አዲስ አበባ፡- የቢዝነስ ጉባዔው በኢትዮጵያና ኦስትሪያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደሚያጠናክር የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ገልጸዋል። የ60ኛ ዓመታት የዲፕሎማሲ አጋርነት አስመልክቶ የኢትዮ- ኦስትሪያ የቢዝነስ ጉባዔ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በጉባዔው ላይ ንግግር ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ የቢዝነስ ጉባዔው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ያጠናክራል። ኢትዮጵያና ኦስትሪያ ጠንካራ የሚባልና ሁለንተናዊ ትብብር ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው። ጉባዔው የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ከማጠናከሩም በላይ በሀገራቱ መካከል ዓለም አቀፍ ትብብርን ያመጣል ብለዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፣ የቢዝነስ ጉባዔው ኢትዮጵያንና የኦስትሪያን በዲሎማሲው መስክ ያላቸውን ግንኙንት በንግድና ኢንቨስትመን ለመድገም ይረዳቸዋል። ቢዝነስና ኢንቨስትመንት ጉባዔው የሥራ እድልን በመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳደግ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ያጠናክራል። ኢትዮጵያን ከኦስትሪያን ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛና ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት ያልተነካ ሀብት አላት ያሉት ሚኒስትሯ፣ ለአልሚዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ሰፋፊ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እየተሠሩ ነው። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ጨምሮ የተደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለውጭ አልሚዎች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ በመሆናቸው የኦስትሪያ አልሚዎች መዋእለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አካታችና ዘላቂ እድገትን እያመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል። መንግሥት ኢትዮጵያ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ልዩ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ኬናፕ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ እና ኦስትሪያ ዘመናትን ያስቆጠረ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት አንድ ምእተ ዓመትን ያስቆጠረ ነው፣ በያዝነው ዓመት የኦስትሪያ ኤምባሲ በአዲስ አበባ የተከፈተበትን 60ኛ ዓመት እንደሚያከብርም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያና ኦስትሪያ በአርትና ባህል ጠንካራ ግንኙነት አላቸው ያሉት አምባሳደሯ፣ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ በከተማ መሠረተ ልማት፣ በኮንስትራክሽንና በሌሎች ዘርፎችም የቆየ ትስስር መኖሩን ገልጸዋል።
ይህንንም ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሠራ አመልክተው፤ የኦስትሪያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በንቃት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል። በቀጣይ በንግድና ኢንቨስትመንት ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር በኦስትሪያ በኩል ሙሉ ቁርጠኛ መኖሩን ገልጸዋል።
የኦስትሪያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ማልማት ይፈልጋሉ ያሉት አምባሳደሯ፣ በሜዲካል ላብራቶሪ፣ በፕላስቲክ ፣ በአግሮ ቢዝነስና በሌሎች ዘርፎች የመሠማራት ፍላጎት አላቸው። ኩባንያዎቹም በበርካታ ሀገራት የቆየ ልምድ ማካበታቸውን ጠቅሰዋል።
በጉባዔው ላይ የቢዝነስ ለቢዝነስ ውይይት እንደሚኖር የተገለጸ ሲሆን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ፣የኢትዮጵያና የኦስትሪያ የንግድ ማህበረሰብ ተገኝተዋል።
ሞገስ ጸጋየ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም