ዌኒስተን ቸርቺል እንደሚሉት፤ የማይቀየር ወዳጅም ሆነ የማይቀየር ጠላት የሚባል ነገር የለም፤ ምን ጊዜም የማይቀየረው የሰው ፍላጎት ብቻ ነው። ይሄንን ብሂል ብዙ ሰዎች ሲደጋግሙት እንሰማለን። ኮምጣጣው ያገሬ ሰው ግን ይህን አይቀበለውም፤ ይልቁንም፡-
“ጠላትማ ምጊዜም ጠላት ነው
አስቀድሞ መግደል አሾክሻኪውን ነው፤” ይላል።
ዝም ብዬ ሳስብ በአንድ በኩል የሀገሬ ሰው ያለው ትክክል ነው። የማይላቀቁ ጠላቶች አሉ። የታሪክ ጸሐፊዎቿ እንደሚያጫውቱን ሀገራችን በታሪኳ ብዙ የውጭ ጠላቶችን እንደአመጣጣቸው አስተናግዳለች። በመጡበት እግራቸው የተመለሱም ተመለሱ፤ የተረፉትንም ያለፈውን ቂም ትተን “ይቅር ለእግዚአብሔር” ተባብለን ከነዚሁ ጋር በሰላምና በፍቅር እየኖርን ነው። ሆኖም አንደ አልቅት ተጣብቃን የማትላቀቀው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ባላንጣ የሆነችብን ግብጽ ነች። የአገሬን ሰው ብሂል እውነት ያስባለች የማትቀየር ባላንጣ ነች። ዓባይን ለዝንተ ዘመን ያለ ተቀናቃኝ የግሏ አድርጋ ስለኖረች አሁንም ለሚመጡት ዝንት ዓለሞች ያለ ተጋሪ የግሏ ሆኖ እንዲቀጥል ያላት ፍላጎት ቀጣይ ነው። በስስት ለምትመለከተው ዓባይ ተቀናቃኜ ነች የምትለው ኢትዮጵያን ነው፡፡
በኢትዮጵያ ላይ ዓይኗን ካደፈረሰች፣ ጥርሷን ከነከሰች ብዙ ዘመን ሆኗታል። ኢትዮጵያን ለማሽመድመድ ቢቻል ለማጥፋት በሚገርም ትጋት ለዘመናት ሣታቋርጥ እየሠራች ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ ግብጽን ላጥፋት ብላ ኢትዮጵያ አቅዳ አታውቅም። ግብጽ ግን ግልጽና ስውር ደባ በኢትዮጵያ ላይ ትሠራለች። የሚገርመኝ ደግሞ ግብጽ የራሷን ብልሀትና ጉልበት ብቻ ሳይሆን ኃያላን መንግሥታትን በማስተባበርና ተገኗ ማድረግን ተክናበታለች። የምትመጣብን እንደ የአውሮፓንና አሜሪካን ያሉ ኃያላንን አስተባብራ የሙጥኝ ብላ ይዛ ነው። የአሜሪካና የአውሮፓ በተለይም ዘረኛ ነጮች ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ በሚሸረብ የግብጽ የጥፋት ዕቅድ ላይ ለመተባበር አያቅማሙም። እኛ ግን በአብዛኛው ማንም ተገን ሳይኖረን የምንጋፈጠው ብቻችንን ነው፡፡
ለምሳሌ፣ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1863 የግብጽን በትረ-መንግሥት የተቆጣጠረው ከዲቭ እስማኤል ያባይን ሸለቆ እንዲሁም ከተመቸም ዘልቆ ገብቶ ቀሪውን የኢትዮጵያን ክፍል ለመቆጣጠር ተመኝቶ ከፍተኛ የጦር ዝግጅት ሲያደርግ የገንዘብም ሆነ የሞራል ድጋፍ ያደረጉት አውሮፓውያን ነበሩ። እርሱም በኢትዮጵያ ላይ የሚዘምተውን የግብጽን ጦር እንዲመሩለት ያሰባሰበው የጦር አዛዦችና ባለሙያዎች ከአሜሪካ፣ ከዴንማርክ፣ ከሲዊይዘርላንድ፣ ከቱርክ የተውጣጡ የደነደነ የጦር ስልት አዋቂዎችን ነበር። ጦሩን እንዲመሩ ሙሉ ኃላፊነት ለቅጥረኛ አሜሪካውያንና አውሮፓውያን ሰጥቶ የግብጽን ሠራዊት በዘመናዊ መሳሪያ አስታጥቆ ወደ ኢትዮጵያ ሲሸኝ ድል በጁ እንደምትገባ ሙሉ እምነት ነበረው። አለንልህ አይዞህ በርታ!! ከማለትም አልፈው ለጦርነቱ የሚውል ገንዘብ ያበደሩት የአውሮፓ መንግሥታት በተለይም የእንግሊዝና የፈረንሳይን ባለሀብቶችም ጦርነቱ በከዲቭ እስማኤል ድል አድራጊነት እንደሚጠናቀቅ አልተጠራጠሩም።
እንደተመኙትና እንደተገመተው ሳይሆን ቀርቶ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት በአጼ ዮሐንስና በአሉላ አባነጋ እየተመራ ቴክኖሎጂውንና ስልጠናውን የተማመነውን የግብጽን ጦር ከነፈረንጅ መሪዎቹ በጉንደት (እ.አ.አ 1875) እንዲሁም በጉራዕ (እ.አ.አ 1876) በተደረጉት በሁለት ተከታታይ የጦር አውድማዎች ሁሉ ሽንፈትን አቀመሷቸው። አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጂራ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው የጦርነቱን ውጤት ሲገልጹ፤ “አጼ ዮሐንስም ሠራዊቱን አስከትቶ ከምስር ታዞ የመጣውን ቱርክ እንደ ካንቻ መታው፤… እየደጋገመ ሁለት ጊዜ ወቃው” ይላሉ። አብዛኛው የግብጽ ጦርና አሜሪካውያንና አውሮፓውያን መሪዎቻቸው ጭምር እዚሁ ጥሪኝ አፈር ሆነው ቀሩ። ቅስሟ ተሰበረ፡፡
