በዓለም በተለያዩ ዘርፎች ለሚከናወኑ ተግባሮች ፍቱን ቴክኖሎጂ እየሆነ የሚገኘው የዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ የምርት እድገት፣ የግንኙትነት መሳለጥ፣ የደህንነትና የመሳሰሉት ጉዳዮች ሲታሰቡ ቀዳሚው ተጠቃሽ ቴክኖሎጂ መሆን ችሏል፤ ዓለም አንድ መንደር ሆናለች ሲባልም ቴክኖሎጂው ይዞት የመጣው ሰፊ እድል ነው።
ግብይት፣ የገንዘብ ዝውውር እየተሳለጠ፣ የትምህርቱ፣ የጤናው፣ ወዘተ ዘርፎች ስራም በርቀት ጭምር እየተፈጸመ ነው። ግብርናው፣ ደህንነቱ፣ መከላከያው፣ ወዘተ ያለዲጂታል ቴክኖሎጂ ብዙ ሊቀላጠፍ ውጤታማ ሊሆን የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ቴክኖሎጂውን መጠቀም አማራጭ ሳይሆን የግድ እስከመሆን ደርሷል።
ይህ ቴክኖሎጂ በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለ፣ ተገቢው ጥበቃ ካልተደረገለት ሊያስከትል የሚችለው ጉዳትም የዚያኑ ያህል መሆኑ እየተጠቆመ ይገኛል። በሳይበር ጥቃቶች የተነሳ ከፍተኛ ጉዳቶች እየደረሱ ናቸው፤ ሊደርሱ ይችላሉ የሚሉ ስጋቶችም ብዙ ናቸው። የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች ብዙዎቹ ሊደርሱ ይችላሉ የተባሉ ጉዳቶችን ከመድረሳቸው በፊት እንዲመክኑ እየተደረገ እንጂ ጉዳቱ አስከፊ ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም መረጃ እንደሚያመላክተው፤ በቀጣይ አስር ዓመታት በዓለም ላይ ከሚከሰቱ ከፍተኛ አደጋዎች መካከል ከአየር ብክለት፣ ከሀሰተኛ መረጃ ስርጭት፣ ከአክራሪነትና ከኑሮ ውድነት በመቀጠል በአምስተኛ ደረጃ የዓለማችን ስጋት ተብሎ የተቀመጠው የሳይበር ጥቃት ሆኗል። የሳይበር ጥቃት ባሕሪው አለማቀፍና ድንበር የለሽ በመሆኑ የዓለም አገራት ሁሉ ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል።
የሳይበር ደህንነት ስጋት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሳይበር ጥቃቶች የሚያስከትሉት ኪሳራ ተበራክቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳይበር ጥቃት እ.ኤ.አ በ2022 የስምንት ነጥብ 44 ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሷል፤ እ.ኤ.አ በ2027 በዚሁ ጥቃት ሊደርስ የሚችለው ጥቃት ከፍተኛ መሆኑ እየተገለጸ ነው፤ በዚህ ጥቃት ብቻ ሊደርስ የሚችለው ኪሳራ ወደ 23 ነጥብ 84 ትሪሊዮን ዶላር ይሆናል ተብሎ ተገምቷል።
ኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነቷ እየሰፋና እየጨመረ መጥቷል። በኢትዮጵያ የተከሰቱ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን ስንመለከትም በ2015 ዓ.ም ስድስት ሺ 959 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች የደረሱ ሲሆን፤ ይህ አሃዝ በ2016 ዓ.ም ወደ ስምንት ሺ854 ከፍ ብሏል። ከነዚህም ውስጥ ከፍተኛው ድርሻ የሚይዙት በቁልፍ መሰረተ ልማቶች ላይ የተሞከሩ ጥቃቶች ናቸው።
ሳይበር ጥቃት እየጨመረ መምጣቱ ደግሞ አገራት ራሳቸውን መከላከል እንዳለባቸውና የዜጎቻቸውና የተቋሞቻቸው የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግን የሚጠይቅ ነው። በዚህም የተነሳ ‹‹የሳይበር ደህንነት›› ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥቅምት ወር እንዲካሄድ ውሳኔ ላይ ተደርሶ በየዓመቱ እየተካሄደ ይገኛል።
‹‹የሳይበር ደህንነት›› ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለአምስተኛ ጊዜ በመከበር ላይ ይገኛል። በአትዮጵያም በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አዘጋጅነት በሀገር አቀፍ ደረጃ ላለፉት አራት ዓመታት የሳይበር ደህንነት ወር ሲካሄድ ቆይቷል። ዘንድሮም ለአምስተኛ ጊዜ ‹‹የቁልፍ መሰረተ-ልማት ደህንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት›› በሚል በመሪ ሀሳብ እየተከበረ ይገኛል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ እንዳሉት፤ የዘንድሮው የሳይበር ደህንነት ወር ዋነኛ ትኩረት የሀገሪቱን ቁልፍ መሰረተ ልማቶች እና ተቋማት የሳይበር ደህንነት በመጠበቅ የሳይበር ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ከዚህ አኳያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ጥቃትን በመከላከል ረገድ የነቃ የሰው ልጅ ሚና ከፍተኛውን ቦታ የሚይዝ በመሆኑ የዜጎችን ብሎም የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊና ለማጎልበት የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን ቀርጾ በመስራት ላይ ይገኛል።
ቁልፍ መሰረተ ልማት ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ የጠቀሜታውን ያህል ደግሞ ጥቃት በሚደርስባቸው ጊዜ በዜጎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንዲሁም በሀገር ብሔራዊ ጥቅም እና ደህንነት ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ልዩና ጠንካራ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ይገልጻሉ።
በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታም ለዲጂታላይዜሽን ሽግግር የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ተከትሎ በርካታ የመንግሥትም ይሁኑ የግል ተቋማት አገልግሎታቸውን ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተደራሽ በሆነ መልኩ ለመስጠት አስችሏል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በቁልፍ መሰረተ ልማቶች እና መሰረተ ልማቶቹ በሚይዟቸው መጠነ ሰፊ መረጃዎችና ዳታዎች ላይ የሚደርሱ የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነቶችና ስጋቶችም እንዲሁ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በአንድ ተቋም ላይ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት ሌሎቹንም የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ሊያቋርጥ፣ ሊያስተጓጉል ወይም ሙሉ በሙሉ ሊያወድም ይችላል። ቴክኖሎጂው የጠቀሜታውን ያህል ጥቃት በሚደርስበት ጊዜ ከፍተኛ ውድመትና ኪሳራ ያስከትላል። ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ስለሚለዩበት ሁኔታ፣ ስለሳይበር ደህንነት ፕሮግራምና የደህንነት ማሕቀፎች፣ ስለተቋማት ኃላፊነትና የአስገዳጅ ሕግ ወይም ቁጥጥር በሚመለከት የሕግ ማሕቀፍ አለመኖሩ ሀገራዊ የሳይበር ደህንነትን በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዳይሆን በማድረግ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል።
ይህንንም መነሻ በማድረግ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በሀገሪቱ የቁልፍ መሰረተ ልማቶችን የሳይበር ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ በማዘጋጀትና በየደረጃ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ አጸድቆ ለማውጣት ለሚመለከተው አካል ተልኳል። ረቂቅ አዋጁ በዋናነት በሀገሪቱ ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን ለመለየትና ልዩ ጥበቃ ለማድረግ ወሳኝ ሚናን ከመጫወቱም ባሻገር የሀገሪቱን ዲጂታላይዜሽን ኢኒሼቲቮች ደህንነት በማረጋገጥ የሀገርን ደህንነትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ ጉልህ አስተዋፅዖ ይኖረዋል።
አስተዳደሩ ከሕግ ማዕቀፉ ባሻገር ሀገራዊ ቴክኖሎጂ በማረጋገጥ እንዲሁም የዘርፉን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል የሰው ኃይል በማልማት ረገድ የተለያዩ ሥራዎች በመስራት ላይ ይገኛል የሚሉት ዳይሬክተሯ፤ በዚህም በሀገሪቱ ቁልፍ መሰረተ-ልማቶች እና እነዚህን የሚያስተዳደሩ ተቋማት የሳይበር ደህንነት መረጋገጥ ለሀገራዊ የዲጂታል ሉዓላዊነት መረጋገጥ ያለውን አበርክቶ በማሳየት በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች መደላድል ለመፍጠር እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚመላከቱበት መሆኑን አስረድተዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው ዓለም ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በገባችበት በዚህ ጊዜ ከሳይበር ደህንነት ርእሰ ጉዳይ ውጪ ወቅታዊ እና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሌላ አብይ ጉዳይ ሊኖር አይችልም ይላሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ ቁልፍ መሠረተ ልማት ከማንኛውም ዘመናዊ ማኅበረሰብ መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው ነው። የእነዚህን መሰረተ ልማቶች ደህንነታቸውን ማረጋገጥ ባለንበት የዲጂታል ዘመን ሀገራዊ ሉዓላዊነታችንን ለመጠበቅ ወሳኝ ነው።
ስለ ዲጂታል ሉዓላዊነት ሲነሳ፣ አንድ ሀገር በዲጂታል ንብረቶቿ፣ ስርዓቶቿ እና ዳታዎቿ ላይ የመቆጣጠር ችሎታና አቅሙን ማዳበር እንዳለበት ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያም የዲጂታል ሀብቶቿን የመከላከል እና የመጠበቅ፣ ነፃ የቴክኖሎጂ ውሳኔዎችን የመወሰን እና የዜጎቿን ደህንነት እና ግላዊነት የማረጋገጥ አቅም ሊኖራት ይገባል ብለዋል። የሀገሪቱ ወሳኝ መሠረተ ልማቶች ማለትም የቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ የኢነርጂ፣ የፋይናንስ ሥርዓቶች፣ መጓጓዣ እና የጤና አጠባበቅ የመሳሰሉ ከዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ጋር በጥልቅ የተቆራኙ ናቸው። እነዚህ መሰረተ ልማቶች ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የጂኦፖለቲካል ተጽዕኖ ለመፍጠር መሰረቶች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ሀገር የዲጂታል መሠረተ ልማታችንን ስንገነባ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከወሳኝ ስርዓታቸው ጋር ስናዋህድ፣ የግድ በንቃትና በጥንቃቄ ሊከወን ይገባል የሚሉት አቶ ማሞ፤ የኃይል ማከፋፈያዎች፣ የባንክ ስርዓቶች፣ የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች ወይም የጤና አጠባበቅ ኔትወርኮች ላይ አንድ ጊዜ ጥቃት ከደረሰ በማህበረሰባችን ላይ ከፍተኛ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል አስገንዝበዋል።
