ካፍ የኢትዮጵያን ጥያቄ እንዲያፀድቅ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፡- የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ ጥያቄ ተቀብሎ እንዲያጸድቅ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጥሪ አቀረቡ።

46ኛው የካፍ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ትናንትና በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ሲጀመር የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ ካፍ የኢትዮጵያን የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄ እንዲቀበልና እንዲያጸድቅ ጠይቀዋል።

“አፍሪካውያን ቤታችሁ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጣችሁ” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ ዐሻራ እንዳላትና ካፍን ከ67 ዓመት በፊት ከመሠረቱ ሀገራት አንዷ እንደነበረች አስታውሰዋል።

የካፍ ፕሬዚዳንት የነበሩት ይድነቃቸው ተሰማ የአፍሪካ እግር ኳስ በዓለም መድረክ የሚገባውን ቦታ እንዲያገኝ የበኩላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እግር ኳስ ወዳዶች ሀገር ናት ብለዋል።

ኢትዮጵያ ይህን በአፍሪካ እግር ኳስ ያላትን ታሪካዊ ድርሻ ከግምት በማስገባትም ከአምስት ዓመት በኋላ በ2029 የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረቧን አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫውን ተጠቅማ የአፍሪካን እግር ኳስ ለማሳደግና በስፖርቱ ሀገር ለመገንባት እንደምትሠራ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ታዬ፣ የአፍሪካ ዋንጫውን ለማስተናገድ ስታዲየሞችን እየገነባችና ያሉትንም ማሻሻያ እያደረገችባቸው እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ያቀረበችው የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጅነት ጥያቄ ካፍ ባለው የአሠራር ሥርዓት እንደሚታይ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ታሪካዊ ሚና እንዳላትና የካፍ መሥራች አባል መሆኗን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነት ትልቅ ሚና የተጫወተች ሀገር እንደሆነች አንስተዋል።

“የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄዋን ያቀረበችው በትክክለኛው ጊዜ ነው” ያሉት ሞትሴፔ፤ ኢትዮጵያውያን ለእግር ኳስ ያላቸው ስሜትና ቁርኝት ከፍተኛ መሆኑን እንደሚረዱና ይህም ሕዝቡን አንድ የሚያደርግ ትልቅ አቅም መሆኑን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ እየተገነቡ ያሉ ስታዲየሞችና የስፖርት መሠረተ ልማቶችን እንዳስጎበኟቸውና ባዩት ነገር መደሰታቸውንም አክለዋል። ኢትዮጵያ የካፍን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በስኬት ማስተናገዷን ገልጸው፣ የኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይነትም አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ ከቀናት በፊት የ2029 አፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ለካፍ በይፋ ጥያቄ ማቅረቧ የሚታወስ ሲሆን፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለካፍ ጠቅላላ ጉባዔ ወደ ኢትዮጵያ ለመጡ ልዑካን በታላቁ ቤተ-መንግሥት የእራት ግብዣ ባደረጉበት ሥነሥርዓት ላይ ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ አቅም እንዳላት ተናግረዋል። የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትንም እየተገነባ የሚገኘውን የብሔራዊ ስቴድየም ካስጎበኙ በኋላ በፅህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።

የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሙትሴፔ (ዶ/ር) በእራት ግብዣው ላይ በኢትዮጵያ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበው፤ የኢትዮጵያውያን ባህል፣ እሴትና እንግዳ ተቀባይነት “ኢትዮጵያ ቤታችን እንደሆነች እንዲሰማን አድርጎናል” በማለት ተናግረዋል። የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖም “የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ የኛም ሀገር ነች” ሲሉ ተናግረዋል።

ካፍ የኢትዮጵያን ጥያቄ በተመለከተ በቀጣይ ዓመት ሞሮኮ በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You