በጤና ለመኖር አስቀድሞ መመርመር

ዜና ሐተታ

እንደካንሰር፣ ስኳር፣ ደም ብዛትና ሌሎችም ቀድሞ ከተደረሰባቸውና ምርመራ ከተደረገ ሊስተካከሉ የሚችሉ በሽታዎች መሆናቸውን የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ደግሞ የጤና እክል ካላጋጠመው በቀር አስቀድሞ ከጤና ባለሙያዎች ጋር የመገናኘትና ወደ ሕክምና ማዕከላት ሄዶ የመመርመር ልምዱ አናሳ ነው።በዚህም አንዳንድ በሽታዎች በጊዜ ሳይደረስባቸው ስር በመስደድ ለከፍተኛ ህመምና ወጪንም ሊያስወጣ ይችላል።

ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንደሚለው ብሂሉ በማንኛውም ወቅት ከሚከሰት የከፋ ህመም ለመጠበቅ በትንሹ በዓመት አንድ ጊዜ ጠቅላላ የጤና ምርመራ እንደሚገባ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ቀድሞ መከላከል የሚቻሉ የጤና እክሎችን በምርመራ በማወቅ እስከ የሕይወት ህልፈት የሚያደርሱ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያችል ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ይጠቁማሉ። ታዲያ የጤና ቅርመ ምርመራ ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? በሚያስገኘው ጥቅሞች ዙሪያ ምን አይነት ግንዛቤ ያስፈልጋል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ኢፕድ የጤና ባለሙያዎችን አነጋግሯል።

የጤና ባለሙያ የሆኑት ሞገስ አብርሃ (ዶ/ር) እንሚያስረዱት፤ በሀገራችን ያለው አነስተኛ ግንዛቤ ምክንያት በአብዛኛው ማህበረሰብ ወደ ጤና ማዕከላት በማቅናት የመመርመርና የማማከር ባህል ዝቅተኛ ነው።

ወደ ህክምና ተቋማት የሚመጡት በሽታው ከፍ ያለ ጉዳት ሲደርስባቸው ብቻ ነው።ስለጤናው ሁኔታ ባለማወቅ እና ቅድመ ምርመራ ባለ ማድረግ ሳቢያም ለከፍተኛ ህመም ብሎም ሞት ይዳረጋል ይላሉ።

ይህንን ለመከላከልም በሽታዎች ከመከሰቱ በፊት በምናደርጋቸው ምርመራዎች እንደ ልብ፣ ስኳር፣ ደምግፊት፣ ኩላሊትና ካንሰር የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቀድሞ መከላከል የሚቻልበት አቅም ስላለ ምርመራ ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ።

ዶክተር ሞገስ እንደሚሉት፤ ቅድመ ምርመራ ማድረግ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች በተጨማሪ በዘር እና በእድሜ መግፋት የሚከሰቱ በሽታዎች የተጋላጭት ስጋት ለመለየትና በቅድመ ጥንቃቄ ለመከላከል ያግዛል።

የደም፣ የሽንት፣ የውስጥ ደቄ፣ የሲቲ ስካንና አጠቃላይ ምርመራዎች የሕመም ምልክቶች በብዛትና ሳይታዩ አስቀድሞ በሽታው እንዲለይና ሕክምና እንዲሰጥ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በበሽታው ሊያደርስ የሚችለውን የከፋ ጉዳት በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ ሁሉም ዜጋ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋመ በመሄድ መመርመር እንደሚገባው ይመክራሉ።

ለአብነትም የስኳር በሽታ የሕመም ስሜት የሚኖረው አምስት ዓመት በሰውነት ውስጥ ከቆየ በኋላ መሆኑን አንስተው፤ የደም ግፊት በሽታ ደግሞ ምንም አይነት ምልክት የማያሣይ መሆኑን ይገልጻሉ። በመሆኑም ማንኛውም ሰው ተመርምሮ ካላረጋገጠ በቀር በሽታ የለብኝም ማለት አይችልም ብለዋል።

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም

Recommended For You