በነዚህ ጦርነቶች በደረሰባት ሽንፈት ግብጽ አፍራ የጤፍ ፍሬ አከለች። የአውሮፓ አይዞሽ ባዮች ሁሉ ተበሳጩ። በዚሁም የተነሳ 1879 ከዲቭ እስማኤልን ከስልጣን እንዲለቅ አድርገው ተውፊቅ ፓሻን አስቀመጡ። የነዚህ ጦርነቶች ዳፋ በግብጽ ውስጥ ከፍተኛ ትርምስን ቀሰቀሰ። በጦርነቱ ምክንያት ከተከሰተው የኢኮኖሚው ቀውስ በተጨማሪ “ጦርነቱን የተሸነፍነው በአመራር ድክመት ነው” በሚል ቁጭት የተቀጣጠለው ወታደራዊ አመጽ የተውፊቅን መንግሥት አሽቀንጥሮ ለመጣል ሲወዘውዘው አይታ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ስትል እንግሊዝ ጦሯን ይዛ ገስግሳ ግብጽ ገባች። በቀላሉም አልተመለሰችም። በዚያው ግብጽም በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ቀንበር የመጠመድ ሂደት ተጀመረ። “ኢትዮጵያን የነካ የለውም በረካ” ይሏል ይሄ ነው፡፡
በአንጻሩ ኢትዮጵያ በድል ላይ ድል እየጨመረች በ1896 በአድዋ የጦር አውድማ በጣሊያን ወራሪዎች ላይ በአጼ ምኒልክ መሪነት ድሏን ደገመች። በቅኝ አገዛዝ ዘመን የነጻነት ባንዲራዋን እያውለበለበች ብቸኛዋ በአፍሪካ አሁጉር ነጻ ሀገር፤ ለጥቁር ህዝብ አብሪ ኮከብ ሆና ቀጠለች። ይመስገን!!
ግብጽን ከ1882-1922 በቅኝ ግዛት ስርአት እንግሊዞች ቀጥቅጠው ገዟት። በነዚሁ ዓመታት ውስጥ እነርሱም ቢሆኑ አይናቸውን ከኢትዮጵያ ላይ አላነሳ አሉ። እንግሊዞች የዓባይን ተፋሰስ ቦጭቀው ከኢትዮጵያ ወስደው ከቅኝ ግዛታቸው ጋር መቀላቀል ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነበር። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1906 ከፈረንሳይና ከጣሊያን ጋር ኢትዮጵያን ለሶስት ለመቀራመት ተግባቡ። በስምምነቱም ከአዲስ አበባ -ጂቡቲ የባቡር መስመር አኳያ ለፈረንሳይ እንዲሰጥ፤ በዓባይ አቅጣጫ ለራሷ ለእንግሊዝ እንዲሰጥ፤ የቀረውን የኢትዮጵያ ክፍል ደግሞ ለጣሊያን ከኤርትራና ከሱማሌ የቅኝ ግዛቶቿ ጋር ቀላቅላ እንድትገዛ ተስማሙ። ይሄንንም ስምምነት ምኒልክ እንዳይሰሙ ምስጢራዊነቱ እንደተጠበቀ እንዲቆይ ተግባቡ። የሚያስቀው አላማችን “የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት መጠበቅ ነው” የሚል ሽፋን ማልበሳቸው ነበር፡፡
የዚህ ስምምነት ሠነድ ዋና አዘጋጅ የነበረው ሎርድ ሀሪንግተን ለአለቃው ለእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ የጻፈው ሪፖርት እውነተኛ ፍላጎታቸውን አጋልጧል። የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ማስጠበቅ ሳይሆን ፈራሚ ኃያላን መንግሥታት በጥቁሮች ላይ የሚከተሉት ፖሊሲ የነጮችን ፍላጎት ያሟላ መሆኑን ማረጋገጥ ነው ብሏል። አፈር ይቅለላቸውና፤ ታዋቂው የታሪክ ጸሐፊ የነበሩት ሪቻርድ ፓንክረስት እንዳስቀመጡት “…his main object was to ensure that the three powers followed a policy in the interests of whites against blacks…” (Richard Pankhurst, Mederek, 1993.)። ይህ መሠሪ ተንኮላቸው አልተሳካላቸውም እንጂ ተሳክቶላቸው ነገሩ ቢፈጸም ምኒልክ የሶስቱን ኃያላን ጦር አሸንፈው የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅ ይችሉ ነበር?! ለማንኛውም አልተሳካላቸውም! ኢትዮጵያም ተረፈች!
