ዓለም አቀፍ የታዳጊዎች ሜዳ ቴኒስ ውድድር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለአንድ ሳምንታት ተካሄዶ ተጠናቋል። ኢትዮጵያ በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በወንዶች ጥንድ ፉክክር የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግባለች።
ከሃያ በላይ የዓለም ሀገራት የተሳተፉበት ይህ ውድድር በኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽንና በዓለም አቀፉ የቴኒስ ፌዴሬሽን ትብብር ከጥቅምት 4 ጀምሮ በአዲስ አበባ ቴኒስ ክለብ ሲካሄድ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ሲጠናቀቅ፣ ሰባት ቀናትን በፈጀው ፉክክር ኢትዮጵያ በአስራ ሦስት ወንድና ስድስት ሴት በድምሩ በ19 ስፖርተኞች ተሳትፋለች።
በሁለቱም ጾታዎች በጥንድና ነጠላ ውድድሮች የሚደረጉ ፉክክሮች ፍፃሜ ሲያገኙ ኢትዮጵያ በወንዶች ጥንድ የወርቅ ሜዳሊያ በማሳካት በስፖርቱ ታሪክ አዲስ ነገር አሳክታለች። ይህን ሜዳሊያ ማስመዝገብ የቻሉትም ዳዊት ሸለመና ዳዊት ፍሰሃ ጥንድ ሆነው ባደረጉት ፉክክር ነው። ሁለቱ ታዳጊ ሞክሼዎች ከጃፓን እና ሕንድ ተወዳዳሪዎች ጋር እልህ አስጨራሽ ፉክክር በማድረግ 64 ለ 25 እና 10 ለ 5 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ድል ማድረግ ችለዋል። በዚህም መሰረት በወንዶች ጥንድ ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያውን ለመጀመሪያ ጊዜ ስታሳካ፣ ጃፓንና ሕንድ የብር፣ ግሪክ፣ ፖላንድና ደቡብ ኮርያ የነሐስ ሜዳሊያን አስመዝግበዋል። በሴቶች ጥንድ ውድድር ደግሞ አሜሪካና ሕንድ የወርቅ፣ ብራዚል የብር፣ ኬንያና ሕንድ የነሐስ አሸናፊ መሆን ችለዋል፡፡
በወንዶች ነጠላ ውድድር ጃፓን የወርቅ፣ ሕንድ የብርና ግሪክ የነሐስ ሜዳሊያ በመውሰድ አጠናቀዋል። በሴቶች ነጠላ እንዲሁ ሕንድና ብራዚል የወርቅና የብር፣ ሕንድና አሜሪካ የነሐስ ሜዳሊያ ወስደዋል፡፡
ከሃያ በላይ ሀገራት ተወጣጡ 19 ሴትና 32 ወንድ በድምሩ 51 ስፖርተኞች ጠንካራ ፉክክርን ባደረጉበት መድረክ በአዋቂዎች መካከል የሚደረገው ውድድር እስከ ጥቅምት 17 የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቴኒስ ውድድሮችን ስታዘጋጅ የመጀመሪያዋ አይደለም። በታዳጊዎች ለአራተኛ ጊዜ እንዲሁም በአዋቂዎች ለሁለተኛ ጊዜ በጥቅሉ ለስድስት ጊዜያት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገዳ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ሜዳ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታምራት በቀለ፣ በመጀመሪያው ዙር የታዳጊዎች ውድድር ማጠናቀቂያና ሁለተኛ ዙር የወጣች ውድድር ማስጀመሪያ መርሃግብር ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ ውድድሩን በማዘጋጀቷ በርካታ ስፖርተኞችን የማሳተፍ እድል ፈጥሮላታል። ይህም ከሀገር ውጪ የሚደረጉ ውድድሮች ላይ በበጀትና ሌሎች ችግሮች ምክንያት ከሁለት ተወዳዳሪ በላይ ለመላክ እንቅፋት የነበሩ ችግሮችን እንደቀረፈ አክለዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በውድድሩ ልምድ ከመቅሰም በላይ ተፎካካሪ ሆና ሜዳሊያ ማስመዝገቧ ስኬት መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ውድድሩን ማዘጋጀቷ ከስፖርታዊ ጥቅምም ባለፈ ከተለያዩ ሀገራት በሚመጡ የስፖርት ቤተሰቦች ገጽታዋን ለመገንባትና ስፖርት ቱሪዝምን ለማስፋፋት ትልቅ ሚና እንዳለው አቶ ታምራት ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ከዚህ በፊት ከተካሄዱት ውድድሮች አንጻር የማስተናገድ አቅም፣ የመወዳደሪያ ስፍራዎች መሻሻል፣ የተሳታፊ ስፖርተኞች ቁጥር መጨመርና ውድድሩን የማሸነፍ አቅም ከፍ ማለቱን አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያስተናገደችው ሌላው የ2024 የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮናም ከጥቅምት 2 እስከ 9/2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲካሄድ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ፍፃሜ
ሲያገኝ ኢትዮጵያ ሁለት ሜዳሊያዎችን አስመዝግባለች። በቡድን፣ በድብልቅ ፆታ፣ በጥንድና በነጠላ በአጠቃላይ በሰባት የውድድር ዓይነቶች ሀገራት ተፎካካሪ በሆኑበት በዚህ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ቡድንና በነጠላ ውድድር ጥሩ ተፎካካሪ ሆና ሶስተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎችን አስመዝግባለች።
ለ27ኛ ጊዜ በተካሄደው የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮና ግብፅና ናይጄሪያ የበላይ ሆነው ሲያጠናቅቁ፣ ኢትዮጵያ ካስመዘገበችው የነሐስ ሜዳሊያ በተጨማሪ በነጠላ ውድድር ዱፌራ መኮንን የነሐስ ሜዳሊያ አስመዝግቧል። ተጫዋቹ ከማጣሪያው ጀምሮ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ብቃቱን ያሳየ ሲሆን በታሪክ ግማሽ ፍጻሜ በመግባት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሆን ችሏል። በማጣሪያው ፉክክር ተጋጣሚው 4 ለ 1 በሆነ ውጤት በመርታት ወደ ሩብ ፍጻሜ ያለፈው ዱፌራ፣ በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ግብጻዊውን ኤል-ቤኢአሊ መሀመድን 4 ለ 2 በመርታት የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ ሆኗል። ኢትዮጵያ በውድድሩ በአጠቃላይ ከግብጽ፣ ናይጄሪያና አልጄሪያ በመቀጠል በሁለት ሜዳሊያዎች አራተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሯን አጠናቃለች፡፡
ኢትዮጵያን ይህን ውድድር በማስተናገዷ የማወዳደሪያ ቁሳቁሶች፣ የባለሙያዎች ስልጠና እና ከረጅም ዓመት በኋላ የተመዘገበው አበረታች ውጤት ማግኘት ችላለች። ከውድድሩ ጎን ለጎንም የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤን አስተናግዳ በስኬት ከማጠናቀቋም በተጨማሪ፣ በአህጉር አቀፉ ኮንፌዴሬሽን በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነት ቦታን መያዝ ችላለች፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም