አንዳንድ ነገር በባህሪው እዚህና እዚያ መርገጥን፤ አንስቶ መጣልን፤ በሀሳብ መብሰልሰልን፣ መባዘንንና መቅበዝበዝን፤ ማለቂያ የሌለው የሀሳብ ድር ማዳወርን፤ ከፍ ሲልም የሀሳብ ዥዋዥዌ መጫወትን ግድ ይላል። በአገራችን እየተስተዋለ ያለውን አሳሳቢ የኑሮ ውድነት ባሰብሁ ቁጥር እየተፈጠረብኝ ያለው ስሜት እንዲህ ያለ ነው። ውሉ የጠፋና መቋጫ የሌለው የሀሳብ አዙሪት። እናም እንደ አገር፣ መሪና ዜጋ ካሉብን ስር የሰደዱ ፈተናዎች ለዛሬ አምስቱን መነሻ አድርጌ ሀሳብ እቀብላለሁ፤ “እሰጥ አገባ፤” እላለሁ፤ ትዝብት አጋራለሁ፤ አጀንዳ አነብራለሁ፤ ሰሞነኛ ገጠመኝን በማሳያነት አቀርባለሁ።
የመጀመሪያው ችግሮች ከመከሰታቸውና ከመባባሳቸው በፊት አነፍንፎ አበክሮ የመከላከል ልምሻ ሲሆን፤ ሁለተኛው ችግሮች ከተከሰቱ በኋላም ቢሆን መንስኤዎቻቸውን አብጠርጥሮ ከመፈተሽ ይልቅ አለባብሶና ሸፋፍኖ የማለፍ አባዜ ነው። ሶስተኛው ደግሞ ችግሮችን ውጫዊ የማድረግ እርግማን ነው። አራተኛው ውጤት ወይም ድል ሲገኝ ደግሞ የመሻማት ክፉ አመል አለብን። አምስተኛው የችግር አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀን አንገታችን ላይ እስኪደርስ ያለመንቃትና የማቅለል ክፉ አባዜ ምርኮኛ መሆናችን ነው።
እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት አብይ ጉዳይ ባለፉት ሰባት ወይም አራት አመታት እንደ አገር፣ መሪና ትውልድ የገጠሙን ፈተናዎች፣ ቀውሶችና ተግዳሮቶች ቢያንስ ላለፉት 100 አመታት ሲንከባለሉ የመጡና በእዳ የወረስናቸው መሆናቸው በደንብ ሊጤኑ ይገባል። ስለሆነም የማነሳቸው ችግሮች በአቅማችን ልንፈታቸው እየቻልን ያልፈታናቸውን፤ የሚያስከትሉትን ጉዳት ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባንችል እንኳ መቀነስ እየቻልን በዳተኝነት ወይም በእንዝህላልነት ያልቀነስናቸውን፤ የማድረግ ወይም የመፈጸም አቅማችንን አሟጠን መጠቀም ባለመቻላችን የተባባሱ ችግሮችን መነሻ በማድረግ እንደምሰናዘር ልብ ይሏል ።
በ2013 ዓ.ም ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ፤ የዋጋ ግሽበቱና የኑሮ ውድነቱ ከኢኮኖሚያዊ ችግርነት አልፎ የሰላም፣ የደህንነት፣ የጸጥታና የህልውና ችግር የመሆን ዕምቅ አደጋ የደቀነ ስለሆነ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝና አጀንዳ እንዲሆን አገር አቀፍ ውይይት እንዲካሄድ በዚህ ጹሑፍ አዘጋጅና “የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት፤” መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ የመነሻ ሀሳብ(ፕሮፓዛል)መዘጋጀቱንና የጠቅላይ ሚኒስቴሩ የፕሬስ ሴክሬታሪያት በየወሩ በሚያዘጋጀው “አዲስ ወግ” አገር አቀፍ መወያያ ርዕስ እንዲሆን ማሰቡን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ በስልክ አወያይቷቸው ነበር፡፡ በወቅቱም “ችግሩ የምርት ዕጥረት ነው። ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ መስራት እንጂ ስብሰባ መፍትሔ አያመጣም።” የሚል ወሽመጥ ቆራጭ መልስ ነበር የሰጡት፡፡ ሆኖም የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በማስረዳት መጨረሻ ላይ የመነሻ ሀሳቡን(ፕሮፖዛሉ)ን ለማየት እንዲልክላቸው ከአንገት በላይ ይስማሙና በቴሌግራም ይልክላቸዋል። መጀመሪያም ፍላጎት ስላልነበራቸው መልስ ሳይሰጡት ይቀራል።
