በኢትዮ ቴሌኮም የድርሻ ሽያጭ ሀገር እና ሕዝብ ምን ያህል ይጠቀማሉ ?

ኢትዮጵያ በመንግስት ይዞታ ስር ያሉ ድርጅቶችን የተወሰነ ድርሻ ወደ ሕዝብ ለማስተላለፍ እንቅስቃሴ ጀምራለች። እንቅስቃሴውም በኢትዮ ቴሌኮም ተጀምሯል። ባለፈው ሳምንትም ኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶውን ድርሻ ለሕዝብ ማቅረቡን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ አድርገገዋል።

በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ ኢትዮ ቴሌኮም ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ኩባንያ ነው። በተቃራኒው ሳፋሪኮም የቅርብ ዓመታት ታሪክ ነው ያለው። ነገር ግን ሳፋሪኮም የብዙ ባለሀብቶችና ስራ ፈጣሪዎች ኩባንያ ስለሆነ ኬኒያ ሳይበቃው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለማልማት ችሏል።

እድሜ ጠገቡ ኢትዮ ቴሌኮም ብዞዎችን የማሳተፍ ልምምድ መፍጠር ባለመቻሉ፤ ከኢትዮጵያ አልፎ ጎረቤት ሀገራት ላይ መስራት አልቻለም። ስለዚህ የድርሻ ገበያ መጀመር ሌሎች ሀገራት በመሄድ ከገበያው ጋር የመሻማት፣ የመስጠት እና የመቀበል ዕድል ያገኛል። የኢትዮ ቴሌኮም የድርሻ ገበያ መጀመር ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የምስራች እንደሚሆንም ገልጸዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው አጠቃላይ የኩባንያው ድርሻ መቶ ቢሊዮን ብር ነው። ከዛ ውስጥ 10 በመቶው ነው ለኢትዮጵያውያን የቀረበው የባለቤትነት ድርሻ። ይህም 100 ሚሊዮን ድርሻ ሲሆን አንዱ በ300 ብር ሲሸጥ አጠቃላይ የቀረበው ድርሻ የ30 ቢሊዮን ብር ዋጋ እንዳለው ነው የገለጹት።

ዛሬ የዝግጅት ክፍላችን ኢትዮ ቴሌኮም ለገበያ ያቀረበው 10 በመቶው ድርሻ ለሕዝብ እና ለመንግስት ያለው ፋይዳ ምንድነው በሚለው ዙርያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን አነጋግሯል።

የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ዳዊት ተሻለ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ኢትዮ ቴሌኮም መንግስት በወሰነው መሰረት 10 በመቶውን ድርሻ ለሕዝብ እሸጣለው ሲል ኩባንያውን ወደ ግል ዘርፍ በማዞር ሂደት ውስጥ የባለቤትነት ድርሻውን ለሕዝብ ማካፈል ማለት ነው።

በአብዛኛው እንደ ባንክ እና ቴሌኮም ያሉ ዘርፎች ከደህንነትም አንጻር ለረጅም ግዜ መንግስት ይዞት የቆየው ነው። ግን አሁን በተጀመረው መንገድ የባንክ ዘርፉ ለውጮች ክፍት እያደረገ ነው። እንደዚሁም የቴሌኮሙን መጀመሪያ ለሀገር ውስጥ እድሉን ሰጥቶ በመቀጠል ወደ ሌሎች እንደሚሄድ ጅማሮውን ለማሳየት ነው 10 በመቶ ጅርሻ እድል የሰጠው ።

ይህ እንደመግስት ተቋም አዲስ ባይሆንም፤ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የመጀመሪያው ጅማሬ ነው የሚሉት ዳዊት (ዶ/ር)፤ በዚህም ለዜጋው አዲስ የገበያ እድል ተከፈተ ማለት ነው።

ባለሙያው እንደሚናገሩት የአክሲዮን ድርሻው መሸጡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሕዝቡ ጠቀሜታ አለው። የመጀመሪያ አንድ ግለሰብ 10 ሺህ ብር አካባቢ የሚጠጋ ገንዘብ አውጥቶ ዝቅተኛውን ድርሻ ሲገዛ የኔ የሚለው ኩባንያ ይኖረዋል ወይም ንብረት የማፍራት ዕድል ይፈጠርለታል።

በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ የኢንቨስትመንት ወይም የንግድ አማራጭ እንደሚሰጥ በመግለጽ፤ በሀገር ደረጃ የተለመዱት የንግድ አማራጮች የሸቀጣ ሸቀጥ እቃዎችን መነገድ፤ ምርቶችን አምርቶ ለገበያ የማቅረብ እና ቤት ገንብቶ ከመሸጥ ውጭ አዳዲስ የገቢ አማራጮች መኖራቸውን ለሕዝብ ያስተዋውቃል። በአክሲዮን የመገበያየት ሂደትን ለሀገራችን ለማስዋወቅ ያግዛል።

ከዚህ ውስጥ ምን ያህል ሕብረተሰብ ይጠቀማል የሚለው ሲታይም፤ በተቀመጠው ከፍተኛ አክሲዮን የመግዛት ጣራ መሰረት ሁሉም ሰው የአንድ ሚሊዮን ብር አክሲዮን ቢገዛ 30 ሺህ ሰው ኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ የባለቤትነት ድርሻ ይኖረዋል። የአንድ ሚሊዮን ብር መግዛቱ ቀርቶ ሁሉም ሰው የ100 ሺህ አክሲዮን መግዛት ቢችል፤ ኩባንያው 300 ሺህ የሚደርስ ዜጋ የባለቤትነት ድርሻ ይኖረዋል። የሚገዛበት ገንዘብ ዝቅ እያለ በመጣ ቁጥር የባለቤቶቹ ቁጥር ከፍ ይላል በማለት ያስረዳሉ።

ባለሙያው እንደሚያስረዱት፤ ከኩባንያው አንጻር ደግሞ ሲታይ በአክሲዮን ሽያጭ 30 ቢሊዮን ብር ወደ ኢኮኖሚው ያገባል። በሁለት መልኩ ሲታይ ለመንግስት ከሚያመነጨው ገቢ እና ለቴሌ እራሱን ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር 30 ቢሊዮን ብር ቀላል አይደለም።

የገቢ ግብር መንግስት ገቢ የሚያገኝበት አንዱ መንገድ እንደመሆኑ በአክሲዮን ሺያጩ የሚገኘው የአገልግሎት ክፍያ እና 15 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ መንግስት ከፍተኛ ገቢ ያገኛል። ይህም መንግስትን ይደጉማል፤ የገቢ ምንጩንም ያሰፋል ይላሉ።

ከኩባንያው አንጻር ደግሞ በሚያገኘው ገቢ አገልግሎቱን በማዘመን እና በማስፋፋት ተወዳዳሪነቱን እንዲያሳድግ ያግዘዋል። እንደ ሳፋሪኮም አይነት ድርጅቶች እየመጡበት ስለሆነ ከአከሲዮን ሽያጭ በሚያገኘው ገቢ የአገልግሎት ጥራት ለማዘመን እና የቴሌኮም አገልግሎት በማስፋፋት ረገድ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ያስችለዋል በማለት ይገልጻሉ።

ዳዊት (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፤ ይህን ሽያጭ በማድረግ መንግስት እስከ 33 ቢሊዮን ብር የማግኘት እድል ስለሚኖረው፤ ትልቅ የገንዘብ አቅም ይፈጥርለታል። በሁለተኛ ደረጃ መንግስትም ገቢ በማግኘት ያቀዳቸውን የልማት ግቦች እንዲያሳካ ይረዳዋል። በረጅም ግዜ ደግሞ የግብር መሰረቶቹን ያሰፋለታል ።

የግሉ ዘርፍ ወደ ቴሌኮም መግባቱ ገቢ ከማግኘት አንጻር የውስጥ አሰራሩን ውጤታማ ያደርገዋል። ያሉትን ሀብቶች በተገቢው መንገድ በመጠቀም ኩባንያው ገቢው እንዲያድግ፣ ወጪው እንዲቀንስ በማድረግ፤ አዳዲስ እውቀቶችን ይዘው የሚመጡ የቦርድ አባላት፣ የአስተዳደር አካላት ሊኖሩ ይችላሉ ሲሉ ይናገራሉ።