በ1922 እንግሊዞች ለግብጽ ነጻነትዋን ሰጧት። ዓባይን ያለተቀናቃኝ ለመቆጣጠር ግብጽ ከፈለገች ኢትዮጵያን ማድከም ከተቻለም መበታተን ብቸኛ መፍትሄ መሆኑን እንግሊዞች እጇን ይዘው አስተምረዋት የወጡ ይመስላል። ምክንያቱም ቀደም ሲል ትከተል የነበረውን ፖሊሲ በአዲስ ቀየረች። በፊትለፊት ጦርነት ኢትዮጵያን ከመግጠም ተቆጠበች። ኢትዮጵያ ዓባይን ለመጠቀም እንዳታስብ ለማድረግ ሶስት የተጋመዱ ስትራቴጂዎች በአዋቂዎቿ አስጠንታ ተገበረች። እነዚህም በኢትዮጵያ የውስጥ ሰላም ማሳጣትና ዘወትር የማያቋርጥ ረብሻና ግርግር እንዲኖር ማድረግ አንደኛው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ዙሪያዋን በእሳት እንድትታጠር ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በድንበር ወይም በሌላ ሰበብ ፈጥሮ ኢትዮጵያን በጥርጣሬ ገፋ ሲልም በጠላትነት እንዲያዩዋት ማድረግ። ያንንም ክትትል አድርጎ ማጎልበት ነው። ሦስተኛው ዘዴዋ ደግሞ የዓለም አቀፍ አጋሮቿ በተለይም አሜሪካና አውሮፓ መንግሥታት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው። ይኸውም ኢትዮጵያ ለእርሻ፣ ለግድብ ሥራ ብድር እንዳታገኝ መዝጋት። በዓለም አቀፍ ደረጃም ኢትዮጵያን ተቀባይነትን ማሳጣት የሚያስችሉትን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ ነድፋ ተንቀሳቀሰች። እነዚህ ዘዴዎቿም ሠርተውላታል። ኢትዮጵያ ወደ ልማት ፊትዋን ሙሉ ለሙሉ አዙራ ለእድገቷ እንዳትሠራ ግብጽ በውስጥና በውጭ ባስቀመጠቻቸው አሽክላዎች በየአቅጣጫው ስትወጥር ለዘመናት በድህነት ቆይታለች።
ላለፉት 70 ዓመታት በተለይም በ1950ዎቹ መጨረሻ ዓመታት ጀምሮ ግብጽ እነዚህን ፖሊሲዎች በከፍተኛ ሁኔታ መተግበር ቀጥላለች። በ1959 ኢትዮጵያን አግልላ ከሱዳን ጋራ የአባይን ውሃ ለሁለት የተከፋፈሉበትን ውል ተፈራረመች። ቀጥሎም ጃንዋሪ 16 ቀን 1960 ኢትዮጵያን ሳታሳውቅ ትልቁን የአስዋን ግድብ አስጀመረች። በወቅቱ ኢትዮጵያ በአባይ ላይ የሚሠሩ ሥራዎችን አስመልክቶ እርሷም ባለድርሻ መሆኗንና ልትታለፍ እንደማይገባ ማስገንዘብና እርሷም አባይን ለልማት ልታውል የምትችልበትን ሁኔታ ማጥናት ስትጀምር ግብጽም በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያን ለማዳከም ከሆነም ለመበታተን ያግዛል የተባለውን ሥራ ሁሉ ለመተግበር ታጥቃ ተነስታ ያለመታከት መሥራቷን ተያያዘችው፡፡
ግብጽ የኢትዮጵያን ጂኦግራፊ ብቻ ሳይሆን ታሪኳን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ኑሮ ሥርዓቷን እያንዳንዱ ብሔረሰብ ያለውን ስሜት ከኢትዮጵያውያን የበለጠ ጠልቀው በዝርዝር አጥንተው በሀገራችን ውስጥ የነበረውን የነገድ፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት ልዩነት አጋኖ በመጠቀምና እርስ በርስ ማለያየት በጭር ጊዜ ያለብዙ ችግር ያሰበችውን ሊያስፈጽምላት እንደሚችል በመረዳት በዚሁ ዙሪያ ሥራዋን ቀጠለች።