ኢትዮጵያ እንደ አገር፣ ኢትዮጵያውያን ደግሞ እንደሕዝብ ከሌሎች የዓለም አገራትና ሕዝቦች ለየት የሚያደርጓቸው በርካታ ነገሮች መጥቀስ ይቻላል። አገራችን ኢትዮጵያ የራሳቸው ፊደልና የዘመን መቁጠሪያ ካላቸው ጥቂት የዓለማችን አገራት አንዷ ከመሆኗ በተጨማሪ በቅዱስ መጽሐፍት በተደጋጋሚ የተጠቀሰች፣ የበርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ቅርሶችና ብርቅዬ እንስሳቶች ባለቤት፣ ከሰማንያ በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፣ የሃይማኖት እኩልነትን ከማንም ቀድማ ያወጀችና ሃይማኖቶቹም ለዘመናት ተከባብረው የኖሩባት፣ እሷን ብለው ለመጡ መጠለያ እንደምትሆን ሁሉ ሊያጠቋት ለመጡ የውጭ ጠላቶች መቀበሪያ የሆነችና የጀግኖች አትሌቶች መፍለቂያ አገር መሆኗን ሁሉም ይመሰክርላታል።
በተጨማሪም ከምንም ነገር በላይ ፈጣሪያቸውን የሚፈሩ ሃይማኖተኞች፣ እንግዳ ተቀባዮች፣ ሰው አክባሪዎችና በተደጋጋሚ ጊዜያት ከውጭ ጠላቶች የሚሰነዘሩባቸውን ጥቃቶች በመመከት ጀግንነታቸውን ያስመሰከሩ እንዲሁም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በጭቆና ውስጥ ለነበሩ ሕዝቦችም የነጻነት ተምሳሌት መሆን የቻሉ ሕዝቦች ያላት ድንቅ አገር ናት።
ከላይ ከተዘረዘሩት ማሳያዎች በተጨማሪ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለየት የሚያደርጓቸው በርካታ ነገሮች መጥቀስ የሚቻል ቢሆንም የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ዓላማ ኢትዮጵያ ለእስልምና ኃይማኖት ያበረከተቻቸውን አስተዋጽዖዎችና ከዓረቡ ዓለም ሙስሊም አገራት ለየት የሚያደርጓትን ነገሮች ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ማስተያየት ነው።
ሼኽ ዑመር ሼኽ በሽር በአረብኛ ቋንቋ በጻፉትና ሼኽ አብደላህ መሐመድ ዓሊ ወደ አማርኛ በተረጎሙት መጽሐፍ እንደተገለጸው፤ ነብዩ መሐመድ ገና ሕጻን እያሉ እናታቸው በሞት ስላጡ እሳቸውን ያጠባች ሐበሻዊት (ኢትዮጵያዊት) ሴት መሆኗ፣ እስልምናን በመቀበላቸው ምክንያት አገራቸውን ለቀው እንዲሄዱ የተገደዱትን የነብዩ መሐመድ ቤተሰቦችና ባልደረቦች (ሶሃባዎች) ማስጠለላችን፣ አረቦች እንዳይተናኮሉን ነብዩ መሐመድ ማዘዛቸው፣ የሐበሻ ሰዎች ጥሩነት በቁርዓን ውስጥ መገለጹ፣ የተሻለ ፍትህ እንዳለን በነብዩ መሐመድ መመስከሩ፣ ነብዩ መሐመድን ከዑሙ ሀቢባ ጋር ያጋባንና በጋብቻ ወቅት የሚከፈለው ክፍያ (መኽር) የከፈልን በመሆናችን፣ የነብዩ ቤተሰቦችና ታላላቅ ሰሃባዎች (ባልደረቦች) ለብዙ ዓመታት በአገራችን መኖራቸው፣ በእስልምና ታሪክ የመጀመሪያው አዛን (ለሶላት የሚደረግ ጥሪ) አድራጊ የቢላል አል-ሐበሻ ወገን መሆናችንና ሌሎችም ነገሮች ሙስሊም አራትን ጨምሮ ከዓለም አገራት ለየት ያደርጉናል።
በሰባተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያዎቹ ዓመታት ነብዩ መሐመድ እስልምናን ማስተማር በጀመሩበት ወቅት የራሳቸው የመካ ሕዝቦች በከፍተኛ ሁኔታ ያሰቃዩአቸው ስለነበር መጠጊያ ያልነበራቸው ተከታዮቻቸው “ወደ ሐበሻ ምድር ሂዱ፤ እዛም እርሱ ዘንድ ማንም የማይበድል የሆነ መንግሥት ታገኛላችሁ፤ ፈረጃ (መፍትሄ) እስኪገኝ ድረስም እዛ ቆዩ” በማለት ወደ ሐበሻ ምድር ላኳቸው።
የስደተኛ ቡድኑ አስራ አንድ ወንዶች እና አራት ሴቶችን ይዞ የነበረ ሲሆን፤ ከእነሱም ነብዩ መሐመድ ከሞቱ በኋላ ሶስተኛው የሙስሊሙ ዓለም መሪ የሆኑት ዑስማን ኢብኑ አፋን እና ባለቤታቸው፣ እንዲሁም የነብዩ መሐመድ ልጅ የሆነችው ሩቂያ ይገኙበት ነበር። ይህ በእስልምና ታሪክ የመጀመሪያው ስደት ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን፤ ቀጥሎም ከ82 በላይ ሙስሊም ስደተኞች በጃዕፈር ኢብኑ አቡ-ጣሊብ እየተመሩ ወደ ሐበሻ ምድር ዘልቀዋል።
ከዚህ ሁሉ በኋላ፣ የበድር ጦርነት በተከሰተና ቁረይሾች በሙስሊሞች በተሸነፉ ጊዜ በቀላቸውን ወደ ሐበሻ በተሰደዱት ላይ ሊወጡ አሰቡ። ከውድ ስጦታዎች ጋር ሁለት ሰዎች ወደ ንጉሥ ነጃሺ ተላኩ። ንጉሥ ነጃሺም በውድ ስጦታዎች ሳይታለሉ የሁለቱም ወገን ሃሳብ ካደመጡ በኋላ ስደተኞችን ከቁረይሾች አስጥለው “በምድሬ ላይ ተረጋግታችሁ ኑሩ፤ እናንተን በክፉ የሚያይ ብርቱ ቅጣት ይጠብቀዋል” በማለት በሰላም እንዲኖሩ ፈቀዱላቸው።
ንጉሡ ወደ ቁረይሽ ተወካዮች ዞረው “ተራራን የሚያህል ወርቅ ብትሰጡኝ እንኳን እነዚህን ስደተኞች አሳልፌ አልሰጣችሁም” አሏቸው። ስደተኛ ሙስሊሞችን ለመበቀል የመጡት የቁረይሽ ሰዎችም የከሰሩ ሆነው ወደ አገራቸው ተመለሱ። ስደተኞቹ ደግሞ በንጉሥ ነጃሺና ማንም በማይበደልባት አገራቸው በጥሩ እንክብካቤ ነብዩ መሐመድ ወደ መዲና እስከተሰደዱበትና ጠላቶቻቸውን እስካሸነፉበት ጊዜ ድረስ በሰላም ቆዩ።
አንጋፋው የታሪክ ተመራማሪ አደም ካሚል (ረዳት ፕሮፌሰር) እንደተናገሩት በወቅቱ ንጉሥ ነጃሺ ስደተኞቹን አሳልፈው ቢሰጡ ኖሮ የሰዎቹ ዕጣ ፈንታ መሞት ነበር፤ የእስልምና መሠረትም ይጠፋ ነበር። በወቅቱ መካ ውስጥ ወደ ሐበሻ የመጡ ስደተኞችን በስቅላት ለመቅጣት ገመድ ተንጠልጥሎ ነበር። በመሆኑም ኢትዮጵያ ለእስልምና ይህን ከባድ ውለታ ባትውል ኖሮ እስልምና አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ላናገኘው እንችል ነበር፤ ሲሉ ነው ረዳት ፕሮፌሰር አደም የሚያስረዱት።
በወቅቱ መካ ውስጥ እስልምናን መቀበል ያሳስር፣ ያስደበድብና ያስገድል ነበር፤ ቁርዓን ማንበብም ያስፈነክት ነበር። ነገር ግን ኢትዮጵያውያንና ንጉሳቸው የክርስትና እምነት ተከታዮች ቢሆኑም፤ ፍትሐዊና ስልጡን በመሆኗቸው በገዛ አገራቸው በእምነታቸው ምክንያት እንዲሰደዱ የተደረጉ ሙስሊም ስደተኞችን ከመቀበልና ከመንከባከብ አላገዳቸውም። ስደተኞቹ በቤተመንግሥት በንጉሡና ቀሳውስት ፊት በነጻነት ቅዱስ ቁርዓን ማንበባቸው በበርካታ ኢስላማዊ መጽሐፍት ተጽፎ ይገኛል።
አላህ (ሱ.ወ) ሐበሻን አስመልክቶ በቅዱስ ቁርዓን ሱረቱል ማኢዳ፥82 እንዲህ ብሏል፦ “…በውስጣቸው የተለያዩ ቄሶችና መነኮሳት ያሉ ሲሆን እነርሱም የማይኮሩና ሐቅ በመጣ ጊዜ የሚቀበሉ በመሆናቸው ነው”።
በወቅቱ ነብዩ መሐመድ ቤተሰቦቻቸውና ተከታዮቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ሲልኩ በአካባቢያቸው በብዙ ነገሮች የሚቀርቧቸው አገራት ወይም ነገሥታት ስላልነበሩ አይደለም ሐበሻን የመረጡት። በወቅቱ ዓለም ላይ ካሉ አገራት በተለየ ሁኔታ የሐበሻ ምድር ማንም የማይበደልባትና ፍትሐዊ መሪ ያላት እንዲሁም ሕዝቦቿና መሪዋ ክርስቲያኖች ቢሆኑም ለእምነት ነጻነትና ለሃይማኖት እኩልነት እውቅና የሚሰጡ ስልጡን ሕዝቦች በመሆናቸው እንጂ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንኳን ተግባራዊ ማድረግ ያልቻላቸውን ከእምነት ነጻነት፣ ከሃይማኖት እኩልነት፣ ከፖለቲካ ጥገኝነት፣ ከሰብዓዊ መብት ማስከበር፣ ስደተኞችን ከመቀበልና ከመንከባከብ፣ ሙስናን ከመዋጋት ጋር በተያያዘ የሚወጡ ዓለም አቀፍ ሕጎች ኢትዮጵያ ከዛሬ አንድ ሺህ አራት መቶ ዓመታት በፊት በንጉሧ አል-ነጃሺ አማካኝነት ተግባራዊ አድርጋቸዋለች።
በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው ነገር የሙስሊም ስደተኞቹ መነሻ አገር የሆነችውና በሸሪዓ (ኢስላማዊ ሕግ) እንደምትተዳደር የሚነገርላት ሳውዲ አረቢያ፤ ዛሬ ላይ ለሥራ ብለው የሄዱ ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ኢትዮጵያ ጠል ከሆኑ ቡድኖች ጋር ተባብራ ከአገሯ እያስወጣች መሆኗ ነው። በዚህም የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት የኢትዮጵያን ውለታ መመለስ አልቻለም፤ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከአንድ ሺህ 400 ዓመት በፊት እንደነበረው የሐበሻው ንጉሥ ወደ አገሩ የገቡ ስደተኞች መንከባከብ ባይችል እንኳን በአገሩ በነጻነት እንዲኖሩ ማድረግ አልቻለም።
ሳዑዲ ዓረቢያ እሷን ብለው የሄዱ ኢትዮጵያውያንን የምታንገላታውና ከአገሯ የምታስወጣው ኢትዮጵያ ለእስልምና የዋለችው ውለታ ወይም ነብዩ መሐመድ ስለኢትዮጵያ (ሐበሻ) የተናገሩትን ሳታውቀው ቀርታ አይደለም። ከሃይማኖት ይልቅ ፖለቲካ ስለምታስቀድም እንጂ!
ወደ ዋናው ጉዳዬ ልመለስና፣ ኢትዮጵያ ሙስሊም ስደተኞችን በመቀበሏ ብቻ አይደለም ከሌሎች የዓለማችን አገራት የምትለየው። ነብዩ መሐመድ ገና ሕጻን እያሉ ወላጅ እናታቸው በሞት ባጡበት ጊዜ ጡቷን አጥብታ ያሳደገች ሐበሻዊት ሴት ናት። በረካ አል-ሐበሺይ (ዑሙ አይመን) ትባላለች፣… ነብዩ መሐመድን ተንከባክባና ጡቷን አጥብታ ወደ አያታቸው አብዱልሙጠሊብ ዘንድ አድርሳለች።
በእስልምና ሕግ መሠረት የጋራ ጡት የጠቡ ማናቸውም ልጆች ወንድማማቾች/እህትማማቾች ናቸው። በዚህም መሠረት በረካ አል-ሐበሺይ ከነብዩ መሐመድ ቤተሰቦች ጋር በመቀላቀሏ ሐበሾች የሆኑት አባቷ፣ እናቷ፣ ወንድሟ፣ እህቷና ሌሎችም ቤተሰቦቿ ሁሉ ከነብዩ መሐመድ ጋር ተቀላቅለዋል ማለት ነው።
ነብዩ መሐመድ ካደጉ በኋላ ለበረካ ክብር ሲሉ ጋቢያቸውን መሬት አንጥፈው እንድትቀመጥበት ማድረጋቸው በበርካታ መጽሐፍት ተጽፎ ይገኛል። ይህም ከእርሷ ጋር የመጡትን ሁሉ ክብር ያጎናጸፈ ነበር። ነብዩ መሐመድ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ በረካ የጀነት (የገነት) መሆኗን አብስረዋታል።
ቡሰይሪ የተባሉ ዓሊም (ምሁር) “ሀምዚያ” በተባለው የግጥም ሥራቸው ላይ በረካ ነብዩ መሐመድን ጡት ያጠባች እንደሆነች ገልጸው፤ ክብሯም “የሰማይ ያህል የሰፋ ነው” ሲሉ ገልጸዋታል። ነብዩ መሐመድም፣ ከሌሎች አገራት በተለየ መልኩ ዓረቦች ሐበሻን እንዳይተናኮሉ “ሐበሾችን ሳይነኳችሁ አትንኳቸው!” በማለት ደንግገዋል።
ነገር ግን አሁን እየሆነ ያለው በተቃራኒው ነው። የነብዩ መሐመድን ትዕዛዝ በመተላለፍና የኢትዮጵያን ውለታ ከቁብ ሳይቆጥሩ ኢትዮጵያን እያስጨነቁ ካሉ አገራት አንዷ እስላማዊ አገር ነኝ የምትለዋ ግብጽ (ምስር) ነች። ግብጽ ኢትዮጵያውያን ትልቁ ሀብታቸው በሆነው የአባይ ወንዝ እየገነቡት ያለውን ታላቁን የህዳሴ ግድብን በመቃወም ኢትዮጵያ ላይ ዘርፈ ብዙ ጫና እንዲፈጠር ስትወተውት ቆይታለች፤ እየወተወተችም ትገኛለች።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሙፍቲህ ሐጂ ዑመር እንድሪስ ይህን ከእስልምና አስተምህሮ ያፈነገጠው የግብጽን አቋም ሲተቹና የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀምን በተመለከተ ሲያብራሩ፤ ሸሪዓው የሚለው የላይኛው የምንጩ ባለቤት ተጠቅሞ ሲያበቃ ለታችኛው ይልቀቅለት ነው፤ ይህ የግብጽ ዑለሞችም ያውቁታል ብለዋል።
“ከዚህ በተረፈ የግብጽ ወንድሞች በብርሃን ሲኖሩ የኢትዮጵያ ወንድሞች በጨለማ ይኑሩ የሚል ሃይማኖታዊም ሆነ ሌላም ሕግ አይኖርም። እናንተም በመብራት እንደምትኖሩት እኛም በመብራት እንኑር ነው ያልነው፤ ይህ ሸሪዓችን ያወድሰዋል እንጂ አያወግዘውም” ሲሉም ለግብጾች ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈውላቸዋል። እስልምናን እና ነቢዩ መሐመድን በመቀበል ብሎም እስልምናን በመርዳት እኛ ሐበሾች እንደምንቀድም፤ እንዲሁም ሙስሊሞች ብቻ ሳይሆኑ ክርስቲያን ወንድሞቻችንም ነቢዩ መሐመድን ረዱ እንጂ አልወጉም ሲሉ ግብጻውያንን ሞግተዋል::
ሌላው ሐበሻን ከዓለም አገራት ለየት ከሚያደርጓት ነገሮች አንዱና ትልቁ የሐበሻ ሰዎች ጥሩነት በቅዱስ ቁርዓን ውስጥ መገለጹ ነው። ሱለይማነል ጀመል ሀዚም የተባሉ ሰው፣ ኢብኑ አባስ አወሩት ብለው እንደገለጹት “እነዚያ እኛ ነሳራዎች (ክርስቲያኖች) ነን ያሉት ወደ ሙዕሚኖች (ሙስሊሞች) የቀረቡና የተወደዱ ሆነው በርግጥ ታገኛቸዋለህ” (ቁርዓን ሱረቱል ማኢዳ፥82) የሚለው የአላህ ንግግር ለሐበሾች እንደሆነ መስክረዋል።
ነብዩ መሐመድን ዑሙ ሀቢባ ከምትባለው ባለቤታቸው ጋር ያጋባንና በጋብቻ ወቅት ለሴቷ የሚሰጥ ገንዘብ (መኽር) የከፈልን መሆናችንም ለየት ያደርገናል። ነብዩ መሐመድ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ከመካ ወደ መዲና ከተሰደዱ በስድስተኛ ዓመት ወደ ነጃሺ አንድ ደብዳቤ ላኩ። በደብዳቤው ውስጥ ዑሙ ሀቢባ ቢንት አቡ ሱፍያን የተባለች ሴት ከባሏ ጋር ወደ ሐበሻ ተሰዳ ሳለ ባሏ በስደት ላይ በመሞቱ ነብዩ ሊያገቧት እንደፈለጉ የሚገልጸው መልእክት ይገኝበታል። ነብዩ መሐመድን በመወከል ለዑሙ ሀቢባ ከነጃሺ የተሰጠው መኽር 400 ዲናር ሲሆን በነብዩ ወገን ሆኖ ለጋብቻው (ኒካህ) ስኬታማነት ትልቁን ሚና የተጫወቱት የሐበሻው ንጉስ ነጃሺ ናቸው።
ሌላው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም በየሄደበት ሁሉ በጣም ከሚደሰትባቸውና ከኮራባቸው ነገሮች አንዱ በእስልምና ታሪክ የመጀመሪያው አዛን አድራጊ (ለሶላት ተጣሪ) ቢላል ኢብኑ ረባህ (ቢላል አል-ሐበሻ) ኢትዮጵያዊ መሆኑ ነው። ቢላል ከነብዩ ታማኝ ባልደረቦች አንዱና ዋነኛው የነበረ ሲሆን እስልምናን በመቀበሉ ምክንያት ከጠላቶች ቅጣትን ከመቀበሉ ባሻገር በቅጣቱ ሰዓት ባሳየው ታላቅ ጽናት የተነሳ “ወደ አላህ ተጣሪ” በሚል ከአላህ ሙግስናን አግኝቷል። በቅዱስ ቁርዓንም “ያ እርሱ ወደ አላህ ከሚጣራው የበለጠ ድምጹ ያማረ ማን ነው?” ተብሎ ተጠቅሷል።
በበርካታ እስላማዊ መጽሐፍት እንደተገለጸው ነብዩ መሐመድ ከአላህ ጋር ለመገናኘት ከጅብሪል (ገብርኤል) ጋር በመሆን ወደ ላይ (ሚዕራጅ) በወጡ ጊዜ በሐበሻ ምድር ብርሃናቸው እንደ ክዋክብት የሆኑ ሰዎች ተመለከቱ። ለጅብሪልም “እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?” ብለው ጠየቁት። “እነዚህማ ከዑመትህ ውስጥ የሆኑ ሐበሾች ናቸው!” ብሎ መለሰላቸው። ነብዩም “ጌታዬ ሆይ! እርዳቸው!” ብለው ዱዓ (ጸሎት) አደረጉ።
የነብዩ መሐመድ ልጅ ሩቂያ፣ በጣም የሚወዷቸውና የቅርብ አማካሪያቸው የሆኑት እንዲሁም ለእርሳቸው ያላቸው ከበሬታ የላቀና የሁለት ልጆቻቸው ባለቤት ዑስማን፣ የአላህ ካዝና በእርሱ እጅ ያለ የሚመስለው ሀብታሙ አብዱራህማን፣ ነብዩን በመልክ የሚመሳሰሉትና የአጎታቸው ልጅ የሆኑት ጃዕፈር፣ የዑለማዎች ኮከብ ተብለው የሚታወቁት ታላቁ አብደላህ ኢብኑ መስዑድ እና ሌሎችም የነብዩ መሐመድ ባልደረቦች ይህቺን አገር መርገጣቸው እንዲሁም ከእነርሱ በክብር ያልተናነሱ ታላላቅ የነብዩ መሐመድ ባልደረቦች በሐበሻ ምድር በሞት መቅረታቸው ዓለም ላይ ካሉ አገራት ሁሉ ኢትዮጵያን ለየት ያደርጋታል።
በተጨማሪም ስለ ሐበሻ ሰዎች የተጠቀሱ የቁርዓን አንቀጾችና ስለ ሐበሻ በነብዩ መሐመድ የተደረጉ ንግግሮች (ሐዲሶች) መኖራቸው፤ ንጉሥ ነጃሺ የነብዩን እጮኛ ማክበራቸውና መኽሩንም በራሳቸው መክፈላቸው እንዲሁም የነጃሺ ባለቤቶች ዑሙ ሀቢባ የተባለችው የነብዩ መሐመድ እጮኛን በተለያዩ ስጦታዎች ማንበሽበሻቸው ከሌሎች ሀገሮች በተለየ የሐበሻ ታላቅነትና ክብር የሚገለጽባቸው ነጥቦች ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ የዓለም ሕዝብ ወደ ስምንት ቢሊዮን እንደሚጠጋ የሚገመት ሲሆን፤ የሙስሊሙ ሕዝብ ቁጥር ሁለት ቢሊየን ይሆናል ተብሎ ይታሰባል። ያለምንም ማጋነን የፖለቲካ ጉዳይ ችግር ካልሆነበት በስተቀር አብዛኛው የዓለማችን ሙስሊም ሕዝብ የአላህ ቃል በሆነው በቅዱስ ቁርዓን እና በነብዩ መሐመድ ንግግሮች ስለፍትሐዊነቷ የተመሰከረላት ሐበሻን (ኢትዮጵያን) መጎብኘት ይፈልጋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች በመላው ዓለም የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች እንዲያውቋቸውና ለኢትዮጵያ ተገቢውን ክብር እንዲሰጡ ማድረግ ይጠበቅብናል። ከቱሪዝም እድገት በተጨማሪ ለዲፕሎማሲያችን መሻሻልም ትልቅ ሚና ይኖረዋል።
ኢትዮጵያ ለእስልምና ሃይማኖት ያበረከተችውን አስተዋጽዖ ያልዘነጉና ለዚህም ክብር የሚሰጡ የዓረቡ ዓለም አገራት እንዳሉ ሁሉ፤ ጥቂት የማይባሉ አገራት ደግሞ ከኢትዮጵያ ጎን መሰለፍ ሲገባቸው ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ባለችበት ወቅት ሲርቋት ታይተዋል። ከመራቅም አልፈው ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመሆን በተለያዩ መንገዶች ኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና እንዲደረግ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
