ኢትዮጵያውያን ከአራት ዓመታት በፊት የትህነግን አረመኔያዊ የአገዛዝ ሥርዓት ገርስሰው በመጣል አዲስ አስተዳደር ለመመሥረት ታላቅ ተጋድሎን አድርገዋል። ዜጎች የፍትሕ፣ የእኩልነት ጥያቄን አንስተው ለውጥ እንዲመጣ መነሻ በመሆናቸውም አሁን መንግሥት መሥርቶ አገሪቷን እያስተዳደረ የሚገኘውን የብልፅግና ፓርቲ እንዲመሠረት ምክንያት ሆነዋል። ይህን ተከትሎ በርካታ አዳዲስ የፖለቲካ ባህልና አመለካከት እያስተናገደች ትገኛለች።
ለሶስት አስርተ ዓመታት ኢትዮጵያውያንን በዘርና በጎጥ መድቦ የቡድን የፖለቲካ ፍላጎቱን ለማሳካት የተንቀሳቀሰው ትህነግ ኢትዮጵያን እንደ ዳቦ ሸንሽኖ ለማፍረስ ያስቀመጠው እቅድ ባይሳካለትም አሁንም በትግራይ ሕዝብ ጉያ ውስጥ መሽጎ እኩይ ጥረቱን መቀጠሉ ግን አልቀረም። ከዚያ ውጪ ለዓመታት የጥላቻ መርዝ ሲሰበክና ሴራ ሲጎነጎንበት የሰበነበተው ወጣትም ትህነግ ከስልጣን መንበሩ ላይ ባይኖርም በተሠራበት የልዩነት ግንብ ምክንያት እዚያም እዚህም ግጭት ሲፈጥርና ወገኖቹን ለሞት፣ ለማፈናቀል ሲዳርግና በተሳሳተ አቅጣጫ ሲጓዝ እየተመለከትን ነው። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የሽብር ዓላማን አንግቦ የሚንቀሳቀሰው የሸኔ ቡድን አባል ነው። ይህ ቡድን የትህነግ የጥላቻ ፖለቲካ የወለደው መሆኑን አንዳች ጥርጥር አይኖርም። ምግባሩም ከፈጣሪው ጋር አንድ ነውና።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ለዜጎች እፎይታን የሰጡ ለውጦች የመምጣታቸውን ያክል በዚያው ልክ ደግሞ በማኅበረሰብ ውስጥ ሰፊ ልዩነቶችን የሚፈጥሩና አብሮ በሚኖር ሕዝብ መሐል የጥላቻ ሽብልቅ የሚሸነቁሩ አመለካከቶችና ድርጊቶች መስተዋላቸው አልቀረም። በተለይ የተለያየ የፖለቲካ ዓላማና ፍላጎትን አንግበው የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞች ልዩነታቸውን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታትና ለማቀራረብ ብዙ ርቀት መጓዝ ባለመቻላቸው ሕዝብንና አገርን አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችን ተመልክተናል።
የሕዝብ ይሁንታን አግኝቶ መንግሥት የመሠረተው የብልፅግና ፓርቲ አዲስ የፖለቲካ ባህል በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ በማስተዋወቅ ስልጣን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመጋራት ጥረት ማድረጉ በጎ ጅምር ተደርጎ ቢታይም አሁንም ግን ጫፍና ጫፍ የረገጡ ፅንፍ አመለካከቶች የተቀራረቡ አይመስሉም። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚነሳው ደግሞ ጦር ሰብቀው ሕዝብን በግራና ቀኝ ስጋት ውስጥ ከከተቱት የትህነግና የሸኔ ሽብር ቡድኖች በተጨማሪ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የመረጡት በርካታ ፓርቲዎች እጅግ የጎላና በቀላሉ ሊታረቁ የማይችሉ አጀንዳዎችን በመጫወቻ ሜዳው ላይ በማምጣት የገመድ ጉተታ ውስጥ መግባታቸው ነው።
መንግሥት ልዩነቶችን ለማጥበብና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በማስፈን ለዜጎች እረፍት ለመስጠት በአጭር ግዜ ውስጥ ብሔራዊ የምክክር መድረክ እንደሚካሄድ አሳውቆ በሂደት ላይ እንዳለ የሚታወቅ ነው። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አሻራቸውን የሚያሳርፉ ፓርቲዎችና ቡድኖች ከጅምሩ ሂደቱ ላይ አመኔታ እንደሌላቸው በተለያዩ አማራጮች ሲናገሩ ይደመጣል። ለመሆኑ ጫፍ የረገጡ አመለካከቶችን ያቀራርባል በሚል ተስፋ የተጣለበትን ይህን መሰል መድረክ ላይ እምነት እንደሌላቸው ይፋ የሚያደርጉ አካላት ዋነኛ ምክንያት ምን ይሆን?