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሃይማኖት ልዩነት ማጋጋል ቅድሚያ ሰጠች። የካይሮ ሬዲዮ በአማርኛ፣ በሶማሊ እንዲሁም በአደሪኛ ቋንቋዎች ማሠራጨት ሲጀምር አላማው የሙስሊሙ ደጋፊ መስሎ ቀርቦ በኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ጦርነትን መቀስቀስ ነበር። የካይሮ ጋዜጦች ኢትዮጵያን እንደ ኢምፔሪያሊስት ቅኝ ገዥ ሀገር አድርገው ፕሮፖጋንዳቸውን በመርጨት ማነሳሳት ጀመሩ። ኢትዮጵያ የቅኝ ገዢ ስለሆነች ከእንቅልፋችሁ ንቁ ለነጻነታችሁ ታገሉ እያሉ ማነሳሳትና ያንድነት ማሰሪያችን ተፈትቶ እንድንለያይና እንድንደክም ያለዕረፍት መስራትን ተያያዘችው። እንዳሰበችው የኢትዮጵያ ህዝብ የሃይማኖት ጦርነት አንስቶ እርሰ በርሱ በወቅቱ ባይጨፋጨፍም፤ ይህ ሥራዋ ውጤት አላስገኘላትም ማለት አይደለም። በ1960 የሙስሊሙን ክፍል አሳምና አነሳስታ የኤርትራ ነጻ አውጪ ድርጅት በካይሮ ሲቋቋም በምስራቅ አፍሪካ ደግሞ የሱማሌ መንግሥት ታላቋን ሶማሊያ የሚለውን መፈክር አንስቶ ኦጋዴንን ከኢትዮጵያ የመገንጠልና የሱማሌ ሪፐብሊክ አካል እንዲሆን ሁለገብ እርዳታዋን ቀጠለች (ሙሉ ዝርዝሩን Teferi Mekonen, The Nile Issue and the Somali –Ethiopian Wars (1960s-78), Annales d’Ethiopie, Annee 2018 ይመልከቱ)። የሱማሌ ብሔረሰብ በኬንያ ኢትዮጵያና ጂቡቲ ያሉ ሲሆን በኢትዮጵያ ላይ ብቻ በተደጋጋሚ ጦርነት የተነጣጠረባት ዋናው ምክንያት ከጀርባው ያለው ኃይለኛው የግብጽ ግፊት እንደሆነ ይታወቃል።
በካይሮ የተጠነሰሰው የኤርትራው እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥ መዋቅሩን ዘርግቶ ቅስቀሳውን አሠራጭቶ ጎልብቶና ደርጅቶ ከብዙ ዓመታት የደም መፋሰስ የንብረት ውድመት በኋላ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ የብቻው ሀገር መስርቷል። ግብጽ የታሪክና የባህል አንድነት የነበራቸውን የኤርትራንና የኢትዮጵያን ህዝቦች ደም አቃብታ አለያይታለች። ኢትዮጵያም 17 ዓመታት በዘለቀው የርስበርስ ጦርነት ተዳክማ ከቀይ ባህር ተገፍትራ እንድትወጣ ተደርጋለች። በሱማሌ በኩል ባስነሳችው ከፍተኛ ጦርነት እጇ እንዳለበት አትሸሽግም። በ1960ዎቹም ሆነ በ1970ዎቹ የተቀሰቀሱትን ሁለቱንም ጊዜ የሱማሌን ጦርነቶች ብናሸንፍም እስካሁን የማይሽር ቁስል ተክላብን በየጊዜው እየተነሳ ያመረቅዛል። በእነዚህ ሁሉ ሂደቶች ግብጽ ኢትዮጵያ ቀና ባለች ቁጥር እየነካካች እያደማችን ትገኛለች።
በቅርቡ የኢትዮጵያ አንድነትን የሚፈልግ መንግሥት ሥልጣን ላይ ሲወጣ ትግሏን አፋፍማለች። በተለይም የዓባይ ግድብ ከፍጻሜ እንደሚደርስ ስታውቀው ንዴቷና ቁጭቷ የመጨረሻውን ጣሪያ ነክቷል። የሱዳን ጦር አልፈሽጋን ግዛታችንን እንዲይዝና በሱዳንና በኛ መካከል የማያባራ ግጭት እንዲኖር ሁኔታውን የጠነሰሰቺው ግብጽ ነች። የጋራ የጦር ልምምድም ካንዴም ሁለቴ አድርገዋል። ደግነቱ የምንጊዜም ወዳጃችን የሆነው የሱዳን ህዝብ እስካሁን አልተለየንም፣ እየተከላከለልንና እየተዋደቀልን ነው!!
በቅርቡ በአዲስ መልክ በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያን ጎረቤት ሀገሮች የመነጠል ስትራቴጂ እየዞረች የወታደራዊ፣ የመረጃ ልውውጥ ወይም የኢኮኖሚ ትብብር በሚል ርዕስ ሰጥታ ስምምነቶችን ከሱዳን፣ ኬንያ ፣ዩጋንዳ ቡሩንዲ ጂቡቲ፣ ታንዛኒያ እና ደቡብ ሱዳን ጋር ተፈራርማለች። አንዳንዶቹን ወታደራዊ ተቋማችሁን ላደራጅላችሁ ትላለች። ኩታ ገጠም ድንበርተኞቻችንን ደግሞ የጦር ሠፈር እንድገነባ መሬት ምሩኝ እያለቻቸው ነው። በተለያዩ አቅጣጫዎች በሚፈሱ ወንዞቻችን ዙሪያም እንዳንጠቀምባቸው ጎረቤቶቻችን በዚህም ዙሪያ ቅሬታዎች እንዲያነሱብንና አጋዥ ለማግኘት ነገሮችን ጠቆም እያደረገች መሆኑ እየታየ ነው፡፡
ኢትዮጵያን ከዓለም ሀገሮች ለማግለል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት መሪዎቿ ለአፍታም የሚተኙ አይመስሉም። ሲጓዙ ይነጋባቸዋል። ኃያላን መንግሥታት ደግሞ ግብጽን እንደ እንቁላል የሚንከባከቡዋትና እሹሩሩ የሚሉበት ዋናው ምክንያት አውሮፓንና ኤሽያን የሚያገናኘውንና መተላለፊያ የሆነውን የስዌዝ ካናል/ቦይ ባለቤትና እንዲሁም ቀደም ሲል ባፈራችው ተሰሚነት ጸብ በተነሳ ቁጥር እስራኤልና አረቦችን ታስታርቃለች ስለሚሉ ነው። ስለዚህም እንድትከፋባቸው አይፈልጉም። እርሷም ይህን አስተሳሰባቸውን እስከ ጥግ አሟጣ እየተጠቀመች ነው። ትክክል ነች አይደለችም ሳይሉ አብረው ተባብረው ምስኪን ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው ፣በኢኮኖሚው እንዲሁም በፕሮፖጋንዳው የሚወቅጡት ለዚህ ነው።
ኢትዮጵያን ባልፈጸመቺው ወንጀል በዓለም አደባባይ ሽንጣቸውን ገትረው በተደጋጋሚ እየገተሯት ለማሸማቀቅ ይሞግቷታል። የመጨረሻውን የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነውን የጦር መሳሪያ አስታጥቀው የሕዳሴውን ግድበ መምታት ነበረብሽ ብለው በገሀድ ያጀግኗታል። መገናኛ ብዙሃኖቻቸው በኢትዮጵያ ላይ የቅጥፈት ወሬ ፈጥረው የዓለምን ህዝብ ያደናግራሉ። የምክር ቤት አባሎቻቸው ከፍተኛውን ማዕቀብ በኢትዮጵያ ላይ ለማስጣል ይሽቀዳደማሉ። የሚገርመው አንዳንዶቹ ያሜሪካ ሰናተሮች ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካርታ ላይ የት እንዳለች ማወቃቸውንም እንጃ። ለዓለም ሰላም፣ ለሰብዓዊ መብትና ዲሞክራሲ ዋስና ጠበቆች ነን የሚሉት የአሜሪካ መሪዎች በአሁኑ ጊዜ የወዳጆቻቸውን ፍላጎት በግድ በኢትዮጵያ ላይ ለመጫን መንግሥትን ያቀረብነውን ተቀብለህ ፈጽም፤ አለበለዚያም 120 ሚሊዮን ህዝብህ ግሮሮ ላይ እንደሚቆሙ እየነገሩት ነው። በሩቅ ሁነን እንደምንሰማው አስበህ ነገረን ብለውታል። ውሳኔውንም እየጠበቁ ነው፡፡
በድህነት አቆራምደውን 120 ሚሊዮን ህዝብ አንገት ላይ ቆመው መንግሥት የሚፈልጉትን እንዲፈጽም እያስገደዱት ያሉት ምን ለማግኘት ነው?። ይኸ ሁሉ የዘመናት ግፍ በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጸመው የግብጽ ህይወት የሆነውን ዓባይን ገድበን ግብጽን የውሀ መጠን ቀንሰን አይደለም፤ ወይንም ህልውናዋን አደጋ ላይ ጥለንም አይደለም። በዓባይ ላይ ያለኝ የበላይነት ይወሰድብኛል ብላ ስለምትጮህ እሷን ለማስደሰት ነው። ከምንጩ ላይ ተፈጥረን ዓባይን በምንም ዓይነት እንዳንጠቀም ስለተፈለገ ነው።
