በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ከታዩ ድንቅ ባለ ተሰጦ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች መካከል ራሺድ ያኪኒ አንዱ ስለመሆኑ በርካቶች ይስማማሉ። የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን የምንጊዜም ኮኮብ ግብ አስቆጣሪው አረንጓዴ ንስሩ በአሳዛኝ ሁኔታ የህልፈተ ህይወቱ ዜና ከተሰማ አንድ ዓመት አለፈ። ከኳስ ውጪ ሌላ ህይወት እንዳልነበረው የሚነገርለት ጭምቱ ኮከብ ጫማውን ከሰቀለ በኋላ የነበረው ህይወትና የሞተበት መንገድ አሁንም ድረስ የስፖርት ቤተሰቡ መነጋገሪያ ነው።
ያኪኒ ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል የኖረበትን የእግር ኳስ ህይወት በአገሩ ሊግ የጀመረ ቢሆንም በቀጣይ ያመራው ወደ ኮትዲቯሩ ክለብ አፍሪካ ስፖርት ናሽናል ነበር። ለህይወቱ ማለፍ ምክንያት ተደርጐ የሚጠቀሰው ጉዳይም ከዚህ ይጀምራል። ያኪኒ በኮትዲቯሩ ክለብ በነበረው ቆይታ የሚያገኘውን ገንዘብ በራሱ ስም በባንክ የሚያስቀምጥ ሰው አልነበረም። ይልቁንም በትውልድ አገሩ በናይጄሪያ ቤቱን ለሚጠብቅለት የቅርብ ጓደኛው በመላክ እንዲያስቀምጥለት ያደርግ ነበር። ይህ ጓደኛውም የሚልክለትን ገንዘብ ተቀብሎ እቤቱ ውስጥ ሲያጠራቅምለት ይቆያል። ከዕለታት አንድ ቀን ግን ይህ ጓደኛው የተጠራቀመው ገንዘብ ልቡን አሸፍቶት ከኮከቡ ጓደኛው ይልቅ ንዋይን መረጠ።
ያኪኒ የኮትዲቯር ቆይታውን ደምድሞ ወደ አገሩ ሲመለስም ጓደኛው ከድቶት ቅንጡ መኪናና ቤት ገዝቶ የተንደላቀቀ ህይወት ሲመራ ተመለከተው። ከዚህ ጊዜ አንስቶም ያኪኒ ሰውን መራቅና ብቸኝነትን ከመምረጥ ባለፈ ማንንም ማመን አቆመ። የያኪኒ ህይወት ግን በዚሁ አላበቃም። ሌላ ተስፋና ሌላ ህይወት የጀመረበትን አጋጣሚ ከወደ አውሮፓ አገኘ። ፖርቹጋል፤ ግሪክና ሌሎች በርካታ አገራት ተዘዋውሮ በመጫወት በራሱ ላብ በክህደት ያጣውን ገንዘብ መልሶ አገኘው።
የ1994 የዓለም ዋንጫ ሲታወስ ያኪኒን አለማስታወስ ይከብዳል። በዚህ የዓለም ዋንጫ ናይጄሪያና ቡልጋሪያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውም እያደረጉ ነበር። ያኪኒ ከፊኒዲ ጆርጅ ያገኛትን ኳስ ወደ ጎልነት ሲቀይራት ራሱም አብሮ ግቡ ውስጥ የገባበት አጋጣሚ አሁንም ድረስ በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ እንደ ትናንት ይታወሳል። ሁለት እጆቹን በመረቡ ቀዳዳዎች በኩል ወደ ውጭ አውጥቶ፣ አይኖቹን ጨፍኖ በስሜት ጮኸ። የፎቶ ካሜራዎች ተንቀጫቀጩ።
የእግር ኳሱ ዓለም ምስሉን ከማይረሱ የውድድሩ ትዕይንቶች ጎራ ፈረጀው። የያኪኒ ግብም ንስሮቹን በከፍታ ላይ አበረራቸው። ጣፋጭ የሦስት ለዜሮ ድልም አጣጣሙ። በዚያ ዘመን ያኪኒ በዝና ላይ ዝና ተጨመረለት። በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው በሰባት ጨዋታ ስምንት ግብ አስቆጥሮ ሀገሩን አሳለፈ። በአፍሪካ ዋንጫም የቡድኑ የውጤት ሞገስ ሆኖ በድል ጨረሰ። በፖርቹጋል ሊግ የስኬት ካባ በደረበበት ዓመትም ከፍቅረኛው ጋር በሰርግ ተሳሰረ። ሁሉም ሙሉ ሆነለት። ብዙ ሳይቆይ ግን የሞላው መጉደል ጀመረ። ያኪኒና ፍቅሩ ወደ ጫጉላ በፍቅር ሄደው በጠብ ተመለሱ።
