እንደ መግቢያ የኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ የፊልም ተመልካች ሁሉ ቃል አውጥቶ እንደልቡ የሚዘልፈውና የሚናገረው ዘርፍ ነው። በብዛት ለእይታ ከሚቀርቡት ፊልሞች መካከልም አንድ ሁለቱን አይቶ በአገሪቱ የፊልም ዘርፍ ተስፋ የቆረጠና ዳግም ላለማየት የማለ አይጠፋም። በዛም ላይ ራሳቸው የፊልም ባለሙያዎች ሆነው አብረው ዘርፉን የሚያሙ አይታጡም። «ምን እናድርግ?» ሲሉ የሚጠይቁ ግን እጅግ ጥቂቶች ናቸው። የፊልሙን ዘርፍ ለማገዝ አንዱና ቀዳሚው ሥራ ብቁ ባለሙያ ማፍራት መሆኑ ይታወቃል።
በአገራችን ያለው ችግርም እዚህ ላይ ነው። የፊልም ባለሙያዎች በራስ ጥረት ከፍ ካለም ልምድ በመለዋወጥ ካልሆነ በቀር በትምህርት ብቁ የሚሆኑበት መንገድ አልነበረም። በጥረታቸው ራሳቸውን አሳድገው ለሌሎች ለመትረፍ የሚጥሩ መኖራቸውን ግን አንዘነጋም። በተረፈ በቅርቡ ነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ የፊልም ትምህርት ክፍል የተከፈተው። ከጎንደር ያመጣነው መረጃ ደግሞ ወዲህ አዲስና መልካም ነገር አቀብሎናል።
እንዲህ ነው፤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በፊልም ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት የሚሰጥ ትምህርት ክፍል ተቋቁሟል። ይህም በአገራችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ደረጃ የመጀመሪያው የሚባል ነው። ዘንድሮ ሁለተኛ ዓመቱን የያዘው ይህ ትምህርት ክፍል፤ በቤተሰብ ውስጥ አርአያውን እንደሚከተሉት ታላቅ ወንድም ወይም እህት ላቅ ያለ ድርሻ አለው። ሌሎች አካሄዱንና መድረሻውን ተከትለው በተመቻቸ መንገድ እንዲጓዙ እድል ፈጥሯልና። ወጣት ምስጋናው ዓለሙ፤ የፊልም ባለሙያ እንዲሁም መምህር ነው።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ፊልምና ቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ትምህርት ክፍል ኃላፊ ነው። ከፍ ሲል እንደውም በጎንደር የፊልምና ቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ትምህርት ክፍልን አሃዱ ብሎ ያስጀመረ ነው። የትምህርት ክፍሉ እንዴት ተጀመረ? ምን ሂደቶችን አለፈ? ምን እየተከናወነበት ነው? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን አንስተን ተነጋግረናል። ምልሰት ምልሰት ይሉታል የፊልም ባለሙያዎች፤ የቀደመውን ነገር የሚያሳዩበትን መንገድ። በዛ ምልሰት ወደኋላ እንመለስ። በአገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውና በመጀመሪያ ዲግሪ የፊልም ትምህርት የሚሰጠው ትምህርት ክፍል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተከፈተው በ2010ዓ.ም ነው።
ታድያ ለሁሉም ነገር ቅድመ ዝግጅት አለውና፤ ቅድመ ዝግጅቱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ተጀምሯል። በቅድመ ዝግጅቱ አብዛኛውን ሥራ የከወነው አሁን ላይ የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ወጣት ምስጋናው ነው። ለትምህርቱ የሚሆን የትምህርት ስርዓት በመቅረጽ ጉዞውን ለብቻው ጀመረ። ከወቃሽ ጋር ወቃሽ፣ ከተቺው ጋር ተቺ መሆንን አልመረጠም። «ጎንደር ደግሞ የኪነጥበብ አገር ነው።» አለ ምስጋናው፤ ከኪነጥበብ ሥራዎች መካከል ደግሞ አንዱ ፊልም ነው። ለፊልሙ ዘርፍ በአቅሙ የሚያደርገው ነገር ሊኖር እንደሚችል በማመን በቅድሚያ ሃሳቡን በልቡ፣ ከዛም በወረቀት ኋላም በተግባር እውን አደረገው።
የፊልም ትምህርት ክፍል እንዲከፈት ጥያቄውን ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ አቀረበ፤ ተቀባይነት አገኘ። እኛም እንጠይቅ፤ አንድ የትምህርት ክፍል እንዲከፈት ብሎ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምን መጠየቅ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ፤ ምስጋናው ምን ሲል የፊልም ትምህርት ክፍልን አሰበው? ዋናው ባለድርሻ አንድ ፊልም የአተራረክ መንገዱን በምልሰት ቢጀምር እንኳ ጎን ለጎን ዋናውን ገጸ ባህሪ ያስተዋውቃልና፤ የነገራችንን ዋና ባለድርሻ ወጣቱን የፊልም ባለሙያና መምህር ምስጋናው ዓለሙን እንወቀው። ምስጋናው የመጀመሪያ ዲግሪውን በቴአትር አግኝቷል። ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ለሁለት ዓመታት አገልግሏል።
ታድያ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በሥራ በነበረበት የመጀመሪያ ዓመት ላይ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ አንድ ፕሮፖዛል አስገባ። ይህም የቴአትር ትምህርት ክፍል እንዲከፈት የሚጠይቅና አቅጣጫ የሚያሳይ ነበር። ዩኒቨርሲቲውም ጥያቄውን ተቀብሎ በ2006ዓ.ም በግቢው የቴአትር ትምህርት ክፍልን ከፈተ። በሚገርም ሁኔታ ትምህርት ክፍሉ ስኬታማ የሚባል ነበር፤ በተቋቋመ በዓመቱ ከትምህርት ክፍሎች ሁሉ በአፈጻጸም አንደኛ ሆኖ ተሸልሟል።
ምስጋናው ጊዜውን አላባከነም፤ በ2008ዓ.ም ለትምህርት ወደ አዲስ አበባ አቀና። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ የፊልም ትምህርቱን ተከታትሎ በዓመቱ የመመረቂያ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ወደ ጎንደር ተመለሰ። ይሄኔ አያይዞ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንደ ቴአትሩ ሁሉ የፊልም ትምህርት ክፍልም ሊከፈት ጥያቄውን አቀረበ። አልተከለከለም፤ ይሁንታን አገኘ። ለመመረቂያው ሲያዘጋጅ ከነበረው ጽሑፍ ጎን ለጎን የፊልም ስርዓተ ትምህርት /ካሪኩለም/ አብሮ ማዘጋጀት ጀመረ።
በዚህ ጊዜ «ሁለት ተከታታይ ቀናት ከወንበሬ ሳልነሳ የቆየሁበት ጊዜ አለ» ሲል ያስታውሳል። ሥራው አድካሚ ነበር፤ ሁለት መቶ ገጽ ያለውን ስርዓተ ትምህርት አዘጋጀ፤ የትምህርት ዓይነት ስያሜዎችና መሰል በሂደቱ አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎች ጊዜ ተሰጥቷቸው በጥንቃቄ በኋላ የተዘጋጀው ሰነድ ማለፍ ያለበት ሂደት ተከተለ፤ የሁሉም ይሁንታ ያስፈልግ ነበርና በግቢው ካሉ ባለሙያዎች ጀምሮ እስከ ትምህርት ሚኒስቴር ድረስ ዘለቀ። ሥራው ድካም ብቻ ሆኖ አልቀረም፤ ይሁን ተባለ። አሃዱ፤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ፊልምና ቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ትምህርት ክፍል በዋናው ባለድርሻ በኩል በዚህ መልክ ተጀመረ። ሲኒማ ቤቶች፣ መገናኛ ብዙሀን፣ የፊልም ባለሙያዎች፣ የውጭ አገራት ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶችና የባህል ማዕከላት … በተፈለጉ ጊዜ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ አለን አሉ።
ምስጋናው ተግባራዊውንም ዲፕሎማሲያዊውንም ሥራ አጠናቀቀ። በ2009ዓ.ም ሁለተኛ ዲግሪውን ከጨረሰ በኋላ በ2010ዓ.ም ሙሉ ጊዜውን ለትምህርት ክፍሉና ለማስተማር ሰጠ። ምስጋናው በግሉ አጫጭር ፊልሞች አዘጋጅቷል፣ የፊልም ጽሑፎች ጽፏል፤ አሁንም ዘጋቢ ፊልሞችን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል። ለሙያው ትልቅ አክብሮትና ጥልቅ ፍቅር አለው። ይህን ስሜት ወደ ተግባር ለውጦ አንዳች ነገር እንዲሠራ ያደረገው ደግሞ ሁሉም ሰው ወቃሽ መሆኑን መታዘቡ እንደሆነ ይናገራል። የፊልም ባለሙያዎች ምንም ሳይሰጣቸው ነገር ግን ጉልበትና ገንዘብ አፍስሰው የወደዱትን ሙያ ይሠሩበታል።
ይህን መሥራት ትልቅ መስዋዕትነት መሆኑን ምስጋናው ይጠቅሳል። ይሁንና አንድ ሰው ወይም የፊልም ባለሙያ ጥሩ ፊልም ሠራ ማለት የኢትዮጵያን ፊልም ያሳድጋል ማለት እንዳልሆነም ያነሳል። ዘርፉን ለማሳደግና ለመለወጥ ከአንድ ፊልም በዘለለ የፊልም ባለሙያዎች ላይ መሥራት ተገቢ መሆኑ ያሳምነዋል። ለዛም ነው የመጀመሪያውን እርምጃ ለብቻው የጀመረው። የፊልም ትምህርትና ትምህርት ክፍሉ የዚህ ሁሉ መግቢያና ምልሰት፤ የዋና ባለድርሻውም ድካም ትምህርት ክፍሉን ማቋቋምና ማጽናት ላይ ነው። በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ፊልምና ቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ትምህርት ክፍል በፊልም ትምህርት ጥቂት ተማሪዎችን ነው ተቀብሎ የሚያስተናግደው። እቅዱም ተማሪዎችን በገፍ ተቀብሎ መበተን ሳይሆን ብቁ የሆኑ ጥቂቶች ላይ አተኩሮ መሥራት ነው። አሁን ላይ የተማሪዎቹ ቁጥር ሲታይ አንደኛ ዓመት የሆኑት አስራ አራት ሲሆኑ፤ ሁለተኛ ዓመቶች ዘጠኝ ናቸው።