ከሰባት ወር በኋላ ግን ሰሞኑን በብዙኀን መገናኛዎች እንደተከታተላችሁት ባለፈው ሐሙስ አሳሳቢው የኑሮ ውድነት የ”አዲስ ወግ” የመወያያ አጀንዳ ሆኗል። ምንም እንኳ ችግሩ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለሆነ መፍትሔውም በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዙሪያ መለስ ርብርብ መፈታት ያለበት ሆኖ ሳለ የመወያያ ሀሳቡን ያቀረቡትና ያብራሩት ሁሉም የመንግስት አካላት መሆናቸውና ተወያዮችም በቂ ጊዜ ተሰጥቷቸው ሀሳቦች በነጻነት እንዳይንሸራሸሩ መደረጉ በመድረኩ ላይ ጥላ ቢያጠላበትም እንዲሁም አጀንዳነቱም የዘገዬ ቢሆንም ከእነአካቴው ከሚቀር ችግሩ መነሳቱ ይበል የሚያሰኝ ነው። ሆኖም የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ ከሰባት ወር በፊት የኑሮ ውድነቱ አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳይ መሆኑን አምነው ተቀብለው የተባለው አገራዊ መድረክ በወቅቱ ተዘጋጅቶ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ግልጽና ጥልቅ ምክክር ተካሂዶ የመፍትሔ ሀሳብ ቀርቦ ሁሉም የቤት ስራውን ወስዶ ቢሰራ፤ መንግስትም ቢያንስ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ትኩረት ሰጥቶ ቢተጋ ኑሮ አሁን የገጠመንን ቀውስ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ባንችል እንኳ ጉዳቱን መቀነስ ይቻል ነበር። ይህ ባለመሆኑ ግን እዚህ ላይ ደርሰናል።
ከፍ ብሎ ለማሳየት እንደተሞከረው ችግሮች ከመከሰታቸውና ከመባባሳቸው በፊት አነፍንፎ አበክሮ የመከላከል እና የችግር አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀን አንገታችን ላይ እስኪደርስ የማነናቅና የማቅለል አባዜ እንደ አገር፣ ዜጋና መሪ የሚስተዋልብን ችግር ቢሆንም፤ እንደ የኢኮኖሚ ከፍተኛ አማካሪው ያሉ ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው ባለሙያዎች ግን እንደኔ ካለ የኢኮኖሚክስ ጨዋ ይልቅ የኑሮ ውድነት በአገር ላይ የደቀነውን አደጋ ቀድመው መረዳትና ደውሉን በመንካት መንግስትን የማንቃትና የማስረዳት ኃላፊነት ነበረባቸው። ይሄን ገጠመኝ ያነሳሁት ለክስ ወይም እንዲህ ብዬ ነበር ብሎ ለመታበይ ሳይሆን፣ መሰል የመሪዎቻችን ከፍተኛ አማካሪዎችና ባለሙያዎች ወደ ራሳቸው ወስደው ውስጣቸውን ሊፈትሹበት ይገባል፤ በሚል ቅን ሀሳብ በመነሳት መሆኑን ያጤኑአል።
በዚህ የአዲስ ወግ ወይይት ላይ የታዘብሁት ሌላው ጉዳይ የመንግስት አካላት የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል የነበረባቸውን ድክመት አፍረጥርጠውና ዘክዝከው ተቀብለው ከስህተታቸው ተምረው አዲስ የመፍትሔ ሀሳብ ይዘው ከመምጣት ይልቅ፤ ችግሩን ውጫዊ ለማድረግ የሄዱበት ርቀት፣ ያሳዩት መፈራገጥና መጋጋጥ አስገርሞኛል። ከብሔራዊ ባንክ የመጡት ባለሙያ የዋጋ ግሽበቱና የኑሮ ውድነቱ የተባባሰው ከ1997 ዓ.ም ወዲህ መንግስት የገንዘብ ፖሊሲውን በማላላት ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ውስጥ በመግባቱ ነው በማለት ችግሩን ውጫዊ ያደርጋሉ። ለውጡ ከባተ ወዲህም ተባብሶ ስለቀጠለው አሳሳቢ የኑሮ ውድነት የብሔራዊ ባንኩ ድክመት ምን እንደነበረ አምኖ ተቀብሎ በቀጣይ የነበረበትን ድክመት አርሞ ምን ለመስራት እንዳቀደና ምን እየሰራ እንደሆነ ግን በበቂ ሁኔታ አላብራሩም።
