በቋንቋ እቅፍ ውስጥ ካሉ ሐረጋት መካከል «እንከን የለሽ» የሚለው አንዱ ነው። እውነትም እንዲህ የሚባል ከሆነ ይህንን ማዕረግ ሊጎናፀፉ ከሚገባቸው ቃላት አንዱና ቀዳሚው «ውይይት» መሆን አለበት። ምክንያቱም «ውይይት» ምንም ዓይነት እንከን ሊወጣለት ስለማይችል። የነጮቹ አፍ በሆነውና የዕለት ተዕለት ቋንቋም «ዲስከሽን» እንበለው፣ አሊያም በፍልስፍናው «ዲያሎግ» በሁለቱም «እንከን የለሽ» ስለ መሆኑ መከራከር የሚቻል አይመስልም። «ይቻላል» ከተባለ እንኳን ሂደቱና ተግባራዊነቱ ላይ እንጂ ጽንሰ ሀሳቡ ላይ ሊሆን የሚችል አይደለም። «ውይይት!!!»
ውይይት በየትኛውም ደረጃ ይካሄድ፤ ምንም ዓይነት እርከን ይበጅለት ውሉም ሆነ አላማው አንድ ነው። አገራዊም ይሁን ብሔራዊ፤ ቡድናዊም ይሁን ቤተሰባዊ … ውይይት ያው ውይይት እንጂ ክርክር አልያም እሰጥ አገባ ሊሆን አይችልም። ሳት ብሎት ወደ እዚያ ከሄደ እንኳን ችግሩ የእኛ የውይይት አያያዝና አጠቃቀም ጥበባችን (በተለይም የ“Dialogical thinking” /የውይይት እሳቤ) ዝንፈት እንጂ የጽንሰ ሀሳቡ አይደለምና በምንም መልኩ በእሱ ማሳበብ አይቻልም።
ውይይት ምን ጊዜም በዘዴ፣ በጥበብ ከተያዘ፤ በእውቀት ከተመራ … አዋጭ ነው። በመደማመጥ ላይ ከተመሠረተ፤ በተወያዮች መካከል የጋራ ራእይና አላማ ካለ፣ እራስ ወዳድነትና የአውዳሚነት (ኒሂሊዝም) መንፈስ ከሌለ፣ ማጀቢያው የራስ ፍላጎት ሳይሆን የሕዝብና አገር ጥቅም ከሆነ …. ከሆነ … ከሆነ … ምን ጊዜም ውይይት አትራፊ እንጂ አክሳሪ ሆኖ አያውቅም። ከላይ የጠቀስነውን ሩሲያዊ ፈላስፋ ጨምሮ በመስኩ ልሂቃን አንደበት ሲነገር እንደሚሰማው ሕይወት ራሷ (Life is dialogic እንዲሉ) በውይይት የተሞላች ነች እንጂ ተናጠላዊ አይደለችም፤ በመሆኑም ውይይት የሕይወት ቅመም እንጂ መርዝ አይደለም ማለት ነው።
እርግጥ ነው ውይይት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለም። ለታክሲ ሳይቀር ስም ስናወጣ እንኳን «ውይይት» ብለን የነበረ (“ነበር” … ሆነ እንጂ) መሆኑ እራሷ «ውይይት» የተባለችው ታክሲ (አሁንም ድረስ ዘሯ አለና) ምስክር ነችና ጉዳዩ የሚያከራክር አይደለም። «ውይይት»ን በዘፈንም ቢሆን በሚገባ አቆለጳጵሰነዋልና አሁንም ለእኛ አዲስ አለመሆኑ ግልፅ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት ለንባብ ትበቃ የነበረችው ተወዳጅ ባለ ሁለት ቋንቋ ጆርናልም ስያሜዋ «ውይይት/ዲያሎግ» ነበርና (አይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እኮ ድሮ ያልቀረ ምን አለ? «ሁሉም ድሮ ቀረ» መባል ካለበት በአንደኛ ደረጃ መባል ያለበት በዚሁ በእናት ዩኒቨርሲቲ ነው።) ስለዚህ ውይይትም፣ መወያየትም፣ ማወያየትም … ለእኛ ብርቅ አይደለምና እዳው ገብስ ነው ለማለት ነው። ይልቅስ ብርቅ የሚሆነው ስለ «ዲሞክራሲ» ከእኔ በላይ ጠበቃ ሲል የሚሰማው አካል «ውይይት» ሲሉት ሲያቅረውና እግሬ አውጭኝ ሲል ማየት ነውና ጉዳዩ ብዙዎችን ቢያሳስብ አይደንቅም።
በተለይ ወደ ሥነጽሑፍ ሥራዎቻችን ስንመጣ «ውይይት» (ሥነጽሑፋዊ ብያኔው “any communication between two characters” ወይም “the written conversation between two characters or more within a narrative” መሆኑን ልብ ይሏል) ለእኛ አዲስ አለመሆኑን በሚገባ እናረጋግጥበታለን። (ለምሳሌ በፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ የተሳኩና ያልተሳኩ ውይይቶችን ልብ ይሏል። (እዚህ ጋ የባክቲን (Mikhail Mikhailovich Bakhtin (1895–1975))ን “Dialogism”ም ማሰብ ይቻላል)፡፡
