(ክፍል አንድ)
“ሁሉም ጦርነቶች ሁለት ጊዜ ይካሄዳሉ ። አንደኛ በጦር ግንባር ፤ ሁለተኛ በአዎንታዊነት አልያም በአሉታዊነት ጥለውት በሚሔዱ ትዝታዎች ወይም ጠባሳዎች ፤ “ ይላል ታዋቂው ደራሲ ትውልደ ቬትናማዊ አሜሪካዊ ቬት ታንህ ንጉየን:: “አዎ የአድዋን ፣ የማይጨውን ፣ የሶማሊያን ፣ የሕወሓትን ፣ የኢትዮ ኤርትራን ፣ እንደገና የሕወሓትን ጦርነቶች ሁለት ሁለት ጊዜ አድርገናቸዋል ። መጀመሪያ በጦር ግንባሮችና ሁለተኛው ትተውት በሄዱት ትውስታ፣ ትዝታ ፣ ጠባሳ ፣ ቁስል ፣ ሕመም ፣ ዳፋ እና ተጽዕኖ ፤ በተለይ ሕወሓት ለ17 ዓመታት ያካሄደው የሽምቅ ውጊያ ወይም ጦርነት መጀመሪያ በተለያዩ የጦር ግንባሮች በማስከተል ዛሬ ድረስ ባልሻሩትና ባልጠገጉት ጠባሳዎችና ቁስሎች የተከናወኑ ናቸው ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው አስደንጋጭ የጥናት ግኝት ቬት ታንህ እንዳለው ያልተቋጨው ሁለተኛው ጦር ግንባር አካል ነው ። ሕወሓት በ17 አመቱ የትጥቅ ትግል በጦር ግንባር ካካሄደው ጦርነት እና በ27 ዓመታት አገዛዙ ወቅት ከፈፀመው ግፍ ባሻገር ጥሎት የሄደው ያልሻረ ጠባሳ ፤ ያልጠገገ ቁስል እንዳለ ያረጋገጠ ነው ። ባለፉት 40 ዓመታት ከ60 ሺህ በላይ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አማራዎችን በማንነታቸው ምክንያት ጨፍጭፏል ። ትቶት የሄደው ቁስልና ጠባሳ ደግሞ ከቁጥር በላይ ግዙፍ ይነሳል። ከእነዚህ 60ሺህ ንጹሐን መጨፍጨፉ ጀርባ ያልታበሱ እንባዎች ፣ ያልተጽናኑ ነፍሶች፣ ያልጠገጉ ቁስሎች ፣ ያልሻሩ ጠባሳዎች፣ ያልተጠገኑ የተሰበሩ ልቦች፣ የፈረሱ ትዳሮች ፣ የፈረሱ ክህነቶች ፣ የተበተኑ ቤተሰቦች፣ የተዘጉ ደጆች ፣ ያለወላጅና አሳዳጊ የቀሩ ልጆች፣ ለንስሐና ፍታት ያልበቁ ነፍሶች ፣ ከቀያቸው የተሰደዱ፣ በኃይል የተፈናቀሉ፣ ወዘተረፈ አሉ። ይህ የዩኒቨርሲቲው አስደንጋጭ ግኝት ከአኅዝ በላይ መተንተን ፣ መተርጎም፣ መብራራትና መበየን አለበት።
የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ብዙኃን መገናኛዎቻችን በነጠላ ዜና ነው ያለፉት ። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትም ሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዓለማቀፍ አጀንዳ ሊያደርጉት ሲገባ ባላየ ባልሰማ ነው ያለፉት ። እነሱን ብሆን መስቀል አደባባይ ወይም በስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማዕታት ሐውልት ተገኝቼ ለዓለማቀፍ ሚዲያ በምስልና በቁጥር የታጀበ መግለጫ በመስጠት ከታሪካችን ባለመማራችን ታሪክ እራሱን እየደገመ መሆኑን አሳይ ነበር ። ሕወሓት ባስገነባው የሰማዕታት ሐውልት የእሱን ሰለባዎች ማጋለጥ አንድምታውን አስቡት!። የጣሊያኑ ፋሽሰት ግራዚያኒ በግፍ ለጨፈጨፋቸው ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የየካቲት ሰማዕታት ሐውልት መግለጫ መስጠት የሚፈጥረውን ዓለማቀፍ ትርጉም እዩት ።
እነሱ በሐሰተኛና የፈጠራ መረጃ አገሪቱን ያጠለሻሉ፤ እኛ እውነትን ታቅፈን እናላዝናለን። ከማዕቀብ አስጥሉን እያልን እንማጸናለን ። ከእኛ እውነት ይልቅ የአመነስቲ ኢንተርናሽናልና የሒውማን ራይትስ ዋች ሐሰተኛ መግለጫ ፣ የከሀዲው ዶ/ር ቴዎድሮስና የጳጳሱ ሐሰተኛና ነውረኛ መግለጫ አየሩን ሲቆጣጠረው እንደማየት የሚያም ነገር የለም። ነባሩ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥልቅ እንቅልፍ ላይ እያለ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሠራው አርዓያነት ያለው ተግባር በልኩ እውቅና ሊሰጠውና ሊወደስ ይገባል። ወደተነሳሁበት ሀሳብ ስመለስ፤በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኅብረተሰብ ጤና መምህር ፣ ተመራማሪና የጥናት ቡድኑ መሪ ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ በተለይም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በዚያ ሰሞን እንደገለጹት፤ በጥናትና ምርምር ውስጥ ዩኒቨርሲቲው አሸባሪው ሕወሓት ላለፉት
አርባ ዓመታት በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ላይ ያደረሰውን ኅልቆ መሳፍርት የሌለውን ወንጀል፣ ግፍና ጥቃት በጀት በመመደብ የሚመለከታቸው ባለሙያዎችን አዋቅሮ ወደ ቦታው በማሰማራት ለ15 ወራት ያደረገውን ጥናት የመጀመሪያ ግኝት ይፋ አደርጓል ። ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ አካባቢውን በወረራ ከያዘ ጊዜ አንስቶ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አማራዎች ባህላቸውን ፣ ቋንቋቸውንና ማንነታቸውን እንዳይገልጹ ይፈጸም የነበረውን ተጽዕኖ ለመለየት ዩኒቨርሲቲው ጥልቅና ሰፊ ጥናት አድርጓል፡፡ የምጣኔ ሀብት ዘረፋና ወረራ ፤ የጤናና ትምህርት አገልግሎት እንዳያገኙ ይፈጸም የነበር ደባ ፤ መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ ይፈጸም ግፍና ጭቆና አደባባይ እንዳይወጣ ይፈጸም የነበረውን አፈና ሳይቀር አካቷል ።
ጥናቱ በአካባቢው ያለውን ማኅበረሰብ በመሰብሰብ በቡድን ውይይት እንዲያደርግ በመጋበዝ ፤ የታሪክ አዋቂዎችን በመጠየቅ ፤ በደል ተፈጽሞብናል ብለው የሚያስቡ ሰዎችን በተለያዩ አግባቦች በማናገር ፤ ከዚያ በፊት በአስተዳደሩ ይኖሩ የነበሩና አሁን በምሕረት ወደ አካባቢው የተመለሱ ሰዎችን በመጠየቅ አጠቃላይ የነበረውን ግፍ የመለየት ጥናት ተካሂዷል ፡፡ አሁን ላይ በቀዬአቸው በሚኖሩ ዜጎች ላይ በተደረገ ቃለ-መጠይቅና በሌሎች 1ኛ ደረጃ ማስረጃዎች 19 በመቶ የሚሆኑ አባወራዎች አድራሻቸው እንዲጠፋ፤ 25 በመቶው ሕዝብ እንዲገደልና 29 በመቶ የሚሆነው ደግሞ አካባቢውን ለቆ እንዲሰደድ ተደርጓል፡፡
በአጠቃላይ 75 በመቶ የሚሆኑት የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አማራዎች እንዲገደሉ ፣ እንዲፈናቀሉና አድራሻቸው እንዲጠፋ መደረጉ በጥናቱ መረጋገጡን ረዳት ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡ አድራሻቸው የጠፋ ሰዎችን አስመልክቶ የጥናት ቡድኑ ባደረገው ምርመራ ሕወሓት በርካታ ሰዎችን “ባዶ ስድስት” በሚል ስያሜ በሚጠራው ስፍራ በጅምላ በማጎር ማኅበረሰቡ የሚደርስበትን ግፍ መረጃ እንዳያወጣ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ማኅበረሰቡ በጭንቀት ውስጥ እንዲኖርና ምንም አይነት መረጃ እንዳይሰጥ ለአርባ ዓመታት በነበረው አገዛዝ ውስጥ የስነልቦና ጫና ሲደረግበት ኖሯል።
በአካባቢው የጥናት ቡድኑ በደረሰበት ወቅት በሕወሓት የደረሰባቸውን ግፍ፣ ግድያ ፣ መፈናቀልና ሌሎች ጫናዎች እያወቁ መናገር አይፈልጉም ነበር ፡፡ ነገር ግን ቀስ በቀስ በተደረገው የማግባባት ሥራ አንድ ጅምላ መቃብር ጭምር እንደተገኘ ጠቅሰዋል ፡፡ በወልቃይት አድኖ ፣ ገሃነም፣ ተከዜ ውስጥ ያሉ የጅምላ መቃብሮች ፣ ትግራይ ክልል ውስጥ ደደቢትና ሌሎች ሶስት ቦታዎች ላይ ጠለምት ውስጥ ፍየል ውሃ ፣ ሰይጣን መጣያ በሚባሉ ቦታዎች የጅምላ መቃብር መገኘቱን የጥናት ቡድኑ ባደረገው ጥናት ማረጋገጥ መቻሉን ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አስታውቀዋል ፡፡ ሰዎች በጅምላ ሲታሰሩና ሲገደሉ እንደነበር በወቅቱ የከብት እረኞች ሳይቀር ያውቁ እንደነበር የጠቀሱት የጥናት ቡድኑ መሪ ፤ ወደፊት የሚወጡ ብዙ መረጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው 12 ከፍተኛ የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውን ጥናቱ አረጋግጧል ፡፡
ከነዚህም መካከል ሰፊ የሚባለውና በዚህ ዓመት በማይካድራ እንደተፈጸመው ጭፍጨፋ በርካታ ሰዎች የተሰቃዩበትና የተቀበሩበት “ገሃነም” በመባል የሚታወቅና ምንም አይነት መሠረተ ልማት የሌለውና ጭው ያለ በርሀ ውስጥ የሚገኘው ቀዳሚው ነው ። የዩኒቨርሲቲው የጥናት ቡድን አባላት በአካባቢው ከአሸባሪው የሕውሓት ቡድን ጋር በቅርብ ሲሰሩ የነበሩ ሰዎችን አግኝቶ በማነጋገር ባገኘው መረጃ ባለፉት 40 ዓመታት ከ60 ሺ በላይ የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ነዋሪዎች በግፍ ታስረው እንዲረሸኑ መደረጉን አስታውቋል፡፡
የጅምላ መቃብሮቹ በተጠናና በሚስጥር በተደራጀ መንገድ የወንዝ ተፋስስ መሠረት አድርጎ በመቀበራቸው በክረምት አጽሙ በጎርፍ እንዲወሰድ ተደርጓል ፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ለወደፊት በታሪክ እንዳይገኝና ማስረጃ ለማጥፋት መሆኑ ተገልጿል፡፡ አብዛኛዎቹ በተፋሰስ የተቀበሩ ሰዎች አጽም ወደ ተከዜ ወንዝ እንዲለቀቁ ተደርጓል፡፡ በጀርመን ናዚ አገዛዝ በአይሁዶች ላይ የተፈጸመውን ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ወንጀል ዩኒቨርሲቲዎች ሰፊ ጥናት በማድረግ እንደሰነዱትና እንደተነተኑት ሁሉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲም በወልቃይት ፣ ጠገዴ ፣ በጠለምትና በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በቀጣይ ይበልጥ በስፋትና በጥልቀት ለማጥናት የዘር ማጥፋት ወንጀል የጥናት ማዕከል እንደሚቋቋም ተጠቁሟል።
ሕወሓት ታሪክም ሆነ ትውልዶች የማይረሱትን ታላቅ ክህደትና የአረመኔነት ጥግ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም መፈጸሙን ተከትሎ መንግሥት ተገዶ የገባበትን ጦርነት ሆነ ፤ ለሰብዓዊነት ሲል የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ ከወጣ በኋላ ሕወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ ጦርነቱ ሁለት ሁለት ጊዜ ተካሂዷል ። ከፍ ብሎ እንደተገለጸው መጀመሪያ በጦር ግንባር በመቀጠል ጥሎት በሄደው ጠባሳና ቁስል። በማይካድራ ፣ በጋሊኮማ፣ በጭና ፣ በአንጾኪያ በገምዛ፣ በንፋስ መውጫ ፣ በቆቦ ፣ በውጫሌ ፣ በኮምቦልቻ ፣ ወዘተረፈ የተፈጸሙ ግፎችና ሰቆቃዎች ፤ በሁለቱ ክልሎች የተፈጸሙ ውድመቶችና ዘረፋዎች ትውልዶች በቁጭት ሲያስታውሷቸው የሚኖሩ ጦርነቶች ናቸው ።
አሸባሪው ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ ሲያሻው በሰብዓዊ ጋሻነት ፤ ለመደራደሪያነት በማገት ፤ ሌላ ጊዜ ነፍስ የማያውቁ ብላቴናዎቹን ከጉያው እየነጠቀ በሕዝባዊ ማዕበል ጦርነት በመማገድ ፤ በስሙ የሚላክለትን እርዳታ በመሸጥና ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲል እንዳይደርሰው መንገድ በመዝጋትና ድልድይ በማፍረስ በረሀብ እንደ ቅጠል እንዲረግፍ በማድረግ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመበትይገኛል ። የዚህ የሽብር ቡድን የኋላ ታሪኩ ሲፈተሽ በዘር ማጥፋት ወንጀል የተካነና በርካታ ማንነቶችን ኢላማ ያደረገ ስለሆነ ጥናቱ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ አገራዊ ሊሆን ይገባል ። ለዚህ ነው አሸባሪው ሕወሓት ለአገዛዝ የበቃውም ሆነ ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ ፤ ከለውጡ ወዲህም ከሶስት ዓመታት በላይ በትግራይ በመንበሩ የቆየው ፤ ሰሞነኛው የአማራና የአፋር ክልሎች የወረረው ዘር በማጥፋትና ዘር በማጽዳት የከረመ ልምምዱ እየተመራ ነው።
የሜሪያም ዌቢስተር የእንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ዘር ማጥፋትን/Genocide/እንዲህ በስሱ ይበይነዋል። “the deliberate and systematic destruction of a racial, political, or cultural group.” ወደ አማርኛ ሲመለስ፦ ሆን ብሎ፣ ዘይዶ ዘርን የፖለቲካ ወይም የባህል ቡድን ወይም ስብስብ ማጥፋት፤”ይላል። በዚህ ብያኔ ብቻ እንኳ በትግራዋይ ፣ በወልቃይት ፣ ጠገዴ ፣ ጠለምትና በሌሎች የአማራ አካባቢዎች እንዲሁም በኦርቶዶክሳውያን እና በእነ ኢዲዩና ኢሕአፓ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል ማለት ይቻላል ። እንግዲህ ሕወሓት በ1968 ዓ.