ሌላው ኩባንያው እየተስፋፋ ሲመጣ ኢንቬስተሮችን የመሳብ አቅሙ እያደገ ይመጣል። የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታንም ያስፋፋል ይላሉ። ሆኖም አክሲዮን በማስተዳደር ሂደት ውስጥ ችግር እንዳይፈጠር የሕግ ማእቀፉ የሰፋና የተደራጀ መሆን አለበት። እንደ ሀገር የካፒታል ገበያ አሰራር አዲስ እየገባበት ያለ እንደመሆኑ ከወዲሁ በቂ እውቀት በመሰብሰብ ተቋም ግንባታ ላይ በደንብ መስራት ያስፈልጋል፡ ይላሉ፡

የአክሲዮን ሽያጩ በቴሌ ብር እየተከናወነ እንደመሆኑ፤ በሺዎች ዘንድ የጥቅም ግጭት እንዳይፈጠር፣ የአክሲዮን ሽያጩ 30 ቢሊዮን ብር ሲደርስ ቶሎ ብሎ ሽያጩን መዝጋት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፤ በቀጣይ ሼሮችን በማስፋት የውጭ ምንዛሬ ማግኛ መንገድ መታሰብ አለበት። ሌላው ከሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ ለሕብረተሰቡ አንገብጋቢ በሆነ ጉዳይ ሊውል እንደሚገባም ሀሳባቸውን ያስቀምጣሉ።

በፖሊሲ ጥናት ኢንስትቲዩት ተመራማሪ እና የኢኮኖሚ ባለሙያ ጀማል ሞሀመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ 10 በመቶ ድርሻ ማለት የኩባንያው አጠቃላይ ሀብቱ እና ትርፍ ተደምሮ ዓለም አቀፍ ገማቾች ባስቀመጡት መሰረት የኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ ዋጋ 100 ቢሊዮን ብር ነው በሚል ሃሳብ ይጀምራሉ ።

የ100 ቢሊዮን 10 በመቶ ደግሞ 10 ቢሊዮን ብር ነው። ስለዚህ አሁን ኩባንያው 10 ቢሊዮን ብሩን ወደ አክሲዮን ቀይሮ እየሸጠ ነው። 10 በመቶ ድርሻ የሚለው ነገር በአጭሩ ይህን ነው የሚያመለክተው ይላሉ።

አክሲዮኑ የቀረበበት ዋጋ የተጋነነ ነው የሚሉት ባለሙያው፤ የ10 ቢሊዮን ብር ሼር አቅርበው 30 ቢሊዮን ብር ነው ለማግኘት የታቀደው። አንድ የአክሲዮን ድርሻ የ100 ብር ዋጋ ነው ያለው። ነገር ግን የቀረበው በ300 ብር ነው። በዚህም አክሲዮኑ ያለው ዋጋ እና ገበያ ላይ የቀረበው ዋጋ በሁለት እጥፍ የጨመረ መሆኑን ያስረዳሉ።

ጀማል (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ ባለፈው ዓመት ኩባንያው ያተረፈው ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ነው። በዚህ መሰረት ትርፉ 20 በመቶ ማለት ነው። ነገር ግን ሁለት እጥፍ የገበያ ዋጋ ተጨምሮበት ሲሸጥ ስድስት በመቶ ማለት ነው።

አንድ ሰው ብሩን ባንክ ቤት ቢያስቀምጥ ሰባት በመቶ ወለድ ያገኛል። ድርሻው የቀረበበት ዋጋ የተጋነነ ነው። ከኢኮኖሚክስ አንጻር ስድስት በመቶ እና ከዛ በታች ትርፍ የሚያስገኝ ከሆነ ገንዘቡ ባንክ ቤት ቢቀመጥ ሰባት በመቶ ትርፍ ስለሚያስገኝ የቴሌ የአክሲዮን ሽያጭ ከዚህ አንጻር ጥያቄ የሚነሳበት መሆኑን ያስረዳሉ።

ባለሙያው እንደሚያስረዱት፤ 10 በመቶ ድርሻ 100 ሚሊዮን ድርሻ ከሆነ ኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ የኩባንያውን ድርሻ አንድ ቢሊዮን ድርሻ ማለት ነው። አንድ ቢሊዮን የአክሲዮን ድርሻ ከሆነ አጠቃላይ የካምፓኒው ዋጋ ለድርሻው ይካፈላል። 100 ድርሻም ከሆነ አጠቃላይ የካምፓኒው ዋጋ ለሼሩ ይካፈላል።

አክሲዮኑ በ100 ብር ወይም በአንድ ሺህ ብር መቅረቡ ሳይሆን ተጽኖ የሚያደርገው አጠቃላይ የካምፓኒው ዋጋ ምን ያህል ነው የሚለው ነው። የአንድ አክሲዮን ዋጋ ትንሽ ሲሆን የባለቤቱ ቁጥር ይቀንሳል። ዋጋው ሲቀንስ ደግሞ የባለአክሲዮኖች ቁጥር ይጨምራል ሲሉ ያስረዳሉ።

የአክሲዮኑ ዋጋው ሲጨምር ደሀው ማኅበረሰብ ላይሳተፍ ይችላል። ከኢትዮ ቴሌኮም ግን ከ10 ሺህ ብር ጀምሮ ሰው ድርሻ ሊገዛ ይችላል። በዚህም በተሳትፎ ደረጃ በርካታ ሰዎችን ያሳትፋሉ። በኢኮኖሚ እይታ ግን ጥቅሙ ዝቅተኛ ነው። ዓላማው በርካታ ሰው ድርሻውን ገዝቶ በባለቤትነት አገልግሎቶቹን እንዲገዛ እና ያለውን ፉክክር ለማዳከም ይመስለኛል ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ምናልባት በቀጣይ የኩባንያው ትርፉ ሊጨምር ይችላል። ነገር ግን አሁን ባለው ትርፍ አያዋጣም። ሰው አክሲዮኑን ቢገዛ ጥሩ ነው። ነገር ግን በተጋነነ ዋጋ ከሚቀርብ አንድ አክሲዮን በ100 ቢቀርብ ጥሩ ነበር ይላሉ።

የኢኮኖሚ ባለሙያ እና የፖሊሲ አማካሪው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮ ቴሌኮም እያደረገ ያለው አሳታፊነትን ለማሳየት የታሰበ ነው። ምክንያቱም ኢትዮ ቴሌኮም አክሲዮኑን ያቀረበበት መነሻ ዋጋ ትንሽ ነው። እናም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሊገዛው የሚችል ነው።

10 በመቶውን ድርሻ በመሸጥ የታሰበው 30 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ነው። በዚህም ኩባንያው አሰራሩን ለማዘመን፤ አዳዲስ እቃዎችን ለማስገባት እና አገልግሎቶችን ለማስጀመር በተለይም ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋራ ሰፋ ያሉ ስራዎች ስለሚጠበቁ ለዛ ሊውል ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮም የመንግስት እንደመሆኑ፤ ገንዘቡን ለማሰባሰብ የፈለገበት ምክንያት ሊኖር ይችላል ሲሉ ሀሳባቸውን ያስቀምጣሉ።

ኢትዮ ቴሌኮም አትራፊ ድርጅት ከመሆኑም በተጨማሪ ከፍተኛ ግብር ከፋይ ነው። የሚሉት ባለሙያው፤ የአክሲዮን ዋጋው ዝቅተኛ መሆን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በቁጠባ ሂሳቡ ላይ ያለውን ገንዘብ ሼሩን በመግዛት የተሻለ ውጤት እንዲያገኝ ያስችላል ይላሉ።

ቆስጠንጢኖስ ዶ/ር እንደሚገልጹት፤ ኢትዮ ቴሌኮም ሆነ መንግስት ከአክሲዮን ሽያጭ በሚገኘው ገንዘብ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለማስፋፋት ያስችለዋል። አክሲዮኑን ገዢዎች በሰባት በመቶ ወለድ 300 ብር ባንክ ቢያስቀምጥ የሚያገኘው ገንዘብ እና ኩባንያው በዓመቱ አትራፊ ሆኖ የሚሰጠው ገንዘብ ከዚህ የበለጠ ነው።

