ልጅነት ሲታወስ
የተወለዱት በቀድሞ አጠራሩ ወለጋ ጠቅላይ ግዛት ነቀምት አውራጃ ነቀምት ከተማ ልዩ ሰሙ ሆስፒታል በሚባል ሰፈር ነው። የመምህራን ልጅ እንደሆኑ የሚናገሩት ዶክተር ገመቺስ ከወላጅ እናታቸው ጌጤ ወዬሳና ከወላጅ አባታቸው አቶ ማሞ ፈጠነ በ1955 ዓ.ም ተወለዱ። እስከ አራት ዓመታቸው ነቀምት ከኖሩ በኋላ ወላጅ እናታቸው የሥራ ዝውውር አግኝተው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ልጆቻቸውን በሙሉ ይዘው አዲስ አበባ ገቡ።
አዲስ አበባም ከገቡ በኋላ ስድስት ኪሎ ልዩ ስሙ ፊት አውራሪ ይብሳ ሕንፃ አካባቢ እናታቸው በተከራዩት ቤት መኖር ጀመሩ። ዶክተር ገመቺስ ዕድሜያቸው ለትምህርት ደርሶ ስለነበር እዚያው ስድስት ኪሎ በሚገኘው አንድ የቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ከቀለም ትምህርት ጋር ተዋወቁ። ትምህርት በአንድ በኩል፤ ጨዋታና ቡረቃ ደግሞ የልጅነት ሌላ ገጽታ።
ያደጉት ስድስት ኪሎ አካባቢ ስለሆነ ጃንሜዳ ቅርባቸው ነበር። በጃን ሜዳ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል ጥምቀት አንዱ ነው። ታዲያ ዶክተር ገመቺስ ይህን በዓል እየጠበቁ ሳር በማጨድ ፣በጭፈራ፣ ታቦት በመሸኘት አሰደሳች እና የማይረሳ ጊዜ በልጅነት ህይታቸው ማሳለፋቸውን ያስታውሳሉ። ሌላኛው የልጅነት ህይወት በነቀምት ከተማ ያሳለፉት ነው።
የቀድሞዋ ነቀምት እንደአሁኗ ከተማ አልነበረችም፤ ዶክተር ገመቺስ እና ጓደኞቻቸውም አብሮ በመሆን የበጋ ግብርና የተለያዩ ሰብሎችን በመትከል እና በመጠበቅ ቤተሰብ በመርዳት ያሳልፉ ነበር። የመምህር ልጅ ተጓዥ ነው የሚሉት ዶክተሩ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አንደኛ እና ሁለተኛ ክፍልን በአዲስ አበባ አጼ ናኦድ ትምህርት ቤት ተማሩ። መምህር የሆኑት አባታቸው አቶ ማሞ ፈጠነ በመምህርነት ሥራ ወደ ወለጋ ጊምቢ አውራጃ ጊቤ ከተማ ተላኩ ፤ዶክተር ገመቺስም አባታቸውን በመከተል ወደዚሁ ከተማ አመሩ።
በጊቤም ከተማ በኑሩበት ሁለት ዓመት ሦስተኛ እና አራተኛ ክፍልን በቀኝ አዝማች ገብረእግዚያብሔር ትምህርት ቤት ከተማሩ በኋላ አባታቸው መምህር ማሞ ወደ ነቀምት ሲመደቡ አብረው ነቀምት ገቡ። የተወሰነ የተረጋጋ የሚመሰለው ኑሯቸው ነቀምት ላይ ሆነና የመጀመሪያ ደረጃ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚው እንዲማሩ ሆነ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በመከታተል ላይም እያሉ አባታቸው ወደ አዲስ አበባ በመዘዋወራቸው ዶክተር ገመቺስም ወደ እዚሁ ከተማ ዳግም አቀኑ። እናም የጀመሩትን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው ኮልፌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ በመግባት ማጠናቀቅ ቻሉ።
ህክምና አጠናለሁ ብለው አስበው የማያውቁትና ሐኪም የመሆን ህልምም ፍላጎትም እንዳልነበራቸው የሚናገሩት ዶክተር ገመቺስ በጣም የሚወዱት የትምህርት ዓይነት ኬሚስትሪ ስለነበረ ከፍተኛ ተቋም ገብተው ማጥናት የሚፈልጉት ይህንኑ ትምህርት ነበር። ዶክተር ገመቺስ እና የዕድሜ እኩዮቻቸው ትምህርት በጨረሱበት ጊዜ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከመሄዳቸው በፊት መንግሥት በመደባቸው ቦታ በመሄድ ለሦስት ወር የሚቆይ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር።
«የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ» የተሰኘው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት፤ አዲስ አበባ ያሉት ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ይላካሉ፤ ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች አስራ ሁለተኛ ክፍልን የጨረሱ ደግሞ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ይመደባሉ። በዚህም መሰረት ዶክተር ገመቺስም የዚሁ ዘመቻ አካል ነበሩ።
የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ በመላው አገሪቱ ያሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ከተማሩበት ከተማ ውጪ መንግሥት በሚመድባቸው የትኛውም ቦታ በመመደብ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የማገልገል ግዴታ ነበረባቸው። በዚህም መሰረት ዶክተር ገመቺስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት አዲስ አበባ ስለነበር መሰረተ ትምህርት የማስተማር የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከአዲስ አበባ ውጪ የመስጠት ግዳጅ ነበረባቸው።
ዶክተር ገመቺስ እንደሚሉት «እኔ እና አንዱ ጓደኛዬ ከእኛ ቀበሌ ወደ ሀረርጌ ስንመደብ፤ ሌሎች ከእኛ ቀበሌ የተመረጡ ሁለት ጓደኞቻችን ደግሞ ወደ ጎንደር ነበር የተመደቡት”፤ ሀረርጌ አሰበ ተፈሪ በጭሮ ወረዳ የአብዶ ሸንበቆ ገበሬ ማህበር የበጎ ፈቃድ ሥራቸውን ለመከወን ከጓደኞቻቸው ጋር ከተሙ።
እዚያው አካባቢ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የጨረሰ እንደነሱ ወጣት የሆነ አካባቢውን የሚያውቅ ተመድቦላቸው በእርሱ አዝማችነት መሃይምነትን የማጥፋት ዘመቻ ጉዞአቸውን አሀዱ አሉ። በመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ወቅት ማስተማር ይገባችኋል ተብለው አቅጣጫ የተሰጣቸው ማንበብ እና መጻፍ ፣አራቱን የሂሳብ ስሌት ሲሆን ዶክተሩ እንደሚሉት ሂሳብ በሚያስተምሩበት ወቅት የሚጠቀሙት የአረቡን መቁጠሪያ ቁጥር ሳይሆን የግዕዝ መቁጠሪያ ቁጥር ነበር።
ቋንቋንም በተመለከተ ኦሮምኛ እና አማርኛን ሆሄ ከማስቆጠር የማንበብ እና የመጻፍ ክህሎት እንዲኖራቸው አድርጓል። የከፍተኛ ትምህርት ምድባ በሚወጣበት ጊዜ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንደነበሩ የሚናገሩት ዶክተሩ ምደባ እንደወጣ ተነግሯቸው የት እንደደረሳቸው ሊያዩ በሄዱበት ወቅት የሌሎች ጓደኞቻቸው ምደባ ወጥቶ የዶክተር ገመቺስ እና አብሮ የተመደበው ጓደኛቸውም ስም እንዳልተለጠፈ ሰሙ።
ምደባው ያልወጣበት ምክንያት ዶክተር እና ጓደኛቸው በዘመቻው ምክንያት ጭሮ በነበሩበት ወቅት መንግሥት በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ሁሉም ተማሪ በድጋሚ ትምህርት ክፍላቸውንና የሚማሩበት ተቋሙን እንዲመርጡ አድርጓል፤ ዶክተርና ጓደኛቸው ባለመስማታቸው ምርጫ ሳይመርጡ አለፋቸው። አባታቸው በወቅቱ የነበረውን የተማሪዎች ምደባ የሚመለከተውን ባለስልጣን በማነጋገር እና ጉዳዩን በማስረዳት ለዶክተር ገመቺስ ምርጫቸውን የሚሞሉበትን ቅጽ ተላከላቸው።
በወቅቱ ማንኛውም ተማሪ ሦስት የትምህርት ክፍል መምረጥ ይችላል። እሳቸውም የመጣላቸውን ፎርም ይዘው በአባታቸው ጠቋሚነት አንድ ምርጫ ህክምና ብለው ሞሉ፤ በዚያን ጊዜ የህክምና ትምህርት የሚሰጠው በጥቁር አንበሳ እና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ነበር። ዶክተርም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ደረሳቸው፤ ዘግይተው ስለነበር ትምህርት ከተጀመረ በኋላ ነው ወደ ተቋሙ የገቡት። ለዩኒቨርሲቲው የህክምና ትምህርት ክፍል ሦስተኛ ዙር ተማሪዎች እንደነበሩም ይናገራሉ።
የከፍተኛ ተቋም የትምህርት ጊዜያቸውን ጨርሰው ከመመረቃቸው በፊት የልምምድ ጊዜ ለማድረግ ተቋሙ ዶክተር ገመቺስን ጨምሮ የተወሰኑትን ዕጩ ምሩቋንን ወደ አዲስ አበባ ላከ። ዶክተር ገመቺስ በአዲስ አበባ ቅዱስ ጳውሎስ፣ የካቲት 12 እንዲሁም በዘውዲቱ ሆስፒታል ተዘዋውረው በመሥራት የአንድ ዓመት የልምምድ ጊዜ አሳለፉ፡፡
የትዳር እና የሥራ ህይወት
ለመመረቅ የሥራ ላይ ስልጠና አንዱ አስፈላጊው መስፈርት ነበር። ዶክተር ገመቺስም ይህንን ግዳጃቸውን ለማሟላት በጳውሎስ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ህክምና የሥራ ላይ ስልጠና ለመውሰድ ነው የተገኙት። በወቅቱ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሐኪም እጥረት በመኖሩ በኢትዮጵያና በኩባ መንግሥታት ስምምነት ተደርሶ፤ በኩባ አገር ይማሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች የሥራ ላይ ስልጠናቸውን በአገራቸው እንዲያደርጉ እና በዚያውም አገራቸውን እንዲያገለግሉ ተፈልጎ ወደ አገር ቤት፤ ከአገር ቤትም አዲስ አበባ ጳውሎስ ሆስፒታል እንዲመደቡ ተደረገ።
በዚያን ወቅት ነበር የዛሬዋን ባለቤታቸው ዶክተር ሙሉዓለም ገሰሰን ያገኟት። ይህ ትውውቅ አድጎ በ1978 ዓ.ም ሦስት ጉልቻ መሰረቱ። ባለቤታቸው ዶክተር ሙሉዓለም ገሰሰ ሐረር ሥራ በመመደብ እና ሥራ በመጀመር የአንድ ወር ቅድሚያ ይወስዳሉ። ዶክተር ገመቺስም ሥራ ከተመደቡበት ጎንደር ቆላድባ የጋብቻ ማስረጃ በማምጣት ወደ ባለቤታቸው ሐረር ዝውውር ተሰጣቸው። ዶክተር ገመቺስ እና ባለቤታቸው ዶክተር ሙሉዓለም ሁለቱም ሐረር በሚገኘው ቢስዲሞ በተባለ ሆስፒታል ማገልገል ጀመሩ።
ሐረር እያገለገሉ ነው ሁለቱን የአብራካቸውን ክፋይ ያገኙት። በቢስዲሞ ሆስፒታል ለሁለት ዓመት ካገለገሉ በኋላ እዚያው ሐረር በሚገኝ ሕይወት ፋና በሚባል ሆስፒታል ተዛውረው ማገልገሉን ቀጠሉ። ዶክተር ገመቺስ ህይወትን በማዳን ሥራ ላይ እየተጉ ባሉበት ጊዜ ሙያቸውን የሚያበለጽጉበት ዕድል አግኝተው አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መጡ። ታዲያ የዶክተር ገመቺስ ወደ አዲስ አበባ መምጣት ለባለቤታቸው ለዶክተር ሙሉዓለምም ወደ አዲስ አበባ ዝውውር የማግኛ ምክንያት ሆነ። ዶክተር ገመቺስ ማሞ በሙያቸው 34 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ በሆነው በጎንደር ክፍለ አገር በፎገራ አውራጃ ቆላድባ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ ጤና ጣቢያ ነበር ሥራን «ሀሁ» ያሉት። ለጤና ጣቢያው የመጀመርያ ሐኪም ሆነው እንደተመደቡ ያስታውሳሉ።
