የሰላም ጉዳይ አገራዊ ራስ ምታት ሆኖ ቀጥሏል። በሁሉም አቅጣጫዎች ሰላም ብርቅ ሆኗል። ሰላማዊ ነው የሚባል ክልል በአገሪቱ አለ ለማለት ያስቸግራል። በአሸባሪው ሕወሓት የተነሳ ትግራይ ክልል ጦርነት ውስጥ ከገባ ወደ ሁለተኛ ዓመቱ እየተዳረሰ ነው። አፋር ክልል በሕወሓት ምክንያት ሰላም ካጣ ወራት ተቆጥረዋል። አማራ ክልል በአንድ ጎን ሕወሓት በሌላ ጎን ውስጡ የተሰገሰጉ ወንበዴዎች ሰላም ነስተውታል። ኦሮሚያ ክልል በሸኔ የሽብር ቡድን የተነሳ ኢመደበኛ ጦርነት ውስጥ ነው። ቤኒሻንጉል ፤ ደቡብ ፤ ሶማሌ የየራሳቸው ሰላም እጦት አለባቸው። መዲናችን አዲስ አበባ ራሷ የራሷ የሰላም እጦት መንስኤዎች አሏት። አሁን ላይ በአገሪቱ ዜጎች የሚሞቱበት ነገር ከመብዛቱ የተነሳ ሰርግ እንኳን ሞት የሚያስከትል ጉዳይ ሆኗል። ብስራት ሬዲዮ ሰሞኑን እንደዘገበው በአማራ ክልል በ8 ወር ውስጥ ሰርግ ላይ በተተኮሱ የደስታ ጥይቶች 11 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
በዚህ ሰአት ሰላም ለምን ይህን ያህል ራቀን? እንዴትስ ሰላማችንን እንመልስ? የሚሉ ጥያቄዎች የሁሉም ሰው ጥያቄዎች ናቸው። መልሱ ግን ቀላል አይደለም። መንግሥት ሰላም ለማምጣት እንዲህ እና እንዲያ እያረግኩ ነው እያለ ነው። እርምጃ ተወሰደባቸው፤ እጃቸውን ሰጡ፤ መሳሪያቸው ተያዘ የሚባሉ ሃይሎች ቁጥር ብዙ ነው። ነገር ግን እነዚህ እርምጃዎች ተጨባጭ እና መሰረታዊ ለውጥ ማምጣታቸውን ለማወቅ አልተቻለም። እርምጃዎቹም በሕዝብ ዘንድ ሰላም እየሰፈነ ነው፤ ሕግም እየተከበረ ነው የሚል መተማመንን መፍጠር የቻሉ አይመስልም። እንዲያውም በተቃራኒው ሰላም የመመለሻ ቀኗም በዚያ ልክ እራቀ ይመስላል። ምኑጋ ነው የተሳሳትነው ምንስ ብናስተካክል ነው የሰላምን መንገድ መልሰን የምናገኘው የሚለው ጥያቄም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ለዛሬ ወደ ሰላም ለመመለስ መደረግ ካለባቸው የመጀመሪያ ነው ሊባል የሚቻለውን ለማንሳት ወደድን። እሱም መተማመን ነው። አሁን ባለን ሁኔታ መተማመን አለ ወይ? ሕዝብ መንግሥት ሰላምን ማምጣት ይችላል ብሎ ያምናል ወይ? የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ጥያቄ ነው። ምክንያቱም የሚታዩት ምልክቶች በአንዳንድ የሕብረተሰብ ክፍሎች መንግሥት ሰላምን የማስከበር አቅም ወይም ፍላጎት የለውም የሚል ሃሳብ እንዲሰነዝሩ አድርጓቸዋል። ሰሞኑን ከሕዝብ ጋር የተደረጉ ስብሰባዎች ላይ በስፋት የታየውም ይሄው ነው። እንዲያውም አንድ በማሕበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር የነበረ ቪዲዮ ላይ አንድ ተሳታፊ ሰብሳቢዎቹን የመንግሥት ሹማምንት “ከሶስታችሁ ሁለታችሁ ሸኔ ልትሆኑ ትችላላችሁ” ብሎ ሲናገር ታይቷል፡፡
ከሰውየው ንግግር በበለጠ ያ ቪዲዮ በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የተሸከረከረበት እና ብዙዎች የተጋሩበት መንገድ ሃሳቡ የአንድ ግሰለብ ብቻ ሳይሆን የብዙሃን እንደሆነ አመላካች ነው። ሕብረተሰቡ አሁን ከአሸባሪዎች ባልተናነሰ መንግሥትን እና ሹማምንቱን እየተጠራጠረ ነው ማለት ነው። ይህን ነገር አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ ሰላምን ማስከበር የማንኛውም መንግሥት የመጀመሪያው መሰረታዊ ግዴታ ከመሆኑ አንጻር ነው። መንግሥት ይህን መሰረታዊ ተልእኮውን ለመወጣት አቅም አጥሮታል ወይም ዳተኝነት አሳይቷል የሚል እሳቤ ሲኖር ደግሞ ለብዙ አደገኛ አካሄዶች መወለድ ምክንያት ይሆናል፡፡
መንግሥት ሰላምን ለማስከበር ዳተኛ ሆኗል ወይም አቅቶታል የሚል እሳቤ ሲኖርና ዜጎች ሰላማቸውን ማስከበር የራሳቸው ግዴታ አድርገው ከወሰዱ ሌላ አዲስ እና በጣም አደገኛ ችግር ይፈጠራል። ይሄ በየክልሎች የተደራጁ ልዩ ኃይሎች የፈጠሩትን አቅም ተከትሎ የሆነብንን እንድናስብ ያደርገናል። አሁንም ከመከላከያም፤ ከብሄራዊ ደህንነት ፤ ከፌዴራል ፖሊስ ፤ ከክልል ፖሊስ ፤ ከክልል ልዩ ሃይል ያለፈ በክልል ደረጃ ሌሎች የወጣቶች አደረጃጀቶችን እየፈጠሩ ነው። ይህ አይነት አደረጃጀትና ታጣቂ ሃይል ሲበዛ አገር ይጠቅማል አይጠቅምም ወደፊት የሚታይ ነው፡፡
እንግዲህ ክልሎች በዚህ መልኩ ሰላምን ማስከበር የራሳቸው ሃላፊነት አድርገው አዳዲስ አደረጃጀት እየፈጠሩ ሌላ አላስፈላጊ የፖለቲካ ሙቀት ከጨመሩ፤ ተራው ዜጋ የራሴን ሰላም ማስከበር የራሴ ሃላፊነት ነው ብሎ መንቀሳቀስ ሲጀምር ደግሞ ምን ያህል ችግር እንደሚፈጠር መገመት አያቅትም። ስለዚህም መንግሥት ሰላም ለማስከበር እና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ብቁ እና ቁርጠኛ እንደሆነ ማሳመን አለበት፡፡
እዚህ ጋር ለያይተን ልናየው የሚገባ ነገር ቁርጠኝነት እና ብቃትን ነው። መንግሥት ሰላምን ለማስከበር የአቅም እጥረት የለበትም በሚለው ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚስማማ ይመስላል። የብዙ ሰው ጥያቄ እና ቅሬታም መንግሥት አቅም ሳያንሰው ነገር ግን ጸረ ሰላም ሃይሎችን ለመቅጣት እና ሰላምን ለማስከበር ዳተኛ ሆኗል የሚል ነው። በእርግጥም አገሪቷ የአሸባሪዎች ሁሉ ቁንጮ እና ሁሉን መጋቢ የሆነውን ሕወሓትን አደብ ማስገዛት