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከላይ ለተነሳው መሠረታዊ ጥያቄ ምክንያት ነው ብሎ የሚያምነው የማክረር ፖለቲካ ውጤት እንደሆነ ነው። በመሠረታዊነት የሕዝብ ጥያቄዎችንና አንገብጋቢ አጀንዳዎችን በመያዝ በፖለቲካ ፓርቲ ስር የሚሰባሰቡ ቡድኖች ዓላማቸውን ማስፈፀም የሚኖርባቸው በሰላማዊና ሕጋዊ የመጫወቻ ሜዳ ላይ እንደሆነ ይታመናል። በተለይ የወከሉትን ማኅበረሰብ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን የመፍታት ኃላፊነትን የወሰዱ ቡድኖች ዜጎችን ስጋት ላይ ለመጣል ሳይሆን መፍትሔ ለማግኘት ተቀራርበው መሥራት ይኖርባቸዋል።
አሁን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እየታየ ያለው ግን ሕዝብን ከሕዝብ የሚያቀራርቡ አጀንዳዎች በመቅረፅ በጋራ መሥራት ሳይሆን በተቃራኒው ፅንፍ ይዞ ገመድ መጓተትን የመረጠ አካሄድን መከተል ነው። ለመግባባት ሳይሆን ላለመግባባት መጨቃጨቅን ምርጫቸው ያደረጉ ኃይሎች በስፋት የሚሳቱበት የፖለቲካ ሂደት አገሪቱ ለገባችበት አያሌ ፈተናዎች ላይ እሳቱን የሚያባብስ ጋዝ የሚያርከፈክፍ ነው።
የሰለጠነ የፖለቲካ ሂደት በውይይትና ድርድር የሚያምን ነው። ከግልና ቡድን ፍላጎት በላይ ትልቁን የአገር ሉዓላዊነትና የዜጎች ደህንነት ከፊት አድርጎ ለፍትሕ፣ እኩልነት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቀን ከሌሊት የሚሠራ ነው። ምንም እንኳን ፖለቲከኞች የሚያቀነቅኑት ሃሳብ እውነትን ያዘለ ቢሆንም የመጨረሻ ውጤቱ የአገርን አንድነትና የዜጎችን ሰላም የሚያውክ ከሆነ ከፊት በማምጣት ሊያቀነቅኑት አይገባም። በፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ድርድር ሲባል “ሰጥቶ የመቀበል” መርህ ከፊት ይመጣል። ውይይትም ሆነ ምክክር ስናደርግ ለመደማመጥና የሰከነ ሃሳብ ልውውጥ ለማድረግ ወኔው ሊኖረን የግድ ይላል።
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች ገመዱን በማክረርና በመጨረሻም በመበጠስ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ የገቡ ይመስላል። የውይይት መድረኩ ላይ የሚቀራረብ ሳይሆን የሚገፋፋ ሃሳብ ይዞ ለመቅረብ አሰፍስፈው ነው የሚታዩት። ሃሳባቸውን በተገቢው መንገድ ለማቅረብ ከመዘጋጀታቸው በፊት በመወያያ ጠረጴዛው ላይ እምነት እንደሌላቸው ለማስረዳት ግዜን ይፈጃሉ። እንወክለዋለን ለሚሉት ማኅበረሰብ ጠቃሚ የሚሆኑ አጀንዳዎች ላይ ከማተኮርና ለዚያም ተፈፃሚነት ከመስራት ይልቅ በእልህና በማን አለብኝነት ወደ ገደል ጫፍ የሚሰድድ ሃሳብ ሲያራምዱ ይስተዋላል። ይሄ ማንንም አይጠቅምም።
በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መረጋጋትን ለማምጣት በመንግሥትም ሆነ በአንዳንድ አካላት በጎ ጅምር እንዳለ እናምናለን። ይሁን እንጂ ጫፍና ጫፍ የያዙ ሃሳቦችና ቡድኖች የማይቀራረቡ ከሆነ አሁንም ይህ ጥረት በቶሎ ይፈታል የሚል እምነት አይኖርም። በተለይ በቅርብ ግዜ ውስጥ ይደረጋል የተባለለት ብሔራዊ የምክክር መድረክ ከመጀመሩ በፊት በዚህ ቦታ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ቡድኖች የሚከተሉትን ነገሮች ማስተዋል ይገባቸዋል ብለን እናስባለን።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ችግሮች በመሣሪያ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ እንደሚፈቱ ግንዛቤ መውሰድ የመጀመሪያው ነው። በመሠረታዊው ጉዳይ ከተግባባን በኋላ ግን ሃሳቦቻችንን በምን መልኩ ማቀራረብ ይኖርብናል የሚለውን ጉዳይ በቅድሚያ ከራሳችን ጋር ጨርሰን መምጣት ይኖርብናል። በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ሸንጎ ላይ ከመቅረባቸው በፊት የሚያራርቁ ሳይሆን የሚያቀራርቡ፤ አንዱን ተቀባይ አንዱን ሰጪ ሳይሆን የሚያቻችሉ አጀንዳዎች እንዳሏቸው መመርመር ይኖርባቸዋል። ከሁሉም በላይ ግን አብሮ የሚኖር ማኅበረሰብ መሃል ሽብልቅን የሚሸነቁሩ ሳይሆን ድልድይ ሠርተው የሚያገናኙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ዋነኛው ጉዳይ መሆን አለበት።
ከመረጃዎች መገንዘብ እንደምንችለው መንግሠት ከመሰረተው ቡድን ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ አደረጃጀት የተመሠረቱ ፓርቲዎች ውስጣዊ አንድነት በእጅጉ የላላ ነው። ይህ ማለት በአንድ ዓላማ ስር የተሰባሰቡ አካላት እርስ በእርስ የሚያግባባ ጠንካራ መሠረት ሳይኖራቸው ከሌላው ተመሳሳይ ችግር ካለበት ቡድን ጋር በዋና ዋና አገራዊ ጉዳይ ላይ ስምምነት ላይ ይደርሳል የሚል እሳቤ አይኖርም። ይህን ችግር በቶሎ በመቅረፍና ሕዝብን እንወክላለን የሚሉ አካላት የቤት ሥራ በሚገባ ሠርተው ለዜጎች ሰላምና ማኅበራዊ እረፍት በቅንነት ሊሠሩ ይገባል።
አንድ አገር ነው ያለን። ወደድንም ጠላንም የጋራ የሆኑ አያሌ ጉዳዮች አሉን። የተጋባን፣ የተዋለድን፣ አብረን ለዘመናት የኖርን “ኢትዮጵያ” የምትባል ዋርካ ስር የምንኖር ሕዝቦች ነን። ነገ ደግሞ በጋራ ኃያል የምንሆንና ታላቅነታችን በጠንካራ ትብብር የምንገነባ ነን። ይህ ከሆነ ታዲያ ልዩነቶቻችንን አቻችለን ነገ ለውይይት እና ሽንቁሮቻችንን ለመድፈን በጠረጴዛ ዙሪያ ከመሰባሰባችን በፊት “በቅድሚያ ከራሳችን ጋር እንታረቅ” የዛሬው መልዕክት ነው።
ዳግም ከበደ
ሚያዝያ 7 ቀን 2014 ዓ.ም