ይህ ስጋት ቴክኒካል ስጋት ብቻ ሳይሆን ጂኦፖለቲካዊ አንድምታ ያለው መሆኑን ጭምር ጠቅሰው፤ የሳይበር ጥቃቶች የብሔራዊ ደኅንነትን ለአደጋ የማጋለጥ፣ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ የማሳጣት እና ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ባላት ቁመና ላይ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም እንዳለው ያብራራሉ።
‹‹ዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ የሳይበር ደህንነት ከሀገራዊ አጀንዳችን መካከል ግንባር ቀደም መሆን አለበት። የሀገራችንን ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ከጥቃት ለመጠበቅ ጠንካራ የፖሊሲና የሕግ ማሕቀፎችን፣ ሀገራዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን፣ በዘርፉ ብቁና ዓለማቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል ማልማት በእጅጉ ይጠይቃል›› ሲሉም አስታውቀዋል።
ከዚህ አኳያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሀገሪቱን የሳይበር ደህንነትና ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ኃላፊነት እንደተሰጠው ተቋም፤ ዘርፉ የሚመራበትን የሕግ ማሕቀፎችን ከማውጣት፣ ሀገራዊ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን በማረጋገጥ፣ እንዲሁም በዘርፉ ብቁ የሆነ የሰው ኃይልና አመራር በማፍራት ረገድ ተጨባጭ ሥራዎችን መስራቱን አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የሳይበር ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። የግሉ ሴክተር ከሀገራዊ ደህንነት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን እንደ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ ፋይናንሺያል እና ኢነርጂ ያሉ በርካታ ስርዓቶችን በባለቤትነት ያስተዳድራል። የሳይበር ስጋቶችን ለመከላከል አንድ ወጥ የሆነ መከላከያ አማራጮችን ለመተግበር በመንግሥት እና በኢንዱስትሪ መካከል ያለው ትብብር አስፈላጊ ነው። አንድ ላይ መረጃን መጋራት፣ ውስን የሆነውን የሕዝብ ሃብት በጋራ በመጠቀምና በትብብር በመስራት ሊከሰቱ የሚችሉ የሳይበር ጥቃት አደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት ያስችላል።
ይህ የሳይበር ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ወር የሳይበር ደህንነት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ወይም በየተቋማቱ ያሉ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሁላችንንም-የጋራ ኃላፊነት መሆኑን የሚያስታውስ ሁነት ብለዋል።
ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ለመጠበቅ እያንዳንዱ የመንግሥት ተቋም፣ የንግድ ድርጅት እና ግለሰብ በዚህ ላይ ሚና አላቸው። በሁሉም የሕብረተሰብ እርከኖች ግንዛቤን ማሳደግ ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ደረጃን ለማሻሻል በጣም ውጤታማ ከሆኑ መንገዶች አንዱ ነው። በትምህርታዊ ዘመቻዎች፣ በማኅበረሰብ ተሳትፎ እና በስልጠና ተነሳሽነት ዜጎቻችን የኢትዮጵያን ዲጂታል ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማብቃት ይገባናል ሲሉ አስገንዝበዋል።
በተለይም የመገናኛ ብዙሃን የማኅበረሰቡን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊና ግንዛቤ ከፍ የሚያደርጉ አስተማሪ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ያሉት አቶ ማሞ፤ ‹‹አምስተኛውን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ወርን ስናከብር ምን ያህል ርቀት እንደሄድን ነገር ግን ምን ያህል መሄድ እንዳለብን እናስብ ሲሉም አስታውቀዋል። የሀገሪቱን ወሳኝ መሠረተ- ልማቶች ከጥቃት መጠበቅ የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ መጠበቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘመን ሉዓላዊ፣ ነጻ እና ጠንካራ ሆና እንድትቀጥል ማድረግ ነው›› ይላሉ።
የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የቁልፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፣ የንግድ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች፣ በሳይበር ደህንነትና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ) ዘርፍ የተሰማሩ አካላት እንዲሁም ሁሉም ዜጋ ለወሳኙ መሠረተ ልማት ደህንነት መጠበቅ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት እንዲያከናውኑም አቶ ማሞ አሳሰበዋል። ‹‹በጋራ፣ አስተማማኝ፣ ሉዓላዊት ዲጂታል ኢትዮጵያን መገንባት የምንችለው በጋራ ተቀናጅተን መስራት ስንችል ነው›› ሲሉም ተናግረዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም