እንደምን አላችሁልኝ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ወዳጆቼ፤ በቅርቡ በአገራችን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ምርጫ ተጠናቆ በቀጣይ ወራቶች ሥራቸውን እንደሚጀምሩ በጉጉት እየተጠባበቅን ነው። ባለፉት አስርት ዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮቻችን ቢቻል ሁሉንም ካልተቻለም ዋና ዋና የምንላቸውን ሰንኮፎች ነቅለን ጥለን አርቀን ለመቅበር ብሔራዊ ደወሉን በእርግጥ ደውለናል።
አገራዊ ምክክሩ ሁሉንም አካታች በሆነ መልኩ ለመፍታትና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ኮሚሽኑ ከሚኖረው ከፍተኛ አገራዊ ኃላፊነት አኳያ ለኢትዮጵያ በሚበጅ ሁኔታ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በመውሰድ አዳዲስ ስትራቴጂዎችን ነድፎ ውጤታማ ሥራዎችን ይሠራል ተብሎ ተስፋ ጥለንበታል።
እንደዚህ ዓይነት ግዙፍ አጀንዳ ለኮሚሽኑ ወይንም ለመንግሥት አካላት ብቻ የሚተው ሸክም ሳይሆን ሕዝብን እንወክላለን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት ኃላፊዎች አገራዊ ምክክሩ በአንዳንድ ልግመኛ ምሁራኖችና ፅንፈኛ ፖለቲከኞች እንዳይጠለፍ መጠንቀቅ አለባቸው:: በተለይ የሰመረ ውጤት እንዳያመጣ ሊያደናቅፉ የሚያስቡትን ሴረኞች ማጋለጥና ታሪካዊ ኃላፊነትን ወስዶ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት ማስጠበቅ ያገባኛል የሚል ኢትዮጵያዊ ሁሉ ግዴታ ነው።
እዚህጋ «አንድነት» ስንል ብሔራዊ የዜግነት ግዴታ ማለታችን ነው። ያለአንድነት አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ያለ አንድነት ሉአላዊነት ጤና ልማት ትምህርት የተለያዩ አጀንዳዎችን ይዘን ብንመጣም ሁሉም ትርጉም የለላቸው፤ የመወያያ እርዕሶች ብቻ ሆነው ነው የሚቀሩት::
በቅድሚያ ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል የምንስማማበት የአንድነት አጀንዳችን መሆን አለበት። በዚህ አጀንዳ የምንስማማ ከሆነ ያሉንን የልዩነት በሰከነና አስተማማኝ በሆነ ብልሀት መፍታት እንችላለን:: ለአገራዊ ምክክር ዋስትና የሚሆነውም ይኸው አብሮነታችን ነው።
በጋራም የምንስማማበት ኢትዮጵያም እንደ አገር ልትፀና የምትችለው በጠንካራ ሕዝባዊ አንድነት በመሆኑ ለችግሮቻችን ሁሉ ስኬታማና አስተማማኝ መፍትሔ ልንሰጥ የምንችለው በአንድነት ለአንድ አገር ስንቆም ነው። ዋናው አገራዊ ውይይት ጠቀሜታው ይኸው ነው::
የሁሉም ብሔረሰቦች እኩልነት እንዲረጋገጥና አንድነታቸው እንዳይፈርስ በባህል፣ በታሪክ፣ በሃይማናት፣ በምጣኔ ሀብት የተቆራኘን በመሆናችን ኢትዮጵያዊነት በታሪክ የተገነባ መሆኑን መተማመን ያስፈልጋል። ዛሬ H.R. 6600 እያለች የምትመፃደቀዋ አሜሪካም ሆነች ሌላው ዓለም የእኛን የእርስ በእርስ ጦርነት ከርሀብና ከበሽታ ከኋላ ቀርነት በአጠቃላይ ከተረጂነት መንፈስ የምንላቀቅበትንና እራሳችንን የምንችልበትን፣ አካሄድ አይፈልጉትም::
የእኛ በአንድነት መቆምና ብዙ የችግር ዘርፎችን ድል ማድረጋችን አገራዊ ምክክር መጀመራችን የምሥራቅ አፍሪካ ኃያልነታችንን እንደሚያበስር ስለሚረዱ ቅን ያሰቡ መስለው አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች የሚል ታፔላ እየለጠፉ እርስ በእርስ ጣት እንድንጠቋቆም ያደርጉናል::
ከዚያም ባለፈ ከተረጂነት መንፈስ እንዳንላቀቅ በዘር ፖለቲካ እንድንታመስ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ደግፈው የተከፈተብንን የህልውና አደጋ በተባበረ ክንዳችን እንዳንከላከል በብድርና በእርዳታ ማዕቀብ የማስፈራሪያ አንቀፅና ሕግ እያረቀቁ ሕዝባችንን የስነ ልቦናና የፕሮፖጋንዳ ሰለባ ያደርጉብናል:: ከአሁን በኋላ ግን ይምረረንም ይጣፍጠንም በታሪክ ፊት ቆመን አንድ እውነት እንመሰክራለን::
ድሮም ያልሆነብንን ዛሬም ሆነ ወደፊት እንዲሆንብን አንፈቅድም፤ በቀጣይም ነፃና ሉአላዊት ኢትዮጵያ አገራችን በውጭ ሞግዚት ልተመራ የምትችልበት ምንም ዓይነት የታሪክ ቆሻሻ ምልክት የለብንም። አገራዊ ምክክሩ ደግሞ ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት በጋራ ስምምነት በአንድነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው:፡
አገራዊ ምክክሩን በፅንፈኛ ፖለቲከኞች የምናጨናግፈው ከሆነና ሕብረት ካጣን የመተማመንና የመረዳዳት እሴት ካልገባን ለወገን ተቆርቋሪ መስለን ለጠላት ካደርን፣ ዘረኛ ፖሊሲ ገንብተን ፅንፈኝነትን ከመረጥን የኢትዮጵያ ክብር መሆን ቀርቶ ማፈሪያ ሆነን የልመና ኮሮጇችንን ይዘን ወደ ሌላ ዓለም በመሰደድ በየእስር ቤቱ ታዛ ወድቀን የመንግሥት ያለህ እያልን ማልቀሳችን የማይቀር ነው::
ይህ ደግሞ ትንቢት ሳይሆን እውነት ሆኖ በዓይናችን ያየነው ስለሆነ እንደ አገር የማንቀጥልበትም ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ:፡ ስለዚህ አገራዊ ምክክሩ በሴረኞች እንዳይጠለፍ ተጠንቅቀን በብልሀትና በፖለቲካ ብቃት ይዘን ብሔራዊ ማንነት ላይ ደርሰን አንድነታችንን ማስቀጠል ይኖርብናል::
ሌላ ሌላውን ቀስ እያልን በሒደት የምንሠራው ቢሆንም ለአገርና ለሕዝብ የማይበጁ አመራሮችን ከመጨረሻው የስልጣን እርብርብ እስከ ከፍተኛው የስልጣን ደረጃ ያሉ ሰዎችን ከተቀመጡበት ወንበር አሽቀንጥረን ጥለን ሊሠሩ በሚችሉት በአዳዲስ የአንድነት ራዕይ ባላቸው የመደመር ጭንቅላቶች መተካት ይኖርብናል:: ለዛሬው በዚሁ አበቃሁ፤ በሌላ ዝግጅት እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን።
ሰላም!
ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4 /2014