በውይይት ተጠቃሚ የሆኑ ብዙ አሉ፤ ሰዎች ተጠቅመዋል፤ ቡድኖች ተጠቅመዋል፤ አገራት (ለምሳሌ ጃፓን፣ አልጄሪያ …) ተጠቅመዋል። መጠቀም ብቻ አይደለም ከገቡበት አዘቅት ሁሉ ወጥተውበታልና ውይይት ፋይዳው ከዚህ መለስ የሚባል አይደለም። ሌላው ሁሉ እንኳን ቢቀር ሩዋንዳዎች ከዚያ ሁሉ ቀውስ ውስጥ አፈትልከው የወጡት (የመሪው ሚና እንዳለ ሆኖ) በውይይትና ግጭት ማስወገጃ ባህላዊ እሴታቸው ነውና ላወቀበት ውይይት ፍቱን መድኃኒት ነው።
ግጭቶች ለምን ኖሩ፣ ተፈጠሩ፣ ተከሰቱ …. ብሎ መከራከሩ ብዙም ፋይዳ የለውም። በተለይ በጥባጭ ባለበት አገር የጠራ ውሀ መጠጣት «ሲያምርህ ይቅር …» ዓይነት ነውና ግጭት(ቶች) መኖራቸው አይደለም ጉዳዩ፤ ጉዳዩ እንዴት ከግጭቶቹ ወጥቶ ወደ ሰላም መመለስ ይቻላል፣ በምን ዘዴ፣ በምን ብልሀት … የሚለው ነው አስጨናቂው። ግጭቶች ወደ «የሕልውና ጦርነት»፤ ወደ «የሕግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃ» … ከመሄዳቸውና ምንም የማያውቁ ንፁሀን በጅምላም ይሁን በቡድን፣ አልያም በተናጠል ሕይወታቸውን ከማጣታቸውና ቀጥለን የምናስታውሰው ዜና ከመደመጡ በፊት ውይይት ቢቀድም ኖሮ፤ ሁሉም ባልሆነ፣ ዜናውም ሌላ በነበረ ነበር።
«በሕወሓት እና በፌዴራሉ መንግሥት መካከል የተጀመረው ጦርነት እና እሱን ተከትሎ የመጣው ሰብዓዊ ቀውስ፣ የረሃብ አደጋ፣ የንጹሃን ዜጎች ግድያ፣ የሕዳሴ ግድብ ድርድር፣ ከሱዳን ጋር የተገባው የድንበር ይገባኛል ውዝግብ፣ አገራዊ ምርጫ እና ሸኔ የኢትዮጵያ የ2013 ዋና ዋና አጀንዳዎች ነበሩ።» ይላል ይህ በጸሐፊ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ሲያገላብጥ ያገኘው ዜና። ልብ ካልን እነዚህ ሁሉ የውይይት ባህል መንጠፍና የ«በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ውሀ ይጠጣል» ውጤቶች ናቸው እንጂ ሌላ አይደሉም። ወይም እኛ ፈጠሪ ለይቶ እንዲህ እንድንሆን ስላደረገን አይደለም።
ሌላው የዚሁ የ2013 አ.ም ዜናም «በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሞተዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ለረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል። በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ቁጥራቸው በውል በማይታወቁት ላይ ደግሞ የተለያየ መጠን እና ዓይነት ያላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል።» በማለት (የወደመውን የንብረት መጠን ዘሎታል) ያለፈውን አመት ቀውስ ያብራራዋል። አሁንም እንድገመውና ይህ ሁሉ የውይይት ባህል መንጠፍ እና ለአገርና ሕዝብ ጥቅም ሳይሆን ለግል ጥቅምና ዝና ሲባል የሆነ አሳዛኝ አገራዊ ትራጀዲ ነው።
ለማጠቃለል፣ ባጭሩ ውይይት ማለት ነፍሳቸውን ይማረውና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በአንድ ቆየት ባለ መጽሔት ላይ «ደህና ሁን ጠመንጃ» እንዳሉት ደህና ሁን ጠመንጃ ማለት ነው። ውይይት ማለት ማህበረ-ባህላዊ እሴታችን የሆነው ምርቃታችን «የጎመን ምንቸት …» እንደሚለው ሁሉ «የሰላም ምንቸት ግባ፤ የግጭት ምንቸት ውጣ» ማለት ነው። ውይይት መደማመጥ ነው፤ ውይይት መነጋገር ነው፤ ውይይት ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሄ መሻት ነው፤ ውይይት እነዚህንና እነዚህን መሰል ጉዳዮች ማለት ነውና ለሁሉም መልካም የውይይት መድረክ እንላለን። ችርስ ውይይት!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5 ቀን 2013 ዓ.ም