አንድን አገር አዘቅት ውስጥ ከሚከቱ ዋነኛ ምክንያቶች መካከል አጠቃላይ የሕግ መከበር እና ማስከበር ችግር ዋነኛው ነው፡፡ አጠቃላይ ሕዝብ ህግ ማክበር አለበት፡፡ ተገልጋይም ሆነ አገልጋይ፣ ሰባኪውም ሆነ ምዕመኑ፣ መምህሩም ሆነ ተማሪው የፓርቲም ሆነ የመንግስት ባለስልጣን ሁሉም ከህግ በላይ ከሆነ ነገር ተበላሸ ማለት ነው፡፡ ሕግ ተገቢውን ሥፍራ ካላገኘ መባለግን እንደተራ ጉዳይ አይቶ ማለፍ ከተበራከተ፤ የአገር ህልውና ፈተና ውስጥ መውደቁ የማይቀር ነው፡፡
በአንዳንድ ቦታ ላይ የሚታዩ ጋጠ ወጥነቶች ለጊዜው ባለጌውን እየጠቀሙ ያሉ ቢመስልም፤ ውሎ አድሮ ሁሉንም መጉዳቱ የማይቀር ነው፡፡ ከሰሞኑ አንድ ዜና ተሰማ፡፡ የአፋሯ ዱብቲ ከተማ ሕብረተሰቡ ውሃውን ከቆጣሪ ውጪ ከዋናው መሥመር ጋር እያገናኘ መጠቀም በመጀመሩ፤ የከተማዋ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ከፍተኛ ኪሳራ እንደገጠመው እና ለሠራተኞቹ ደመወዝ መክፈል እንደተሳነው ተገልጿል፡፡ በመጨረሻ ተቋሙ ለከተማው ሕዝብ አገልግሎት መሥጠት የማይችልበት ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በሌሎችም አንዳንድ ክልሎች የተሰበሰቡ ወጣቶች ኢንቨስተርን እና ባለሃብትን፣ ከባለሃብት አልፎ ተራውን ሕዝብ ሳይቀር እያስፈራሩ እየዘረፉ አልፈው ተርፈው እየገደሉ ስለመሆኑ ይወራል። እነዚህ ወጣቶች ሕግ አይገዛቸውም፡፡ በህግ ተከራክሮ ማስጠየቅም ሆነ ማስቀጣት ዘበት ነው፡፡
አንዳንዴ መኪና ለማሳለፍ የኮቴ የሚያስከፍሉ አልፈው ተርፈው ሰዎችን በየመንገዱ አለፍ ሲልም ቤት ድረስ ሔደው እያስገደዱ ገንዘብ የሚቀበሉ ቡድኖች ‹‹ሸኔ ናቸው›› ተብሎ ቢወራም በቅርብ ርቀት ተጠግተው ወንጀል እስከ መስራት የደረሰ ድፍረት በሸኔ የተፈፀመ ነው ለማለት ያዳግታል፡፡ እርግጥ ነው፤ ኦነግ ሸኔ ብዙ ጥፋት አስከትሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ለሆኑ አካላት ተላላኪ በመሆን በወንጀል ሥራ ላይ በመሠማራት ብዙዎች እንባቸው እንዲፈስ አድርጓል፡፡ ነገር ግን ደግሞ በኦነግ ሸኔ ስም ጥፋት ላይ የተሠመሩ እንደማይጠፉም ተጎጂዎች እየገለፁ ነው፡፡
መንግስት ሸኔን ማጥፋት፤ በመንግስት መዋቅር ሥር ተሰግሥገው አገር እያመሱ እያተራመሱ፤ ገንዘቡንም እያፈሱ ያሉትን ህግ ፊት በማቅረብ ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› እንደተባለው ሸፋፍኖ መሾም፤ ሕግን ከማስከበር ይልቅ ጥፋት ማድረሳቸው እየታወቀ፤ በመረጃ እና በማስረጃ እየተረጋገጠ እንዲሁ በለሆሳስ ማለፍ ሕዝብን ያሳዝናል፡፡ ያው እንኳን የሕዝብ ማዘን የግለሰብ ሀዘንም ቢሆን ለታዘነበት አካል የሚበጅ አይደለም፡፡ እንግዲህ ዘመን ተገልብጦ ታሪክ የሚቀየርበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ያኔ ለጥጋበኛው ማዘን የግድ ይሆናል፡፡
መንግስት ትናንት ከነበረው በመማር ማንም ቢሆን ሕግ እንዲያከብር ማስገደድ አለበት፡፡ ለዚህም ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ ካልሠራ ምኑን የተሻለ መንግስት ሆነ የሚል ወቀሳን ያስከትላል፡፡ መንግስት ባለበት በዚህች ትልቅ አገር ውስጥ በሰላም ወጥቶ መግባት እንደትልቅ ጉዳይ ታይቶ በአጀንዳነት ሊቀርብ አይገባም። በመንግሥት የተሾመ ባለሥልጣን ዝርፊያ ውስጥ ገብቶ ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት እና በእርግጥም ሠላም ለማስፈን የሚያስችል ሁኔታን ማመቻቸት ከተሳነው እሹሩሩ ማለት አስፈላጊ አይደለም፡፡ በመዋቅር ውስጥ የተሰገሰገው ኃይል ከህግ በላይ አለመሆኑን ማወቅ አለበት፡፡