እነዚህ አገራት የኢትዮጵያን ውለታ ዘንግተውት አይደለም ከኢትዮጵያ በተቃራኒ የቆሙት። ግብጽ እኛ ኢትዮጵያውያን ተፈጥሮ የለገሰችን የአባይ ወንዛችንን ገድበን እንዳንጠቀም ለማድረግ ስትንቀሳቀስ የኢትዮጵያን ውለታ ወይም “ሐበሾች ሳይነኳችሁ አትንኳቸው!” የሚለው የነብዩ መሐመድን ንግግር ረስታ አይደለም። ሳዑዲ አረቢያ ዜጎቻችን ስታሰቃይና ከአገሯ ስታስወጣ የኢትዮጵያን ውለታ ወይም የነብዩ መሐመድን ንግግር ጠፍቷት አይደለም። ሱዳን እንኳን በአቅሟ ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ የገባችበትን ወቅት ጠብቃ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ በመግባት መሬታችንን ስትወር ነብዩ መሐመድ ስለሐበሻ የተናገሩትን አጥታው አይደለም። ከላይ የተጠቀሱን የሦስቱ አገራት ድርጊት የአላህ ቃል የሆነውን ቁርዓንና የነብዩ መሐመድን ንግግር (ሐዲስ) የጣሰ እንዲሁም ኢትዮጵያ ለእስልምና የዋለችውን ውለታ ያላገናዘበ ነው።
ከላይ የተጠቀሱ አገራት ችግር እውነታውን አለማወቃቸው ሳይሆን “አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንደሚባለው የግል ፍላጎታቸው ጆሯቸውን ስለደፈነው ከእውነትና ከታሪክ ጋር እንዲጣሉ አድርጓቸዋል። ሆኖም ግን ያለመሰልቸት እውነታውን ከማሳወቅ አንጻር ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራበት ይገባል።
እንደ አጠቃላይ ከላይ ከተጠቃቀሱ ነገሮች ጋር ተደምሮ የነብዩ መሐመድ ቤተሰቦችና ታላላቅ ባልደረቦች ለበርካታ ዓመታት በአገራችን መኖራቸው ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት የተለየች ያደርጋታል። በመሆኑም በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች የሆኑ ሙስሊሞች ለኢድ ሰላት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ “ከኢድ እስከ ኢድ” (ከኢድ አል-ፊጥር እስከ ኢድ አል-አድሃ) በሚል መሪ ቃል በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የቀረበው ጥሪ ኢትዮጵያ ለእስልምና ኃይማኖት ያበረከተችውን አስተዋጽዖ ለመላው ዓለም ከማሳወቅ አንጻር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
አብዱረዛቅ መሐመድ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4 /2014