ኃያላኑ የግብጽን ሽርክና እናቆያለን ብለው በኢትዮጵያ ላይ በሚፈጽሙት በደል በዓለም ፊት ክብርና ሞገሳቸው እየተገፈፈ ፣ እያደር እየቀለሉ ነው። ንዴታቸውም በዚያው መጠን ከፍተኛ ነው። እኔ በግሌ ከነርሱ ፍትህን መጠበቅ የዋህነት ነው። ምክንያቱም ምንጊዜም ወዳጃቸው ፍላጎታቸውን ያሟላ ብቻ ነው። ግብጾች እያንዳንዱ ብሔረሰብ ስለ ሌላው ያለውን ስሜት ከኢትዮጵያውያን ይልቅ ጠልቀው በዝርዝር አጥንተዋል። እንደዚህ ያለው ዝርዝር ጥናት ኢትዮጵያን ያለብዙ ችግር ለመከፋፈልና ለማለያየት የሚያስቡ ድርጅቶችን ለመፍጠር አስችሏል። በተለይም ኢትዮጵያ ኢምፔሪያሊሰት ቅኝ ገዥ ሀገር ነች የሚለው የግብጽ ቅስቀሳ የዋህ ወጣቶችን ስቧል። ከኢትዮጵያ ነጻ እንወጣለን ብለው ሽር-ጉድ የሚሉ አድርባይ ድርጅቶች እንዲፈለፈሉ አድርጋለች። የትግራይ፣ የኦሮሞ፣ የቤኒሻንጉልጉሙዝ፣ የሱማሌ፣ የአገው፣ የኦጋዴን፣ የወላይታ የሲዳማ፣ የአፋር፣ ወዘተ. ነጻ አውጪ ድርጅቶች ነን እያሉ በሀገሪቱ ላይ የማያቋርጥ ሁከት በየቦታው የሚጭሩ ህዝቡን ሰላም የሚነሱ አብዛኛዎቹ የግብጽ ፕሮፓጋንዳ ሰለባዎች ናቸው። አንዳንዶቹ እርሷን ወክለው ኢትዮጵያን እየወጉ መሆናቸውን ግብጾቹ እራሳቸው በኩራት ይናገራሉ።
አንድ ጊዜ መሐመድ ሙርሲ የግብጽ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት በተደረገው በአንድ ቀጥታ ስርጭት በነበረ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በተካሄደ ስብሰባ ከታዳሚዎች መካከል የአንድ ፓርቲ መሪ ተነስቶ እንደገለጸው “ካስፈለግ በኢትዮጵያ ውስጥ ባደራጀናቸው ኃይሎች ኢትዮጵያን ማተራመስ ይቻላል” የተባለው በቀጥታ የተሠራጨና ገሀድ ወጥቶ ዓለም የሰማው ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግድቡ አካባቢ የሚደረገው የጉሙዝ ነጻ አውጪ በሚባለው ድርጅት የሚካሄደው የንጹሀን ዜጎች ጭፍጨፋ ለግብጽ መንግሥት እንጂ ለጉሙዝን ህዝብ ጥቅም ነው እንዴ?!። የተሰጣቸው ተልዕኮ ስለሆነ በየቀኑ ንጹሀንን እየፈጁ ነው።
ከመቼ ወዲህ ነው ምስኪን የአማራ ገበሬ ኢምፔሪያሊስት ቅኝ ገዢ የሆነውና ዛሬ በተገኘበት እየተከበበ የግፍና የጭካኔ ድርጊቱ ጥግ በደረሰ ሁኔታ የሚፈጸምበት?። ምንም መሳሪያ የሌለውን የአማራን ምስኪን ድሀ ገበሬ ቤቱን ማቃጠል እርሱን መግደል፣ ሚስትና ሴት ልጁን መድፈር፣ የትግራዋይን ወይንም የኦሮሞን ወይንም የጉሙዝን ህዝብ ከምንና ከማን ነጻ ያወጣዋል?? የትስ ያደርሰዋል ?? ጥያቄውን አነሳሁት እንጂ ነጻ አውጪ ነን የሚሉትም ቢሆኑ ነጻ እናወጣለን ለሚሉት ህዝብ ጥቅም እንዳልሆነ ያውቁታል። ህዝቡም ጠመንጃ ስለያዙ ፈርቶ እንጂ ከመካከሉ አብሮት የኖረው ድሀ ገበሬ ጎረቤቱ አማራ ስለሆነ ብቻ ጨቋኝ ተብሎ እንደከብት ተጎትቶ ሲታረድ የኦሮሞ ህዝብም ይሁን የትግራይ ህዝብ ወይም ፣የጉሙዝ ሕዝብ የህሊና እረፍት ይሰጠዋል ብዬ አላስብም። ገዳዮቹ ግን አድርጉ የተባሉትን ነው እያደረጉ ያሉት።
ግፉን እየፈጸሙ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የግብጽ ጦር ሠራዊት አካል ናቸው ማለት ይቻላል። እነዚህኮ በህዝቦቻችን መካከል መሽገው ለጠላቶቻችን ወግነው ጦርነቱን ጀምረውላቸዋል።