ትምህርቱ ደግሞ የአራት ዓመት መርሃ ግብር ነው። የክፍሉ ኃላፊ ወጣት ምስጋናው ታድያ ትምህርት ክፍሉ እንደተለመደው አስተማሪ እያስተማረ ተማሪ የሚሰጠውን ሁሉ የሚቀበልበትና የሚወስድበትን መስመር ማስቀጠልን አልመረጠም። በዛ ስርዓት ተማሪው ተመርቆ ሲወጣ «ብዙ ጉራ… ትንሽ ክህሎት ይዞ ይወጣል» ይላል ምስጋናው። በአንጻሩ ተግባራዊ ትምህርቶች ላይ ትኩረት ያደርጋል። ከዛም በተጨማሪ የፊልም ባለሙያ እንዲሆኑ የሚማሩ ተማሪዎች የሃሳብና የታሪክ ግብዓት እንዲሆናቸው በአገር ጉዳይ ላይ፣ ይልቁንም ታሪክ፣ ባህል፣ ፎክሎርና ልብወለድ በመሳሰሉ ዘውጎች ጋር በቂ ትውውቅ እንዲኖራቸውም ይደረጋል ብሏል።
ለዚህም የሚረዱ አጋዥ የትምህርት ዓይነቶች መኖራቸውን ነው የሚጠቅሰው። ከዚህ በተጓዳኝ የትምህርት ክፍሉ ስያሜ ፊልምን ብቻ ሳይሆን «የቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን» የሚልም ተካቶበታል። ይህ ያለምክንያት አልተደረገም፤ ምስጋናው እንዳለው ተማሪዎች በፊልም ዘርፍ ብቻ ተብሎ ተመርቀው በተለያየ አጋጣሚ ቀጥታ ወደ ሥራው ላይገቡ፤ ቀጣሪም ላያገኙ ይችላሉ። እናም እነዚህ ተማሪዎች ባለሙያ ከሆኑ በኋላ እንዳይቸገሩ በቴሌቪዥንም መስክ ብቁ ሆነው እንዲወጡ ይደረጋል። በአራት ዓመት መርሃ ግብር ተማሪዎቹ በሁሉም ዘርፍ የተሟላ ነገር እንዲያገኙ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ ነው ምስጋናው የሚናገረው። ሜዳውና አቀበቱ በአገራችን ጥቂት የሚባሉ ነገር ግን
ተጽእኖ መፍጠር የቻሉ የፊልም ባለሙያዎችን እናውቃለን። በስማቸው እና በዝናቸው ብቻ እንኳ ብዙ ተደማጭነት አላቸውና ብዙ በሮች ለእነርሱ ክፍት ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ይታመናል። ሆኖም «የፊልም ሙያና ጥበብ በመንግሥት በኩል ትኩረት ተነፍጓል» ከማለትና ከመባባል ውጪ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ትምህርቱ እንዲሰጥ ያደረጉት ጥረት አልታየም፤ ቢኖር እንኳ ፍሬ ሳያፈራ ብዙ ቆይቷል። ለምን? አቀበቱ ብዙ ስለሆነ ነው። እንዲህ ያለው አቀበት ከምስጋናው እንዲሁም ሥራውን ከተቀላቀሉትና ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፊት ሳይደቀን ቀርቶ ነው? አይደለም። «እየፈራን ከሄድን መቼም አንሠራውም ብለን ነው የተጋፈጥነው » ይላል ምስጋናው።
ሥራው ገና ሲጀመር አስተማሪ ከየት ይመጣል? ቁሳቁስ እንዴት ይሟላል? … የሚሉ ጥያቄዎች ተፈጥረው ነበር። «ከጎደለው ነገር ይልቅ ያለውን ማሰብ ይበልጣል» የምስጋናው አስተያየት ነው። ቃል በቃል እንዲህ ሲል ይገልጻል። «በእኛ ግቢ የሌለውን ከቆጠርን ችግሩ ይበዛል፤ ሌሎች ጋር ያለውንና እኛም ጋር የሚገኘውን ብንቆጥረው ግን ብዙ ነው። ለፊልም ደግሞ ተፈጥሮ የሰጠችን ነገር አለ። ራስ ዳሽን እና ጉና ትልቁ ተራራ አለ፣ ሜዳው አለን፤ ትልቁ ጣና አለ። ታሪካዊ ቦታዎች ቅርብ ናቸው። ዛፉም ተራራውም ድንጋዩም ለዚህ ምቹ ነው። ሕዝብም ብዙ ታሪክ አለው። ታሪኩ ለፊልምና ለኪነጥበብ የሚሆን ነው።
በብዙ መንገድ የሚገለጽ ባህልም አለ። ሃሳቡና ታሪኩ ካለን ባለሙያውን ማፍራት ነው ቀሪው ሥራችን። ባለሙያው ደግሞ በተፈጥሮ የተሰጠውን ጸጋ የማሳደግ ነገር ነው። ይህ ግላዊ ቁርጠኝነትን ነው የሚጠይቀው። እኛም አምነን የመጣውን ለመጋፈጥ ነው።» የትምህርት ክፍሉ ይከፈት የተባለ ጊዜም አይሆንም ብለው የተቃወሙም እንደነበሩ ምስጋናው ያስታውሳል። እነርሱም ይህን ያሉት በስጋት ነው፤ የሰው ኃይል የለም በሚል ስጋት። «እኔም በእኔ ብቻ ይሸፈናል ብዬ አልጀመርኩም።» አለ ምስጋናው። ሥራውን
የተቀላቀሉትም ሁሉ ዘልቀው የሚመጣውን ችግር በጋራ ለመጋፈጥ ተስማሙ። የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች እስኪመረቁ ድረስ ፈተናው ሊበረታ እንደሚችልና እስከዛ ድረስ በጥንካሬ የመጣውን ሁሉ ለመቋቋም ወሰኑ። በዚህ መሰረት አቀበቱን ወደ ሜዳ ለመቀየር ሁሉም የሚችለውን አነሳ። እነ ምስጋናው፣ የፊልም ባለሙያዎች፣ የትምህርት ቤቱ አመራርና የመሳሰሉት። ምስጋናው ይላል፤ አዲስ አበባ የሚገኙ የፊልም ባለሙያዎች በጣም ይተባበራሉ፤ እንቢ አይሉም። በቀናነት ለወራት በጊቢው ተመላልሰው ያስተምራሉ።
ኑልን ሲሏቸው አሻፈረኝ አይሉም፤ ሲጠሯቸው አቤት ሆኑ። ራሳቸውን አስተምረው ብዙ ፊልም የሠሩና በተግባር ተፈትነው ብዙ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች ለአዳዲሶቹ የነገ ተስፋዎች ሃሳባቸውንም፣ ጆሯቸውን እንዲሁም ልምዳቸውንም እየሰጡ ይገኛሉ። ሄኖክ አየለ፣ ዳንኤል ወርቁ፣ እስክንድር ኃይሉ፣ ደበበ እሸቱ፣ አዜብ ወርቁ፣ ዓለማየሁ ታደሰ፣ ሚካኤል ሚሊዮን፣ ደሳለኝ ኃይሉ፤ እንዲሁም አሁንም አቤት ከማለት ያልተቆጠቡት ያሬድ ሹመቴ፣ ሰውመሆን ይስማው ሌሎችም፤ «እኛ ጠይቀን እንቢ ያሉን የሉም። የእኛ ወደነሱ መሄድ ካለ እነሱ ለመምጣት ዝግጁ ናቸው።» የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ይናገራል። ሌላው አቀበቱን ቀንሶ ያደላደለው የጊቢው አስተዳደር ነው። ትምህርት ክፍሉን በተለየ ሁኔታ ማስተናገድና የተለያዩ ክፍያዎች እንዲፈጸሙ በማመቻቸት በኩል የጊቢው አስተዳደር ከፍ ያለውን ሚና ተጫውቷል። ከነምስጋናው ጥረት በተጓዳኝ ሥራውን ስኬታማ ያደረገው የግቢው አመራሮች ለኪነጥበብ ያላቸው መልካም እሳቤና ተቆርቋሪነት መሆኑንም ያነሳል። «ትምህርት ክፍሉ ይሄ ይሄ ያስፈልገዋል ብሎ የሚያስብ አመራር ማግኘት መታደል ነው።