የቻለ የጸጥታ ሀይል አላት። ከአገርም አልፎ በአህጉር ደረጃ ሰላም ማስከበር የቻለ ሰራዊትም የኛ ነው። ታዲያ ዋናውን አሸባሪ ወደ ሳጥኑ መመለስ የቻለው መንግሥት ደቃቆቹን አሸባሪዎች መቅጣት አቅቶት ነው? ወይስ እነዚህ ሃይሎች ከአመት በፊት በከፍተኛ ድምጽ አሸንፎ ሥልጣን ለመያዝ ከበቃው መንግሥት የበለጠ ሕዝባዊ ድጋፍ ኖሯቸው ነው? ወይንስ አንዳንዶች እንደሚሰጉት የመንግሥት መዋቅር ራሱ ተጠልፎ ነው? ለነዚህ ጥያቄዎች ብዙ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ማብራሪያዎች ከመንግሥት በኩል እንደሚሰጡ እርግጥ ነው። ነገር ግን ማብራሪያዎቹ ምንም ያህል አሳማኝ ቢሆኑ እንኳ አሁን በመንግሥት እና በሕዝብ መሀከል በሰላም ዙሪያ ያለው መተማመን ካልተሻሻለ ሰላምን ማስከበር አይቻልም፡፡
መተማመኑ አስፈለጊ የሚሆነው በዋነኝነት ሰላምን ማስከበር የሕዝብ እና የመንግሥት የጋራ ስራ ውጤት ስለሆነ ነው። ሁለቱ እንደ ቀኝ እጅ እና ግራ እጅ ናቸው። የጸረሰላም ሃይሎችን ጉሮሮ አንቆ ትንፋሻቸውን ለማቋረጥ ሁለቱም እጆች መተጋገዝ አለባቸው። ለጊዜው ግን ቀኝ እጅ ግራ እጅን እያመነው አይመስልም። ስለዚህም ግራ እጅ ሆን ብሎ እየለገመ እንዳልሆነ ለቀኝ እጅ ማሳመን አለበት። መንግሥት እና ሕዝብ ካልተማመኑ ክልሎች ሊተማመኑ አይችሉም። መንግሥት እና ሕዝብ ካልተማመኑ የፌዴራሉ የጸጥታ መዋቅር እና የክልሎች የጸጥታ መዋቅር ሊተማመኑ አይችሉም። መንግሥት እና ሕዝብ ካልተማመኑ የላይኛው መዋቅር እና የታችኛው መዋቅር ሊናበቡ አይችሉም። ስለዚህም መንግሥት ሰላም ለማስፈን ቁርጠኛ መሆኑን በተግባር ሊያሳይ እና በሕዝብ ዘንድ አመኔታን ሊፈጥር ይገባል፡፡
ሕዝብ አሁን የደህንነት መስሪያ ቤቱ የማይታዩትን የአገር ጠላቶች ካሉበት ጉድጓድ ጎትቶ ሲያወጣ ማየት ይፈልጋል። ሕዝብ መከላከያ ሰራዊቱ አሁንም ቢሆን የአገር ሉአላዊነትን ለማስከበር ዝግጁ እና ብቁ አንደሆነ ማወቅ ይፈልጋል። ሕዝብ የፌዴራል ፖሊስ በየስርቻው በታጠቁ ወሮበሎች ሲገድል ሳይሆን የክልሎችን ድንበር አቆራርጦ እየሄደ የሽብር ቁንጮዎችን ሲቆጣጠር መመልከት ይፈልጋል። ሕዝብ አሁን አንዱ ክልል ሌላውን በስጋት ሲያይ ሳይሆን በጋራ ተባብረው ሲሰሩ ማየት ይፈልጋል። ሕዝብ የክልል ፖሊስ እና ልዩ ሃይል የፖለቲካ መሳሪያ ሳይሆን የሰላም ዘብ ሆነው መመልከትን ይጠብቃል። በጥቅሉ ሕዝብ መንግሥት በመሰረታዊነት የሰላም ማስጠበቅ ስራውን መስራት እንደሚችል እንዲያሳየው ይፈልጋል። መንግሥት ደግሞ ይህን በማሳየት እምነትን መፍጠር ይጠበቅበታል፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2014 ዓ.ም