ባለሥልጣንም ሆነ ባለሙያ ተገልጋይም ሆነ ማንኛውም ቡድን እና ግለሰብ ከሕግ በላይ ልሁን ብሎ ጥፋት ከፈፀመ፤ በጥፋቱም የማይጠየቅ ከሆነ እና ፍትሕ ከተደፈጠጠች የሕዝብ ጥላቻ እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ ኢትዮጵያ አገር ሆና መቆም የማትችልበት ደረጃ ላይ መደረሱ የማይቀር ነው፡፡ አገር ከፈረሰ ባለስልጣን፣ ወጣት ብሔርም ሆነ ጎሳ እንዲሁም ሃይማኖት ብሎ ነገር አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር በእግሯ መቆም ካልቻለች በአፍ እየተለፈፈ ያለው እና ብዙዎች ውስጥ ሥር እየሰደደ ለውጥ ያመጣል የሚባለው አንድነት ብሎ ነገርም አደጋ ያንዣብብበታል። አንድነት ቀርቶ መፈረካከስ ግድ ይሆናል፡፡ ለእዚህ ዋነኛው መፍትሔ ማንም ሆነ ማን በሕግ አደብ እንዲገዛ ማድረግ ብቻ ነው፡፡
በሥልጣን መባለግም ሆነ ሥርዓተ አልበኝነት አሁኑኑ በመንግሥት አሠራር እንዳይኖሩ መከላከል ያስፈልጋል፡፡ ለእዚህ መፍትሔው ተቋማትን ማጠናከር ነው፡፡ ሕዝብ የሚፈልገውን አገልግሎት ለመስጠት፣ ከሕዝብ ወቀሳ ለመዳን ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት አሠራርን መዘርጋት ይገባል፡፡ ተቋማት ከማህበረሰቡ ፍላጎት እና ከዘመኑ ጋር የሚመጥን ዕድገት እንዲኖራቸው በአመራር፣ በባለሙያ፣ በቴክኖሎጂና በተለያዩ ግብዓቶች ማደራጀት የግድ ነው፡፡
ነገር ግን አመራሩም ሆነ ባለሙያው የብቃት ችግር ኖሮበት፤ ያለበትንም የብቃት ችግር ሳይረዳ መፍትሔ ከማመላከት ይልቅ የሕዝቡን ሥቃይ የበለጠ ማባባስ ላይ ከተሠማራ አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡ ይህንን ችግር ለማቃለል አመራሩም ሆነ ባለሙያው በሕይወቱ ስኬታማ ኑሮን እንዲመራ ራሱንም ሆነ አገሩን እንዲጠቅም በሚችለው ሥራ ላይ እንዲሠማራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ቢቀር ራሱን የሚያሻሽልበትን ሥልጠና መስጠት ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በእዚህ በኩል እርምጃ ለመውሰድ ነገ ዛሬ ማለት አይገባም፡፡
አመራር ሲመሰገን እንጂ ሲወቀስ መሰማት የለበትም። ሙሉ ለሙሉ ሁሉም ያመስግነው ለማለት ቢያዳግትም ሁሉም ተገልጋይ ወቃሽ ከሆነ እርሱ እየሔደበት ያለው መንገድ እና እየሰጠ ያለው አገልግሎት ትክክል ነው ብሎ ቢያምንም ብዙ ሕዝብ አልስማማም ካለ ራስን መፈተሽ ይገባል፡፡
በመንግስት በኩል የሕዝቡን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማፈን ነፃ ሃሳባቸውን የሚያስተላልፉን ማሰር፣ ማሳደድና መግደል ቆሟል ቢባልም ቡድኖች የሚፈፅሙትን ዘግናኝ ተግባር በጊዜ መቆጣጠር ከልተቻለ ሕግ ካልተከበረ ዞሮ ዞሮ አደጋው መንግስት ላይ አልፎ ተርፎም ሕዝብ ላይ መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡
ኢትዮጵያ ሰፊ መሬትና ትልቅ የውኃ ሀብት ለዛውም ሊሠራ ከሚችል ወጣት ኃይል ጋር የታደለች በመሆኗ ይህንን ዕድል መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ይህን ሃብት በተገቢው መንገድ መጠቀም ከተቻለ ከልመና ተላቃ በአፍሪካ አህጉር በነፃነት ፋና ወጊነቷ የምትታወቀዋ አገር በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን የምትችልበት ደረጃ ላይ መድረስ አይሳናትም፡፡ ለእዚህ ግን መነሻውም ሆነ መድረሻው የሕግ የበላይነት ነው፡፡
ይህ እንዲሆን ደግሞ የእዚህ ዘመን ትውልድ ትልቂቱን ለነገው ትውልድ ለማስተላለፍ ከትዕቢት፣ ከማናለብኝነት፣ ከዘረፋ እና ከወንጀል ድርጊት ራሱን ማራቅ አለበት፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በትጋት በመሥራት ለራሱ እና ለቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን ለአገሩ እና ለዓለም የሚሆን በረከትን በመሥራት የተፈጠረበትን ዓላማ ማሳካት ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ለእዚህ ዋነኛ መነሻውም ሆነ መድረሻው አሁንም ህግ አክባሪነት ነው፡፡ በትክክልም ሕዝቡ ህግ አክባሪ መሆን አለበት። ወጣቱን ጨምሮ አጠቃላይ ሕዝቡ ሕግ እንዲያከብር መንግስት በተለይም በፀጥታ ሃይል በኩል ያሉ አመራሮች ሃቅ ላይ ተመስርተው ዘመድ ባዳ ሳይሉ ህግ የማስከበር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2014