አዲስ አበባ፡- ሰውን መጉዳትና እግዚአብሔርን መዳፈር በማቆም ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እድል መስጠት ይገባል ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትሪያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔን ትናንት አስጀምረዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔን ሲያስጀምሩ እንደገለጹት፤ በሀገራችን አለመግባባት፣ ማኩረፍና መቀያየም በዝቷል። ችግሩም ከሕዝብ አልፎ የአምልኮ መፈጸሚያ ቦታዎችንና የአምልኮ ፈጻሚዎችን ኢላማ ያደረገ ነው።
ይህ አይነቱ ተግባር ለሀገርና ሕዝብ የውድቀት ምክንያት ከመሆን ባለፈ የዕድገት ምልክት ሊሆን እንደማይችል ገልጸው፤ ይህ ክፉ ድርጊት እየተፈጸመ ያለው በእኛው ልጆች መሆኑ ደግሞ የበለጠ ያሳዝናል ብለዋል።
በከተማም፣ በጫካም፣ በገጠርም በየትኛውም ስፍራ የምትገኙ ልጆቻችን ምንም ይሁን ምን ሀገርንና ሕዝብን ከመጉዳት ተቆጠቡ ሲሉ አሳስበዋል።
በተለይም ከቤተክርስቲያንና ከሀገር እንደዚሁም ሕዝቡን ከሚያገለግሉ ካህናትና ሲቪል ሠራተኞች እባካችሁ እጃችሁን አንሡ ሲሉ ጠይቀዋል።
ሰውን መጉዳትና እግዚአብሔርን መዳፈር በማቆም ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እድል ስጡ ሲሉ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ክፉው መንፈስ በተራቀቀና በተራዘመ ስልት ሊውጠን በተነሣ ልክ እኛም ከእሱ እጥፍ በሆነ መለኮታዊ ኃይል ልንመክተው ካልቻልን በፈጣሪም ሆነ በትውልድ እንደዚሁም በታሪክ ፊት በኃላፊነት መጠየቃችን አይቀርም ሲሉ አስታውቀዋል።
ችግሩን መከላከል የምንችለው ሕዝቡን በደምብ በማስተማርና በመጠበቅ፣ ለመሪነታችን ዕንቅፋት ከሚሆኑን ዓለማዊ ነገሮች ራሳችንን በማራቅ እንዲሁም ሕዝቡን መስለን ሳይሆን ሆነን ስንገኝለት ነው ብለዋል።
የምናስተምረው ሌላ የምንሠራው ሌላ ከሆነ ከሕዝቡ አእምሮ መውጣታችን እንደማይቀር መገንዘብ አለብን ያሉት ፓትሪያሪኩ፤ በመሆኑም በሰብእናችን፣ በአስተዳደራችን፣ በአመራራችንና በጥበቃችን ሁሉ እንደቃሉ ለመፈጸም መትጋትና በቁርጥ መነሣት ጊዜው አሁን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ ሲሆን በምእመናንና በእኛ መካከል ያለው ግንኙነት አስተማማኝና እንከን የለሽ ከመሆኑም ባለፈ የመሪነት፣ የእረኝነትና የመልካም ተምሳሌነት ኃላፊነታችንን በትክክል ተወጥተናል ማለት እንችላለን ነው ያሉት።
ዓለማዊው አስተዳደር የተመቻቸ መደላድል ሊፈጥርላቸው ግድ ነው ያሉት ፓትሪያሪኩ፤ ዓለማዊው አስተዳደርም የመለኮትን ተልእኮ ለመፈጸም የተሾመ ሹመኛ እንደመሆኑ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በትክክል መምራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዓመት ሁለት ጊዜ ከሚካሄዱት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔት አንዱ የጥቅምት 2017 ዓ.ም ጉባኤ ሲሆን፤ ምልዓተ ጉባዔው በቤተክርስቲያኒቷና በሀገራዊ ዓበይት ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አጀንዳዎችን አውጥቶ በዝግ ላልተወሰኑ ጊዜያት ሲወያይ እንደሚቆይ አመላክተዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም