ምግብ ነክም ሆነ ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ዋጋ በፍጥነት መጨመሩን ቀጥሏል፡፡ ገና በዓል ሳይደርስ ሽንኩርት እንኳን በአቅሙ 40 ብር ገብቷል፡፡ እንዴውም አንዳንድ ቦታዎች ኪሎው እስከ 50 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ይሄ የሽንኩርት ዋጋ ያገባኛል የሚል የሚመለከተው አካል ቁጥጥርና ክትትል እስከሌለ ድረስ ውሎውንና ማምሻውን ሳይጠብቅ በደቂቃዎች ውስጥ 60 እና 70 ብር እያለ ጭራሹን ኸረ በአንድ ጊዜ 100 ብር የማይገባበት ሁኔታ አይኖርም ተብሎ አይታሰብም፡፡ ምናልባትም እንደ አንዳንዶች የፌዝ ሥጋት እንደ አምስት ሊትሩ ዘይት በአንዴ ዘጠኝ መቶና አንድ ሺህ ብር ሊገባ የማይችልበት ሁኔታ አይኖርም ተብሎ አይገመትም፡፡
የዋጋ ንረቱ ዋንኛ መንስኤዎች ከሚባሉት ውስጥ የደላላ ፈላጭ ቆራጭነት የምርት እጥረት፣ የውጪ ምንዛሪ እጥረት፣ በምንዛሪው እጥረት ምክንያት ጥሬ ዕቃ አለመኖር፣ የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን፣ የመሰረታዊ ፍጆታዎች ፍላጎት ማደግ፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም በንግዱ ጉዳይ ላይ ያገባናል የሚሉ የንግዱ አመራሮችና ነጋዴዎች የአምራቾች በምርቶቻቸው ላይ ዋጋ መጨመርን እንደምክንያት ያነሳሉ፡፡
እኔ እንደታዘብኩት ዋንኛው ምክንያቶች ነጋዴው፣ በተለይም በአዲስ አበባ ሕብረት ሥራ ኤጄንሲ አስተባባሪነት አዲስ አበባ ከተማ ላይ የዋጋ ንረትን በማርገብና ገበያ በማረጋጋት ስም ወደ እሁድ ገበያ እንዲወጡ ጭምር የተደረጉት የሕብረት ሥራ ማህበራት እንዲሁም የቁጥጥርና ክትትል ተግባሩን ዘንግቶ ሳይሆን ‹‹አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› እንዲሉት ዓይነት ዘይቤ ሕብረተሰቡ በነዚህ ሁለት አካላቶች ሲበዘበዝ ዝም ብለው የሚመለከቱት ከላይ እስከ ታች ያሉት የንግዱ ተቋማት አመራሮች ናቸው፡፡
ምክንያቱም፣ እነዚህ ሦስት አካላት በተለይም በቁጥር አንድ ደረጃ የንግድ አመራሩ ከሚኒስቴሩ ጀምሮ እስከ ታች ቀበሌ ወይም ወረዳ ያለው አደረጃጀት ኃላፊነታቸውን አልተወጡም፡፡ ሁለተኛው በተለይ የዋጋ ንረት በማርገብ ስም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አማካኝነት ወደ እሁድ ገበያ እንዲገቡ የተደረጉትና ከነጋዴው ጋር በመመሳጠር የሸቀጥና ሌሎች ምርቶችን አየር በአየር እየሸጡ የግል ጥቅማቸውን በማጋበስ ሕብረተሰቡን ቁም ስቅሉን እያሳዩት ያሉት የሕብረት ሥራ ማሕበራት ለሕግና ለህሊናቸው አልተገዙም፡፡
ሦስተኛው ነጋዴው ቁጥጥርና ክትትል ባለመኖሩ የፈለገውን ምርትም ሆነ ሌሎች ሸቀጦች በፈለገው ዋጋ ይሸጣል፡፡ ወደድንም ጠላንምና ዕውነታውን መጋፈጥ ፈለግንም አልፈለግንም የኑሮ ውድነቱ ዋንኛ መንስኤዎች እነዚህ ሦስቱ አካላት ናቸው፡፡ ይሄን የምለው የነዚህ አካላት ስም ለማጥፋት ወይም በተለይ ሁለቱ አካላት ከዚህ በፊት ከነበራቸው ጥሩ ያልሆነና ስነ ምግባር የጎደለው አሰራር ተነሳስቼ አይደለም፡፡
‹‹ማየት ማመን ነው›› እንዲሉ ካየሁትና ከታዘብኩት ዕውነታ ተነስቼ በትክክለኛ መረጃ ነው፡፡ ዓይኔን እማኝ ካደረገው ትዝብቴ አስቀድሜ አንዱ የሆነው ገበያ በማረጋጋት ስም ወደ እሁድ ገበያ በመግባት ጭምር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕብረተሰቡን እንዲያገለግል ስለተደረገው የሕብረት ሥራ ማሕበር አገባብ ልጀምር፡፡
በመንግስት ዘንድ የሕብረት ሥራ ማህበራትና በነዚህ ማህበራት ሥር የሚገኙ መሰረታዊ ሕብረት ሥራ ማሕበራት የምግብና ሸቀጦችን የዋጋ ግሽበት ያሻሽሉና በፍትሃዊነት ሕብረተሰብ ያገለግላሉ የሚል ዕምነት አለ፡፡ ከግብሩ እንደታየው ይሄ ዓይነቱ ዕምነት የዋህነት ቢመስልም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፊናው ይሄንኑ ዕምነት በመያዝ ነው በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ በ10 የሕብረት ሥራ ማሕበራትና በነዚሁ ማሕበራት ሥር የሚገኙ 148 መሰረታዊ ሕብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት የእሁድ የተለያዩ ምርቶች ገበያ እንዲጀመር ያደረገው፡፡
ታድያ እንደ እኔ ትዝብት የዕለቱ ዕለት ምን አልባትም በቀጣዩ ሳምንት ገበያው የዋጋ ግሽበት በማሻሻል ብሎም የኑሮ ውድነቱን በመጠኑም ቢሆን በማርገብ ከተማ አስተዳደሩ ያለመለትን ግብ ማሳካት ችሏል፡፡ ከሩዝ ጀምሮ እስከ ጤፍና ዱቄት እንዲሁም ፓስታና ዘይት ድረስ በተለይም ሽንኩርት ከስምንት ብር እስከ 16 ብር በማህበራቱ አማካኝነት ለገበያ ቀርበው በተመጣጣኝ ዋጋ ተሸጠዋል፡፡
በሦስተኛው ሳምንት ግን ከስኳር በቀር የድጎማ ዱቄቱና ሸቀጦች አንደኛ ደረጃ ነው እየተባለና ሌሎች ውሸቶችና ሰበቦች እየታከሉ ዋጋቸው እየጨመረ መጣ፡፡ አበስኩ ገበርኩ! ኪሎው ዱቄት ዋጋው ያው የተለመደው 46 ብር ሆነ፡፡ ኪሎው ሩዝ ከ36፣ 38 እያለ ሁለት ሁለት ብር በመጨመር በፍጥነት 40 ብር ገባ፡፡ ፓስታውም በየአካባቢያችን ያሉ መደብሮች ከሚሸጡበት እኩል ሆኖ አረፈ፡፡ የሌሎቹ ሸቀጦችና ምርቶች ዋጋም በሙሉ በአንድ ጊዜ ከመደበኛው ዋጋ ጋር ተመሳስሎ ቁጭ አለ፡፡ በደምሳሳው የእሁድ ገበያው እንደታሰበው የዋጋ ግሽበቱን የማሻሻሉና የኑሮ ውድነቱን የማርገቡን ዓላማ ሳያሳካ ቀረ፡፡ እንደውም ጭራሽ ለዋጋ ግሽበቱና ለኑሮ ውድነቱ መንስኤ ሆኖ አረፈው፡፡
ምክንያት ብትሉኝ አሁን ላይ በየትኛውም መንገድ አጣሩ በየአካባቢያችን ያሉት የሸቀጥና ምርት መደብሮች ይሄን የእሁድ ገበያ መሰረት አድርገው ነው የሸቀጥና ምርት ዋጋዎቻቸውን የሚተምኑት፡፡ አንድ ኪሎ ማኮሮኒ 50 ብር የሸጠልኝ ባለመደብር ከደቂቃዎች በኋላ 60 ብር ለምን እንዳደረገብን ስጠይቀው ማሕበራቱ 50 ብር ሲሸጡ አላየሽም፡፡ እኛማ አትራፊዎች ነን፣ ከትራንስፖርት ጀምሮ ብዙ ወጪዎች አሉብን፡፡ ቢያንስ ከነሱ 10ብር ጨምረን ነው መሸጥ ያለብን አለኝ፡፡ ዱቄቱም፣ፓስታው፣ ዘይቱ እንዲህ እያለ ነው ዋጋው የሚያሻቅበው፡፡
እነዚሁ “ሸማቾች ማሕበር ነን” በማለት በብልሹ አሰራራቸው በየአካባቢው ሕብረተሰቡን ቁም ስቅሉን በማሳየት ሲጠብሱት የኖሩ ሕብረት ሥራ ማሕበራት ዋጋ የሚጨምሩት የአምራቹን ጭማሪ መሰረት ባደረገ ሳይሆን ያለ ምክንያት ለመሆኑ አንድ ማሳያ ልጨምርላችሁ፡፡ ባለፈው እሁድ 27 ብር ሲሸጡት የነበረውን ሽንኩርት ከደቂቃዎች በኋላ ከቤተክርስቲያን የሚመለሱ ሸማቾች ግር ብለው ሲገዟቸው በአንዴ 32 ብር አደረጉት፡፡ ያመጡበት ዋጋ ግን ያው በ27 ብር ሲሸጡበት ከነበረው አልጨመረም፡፡ እነዚህ ሸማች ማህበራት ሰሞኑን በሸማቾች ቁጥር የመጣውን ዘይት ለአንድ አምስት ሰው ሰጥተው አየር በአየር በመሸጥ አለቀ ያሉበትም አካባቢ ብዙ ነው፡፡
እንደውም አንዳንዶች ባለ 20 ሊትር ዘይት አምጥተው ያከፋፍሉ የነበሩ አልጠግብ ባይ ማህበራት የሕብረተሰቡን ኮታ አየር በአየር ሸጠው ያገኙት ሕገወጥ ብልፅግና ሳይበቃቸው በአሳፋሪ ሁኔታ ዘይቱን ገልብጣችሁ ጀሪካኑን መልሱ በማለት ጭምር ሕብረተሰቡን ሲያተራምሱት ነበር፡፡
በመሆኑም እነዚህ ማህበራት ለባለ መደብሩ ጥሩ አርአያዎች ባለመሆናቸው ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆነውታል፡፡ ከዚህ የተነሳ ግማሽ ሊትሩን ዘይት 110 ብር ብሎኝ የነበረ አንድ ባለመደብር ሌላው መደብር ጠይቄ እስክመጣ ባሉት ደቂቃዎች ውስጥ 180 ብር ያገባት መሆኑንም ታዝቢያለሁ፡፡ አሁንም የጭማሪው መንስኤ የነጋዴው ስግብግብ ፍላጎት እንጂ ከፋብሪካው ዘይቱ በውድ ዋጋ መምጣቱ አይደለም፡፡ የቁጥጥርና ክትትሉ ኃላፊነት የተጣለበት ሦስተኛው አካል የሕብረተሰቡ አካል እንደመሆኑ ከላይ እስከ ታች ባለው መዋቅሩ እነዚህን ዋጋ ንረት መንስኤዎች ያውቃቸዋል፡፡ ሆኖም ‹‹አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይነቃም›› እና መፍትሄ ማምጣት አልቻለም፡፡
ጌቴሴማኔ ዘ-ማርያም
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2014