ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል ፡፡ የምግብ እህል ፣ የቤት ኪራይ ፣ የነዳጅ ፣ የሸቀጣሸቀጥ ፣ ማዳበሪያ፣ የዘር እህል ወዘተ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ አብዛኛው ሕዝብ የእለት ጉርሱን ፤ የዓመት ልብሱን፤ አንገት ማስገቢያ ጎጆ እንዲያገኝ እያደረገው ይገኛል፡፡ በአገራችን የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ምክንያት እየሆነ ነው ተብሎ በተለያዩ አካላት የተለያዩ ምክንያቶች ሲጠቀሱ ይስተዋላል ፡፡ በአንድ በኩል የንግዱ ማኅበረሰብ የሚፈጥራቸው ችግሮች ዋነኛው መንስኤ እንደሆነ ሲነሳ በሌላ በኩል አገሪቱ የገባችበት ጦርነት ያስከተላቸው ኢኮኖሚያዊ መዘዞች ችግሩ እንዲባባስ ስለማድረጉ ይነሳል ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የአገሪቱ የግብርና ዘርፍ አለመዘመን የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወጣ ሲያነሱ አንዳንዶቹ ደግሞ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሮች የፈጠሩት እንደሆነ ያነሳሉ ፡፡ በሌላ በኩል ከላይ የተዘረዘሩ ምክንያቶች ድምር ውጤት ነው ይላሉ ፡፡
የኑሮ ውድነት መንስኤዎች ናቸው ተብለው በተለያዩ አካላት የሚጠቀሱ ምክንያቶች እንደሚለያይ ሁሉ እንደመፍትሔ የሚጠቀሱትም ይለያያል። አንዳንዶች ምርትና ምርታማነትን ማሳደግን እንደመፍትሔ ሲያነሱ ፣ ሌሎቹ የንግዱን ማኅበረሰብ አደብ ማስገዛትን እንደ ዋነኛው መፍትሔ ይጠቅሳሉ። ሌሎቹ ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ መቋጨትን እንደመፍትሔ ያነሳሉ ፡፡ በአጠቃላይ እንደ ምክንያትና መፍትሔ የሚጠቀሱ ነገሮች ከመንግሥትና ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር የሚገናኙ ናቸው ማለት ይቻላል ፡፡
በዚህ ሁሉ መሐል አንድ ቁልፍ መፍትሔ የተዘነጋ ይመስላል ፡፡ የትኛውም ጥረት ግብ ሊመታ የሚችለው የሕዝብ ተሳትፎና ባለቤትነት ሲታከልበት ነው፡፡ በአገራችን የብዙዎች ራስ ምታት የሆነውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ግለሰቦችና ቤተሰቦች የሚወስዷቸው የመፍትሔ እርምጃዎች ትልቅ ሚና እንዳላቸው ሊዘነጋ አይገባም ፡፡ የችግሩ መፍትሔ በመንግሥት እጅ ብቻ እንዳለ ማሰብ ችግሩን ለመፍታት አያስችልም ፡፡ መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር እያንዳንዱ ግለሰብ ወጪ መቀነሻ ዘዴዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል ፡፡
የዜጎች የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል የማድረግ ዋነኛ ኃላፊነት የመንግሥት ቢሆንም በአገራችን ውስጥ አሁን ከሚታየው የኑሮ ውድነት ከባድነት ለመላቀቅ ዜጎች የኑሮ ውድነት እያስከተለ ያለውን ጫና ለመቋቋም በፕሮግራም መኖርና በፕሮግራም መሸመት እጅግ ወሳኝነት አለው ፡፡ በፕሮግራም የማይሸምት ሸማች ገበያ ውስጥ ውሳኔ መስጠት ይቸገራል ፡፡ ያለ እቅድ ገበያ በወጣ ቁጥር የሚያምር እቃ ሲያገኝ ወይም ሰዎች በብዛት የሚገዙትን እቃ ሲያገኝ የሚገዛ ሸማች የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቋቋም ይቸገራል ፡፡