ጤና ጣቢያው ምንም እንኳን በአገሪቱ የመጀመሪያ ቢሆንም አስፈላጊ ቁሳቁሶች አልተማሉለትም ነበር። በጤና ጣቢያው ምንም ዓይነት የደምም ሆነ የሽንት መመርመሪያ ላብራቶሪ ባለመኖሩ እውቀታቸውን ብቻ በመጠቀም ሲያገለግሉ እንደነበር ያስታውሳሉ። ከእሳቸው አቅም በላይ ሲሆን ደግሞ ወደ ጎንደር በመኪና ይልካሉ። በቆላድባ ወረዳ ጤና ጣቢያ የጀመሩት የሕክምና ጉዞ በኢትዮጵያ የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አድርሷቸዋል።
በእነዚህ የሙያ ጉዞዎችና የሥራ ዓመታት ብዙ ገጠመኞችን አስተናግደዋል። በርካቶችን አክመዋልም። እስከአሁን ምን ያህል ሰዎች ማከም እንደቻሉ በቁጥር መግለጽ ባይቻልም ‹‹በትንሹ በቀን 30 ሰው አያለሁ፣ በሳምንት ስድስት ቀናት እሠራለሁ። ታምሜ ካልቀረሁ በስተቀር ከሥራ ቀርቼ አላውቅም። እንግዲህ ይህንን አስላው›› አሉ እንደ ማሰብ ብለው። ሂሳቡን የማስላት ዳገቱ ታየኝና እኔም እሳቸውም ለእናንተ ተውነው። እንደ ዶክተር ገመቺስ ላሉ ሐኪሞች ታካሚዎችን ሊያሳዝን የሚችል የምርመራ ውጤት መግለጽ በራሱ ሌላ ፈተና ነው። የመዳን ተስፋ ይኖረኝ ይሆን ብሎ ከፊቱ የሚታይን ጭላንጭል ተስፋ እፍ ብሎ ማጥፋት ማንስ ይደፍራል?። በተለይ በሽታቸው ዕድሜ ልካቸውን እንደ ጥላ የሚከተላቸው ዓይነት ጭንቀቱ ከባድ ይሆናል።
በዚህ ረገድ ዶክተር ገመቺስ ‹‹ከታካሚዬ ጋር አብሬ አልቅሼ አውቃለሁ›› ሲሉ ለታካሚው የማይድን በሽታ እንደያዘው መግለጽ ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ። በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደ አሁኑ ደግሞ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ወሳኝ የሆኑ መድኃኒቶች በሚጠፉበት ጊዜ ይህንን ግዛ ብሎ ማዘዣ መጻፍ ሌላው ፈተና ይሆናል። ‹‹በቀላሉ ማከም እየቻልን ለታካሚው የምንጽፈው መድኃኒት ጠፍቶን እንጨነቃለን።
በሌላ በኩል ደግሞ መድኃኒቱ ስላለ ብቻም ማዘዝ አይቻልም። ታካሚው መግዛት ይችላል ወይ የሚለውንም ማወቅ ያስፈልጋል። ዝም ብለን ጽፈን ብንሰጠው ዋጋውን ይጠይቅና ይቅርብኝ ብሎ ሂዶ ዳማከሴውን ይወስዳል፤›› ሲሉ ለሐኪሙ በአገር ውስጥ ያለውን የመድኃኒት አቅርቦት፣ የታካሚውን የመግዛት አቅም ማገናዘብ ሌላው የሙያው ፈተና እንደሆነ ይገልፃሉ። ‹‹ሞት ለሁላችንም የማይቀር ነገር ቢሆንም ለአንድ ሐኪም ትልቁ ሐዘን የሚያክመው ታካሚ ሳይጠበቅ ድንገት ሲሞቱ ነው። ያኔ ውስጥ በጣም ያዝናል፤ ትጎዳለህ። መትረፍ እየቻለ ሰው ሲሞት ሐኪሙም በትንሽ በትንሹ ውስጡ ይሞታል።
