አሳታፊው የሀገራዊ ምክክር ሒደት

ባለፈው ሳምንት የሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማን ጨምሮ በሌሎች ሦስት ማዕከላት የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ልየታ መድረክ ሲከናወን ቆይቷል።የአጀንዳ ልየታው ተጠናቅቆ ወደ ባለድርሻ አካላት ምክክር ተሸጋግሯል።

ሂደቱን በማስተባበር እያካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የማይናወጡ መርሆዎቼ ናቸው ብሎ ካስቀመጣቸው ምሶሶዎች ውስጥ አንዱና የመጀመሪያ ረድፍ ላይ ያለው “አካታችነት” ነው።አካታችነት በምክክሩ ውስጥ ባለ የአጀንዳ እና የሃሳብ ማዋጣት ተሳትፎ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲሳተፍ የሚያደርግበት መንገድ መሆኑን የሚዳስስ ጽንሰሃሳብ ሆኖ እናገኘዋለን።

በዚህ አካሄድ ተጠቃሚ ሆነው ውክልና ተሰጥቷቸው በምክክሩ ላይ ሲሳተፉ ካገኘናቸው ውስጥ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይገኙበታል።

ሰዎች በሚሠሩት ሥራ ወይም በሌላ አንዳች ምክንያት አልያም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ጎሳዎች በመሆናቸው በአንዳንድ አካባቢዎች መገለል ይደርስባቸዋል።እነዚህ ዜጎች ኢትዮጵያዊ እንደመሆናቸው መጠን የራሳቸውን ጥቅም የሚያስጠብቅ፤ ለሀገር ያላቸውን አስተዋፅኦ የሚያበረታ እንዲሁም ዕኩልነታቸውን በግልፅ የሚያውጅ አጀንዳ ማንሳትና መወያየት ያስፈልጋል።በመሆኑም በሀገራዊ ምክክሩ ተገቢው ቦታና ውክልና ተሰጥቷቸው እየተወያዩ ይገኛል።

በምክክሩ በተለያየ ምክንያት የተገለሉ ማኅበረሰቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ዕኩልነት ፋይዳ ያላቸው አጀንዳዎችን መለየታቸውንም በሶማሌ ክልል ሀገራዊ ምክክር የተገለሉ ማኅበረሰቦች ተወካዮች ለኢፕድ ተናግረዋል።

በሶማሌ ክልል ሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ልየታ የተሳተፈው አቶ አብዱአዚዝ ዩሱፍ፤ በክልሉ በአካል ጉዳተኝነት እና በጎሳ ምክንያት የተገለሉ ሰዎች አሉ ይላል።

በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ማኅበረሰቡ ባያገልላቸው እንኳን ራሳቸውን የሚያገልሉ ጥቂት ሰዎች እንዳሉ በመጥቀስ፤ በትንሹም ቢሆን የመገለል ችግር ከታየ በምክክር ሊፈታ እንደሚገባው ነው የሚናገረው።

ኢትዮጵያ የትኛውንም የኅብረተሰብ ክፍል ዕኩል የምታይ ሀገር መሆን ይኖርባታል የሚል ዕምነት እንዳለውም ወጣት አብዱአዚዝ ይጠቅሳል።

በምክክሩ ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና ዕኩልነት ፋይዳ ያላቸው አጀንዳዎችን በመለየት መሰል ችግሮች በምክክር ተፈትተው ኢትዮጵያ ሰላማዊ እና ለሁሉም ዕኩል የምትመች ሀገር ሆና የማየት ተስፋ እንዳለው ይናገራል።

የተለዩ አጀንዳዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ውይይት ተደርጎባቸው ወደ ተግባር ይገባሉ የሚል ዕምነት እንዳለው ገልጾ፤ ጎን ለጎን ለማኅበረሰቡ ሁሉም ሰው ዕኩል ስለመሆኑ ግንዛቤ ማስጨበጥ ይገባል ይላል። የማግለል ትንሽ ትልቅ የለውም የምትለው ደግሞ ከሽኒሌ ወረዳ የምክክሩ ተሳታፊ የነበረችው ወጣት ኢክራም ኢብሳ ናት።

በአንዳንድ ቦታዎች ማግለል ባይኖር እንኳን በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ጎሳዎች ራሳቸውን የሚያገሉበት ሁኔታ እንዳለ የምትገልጸው ወጣት ኢክራም፤ በየትኛውም መንገድ ቢሆን ኢትዮጵያ የሁላችን ሀገር መሆኗን በመገንዘብ ሁሉንም ስህተቶች በምክክር ማረም ይገባል ትላለች።

በምክክሩ የተገለሉትን ዜጎችን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና ዕኩልነትን የሚያሰፍኑ አጀንዳዎች መለየታቸውን ነው የጠቆመችው።

በተለዩ አጀንዳዎች ላይ የሚደረግ የባለድርሻ አካላት ውይይት አስፈላጊ መሆኑን አንስተው፤ በአጠቃላይ የሀገራዊ ምክክሩ ለሀገር የሚበጅ ውጤት ያመጣል የሚል ተስፋ አለኝ ስትል ትገልጻለች።

ከጀረር ዞን ዮአሌ ወረዳ የተገኙት የምክክሩ ተሳታፊ አቶ ባሪ ቆረኒ በበኩላቸው፤ ምክክር ለአንድ ሀገር ቀጣይ ጉዞ ወሳኝ መሆኑን ያነሳሉ።

የተገለሉ ማኅበረሰቦች ከሕዝቡ ጋር በዕኩልነት እንዲኖሩ ማስቻል ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ባሪ፤ ጉዳዩን አጀንዳ አድርጎ በመወያየት እና የሕዝቡን ግንዛቤ በማሳደግ መሰል ችግሮችን መፍታት እንደሚያስፈልግ ያብራራሉ።

ሀገራት ችግሮቻቸውን በምክክር ሲፈቱ ያለ ተጨማሪ ጉዳት ምቹ ከባቢን መፍጠር እንደሚችሉ አስገንዝበው፤ ምክክሩ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም ዕድልን ይዞ እንደመጣ ዕምነታቸው መሆኑን ነው ያመላከቱት።

ውብሸት ሰንደቁ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም

Recommended For You