ከሕብረት ስራ ኮሚሽን የመጡት የስራ ኃላፊም ኮሚሽናቸው የኑሮ ውድነቱን ለመከላከል በነበረው ሒደት የነበረበትን ድክመት አፍረጥርጠው ከማቅረብና ከዚህ ተምሮ ምን ለመስራት እንዳሰበና ምን እየሰራ እንደሆነ በተጨባጭ ከማስረዳት ይልቅ፤ የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ያለው እሴት የማይጨምረው የንግዱ ተዋናይ ነው በማለት ችግሩን ውጫዊ አድርገውታል። ከፕላንና ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር የመጡ የስራ ኃላፊዎችም ያለባቸውን ድክመት ያለምንም ማቅማማት ከመቀበል ይልቅ ኮቪድ 19ኝንና የራሽያን ጦርነት የሀጢያታቸው ተሸካሚ ማድረግን መርጠዋል ። እዚህ ላይ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ኮቪዱም ሆነ ጦርነቱ አሉታዊ ተጽዕኖ የለውም እያልሁ ሳይሆን ችግርን ውጫዊ ከማድረግ ይልቅ የራስን ችግር ቆጥሮ ወስዶ ማረም ይቅደም ለማለት ነው።
ባለፉት ሰባት አመታት በተለይ ለውጡ ከመጣ ወዲህ የተከሰቱ ግጭቶች፣ ጦርነቶች፣ ቀውሶችና ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮች ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ከፍተኛ አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚያጠያይቅ አይደለም። ሸማቹም ሆነ ሕዝብ ግን መንግስት ላይ ቅሬታ እያቀረበ ያለው በአቅሙ ልክ መስራት የሚገባውን አልሰራም በሚል እንጂ ከአቅሙ በላይና ያልተጠበቁ ውጫዊ ችግሮች የሉም አላለም ።
ሕዝብ ያለው፣ የሚችለውን ማለትም፡- በግብይት ሰንሰለቱ ከጉልት ወይም ከማሳ እስከ ጅምላ አከፋፋይ የተሰገሰገውን ደላላ ከግብይት ስርዓቱ ቆርጦ ያውጣልን፤ መሠረታዊ ሸቀጦችን በሚደብቁ አልጠግብ ባይ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ አስተማሪ ሕጋዊ እርምጃ ይውሰድልን፤ ዋጋን በአድማና በመነጋገር የሚውስኑ የቀን ጅቦችን ይያዝልን፤ ሙስናንና ብልሹ አሰራሮችን ከመዋቅሩ ያጽዳልን፤ በድጎማ የሚገባው መሠረታዊ ሸቀጥ ለሸማቹ በቀጥታ መድረሱን የሚያረጋግጥ አሰራርና ስርዓት ያበጅልን፤ በነጻ ገበያ ስም ስድ የተለቀቀው የግብይት ስርዓት ላይ ልጓም ያብጅልን፤ መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ተመንና የትርፍ ህዳግ ይቀመጥልን፤ የንግድና የመኖሪያ ቤት ኪራይ ተመን ይውጣልን፤ ገበያውን እንደ ወልመርት፣ አሊባባና አማዞን ላሉ የውጭ ኩባንያዎች ክፍት ያድርግልን ፤ ብልጽግናም ሆነ ተፎካካሪዎች ቄሮም ሆነ ፋኖ ከባለሀብቱ ጋር ያላቸውን መርህ አልባ ግንኙነቶች ያቋርጥልን፤ የኑሮ ውድነቱንና ግሽበቱን ታሳቢ ያደረገ የደመወዝ ጭማሪ ያድርግልን፤ ለመንግስት ሰራተኛው የታክስ ወይም የግብር ቅነሳ ያድርግልን፤ የታጠፈውና ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር የተዳበለው የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ስልጣኑና ተግባሩ ተሻሽሎለት ራሱን ችሎ ይደራጅ፤ ከሚኒስቴሩ ጋር መዋሀዱም የጥቅም ግጭት ስላለው ይታረም፤ የሸማቾችን መብት ለማስከበር ከሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ይስራልን ፤ ወዘተረፈ አለ እንጂ፣ ሕዝብ ከመንግስት አቅም በላይ የሆነ ነገር አልጠየቀም። ይህ ሕዝብ ምን ያህል አስተዋይና አርቆ አሳቢ እንደሆነ መቼም ቢሆን አጠያይቆ አያውቅምና።
ዛሬ እያስተዋልን ያለነው ታፍኖ ሲብላላና ሲባባስ የኖረው ቀውስ ጡዘት(climax) ላይ መድረሱን ነው። ይህ ትውልድና መንግስት በታሪክ አጋጣሚ የዚህ ጡዘት ባለዕዳ ሆኗል። የዕዳው መጠን ቢለያይም፤ በደርግ በሶሻሊዝም ስም ሕዝቡ ማህበራዊ ወረቶቹን እንዲጥል ተገደደ። ፈጣሪውን ባህሉንና ወጉ ለማስጣል ብዙ ግፊት ተደረገበት። አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ተባብሎ ተሳስቦና ተዛዝኖ እንዳል ኖረ በዕዝ ኢኮኖሚ በአምራቾችና በኮታ ተተበተበ። ሕወሓት/ኢህአዴግ ወደ አገዛዝ ሲመጣ ደግሞ አንድን ቡድንና ጭፍራውን ተጠቃሚ ለማድረግ መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ ተሰራ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሌብነት እስካልተያዙ ድረስ ሙያ ነው እስከመባል ተደረሰ። ሌብነት ጀግንነት ሆነ። በአንድ ጀምበር በአቋራጭ መክበር እና ጥሎ ማለፍ እንደ ስኬት ተወደሰ። የሃይማኖት ተቋማት ሳይቀሩ በዚህ ተቃኙ።
በደርግ ጊዜ መዛበት የጀመሩ ሕዝቡን አጋምደው የኖሩ የውሃ ልኮች መናድ ጀመሩ። የሃይማኖት ወይም የትምህርት ተቋማት የዚህ መዛነፍ አካል ሆኑ። ፈሪኣ ፈጣሪም ሆነ መልካም ስነ ምግባር ከሕዝቡ የልቦና ውቅር ተደለዙ። ባለስልጣኑ፣ ተቃዋሚውና ሲቪል ሰረቫንቱም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከዚህ ቡድን እንደ አስተዋጾው ፍርፋሪ ደርሶታል። ምንም እንኳ እንደተሳትፎው መጠን የደረሰው ፍርፋሪ የተለያየ ቢሆንም። የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሌላው ለዛሬው አጣብቂኝ የዳረገን ችግር ነው። የደርግ የዕዝ ኢኮኖሚ ፈጠራንና ሀብትን የማያበረታታ ሲሆን፤ ሕወሓት/ኢህአዴግ ደግሞ አንዴ ልማታዊ ሌላ ጊዜ ነጭ ካፒታሊስት ነኝ ቢልም ኢፍትሐዊና አንድን ቡድን ልዩ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ስለነበር ኢኮኖሚውን ለመዋቅራዊና ተቋማዊ ችግር ዳርጎታል። በሕወሓት/ኢህአዴግ የተንሰራፋው የገነገነ ሙስና አገሪቷን በቁሟ ግጦ ግጦ መለመሏን አስቀርቷታል። ከአገር ውስጥ ጥቅል ምርት እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ዘርፏል። ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋን ሀብት ከዚች ድሀ እናት መቀነት ቆረጦ አሽሽቷል። የሚያሳዝነው የዘረፍኸውን አርፈህ ብላ ቢባልም በጄ አለማለቱ ነው። ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት በዘረፈው ሀብት አገራችንን ለማፍረስ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። ያልወጣው አቀበት ፤ ያልወረደው ቁልቁለት የለም።