መንገዱን ከፍተውላቸዋል ። እየተዋደቁላቸው ነው። ከነዚህ ነፍጥ አንስተው ሕዝቡን ከሚጨርሱት በተጨማሪ ሰላማዊ ትግል እያካሄድን ነው እያሉ ያለምንም ሀይ ባይ በህዝቡ መካከል መርዛም ንግግራቸው የሚረጩትን ድርጅቶችም ሆኑ የሃይማኖት አባቶች ነን ባዮች ከእነዚህም ተነጥለው የሚታዩ አይደሉም።
ነጻ አውጪ ነን ያሉትን ሁሉ ንጹሁን ከወንጀለኛው ሳትለይ ጨፍልቀህ ሁሉንም የግብጽ ቅጥረኞች ናቸው ብለህ ኮንነሀል የሚል ካለ ምላሹ አዎ ነው። ነጻ አውጪ የሚለውን ስም ሲመርጡ ቢያንስ ከግብጽ ጋር በሃሳብ ማግጠዋል። በውስጣቸው መርዝ የሆነ የሀገር ጥላቻ አለ። የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት 27 ዓመት ሲገዛ የአንድነትን ቋጠሮ አንድባንድ ሲበጥስ ከርሞ ከሥልጣን ሲወርድ ትግራይን ከኢትዮጵያ እገነጥላለሁ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ ባለበት በአሁኑ ወቅት ግብጽም ምዕራባውያኑም ይህቺ ሃሳብ በሌሎችም ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ባላቸው ኃይል ሁሉ እየደገፉት ናቸው።
እዚህ ላይ ያለፉትም ሆኑ አሁን ያለው መንግሥት ህዝብን የሚያስከፋ ሥራ አይሠሩም፤ የህዝብ ብሶትና ምሬት አልነበረም ወይም የለም ማለቴም አይደለም። ያለፈውን ተውና በአሁኑ ሰዓት አንኳን በነዚህ ወንጀለኞች ላይ እርምጃ መውሰድ ሲገባቸውና መውሰድም እየቻሉ የማይወስዱ፣ እኩይ ተግባራቸውን እያወቁ የማይናገሩ፣ ሙያቸው የሚጠይቀውንና እጃቸውን አንስተው በህዝብ ፊት ለሙያቸው ክብር የማሉትን መሀላ ረግጠው ወንጀለኞችን ለፍትህ የማያቀርቡ የፍትህ አካላት የወጀለኞች አጎልማቾች መሆናቸውን አምናለሁ። ይህ ድርጊት ዜጎችን እያበሳጨ መሆኑን አላጣሁትም። ግን እነዚህን ባለሥልጣናትና ያንዳንድ ህብረተሰብ ክፍሎች ስህተቶችን አዚሁ በመታገልና በማስተካክል ፋንታ ሀገርን ለማጥፋት ዘወትር ከሚዶልት ጠላት ጋር ማበርን አላምንበትም። ጀግና የሆነ ትውልድ ሀገሩን አይከዳም። ከኢትዮጵያም መሰደድ መፍትሄ አድርጎ አይቀበልም።
ምትክ አድርጎ የሚሰደድበት ሀገር ዋናዋን ሀገሩን በምንም አይተካለትምና! ወደዋናው ነገሬ ለምለስና ግብጽ ይህን ሁሉ ማድረጓን እያየን እንዲህ መከበባችንን ስናውቅ፤ አባይን አንዲት ጠብታ ውሃ አትነኩብኝም ብላ ታጥቃ መነሳቷን ስንረዳ፤ የዓለም ኃያላንን አስተባብራ በውስጥ በገንዘብዋ የተገዙ ድርጅቶችን መሳሪያ አድርጋ በተለያዩ ዘዴዎች ያንድነት ማሰሪያችን በመበጣጠስ እንድንለያይ ያለእረፍት እንደምትሠራ ስናውቅ እንደዜጋ ምን እያደርግን ነን። ምን መደረግ አለበት ብሎ ህዝብና መንግሥት መምከር ያለባቸው አሁን ነው!! ዓባይንም ኢትዮጵያንም እንዳናጣ ልዩነታችንን ለሌላ ጊዜ አስቀምጠን አሁን እንተባበር! ለሀገር አንድነት ሲባል የዛሬን ችግር በጋራ እንቋቋም፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትስ ምን ማድረግ አለበት? የሚል ካለም፤ እኔ የበኩሌን ሃሳብ እሰጣለሁ፤ ሌላውም እንዲሁ ይስጥ። የውስጡ ሰላም ማስጠበቅ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው። ሕዝባችን በየቦታው እየተገደለ ነው ። በሀገር ደረጃ ያፈራነው ሀብት እየወደመ ነው። ሰላም የለንም። የወደፊት ህይወታችን በተስፋ ዕየተሞላ አይደለም። በሀገር ውስጥ መሳሪያ አንስተውም ይሁን በወንበራቸው አማካኝነት ወይም በማይክሮፎናቸው ጫፍ እየወጉን ያሉትን የውስጥ አዳካሚዎች በጠንካራ ክንድ መንግሥትም በሚቻለው ፍጥነት ማስወገድ አለበት። ህዝቡ ሥራውን እንዲሠራ፣እንዲያመርት፣ ኢኮኖሚው እንዲስፋፋ ለማስቻል የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍሎ መንግሥት ሰላምን ማስፈን አለበት። አበው ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንዲህም ከሆነ ጅቡ ቀድሞ ከሚበላህ በልተከው ተቀደስ ይላሉ!! እኔም የምለው ይሄንኑ ነው፡፡