ባንኮች በያመቱ ለባለ አክሲዮኖች ከ40 እስከ 60 በመቶ ድረስ የትርፍ ክፍፍል ይሰጣሉ። ስለዚህ አንድ ሰው ብሩን ባንክ አስቀምጦ ሰባት በመቶ ወለድ ከሚያገኝ፤ የባንኮቹን አክሲዮን ቢገዛ የተሻለ ገንዘብ ያገኛል ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።

ለምሳሌ አንድ ሰው ብሩን ባንክ ከሚያስቀምጥ የ100 ብር የባንክ አክሲዮን ቢገዛ 60 በመቶ የሚያተርፍ ከሆነ በዓመት 60 ብር ያገኛል። በሁለት ዓመት ገንዘቡ ተመላሽ ይሆናል ወይም ደግሞ አክሲዮኑ እጥፍ ይሆናል። ነገር ግን ይሄ ብር ባንክ ቢቀመጥ 14 ብር ብቻ ነው የሚያገኘው ሲሉ ይገልጻሉ።

ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፤ ኩባንያው እንደ ፋብሪካ እቃ ብቻ የሚያመርት ወይም አገልግሎት ብቻ የሚሰጥ አይደለም። ስልክ የመደወል አገልግሎት፣ የኢንተርኔት አገልግሎት እና ሌሎች የተለያዩ ዘርፎች ላይ ይሰራል። ወደፊት የክሪፕቶ ገንዘቦች ወደ ስራ ከመጡ እነሱን ይጠቀማል። ስለዚህ ድርጅቱ አትራፊ ስለሆነ አክሲዮን ገዢዎች ተጠቃሚ ናቸው።

ለሕዝብ የዞረው ድርሻ 10 በመቶ እንደ መሆኑ ባለአክሲዮኖች በዓመት የሚያገኙት የትርፍ ድርሻ 10 በመቶ ነው። ለአብነትም ኩባንያው 100 ብር ቢያተርፍ 90 ብሩ የኩባኒያው ሲሆን 10 ብሩ ደግሞ የባለአክሲዮኖች ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

በመንግስት የተያዙ ድርጅቶች ለግሉ ዘርፍ በማዛወር መንግስት በዋና ስራዉ እንዲያተኩር ነው። ሀገር የመጠበቅ፣ ሕዝብ የማስተዳደር እና ሕዝብ ከድህነት ወለል እንዳይወርድ የማድረግ ስራዎች ለመስራት እና በአክሲዮን ሽያጭ በሚገኘው ገቢ ደግሞ ሌሎች የልማት ስራዎችን ለመስራት ታስቦ ነው ካፒታል ማርኬት የተቋቋመው ይላሉ።

ሌላው ደግሞ ድርጅቶቹ ከመንግስት ቁጥጥር ሲወጡ፤ እነዚህን ድርጅቶች መንግስት በተለያዩ መንገድ ሲያደርግላቸው ከነበረው የድጎማ ጫና ይወርዳል። አብዛኛው ስራ በተቋሙ የሚሰራ እንደመሆኑም የተቋሙን አቅም ለማጠናከር ይረዳል በማለት ይናገራሉ።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንደሚገልጹት፤ መንግስት ኢትዮ ቴሌኮምን በከፍተኛ ሁኔታ ሲደጉም ነው የኖረው፤ ሶስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ከቻይና ተበድሮ ነው እስካሁን ድረስ ኩባንያውን በዘመናዊ መልክ ያቋቋመው። ካሁን በኋላ ግን ኩባንያው አክሲዮን እየሸጠ ስራውን እያስፋፋ ይሄዳል። ሁለተኛ ደግሞ ለመንግስት ፈሰስ እያደረገ በማኅበራዊ ልማት ውስጥ ይሳተፋል። በተጨማሪም የግል ዘርፉ በማይገባበት ዘርፍ መንግስት እየገባ ይሰራል በማለት ያስረዳሉ።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም

Recommended For You