እኛም ያንን አግኝተናል።» ይላል፤ ምስጋናው። ከሰማንያ በላይ የትምህርት ክፍል ባለበት ተቋም ውስጥ የዚህ ትምህርት ክፍል ነገር አሳስቧቸው ደጋግመው እየደወሉ የሚጠይቁ የግቢውን ከፍተኛ አመራሮችንም ያስታውሳል። ነገሩ ወደ አንድ ሃሳብ ያመላክተናል ይላል፤ ይህም ከበረታ ከሰው ቁጥጥር ውጪ ፈታኝ የሆነ ነገር የለም የሚል ነው። እናስ በሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይህ እንዳይሆን ምን ይከለክላል? ምስጋናው እንደሚለው ሌሎችም ይህን ድፍረት ማግኘት ከቻሉ የትምህርት ክፍሉን መክፈት ይቻላል። በእነርሱ በኩል ቁርጠኛ መሆናቸው ለዚህ ውጤት እንዳበቃቸው አስታውሶ «እኛ ስንጀምር እጃችን ላይ ትንንሽ የፎቶ ካሜራ ይዘን ነው እንጀምር ብለን ያጸደቅነው።
አሁን ላይ ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ተመድቦ በቅርቡ የሚገቡ ሙሉ የፊልም ቁሳቁሶች አሉና ከዚህ በኋላ ትምህርት ክፍሉ የፊልም መሠረታዊ መሣሪያዎች ሁሉ ይኖሩታል።» ብሏል። ከሁለት ዓመት በኋላ- ርዕይ ከሁለት ዓመት በኋላ በፊልም ዘርፍ የመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች ከጊቢው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይቀበላሉ። «ተማሪዎቻችን ለእኛ የመጀመሪያ ልጆቻችን ናቸው፤ ለኢትዮጵያም እንደዛው።» አለ፤ ምስጋናው። እነዚህ ተማሪዎች ከኢትዮጵያ ሁሉም አቅጣጫ የተገኙ በመሆናቸው ሲበተኑም ወደተለያየ አቅጣጫ በመሄድ ለሁሉም ይደርሳሉና ነው። ለትምህርት ክፍሉ የመጀመሪያውን ድንጋይ ያኖረውና አሁንም በኃላፊነት ላይ ያለው ወጣት ምስጋናው ጨምሮ፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ተመርቀው የሚወጡት ልጆች የሚመኩባቸው እንደሚሆኑ ይናገራል። እንዲህም አለ፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መታወቂ እንዲሆኑ፣ «ጎንደር የተመረቁት» እንዲባሉ፣ «ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተመረቁትን…» የሚያስብሉ ተመራጭ ባለሙያዎች ሆነው እንዲገኙ «በጎንደር ዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች የተሠራ…»
ተብሎ የሚደነቅ ሥራ የሚሠሩ እንዲሆኑ ነው የትምህርት ክፍሉ ፍላጎት። ወጣቱ መምህር ምስጋናው፤ የመጀመሪያዎቹ ልጆች የተመረቁ ጊዜ ስሜቱ እንዲህ ነው የሚሆነው ይላል፤ ልክ የመጀመሪያ ልጅን ወግ ማዕረግ እንደማየት። እናም ባለሙያዎቹ በሙያዊ ስነምግባር የታነጹና «መማርማ እንዲህ ነው!» የሚያስብሉ እንዲሆኑ ነው ፍላጎቱ። አስተምሮ መሸኘት ብቻ አይደለ፤ በስነምግባር፣ በሙያ፣ በክህሎትና በእውቀት የተሻሉ፤ ተጽእኖ መፍጠር የሚችሉ፤ ዘርፉ ላይ ለውጥ የሚያመጡ፤ ሙያው ላይ የሚጨመሩ ሳይሆን አዲስ ነገር የሚያቀረቡ ልጆች ሆነው ማየት ነው ህልማችን ይላል። መልዕክተ ምስጋናው በአንድ በኩል በልምድ ራሱን ያሳደገ፤ ጎን ለጎን ደግሞ በትምህርት የተገነባ ባለሙያ፤ ሁለቱ በጋራ ሲሆኑ የበረታ ለውጥ ይመጣል።
ይሁንና ዘርፉ ላይ ያለው ተማሪውን፣ የተማረው የተባለው ዘርፉ ላይ የሚንቀሳቀሰውን ይንቃል፤ ይናናቃሉ። ምስጋናው ግን ይህ ሊሆን አይገባም ባይ ነው። ሁሉም ባለሙያ የእኔ የሚለውን የፊልም መንደር መመሥረትም እንደሚያስፈልግ ነው የሚያነሳው። ይሄኔ ሁሉም ባለቤት ይሆናል። ይህ ማለት እነዚህ ተመርቀው የሚወጡ ልጆች የሁሉም ልጆች ይሆናሉ ወይም ናቸው ማለት ነው። ተማሪዎቹ ተመርቀው ሲወጡ ለዘርፉ ባይተዋር አይሆኑም። ስለምን ቢሉ ያስተማሯቸውና ልምድ ያካፈሏቸው በጥረታቸው ራሳቸውን ያሳደጉትና ዘርፉ ላይ የሚንቀሳቀሱት ናቸው። እነዚህን ተማሪዎች አብዛኞቹ የፊልም ባለሙያዎች አሻራቸውን ስላኖሩባቸው፤ «የእኔ ተማሪ» ይሏቸዋልና፤ በጋራ አንድ ርዕይ ለመያዝና አንድ ህልም ለማሳካት ሁኔታው ይመቻቻል። የሥራው ዓለም ሌላ፤ የትምህርቱ ዓለም ሌላ ተደርጎ የመወሰዱ ነገርም በዚህ ያከትማል። ምስጋናው ሊያስተላልፈው የፈለገው መልዕክት እርሱም መነሻ የሆነው ሃሳብ ነው። አንድ ባለሙያ ምርጥ ፊልም ሊሠራ ይችላል፤ የኢትዮጵያን ፊልም ዘርፍ በዛ ሥራ ያሳድገዋል ማለት ግን አይደለም። ይላል፤ አሳን አጥምዶ ማቅረብ ሳይሆን የአሳን አጠማመድ ማስተማር ያስፈልጋል። ሰዎች ላይ በመሥራት አገርን መጥቀም ይቻላል ብሎ አምኗልናም ሰው ላይ እየሠራ ይገኛል። «መምህር መሆንን የመረጥኩት ለዛ ነው። ሰውን ከመውቀስ ሰው ላይ መሥራት ያስፈልጋል ብዬ» ብሏል። በግሉ በግጥም ፍቅር ልቡ የዘለቀው የጥበብ ነገር በቴአትር ከዛ በፊልም ዘልቆ እንዲገባ አድርጎታል።
ወደፊትም በፊልም ሶስተኛ ዲግሪ የመሥራት ሃሳብ አለው። ይሁንና አሁንም ሠርቻለሁ አይልም። እናሳ? «በሩን እያንኳኳሁ ነው» ፊልም ላይ ያደረገውን አስተዋጽኦ የሚያደምቅለት የፊልም መንደር ተመሥርቶ ማየት መሆኑን ያነሳል። እስከዛ ግን በቻለው ፍጥነት ይራመዳል፤ የቻለውን ርቀት ይጓዛል። ሥራው የመጀመሪያ መሆኑ በፊልም ታሪክ የሚመዘገብ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ይህ እንደማያኮራው ይናገራል። ኩራቱ ያኔ ነው! ልጆቹ ተመርቀው ሲወጡና የመጀመሪያ የሆነ ሥራን ሲሠሩ። እናብቃ! አንድ ሰው ብቻውን ለውጥ አያመጣም ወይ? ይሄን ታሪክ ከሰማን በኋላ ልንጠይቅ የምንችለው ጥያቄ ነው። ቁርጠኝነትና ጥንካሬ ካለ ነገሩ ቀላል ይሆናል። ከመወሳሰቡ የተነሳ መቋጠሪያ ውሉ የጠፋ የሚመስለውና ብዙ የሚታማው የአገራችንን ፊልም ዘርፍ፤ አብሮ ከመተቸት ወጥቶ የሚሠራለትን አግኝቷል። ይህ አንዱ እርምጃ ነው። የኢትዮጵያ ፊልም ፀሐይዋ በጎንደር በኩል እየታየች ነውና፤ ስኬትና መልካም እድል እየተመኘን የዘርፉን ንጋት ከዛ እንጠብቃለን። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 8/2011
ሊድያ ተስፋዬ