የሀገራችንን ዳርድንበር ለማስከበር የውሃ ሀብታችንን ለመጠቀም የውስጣችንን ሰላም ለማስጠበቅ የሚችለው መንግሥት ግልጽ አካሄድና የፈረጠመ ጉልበት ሲኖረን ብቻ ነው። ሥልጡን ወታደርና አሻግሮ የሚመታ መሳሪያ ከምጊዜም በላይ ዛሬ ያስፈልጉናል። ግድባችንን ቢመቱ የሚሳሱለትን ቦያቸውን የምንመታበት የተዘጋጀ ኃይል ያስፈልጋል። የሰላ አንደበትና ብቃት ያላቸው ዲፕሎማቶች የጠላቶቻንን ሸር/ደባ በዓለም አደባባይ ለማጋለጥ ይረዱናል። እናም በዚህ መልኩ በሚቻለው ፍጥነት ማሰማራት ያስፈልግ ይመስለኛል ፡፡
በተለይ ወጣቱ በጽንፈኝነት እንዲንተከተክ የሚያደርጉትን የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ዓላማቸውን ተከታትሎ ይድረስበት። ጽንፈኝነትና የሃይማኖት አክራሪነት በቀላሉ በስሜት የሚያስገነፍሉና የአብሮነትን ብርሃን የሚያጨልሙ ናቸው።
እስካሁን የነበረን ጽኑ መቋቋም በአጠቃላይ ግብጽንም ሆነ ኃያላኑ መንግሥታት የውሸት ድለላ ተቋሞቻቸውና ነውረኛ ሥራቸው በዓለም ፊት በገሀድ እንዲታይ አድርጓል። በነጻነት የኖረ ህዝብ ጨዋና በቀላሉ ገፍትረው ክብሩንና ንብረቱን መንጠቅ እንደማይችሉ አሳይቷል። ይሁንና ጠላቶቻችን እጃቸው ረጅምና መምጫ መንገዳቸው ብዙ ነው። በየጊዜው ዙሩን እያከረሩት ነው። ዛሬ የመዘዙትን ካርድ (ኤች አር 6600 እና ተጓደኞቹ) በመንግሥት ዘዴኛነት በህዝብ አንድነትና ድጋፍ ይከሽፋል!
እኛም አንድነታችን እየጠከረ በእልህ የቅጣት ምታቸውን ፊት ለፊት ተደርድረን መከላከል አለብን። ጊዜ የለንም! ቸልተኝነት አያዋጣም። ቸልተኝነት በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ (1928-1933) ወቅት አባቶቻችንን ከባድ ዋጋ አስከፍሏል። የኢትዮጵያ ገዢዎች ጣሊያን ጦሩን ሲያስጠጋ ምሽጉን ሲምስ ድንበር ሲገፋ ፕሮፓጋንዳውን በህዝቡ ውስጥ እንደልቡ ሲያሰራጭ በውስጥ ሹኩቻ ላይ ተጠምደው ነበር፡ ጦርነቱ እደጃቸው ሲደርስ ነው በቂ ዝግጅት እንዳለነበራቸው ያወቁት። ጦርነቱ ሲከሰት የሰለጠነ ወታደር፣ ስንቅ ትጥቅ የህክምና እርዳታ በበቂ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ህዝቡ ከዘመናዊው የጣሊያን ወራሪ ጦር ጋር መጋፈጥ ነበረበትና ተማገደ። በጥንቃቄ ጉድለት ለአምስት ዓመታት በጅምላ የመሞት የመከራና የስደት ጊዜን እንዲያሳልፍ ተደረገ፡፡
አባቶቻችን ያቺን ወቅት አምስቱ የመከራ ዘመን ይሏታል፡፡እኛም ዛሬ ያቺን ታሪክ አንርሳ። መንግሥት ግብጽንም ሆነ ሌሎች ክፉ አሳቢዎችን የት ላይ እንደሚመታ አውቆ እዚህም ቤት እሳት እንዳለ የሚያሳይ ዝግጅት እንደሚኖረው አልጠራጠርም። እዚህ ላይ ብዙም አልናገርም። ሊገድል የመጣ ጠላት አባባ ቢሉት አይምርምና የሚመለከተው ያስተውል። ቸር ይግጠመን፤ አበቃሁ፤ ሰላም!
በአብዲ ወዬሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3 /2014