደሮቻችን ከመከላከል እሳት ከማጥፋት አባዜ አሁኑኑ ይውጡ !”፡፡
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9 ቀን 2014 ዓ.ም