ም ማንፌስቶው አማራንና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶን በግልጽ በጠላትነት ፈርጆ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፤ በአማራ፣ በኦርቶዶክሳውያንና በተከታዮቿ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል ። ቤተ ክርስቲያኗ በትግራይ የነበራትን ማኅበራዊ ልዕልና እንድታጣ ሆን ብሎ በቁሟ አፍርሷታል ። ቤተ መቅደሷን የጦር መሳሪያ ማከማቻና ምሽግ ፤ አጸዷን የመሳሪያና የብር መቅበሪያ ያደረገው ፤ አገልጋዮቿንና ልጆቿን ካድሬ አንጋችና የሸፍጡ ግንባር ቀደም ተዋናይና ተባባሪ ማድረግ የተሳካለት መጀመሪያ ስላፈረሳት ነው።
በትጥቅ ትግሉ ወቅት የኢዲዩ ደጋፊና አባል ናቸው ያላቸውን ከ40ሺህ በላይ ትግራዋይን ለዛውም ነቃ ያሉ አርሶ አደሮችንና ልሒቃን ወይም የማኅበረሰቡ አስኳልና የማዕዘን ራስ የነበሩን በግፍ ገድሏል ። ይህን ያደረገው ርዕዮተ አለሙና የፓርቲው ፕሮግራም ያለተቀናቃኝ ብቸኛ ገዥ ሀሳብ ሆኖ እንዲወጣ ነው ። ዛሬም በተግባር እየሆነ ያለው ይሄው ነው ። ሕወሓት ወደ ጣኦትነት የተቀየረው እንዲህ ባለ ቅየዳ ነው ። በ17 አመቱ የትጥቅ ትግል ከ70ሺህ በላይ የትግራይ ወጣቶች በከንቱ ከመሰዋታቸው ባሻገር ቁጥራቸው ከዚህ የማይተናነስ አካል ጉዳተኛ በማድረግ ትግራዋይ እናቶችን የወላድ መካንና ጧሪ ደጋፊ አልባ አድርጓል ።
ደም ምሱ የሆነው ይህ አሸባሪ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በተከተለው የተሳሳተ የውጊያ ስልት ከ70ሺህ በላይ ወጣቶችን አስጨርሷል ። ይሄን ወጣት ያስጨረሱትን የሕወሓት ጄኔራሎች ነው እንግዲህ እነ ማርቲን ፕላውትና ቢቢሲ አፍሪካዊ የጦር ስትራቴጂስት እያለ የሚያንቆለጳጵሳቸው ። በጦርነቱ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሩጠው ያልጠገቡ ወጣቶችን አካል ጉዳተኛ አድርጎ ፤ በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠር የሀገር አንጡራ ሀብት አውድሞ ለሰላም ስምምነት አልጀርስ ሲገኝ ግን የቀደመው አልነበርም ። ይህ አልበቃ ብሎት የድንበር ግልግሉ ፍርድ ቤት ባድመን ለኤርትራ ወስኖ እያለ ለኢትዮጵያ ተወሰነ በማለት በሰማዕታቱ አጽም ተሳልቋል ። ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላም ያ ለአገሩ የዘመተና መስዋዕት የከፈለ ወጣት ፍትሕን እኩልነት ነጻነትንና ዴሞክራሲን ሲጠይቅ አደገኛ ቦዘኔ ብሎ ከመፈረጅ አልፎ በ97 ምርጫ በመለስ ትዕዛዝ በአንድ ቀን በአግአዚ ልዩ ኃይል ከ200 በላይ የአዲስ አበባ ወጣቶችን በጭካኔ ጨፍጭፏል። ለዛሬው በዚሁ ላብቃ፤ ፍትሕ ለግፉአን! ሰላም!
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2014