አገዛዝ ላይ ለመቆየት ያነበረው የማንነት ፖለቲካ በዜጎች ዘንድ እንዲሰርጽ ለ30 አመታት በጀት መድቦ ተቋማዊና መዋቅራዊ አድርጎ ሌት ተቀን በመስራቱ ጥላቻ፣ አለመተማመንና መጠራጠር በመላ አገሪቷ እንደ ሰደድ እሳት ተዛመተ። በአናቱ የዘረፈውን ሀብት በመጠቀም በመላ አገሪቱ ግጭትና ብጥብጥን በመጥመቅ ለፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳረጋት። ይህ አልበቃ ብሎት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ ትውልድም ሆነ ታሪክም ይቅር የማይለውን ክህደት እና ለማየት የሚዘገንን ለመስማት የሚሰቀጥጥ ጭፍጨፋ ፈጽሞ አገሪቱን አስገድዶ ጦርነት ላይ ዘፈቃት። ሶስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አከርካሪው ቢሰበርም ግልጽ ድህረ መቐሌ ስትራቴጂ ባለመኖሩ ወታደራዊ ድሉን ማጽናትና ማዝለቅ ባለመቻሉ ሕወሓት አፈር ልሶ ከመነሳት አልፍ የአማራና የአፋር ክልሎችን በመውረር ህልቆ መሳፍርት የሌለው ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ፈጥሯል።
በሁለቱ ክልሎችና በአገሪቱ ያደረሰው አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በብዙ መቶ ቢሊየኖች የሚገመት ሲሆን ሰብዓዊና የስነ ልቦና ጉዳቱ ደግሞ እጅግ የከፋና በምንም ሊተመን የማይችል ሆኖ ሰንበሩ ለአመታት አብሮን ይኖራል። ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዳፋውም ለአመታት ማንገዳገዱ አይቀርም። ይህ አላንስ ብሎ መጀመሪያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እሱ ትንሽ ጋብ ሲል ደግሞ የዩክሬንና የራሽያ ጦርነት ተጨምሮ ኢኮኖሚውን እንደ ሀይለኛ የጎን ውጋት ቀስፎ ይዞታል። በአገሪቱ ከተንሰራፋው ሙስና፣ ብልሹ አሰራር፣ አልጠግብ ባይነትና ስግብግብነት ጋር ተጃምሎ የዋጋ ግሽበቱና የኑሮ ውድነቱ ዜጋውን ለረሀብና ለእርዛትና ለበሽታ ዳርጎታል። ተስፋ እንዲቆርጥ፣ መፈጠሩን እንዲጠላና እንዲያማርር አድርጓታል። በድህረ የብልጽግና 1ኛ ጉባኤ በመላ አገሪቱ በተዘጋጁ ሕዝባዊ መድረኮች ጮህ ብለው የተሰሙ ድምጾች ይሄን ሀቅ አረጋግጠዋል።
ከማህበራዊና ከፖለቲካዊ ችግርነት አልፎ የህልውና፣ የሰላም፣ የጸጥታና የደህንነት ችግር ሆኖ ከእጃችን እንዳይወጣ የቀውሱን አንገብጋቢነት በልኩ መረዳት፤ ገዥው ፓርቲም ወጥና ሀቀኛ በሆነ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ቀውሱ የደቀነውን አደጋ ተገንዝቦ ለዙሪያ መለስ መፍትሔው ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆን ይጠበቅበታል። በየደረጃው ያለ ስግብግብና አልጠግብ ባይ ነጋዴም ዛሬ መሠረታዊ ሸቀጥ እየደበቀና እጥረት እየፈጠረ የሚያጋብሰውን ሀብት ነገ ሊበላው፤ ልጆቹን አስተምሮ ለወግ ለማዕረግ ማብቃት የሚችለው አገር ሰላም ሲሆን ነውና ቆም ብሎ ሊያስብ ይገባል። በሰሞነኛው አንድ መድረክ እንደተገለጸው እሱ እየበላ ጎረቤቱ እየተራበ ሊቀጥል አይችልም። ሲብስበት በሩን ሰብሮ ይገባለታል። በሕዝብ ረሀብና ችግር እያተረፈ ያለው ደላላም ቆም ብሎ ሊያስብና ወደ ህሊናው ሊመለስ ይገባል። በእርግጥ ህሊና ካለው። ቸር እንሰንብት ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2014 ዓ.ም