በዚህ የተነሳ ሥራ መሥራት የሚያቅታቸው፣ ድብርት ውስጥ የሚገቡ ወጣት ሐኪሞች ብዙ ናቸው። እኛ እንኳ በጊዜ ሒደት ተላምደነዋል›› ያሉት ዶ/ር ገመቺስ። አንድ ሐኪም በቀን በትንሹ እስከ 30 ሰዎችን የማየት ኃላፊነት አለበት። ካለው የአገልግሎት ፍላጎት አንፃር ይህም በቂ የሚባል አለመሆኑን በረዥም ቀጠሮ የሚመላለሱ ታካሚዎችን ማየት ብቻ በቂ ነው። ሆስፒታሎች ወሳኝ የሆኑ መገልገያ መሣሪያዎች በምን ያህል መጠን ያገኛሉ? የሚለው ጉዳይም አጠያያቂ ነው። አገር ውስጥ ባሉ ባለሙያዎችና መሣሪያ መሠራት አይቻልም በሚል ውጭ አገር ሄዶ ለመታከም የሚገደዱ ብዙ ናቸው።
ለ31 ዓመት በሙያ ማህበር አባልነት
ዶክተር ገመቺስ ማሞ የህክምና ማህበሩን እንዴት እንደተቀላቀሉ ሲያስታውሱ “እንደዛሬው ሁኔታዎች ሳይበላሹ ፤ እኔ የህክምና ትምህርት በጨረስኩበት ወቅት ማንኛውም የህክምና ምሩቅ በቀጥታ የማህበሩ አባል ይሆን ነበር፤ በዚህም መሰረት እኔም አባል ሆኩኝ። ሌላው ቀርቶ የአባልነት ክፍያ እንኳን ከወር ደመወዛችን ነበር ተቆርጦ የሚገባው።” ይህም የሚከናወነው ባሉበት በየትኛወም ቦታ አንድ ተወካይ ይኖራቸዋል፤በዓመት አንድ ጊዜ ከያለንበት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እንሰበሰብ ነበር፤በቁጥርም ጥቂት ነበርን።
በማህበሩ ውስጥ በአባልነት ያለምንም ሐላፊነት የቆዩ ቢሆንም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ግን አንደበተ ርቱዕ የመድረክ ሰው እንደሆኑ የሚነገርላቸው ዶክተር ገመቺስ ወደሥራ አስፈጻሚነት ብቅ ማለት ጀመሩ። የአመራር ሐላፊነት ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት ለአንድ የሥራ አስፈጻሚ ዘመን በጸሐፊነት፣በሌላኛው ደግሞ በኮሚቴ አባልነት አገልግለዋል።
ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ ደግሞ በህክምና ማህበሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎች ውስጥ በፕሬዚዳንትነት እያገለገሉ ይገኛሉ። ስለሙያ ማህበራቸውም ሲናገሩ ብዙዎቹ በዚህ ዘመን ያሉ የህክምና ባለሙያዎች «ምን ያደርግልኛል እንጂ እኔ ምን ማድረግ አለብኝ» ስለማይሉ ወደ ሙያ ማህበሩ ብዙ ወጣቶች አይቀላቀሉም።
ማህበሩ አንጋፋ እና በንጉሱ ቻርተር እንደተቋቋመ የሚናገሩት ዶክተር ገመቺስ ማህበሩ ዓላማዬ ብሎ ከተነሳባቸው ዓበይት ምክንያቶች መካከል የአባላቱን ዕውቀት እና ክህሎት ማዳበር፣ ሳይንስ እና ምርምርን ማሰራጨት ፣በምርምር እንዲሁም በጤና ሁኔታዎች ላይ ማማከር ነው። በቀድሞ ጊዜ የአባላት መብት የሚባል ነገር የለም፤ ምክንያቱም በወቅቱ የማህበሩ ትኩረት ሳይንስን ብቻ ማዕከል ያደረ ነበር። ያንን በማድረጉ በጎ ተፅእኖ የፈጠረ ሲሆን በዓመት አራት ጊዜ የሚታተም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠቀስ የሳይንስ መጽሔት ለማዘጋጀት በቅቷል። በተጨማሪም በዓመት አንዴ በሚደረገው አጠቃላይ ስብሰባ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡበት ባለሙያው በጓደኞቹ የሚተችበት፣ የሚማርበት፣ የሚያሳውቅበት፣መድረክ እንደሆነ ዶክተሩ ይጠቅሳሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ተከታታይ የሆነ ለሙያ ማሻሻያ የሚሆኑ የገጽ ለገጽ ትምህርቶች እና ስልጠናዎች ይሰጣሉ። በዚህ መነቃቃት ውስጥ እያለ ነው ደርግ የገባው። ደርግም