በአገራችን ለምርቶች ዋጋ መናር እና ከገበያ መጥፋት አንዱ ምክንያት እየሆነ ያለው የንግዱ ማኅበረሰብ እንዲሁም ሸማቾች የእቃዎች ወይም የምርቶች ዋጋ በቀጣይ ጊዜያት ሊጨምር ይችላል በሚል ስጋት ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ገዝቶ ማከማቸት ነው ፡፡ ሸማቾች ባልተረጋገጠ መረጃ ላይ በመመርኮዝ ምርቶችን በማከማቸት ለዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት መባባስ ምክንያት ሊሆኑ አይገባም ፡፡ አንድ ሸማቾች ለወራት የሚሆን ምርት በሚሰበስቡበት ወቅት በገበያ ውስጥ የምርት እጥረት ስለሚያጋጥም ወቅት ለዕለት የሚሆን ምርትና ሸቀጥ የሚፈልጉ ሸማቾች ችግር ውስጥ ሊወድቁ እንደሚችሉ ከግምት ማስገባት አለባቸው ፡፡ የወር የመግዛት አቅም የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ችግር ውስጥ እንዲወድቁ መፍረድ አይገባም ፡፡
የራስን ሸመታን በፕሮግራም እና በዝርዝር ማከናወን ሌላኛው መፍትሔ ነው ፡፡ ሰዎች ገበያ ከወጡ በኋላ ሳይሆን ከመውጣታቸው በፊት ስለሚሸምቱት ነገር እና መጠን መወሰን ፤ ካሰቡት የሸመታ ፍላጎት በላይ በጀት ይዞ ወደ ገበያ ያለመውጣት በጣም ተገቢ ነው ፡፡ ካሰቡት የሸመታ ፍላጎት በላይ ገንዘብ ይዘው የሚወጡ ከሆነ ያላሰቡትን ምርትና አገልግሎት የመሸመት እድል ይሰፋል ፡፡ ይህንን ችግር ለመከላከል መፍትሔው የተመጠነ በጀት ይዘው መውጣት ነው፡፡
የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ሌላኛው መፍትሔ ማተካካት ነው ፡፡ ዋጋው ከፍ ያለውን ምርት በመተው ዋጋው ተመጣጣኝ ነገር ግን ዋጋው ከፍ ካለው ምርት ጋር ተቀራራቢ ጥቅም ሊሰጥ የሚችል ምርት መሸመትን መልመድ ያስፈልጋል ፡፡ ለአብነት ያህል አንድ ሸማች ምስር ሊገዛ ወጥቶ የምስር ዋጋ ካሰበው በላይ ከፍ ብሎ ካገኘ እና የሽሮ ዋጋ መጠነኛ ቅናሽ የሚታይበት ከሆነ ምስርን በሽሮ መተካት የኑሮ ውድነትን በጊዜያዊነት ለመቋቋም ይረዳል፡፡
ከገቢ አንጻር ሰዎች የሚጠቀሟቸውን ምርቶችና አገልግሎቶችን ተመጣጣኝ ወጪ በሚያስወጡ ምርቶችና አገልግሎቶች መተካት የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ሚናው ከፍ ያለ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ሊህቃን ያስረዳሉ ፡፡
ብድር የወጪ ሁኔታን የማዛነፍ አቅም እንዳለው የዘርፉ ምሑራን የሚያስረዱ ሲሆን ፤ ወደፊት የሚኖር የወጪ ምክንያት እንዳይጨምር ከብድር ራስን ማራቅ፡፡ የነበረ ብድር ካለ በፍጥነት በተቻለ አቅም ከፍሎ ከእዳ መላቀቅ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ሚናው የላቀ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል ፡፡
የተሻለ ዋጋ ያላቸው ገበያዎችን መርጦ መሸመት ሸማቾችን ከአላስፈጊ የዋጋ ጭማሪ የሚከላከል በመሆኑ፤ የገበያ ዋጋ ጥናት ቀድሞ በማድረግ ምርቶችና አገልግሎቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ከሚሸጥባቸው አካባቢዎች መሸመት የራሱ ሚና አለው ፡፡ በአጠቃላይ ግን ሸማች የኑሮ ውድነትን ለመከላከል አንዱ የመፍትሔው አካል መሆን እንደሚችል ማመን አለበት። ወጪ ቀናሽ ምርቶች ላይ ማተኮር፤ አማራጭ ምርቶች ላይ ማተኮር፣ ባለመግዛት አድማ ማድረግ በመፍትሔነት የሚያገለግሉ መሆናቸው መዘንጋት የለበትም። ለእያንዳንዱ ችግር ሁሉም በራሱ መላ ቢፈልግለት ችግሩን በመጠኑም ቢሆን ሊቀንስ ይችላል። ሁልጊዜም መንግሥትን ብቻ ከመጠበቅ በራስም የመፍትሔ አካል መሆን ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9 ቀን 2014 ዓ.ም