እስራኤል በኢራን ላይ ያቀደችውን ጥቃት አሜሪካ የገመገመችበት ሰነዶች ሾልከው ወጡ

እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም ማቀዷን አሜሪካ የገመገመችበት ምሥጢራዊ ሰነዶች እንዴት ሾልከው እንደወጡ ምርመራ መከፈቱን የሀገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ማይክ ጆንሰን ገለጹ። ኢራን መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም ለፈጸመችው የሚሳዔል ጥቃት ምላሽ ለመስጠት እስራኤል ወታደራዊ ንብረቶችን ማንቀሳቀሷን የሚያሳዩ የሳተላይት ምሥሎችን የያዙ ሰነዶች ባለፈው ሳምንት ከኢራን ጋር ግንኙነት ባለው ቴሌግራም ገጽ ላይ ለህትመት በቅተዋል።

በከፍተኛ ምሥጢር እንደተያዙ የሚያመለክቱት እነዚህ ሰነዶች በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በካናዳ፣ በኒውዚላንድ እና በአውስትራሊያ የደህንነት እና የስለላ ጥምረት ብቻ እንዲታዩ የሚገልጽ መሆኑን ተዘግቧል። ኢራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳዔሎችን ወደ እስራኤል አስወንጭፋ ጥቂቶቹ የእስራኤልን ግዛት እንደመቱ ይታወሳል።

ለሳምንታት እስራኤል ኢራን ለፈጸመችባት ጥቃት እንዴት እና መቼ ምላሽ እንደምትሰጥ ስታሰላስል መቆየቷ ተዘግቧል። የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር ምላሹ “የከፋ እና ድንገተኛ እንደሚሆን” ሲያስጠነቅቅ ነበር። ሁለቱ ሾልከው የወጡ ምሥጢራዊ ሰነዶች የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ኤጀንሲ (ኤንኤስኤ) እና ብሔራዊ ጂኦስፓሺያል ኢንተለጀንስ ኤጀንሲ ግምገማ ያደረጉባቸው እንደሆነ ሪፖርት ተደርጓል።

ሰነዶቹ “ሾልከው መውጣታቸው አሳሳቢ ነው” ሲሉ የተናገሩት አፈ ጉባኤው ጆንሰን ሀገራቸው በዚህ ጉዳይ ላይ ምርመራ እያካሄደች መሆኗን መናገራቸው ተዘግቧል። ፔንታጎን ሰለ ሰነዶቹ የወጣውን ሪፖርት እንደሚያውቅ ቢያረጋግጥም ተጨማሪ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

በግምገማው ላይ ተሳትፈዋል የተባሉት የአሜሪካ ተቋማት እንዲሁም የእስራኤል መንግሥት ሾልከው ስለወጡት ሰነዶች በይፋ የሰጡት አስተያየት የለም። ሰነዶቹ ሾልከው መውጣታቸውን መጀመሪያ የዘገቡት ሲኤንኤን እና አክሲዮስ ሚዲያዎች ሲሆኑ፣ በዚህም አሜሪካ የቅርብ አጋሯን እስራኤልን እንደምትሰልል በድጋሚ የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል።

አንደኛው ሰነድ አሜሪካም ሆነ እስራኤል በይፋ የማያምኑት የእስራኤልን የኑክሌር አቅምን የሚያመለክት ሲሆን፣ በየትኛውም ጥቃት የኑክሌር መሣሪያን መጠቀምን አማራጭ ይከለክላል። እነዚህ ሰነዶች አሾልኮ የወጣበት መንገድ በኢራን ላይ የታቀደውን የበቀል ጥቃት መጠን ለማጋለጥ ወይም ምናልባት ለማደናቀፍ የተደረገ ሙከራ እንደሆነ አንድ የቀድሞ የአሜሪካ የስለላ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አሜሪካ መረጃው ሆን ተብሎ በአሜሪካ የደህንነት ሠራተኛ ይፋ የተደረገ ወይም የተሰረቀ ስለመሆኑ እየመረመች እንደሆነና ምናልባትም በምዝበራ ተገኝቶ ሊሆን እንደሚችል ባለሥልጣናቷ ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል። ሁለቱ ሰነዶች ጥቅምት 5 እና 6 ቀናት 2017 ዓ.ም. በተገኙ የሳተላይት መረጃ ላይ መሠረት ያደረጉ ናቸው።

በሰነዱ ላይ አንደኛው ርዕስ የእስራኤል አየር ኃይል በኢራን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ዝግጅቱን አጠናክሮ መቀጠሉ እና ለሁለተኛ ጊዜ እያደረገ ያለውን ከፍተኛ የኃይል ስምሪት እንደሚያትት የሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በዚህም የባለስቲክ እና ከአየር ወደ መሬት የሚወነጨፉ የሚሳኤል ጥቃቶችን ቅንጅትን ሲያብራራ፣ ሁለተኛው ርዕስ የእስራኤል የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) እንቅስቃሴ የሚመለከት መረጃ ይዟል። አርብ ዕለት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እስራኤል በኢራን ላይ ልትፈጽመው ስላቀደችው ጥቃት በአንድ ጋዜጠኛ በተጠየቁበት ወቅት “ጥሩ ግንዛቤ” እንዳላቸው ቢናገሩም ዝርዝሩን ከመናገር ተቆጥበዋል።

እስራኤል በኢራን ላይ የበቀል ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ቀውስ ይባባሳል የሚል ስጋት ያላት አሜሪካ የእስራኤልን ዝግጅት በቅርበት እየተከታተለች ነው።’ሚድል ኢስት ስፔክቴተር’ በተባለው የቴሌግራም ቻናል ላይ ይፋ የሆነው የአሜሪካ የስለላ መረጃ፣ ከወዳጇ እስራኤል ጋር መቃቃርን ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

ምክንያቱም ሾልከው ወጡት ሰነዶች አሜሪካ በተለያዩ መንገዶች ያሰባሰበቻቸው ወታደራዊ የስለላ መረጃዎች በመሆናቸው እስራኤል ስለላ እየተካሄደባት መሆኑን በመግለጽ ተቃውሞ ልታሰማ ትችላለች በሚል ነው። ከአንድ ዓመት በፊት በሀገራት ላይ የተካሄደ የወታደራዊ ስለላ መረጃ በአንድ የአሜሪካ ሠራዊት የደህንነት አባል ሾልኮ ወጥቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ይፋ በተደረገበት ጊዜ ደቡብ ኮሪያ እና ዩክሬንን ጨምሮ የአሜሪካ አጋሮች ቁጣቸውን ገልጸው ነበር።

አሁንም የእስራኤል ወታደራዊ ዝግጅትን በተመለከተ አሜሪካ ያሰባሰበችው መረጃ ለኢራን ቅርብ ነው በተባለ የቴሌግራም ቻናል በኩል ይፋ መሆኑ በእስራኤል ባለሥልጣናት በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። እንዲሁም ይህ ክስተት በአሜሪካ በኩል የመረጃ አጠባበቅ ደህንነት ጥያቄን ያስነሳ ሲሆን፣ ይፋ የሆነው ሰነድ ለኢራን ቅርብ በሆነው የማኅበራዊ ትስሰር ገጽ ይፋ የሆነው ተሰርቆ ከሆነ አሜሪካ ከኢራን ጋር ወደ ተጨማሪ ውዝግብ እንድትገባ ያደርጋታል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም

Recommended For You