የጤና ባሙያዎች በሙሉ አንድ መሆን አለባቸው የሚል መመሪያ በማውጣት የሐኪሞች ማህበር ጠፍቶ የጤና ባለሙያዎች ማህበር ሆነ፤በዚህም ምክንያት የሙያ ማህበራቸው መድረስ የሚገባው ደረጃ እንዳይደርስ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ዶክተር ገመቺስ ይናገራሉ። ኢሕአዴግ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ደግሞ ማህበሩ በመጀመሪያ የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት እየጣረ ነው። ‹‹ለሕክምና አገልግሎት ወሳኝ ብለን ካነሳናቸው ነገሮች አንዱ ጥራት ያለው የሕክምና ትምህርት ነው።
የተንሻፈፈ ትምህርት የተማረ ሐኪም በቂ የሆነ አገልግሎት መስጠት አይችልም። ዝም ብሎ ፎቅ ስለተሠራ ብቻ ሆስፒታል አይሆንም። በውስጡ አስፈላጊው የሰው ኃይልና መገልገያ ቁሳቁስ መኖር ግድ ነው። የግብአት ችግር ሐኪሙን እጀ ሰባራ ያደርጋል፤›› በማለት ዶ/ር ገመቺስ ጥራት ያለው ሕክምና ለሕዝቡ ለማድረስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ። በአደጋ የተጎዳን፣ በቁርጠት የተዋከበን፣ በከባድ ደዌ የተንገላቱትን፣ በሞትና በሕይወት መካከል ሆነው የሚያጣጥሩትን በወሳንሳ አጋድሞ፣ በአምቡላንስ አጣድፎ፣ ሐኪም ቤት ማድረስ አማራጭ የሌለውና የተለመደ ጉዳይ ነው። ታዲያ ይህንን ስቃይን የማስታገስና ከሕመም የመፈወስ ፀጋ የተሰጣቸው ሐኪሞች ከዚህ ሁሉ ችግር የሚገላግሉ ሙያተኞች ናቸው። ስለዚህም እነዚህ የህክምና ባለሙያዎች በሥራቸው ሊመሰገኑ ሲገባ ወቀሳ እንደሚበዛባቸው፣ ዶ/ር ገመቺስ ማሞ ይናገራሉ። ሐኪሞች በሠሩትና ባደረጉት ነገር ምሥጋና ሊቸራቸው ይገባል።
ይህ መሆኑ ቀርቶ ግን ኅብረተሰቡን ይበድላሉ ከማለት ውጪ ምሥጋና ተችሯቸው አያውቅም ይላሉ። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ ሐኪሞችን ቅር ከማሰኘት አልፎ በእጅጉ ማሳዘኑ አይቀርም። ዶክተር ገመቺስ ይናገራሉ ‹‹እንዲረዳንና እንዲያመሰግነን የምንፈልገው ኅብረተሰቡ ነው። እኛን ያመሰገነ ሰው ሁሉ እንደወደደን ነው የምንቆጥረው፤›› ብለዋል። ሐኪሞች በሥራ ውጤታቸው በተመሰገኑ ቁጥር አገልግሎታቸውን በጥራትና በብቃት እንዲያከናውኑ የሚያደርጋቸው ሲሆን፣ ለበለጠ ሥራም ያነሳሳቸዋል። ከዚህ አኳያ የሕክምና አገልግሎት በጥሩ ሁኔታ ያገኘ ሰው የረዳውን ሐኪም ቢያመሰግን ሞራል ይሰጠዋል።
በአንፃሩም ሐኪሙም ሲመሰገን በሥራው መከበሩ «ከእኔ በላይ …» የሚል መታበይ እንዳይፈጠርበት መጠንቀቅ እንዳለበት ነው የጠቀሱት። እስከአሁን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባልደረቦቻቸው የተቸራቸው ምሥጋና ካልሆነ በስተቀር በመንግሥት ደረጃ አንድም ዕውቅና ተችሯቸው እንደማያውቅ አስታውሰዋል። ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ በፓርላማ ምሥጋና ማግኘታቸውን ይናገራሉ። ይህም ሁኔታ ለሌሎች ሐኪሞች ጭምር ስንቅ ሆኗቸዋል። እኛም የአገርና የሥራ ወዳድነታቸውን ፣ለሙያው የሚሰጡትን ክብር አድምጠንና ጽፈን ስንጨርስ፤ያጽናልዎት አልን። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 8/2011
አብርሃም ተወልደ