ትዳሩም ሳይጀመር ተጠናቀቀ። ለናይጄሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ሲጫወት፣ ያን ሁሉ ጀብድ የሰራው ሳተና በወረት ዋግ ተመታ። የደጋፊ ተቃውሞ በዝቶበት መንፈሱ ላይጠገን ተሰበረ። ከዚያ ወዲህ አረንጓዴውን ማሊያም አልለበሰም። ያኪኒ ብዙ ባልንጀራ የለውም። የልቤ ሰው የሚለው ብዙ የለውም። ጭንቅ የማይችል፣ መታየት የማይወድ፣ ሁሉ በሆዱ ሰው ነበር። ለአንድ ሰው ብቻ ግን ግልጽ ነበር። ኢብራሂም ይባላል። ያኪኒ ይቀርበዋል፣ ያምነዋልም። ከተጫዋችነት ከተገለለ በኋላ፣ ደመወዙ ሲነጥፍ እንደማንኛውም ስፖርተኛ ቢዝነስ ውስጥ ለመግባት ከጀለ።
ኢብራሂም መንገዱን ያውቀዋል፣ ያኪኒ ደግሞ ገንዘብ አለው። ስለዚህ ያፈራውን ጥሪት ወደ ገንዘብ ቀይሮ፣ ያለውን ሁሉ አራግፎ ለኢብራሂም አስረከበው። ጌጣጌጥ ንግድ ታሰበ። የውጭ ምንዛሪ ስለሚያስፈልግ የያኪኒ ገንዘብ ባስፈለገ መጠን ተመነዘረ። ግን የዕቅዱ ምስጢር አልተጠበቀም ነበር። ይህም ሌላ መዘዝ ይዞበት ከች አለ። በቅርብ ሲከታተሏቸው የነበሩ ዘራፊዎች ጓደኛውን እቤት ውስጥ ገድለው ጠቅላላ ገንዘቡን ይዘው ተሰወሩ። አሁን ያኪኒ ልቡ ክፉኛ ተሰበረ፤ ያመነው ጓደኛው ከዳው፤ የታመነለት ደግሞ በዘራፊዎች ተገደለ፤ ይህም ቅስሙን ሰበረው።
ኢብራሂምን ያጣው ያኪኒ። ያለገንዘብ ብቻውን ቀረ። ህመሙን ለብቻው ታመመ። በአንድ ጀንበር ሁሉን አጣ። ከዚያ በኋላ ህይወቱ መቅኖ ቢስ ሆነ። ከህዝብ ተደበቀ። ከዘመዶቹ ርቆ በኢባዳን ከተማ ተገልሎ መኖርን የመረጠበት ምክንያትም ይህ ነው። ያኮራት ናይጄሪያም በዚህ ወቅት ሲቸገር አልፈለገችውም። ጎረቤቶቹ ግን የዝናው ዘመን አብቅቶ ሞራሉ የደቀቀውን ያኪኒን ከሰው ተራ ወጥቶ፣ በጎዳና ዳር የሙዝ ጥብስ የሚሸጡ ጉልቶች ዘንድ ቆሞ ያዩታል።
በኢባዳን ከተማ ጎዳና ዳር ባለ ጥሻ ውስጥ ተፀዳድቶ ሲወጣ አይተነዋል የሚሉም አሉ። የመጨረሻዎቹ ዓመታት ያኪኒ ከሰው ተገልሎ «ጠላቶቼ ኢብራሂምን ገድለው ለዚህ አበቁኝ» በሚል እምነት ብቻ ከራሱ ጋር ረጅም ሃዘን ተቀመጠ። ከአምስት ዓመታት በላይ በጭንቀትና በድብርት አሳለፈ። ያኪኒ በዚህች ትንሽ ከተማ ህይወቱን መምራት በጀመረበት ወቅት ይታይበት የነበረው ያልተለመደ ባህሪን ተከትሎም ነበር የመገናኛ ብዙሃን እይታ ውስጥ የገባው። ያኪኒ በዚህ ወቅት እጅግ ብቸኛ ከመሆኑ ባሻገር የአዕምሮ እክል ገጥሞት እንደነበር መረጃዎች ወጥተዋል። ሲከታተሉት የነበሩ የናይጄሪያ መገናኛ ብዙሃን ያኪኒ የቅርብ ቤተሰቦቹን ጭምር እቤቱ ሲመጡ ያባርራቸው እንደነበር በወቅቱ ዘግበዋል።
ያኪኒ ከዚህ ካልተለመደ ባህሪው ባሻገር በአካባቢው ያሉ ሰዎችና ጎረቤቶቹ የአዕምሮ ችግር እንዳልነበረበት አስተያየት ሲሰጡ ተደምጠዋል። እንዲያውም ያኪኒ በአካባቢው ካሉ ድሃ ማህበረሰቦች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንደነበረውና ከገንዘብ አንስቶ እስከሚመገቡት ሩዝ ሲያከፋፍል እንደኖረ ይናገራሉ። ይህም የእውነት ያኪኒ የአዕምሮ ችግር ነበረበት ወይስ የደረሰበት ስነ ልቦናዊ ጉዳት ራሱን ከቅርቦቹ ሰዎች እንዲያገል አደረገው የሚል ውዝግብ እንዲነሳ አድርጓል።
ረጅሙ አረንጓዴ ንስር ልክ የዛሬ ዓመት ከቤቱ ያለፍላጎቱ ተጎትቶ ለመውጣት ሲገደድ በአካሉ ላይ ደም ይታይበት ነበር። ከምስክሮች አንዳንዶች «እገታ ነው» አሉ። ሌሎች ደግሞ ውለታው የከበዳቸው ወገኖች ከቤቱ ወስደው አስገድደውም ቢሆን ሊያሳክሙት ስለፈለጉ ነው ብለው አመኑ። ምንም ይሁን ምን፣ ያኪኒ ከራሱ ዓለም ውጭ መኖርን አልፈለገም። ራሱ ባጠረው ቅጥር ውስጥ እስከ ህይወቱ ፍፃሜው ቆየ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 8/2011
ቦጋለ አበበ