ዓለም በሁለት ጥንድ አስተሳሰብ ስር የወደቀች ይመስለኛል፤ ለምሳሌ፣ አገር በአንድ አይነት ሀሳብ ብቻ የሚገነባ የሚመስላቸው እና የተለያዩ ሀሳቦችን ወደ አንድ በማምጣት አገር መገንባት የሚቻል በሚመስላቸው ሰዎች። ርዕይ ያላቸውና አገር ለማቆም የሚተጉ ልቦች አገር በተለያዩ ሀሳቦች ነገር ግን በአስታራቂ እውነት እንደምትገነባ የሚያምኑ ሲሆን፤ በተቃራኒው እንደ እኛ አይነት ከመግባባት ይልቅ በተቃርኖ ሀሳብ ጦር መማዘዝን ባህል ያደረጉ አገራት ለምንም ነገር አንድ አይነትነትን የሚያስቀድሙ ናቸው። ይሁን እንጂ ዓለም አንድ አይነት የሆነ ምንም ነገር የላትም። ከትላንት እስከዛሬ በመለያየትና በተቃርኖ ነገር ግን በአስታራቂ ሀሳብ የቆመች ናት። ለምንም ነገር አንድ አይነት መሆንን የሚመርጡ ግለሰቦች ገና የዘመናዊውን ዓለም ሰፊ ምህዳር ያልዳሰሱ ናቸው ብዬ በግልጽ መናገር እችላለሁ። በእንዲህ አይነት አስተሳሰብ ስር የወደቁ አገራት አይደለም ትውልድ፣ አይደለም አገርና ሕዝብ ቀርቶ ራሳቸውን እንኳን ከራሳቸው ጋር ማግባባት አይችሉም።
አገር የተለያየ ሀሳብ ነው የሚያስፈልጋት። የአሁኑ ስልጣኔና እርምጃ የመጣው በተለያዩ ሰዎች የተለያየ ሀሳብ ነው። ሀሳባችን ሌሎችን እስካልጎዳ ድረስ የተለየ መሆኑ ያን ያክል ችግር ይኖረዋል ብዬ ባላስብም በመነጋገርና በመወያየት ሁሉንም ወደሚያስማማ እውነት መጠጋት ግን የበለጠ አዋጭ እንደሆነ አምናለሁ። የትኛውም አገርና ሕዝብ በተመሳሳይ ባህልና ሥርዓት፣ ወግና ልማድ፣ አስተሳሰብና ርዕዮተ ዓለም አልቆምም። አገራችን ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰብ ጉራማይሌ መልክ ናት፤ ከነዚህ በርካታ ብሔረሰቦች መካከል የሚወጣው የሀሳብ መልክ ደግሞ የተለያየ ነው። እኚህ የተለያዩ የብሄር ሀሳቦች ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ውበት እንጂ ተጨማሪ ስቃይ እንዲሆኑ መፍቀድ የለብንም። እኛ ከተግባባን፣ ፖለቲከኞቻችን ለመስማማት ከተዘጋጁ ወደ ጦርነት የሚወስድ ሀሳብ ይኖረናል ብዬ አላስብም። ሁሉም ሀሳቦች ምንም ያክል ቢጎረብጡም በንግግር የሚታረቁ ናቸው። ሆኖም ለአመታት እኔ ብቻ ነኝ ልክ በሚል አጉል አመለካከት ተተብትበን አገራችንን ላልተገባ ስቃይ ስንዳርጋት ኖረናል፤ አሁን ግን ጊዜው ለዚህ የሚሆን አይደለም፤ በመነጋገር መስማማት ይኖርብናል።
ብዙዎች በመነጋገር ከኋላችን ተነስተው ጥለውን እየሄዱ ነው፤ ብዙ አገራት በእኛ መፈጠር ተፈጥረው እኛን ለማሸማገል መሀላችን ሲገቡ እያየን ነው፤ ይሄ ለእኛ አይመጥነንም። ይሄ ለታላቋ ኢትዮጵያ አይገባም። በእርቅና በመግባባት የጥንቱን ታላቅነታችንን መመለስ ይኖርብናል። ለብዙ የዓለም አገራት፣ ለብዙ የአፍሪካ አገራት ለሰላም ግንባታ ሰራዊቶቿን እየላከች ሰላም ስታሰፍን የቆየች አገር ዛሬ ሰላም ርቋት ስትታይ ያሳዝናል። ምስራቅ አፍሪካ እኮ ኢትዮጵያን ተደግፋ ነው የቆመችው። የአፍሪካ እናት እኮ ኢትዮጵያ ናት፤ ችግሮቻችንን በሀሳብ የበላይነት በማሸነፍ ስማችንን ማደስ ከሁላችንም የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። ህንድ በሕዝብ ብዛት ከዓለም ሁለተኛ ናት፤ በውስጧም ከሁለት ሺህ በላይ ቋንቋዎች ይነገሩባታል፤ ላለፉት እጅግ በርካታ አመታት ምንም አይነት ጦርነት ተስተናግዶባት አያውቅም። ናይጄሪያ በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለምም ከቀዳሚዎቹ ተርታ ናት፤ በውስጧም ከአምስት መቶ በላይ የተለያዩ ጎሳዎች ይኖራሉ፤ የሕዝብ ብዛቷና የጎሳዋ መብዛት ግን ችግር አልፈጠረባትም። መነጋገርን ያስቀደመ ማህበረሰብ ልዩነቶቹ ምንም ያክል ቢጎሉም ኢምንት ናቸው።
ነገሮች በእኛ አስተሳሰብ ስር ናቸው፤ አስተሳሰባችንን መቆጣጠርና መግራት ካልቻልን ለነገሮች ባሪያና አልሸነፍ ባይነትን ነው የምንለምደው። በሀሳባቸው ተፅዕኖ ስር የወደቁ ሰዎች ተነጋግሮ መግባባት አይቻላቸውም። አይደለም ከሌላው ጋር ከራሳቸው ጋርም መግባባት አይቻላቸውም። የአገራችን አብዛኛው ችግር ይሄ ነው፤ ለሀሳቦቻችን ቅድሚያ የሰጠን ነን። ምንም ያክል አዋጪና በላጭ አስተያየት ብንሰማ እንኳን እኔ ያልኩት ካልሆነ የምንል አይነት ነን። እኚህ አስተሳሰቦች ናቸው ዛሬ ላይ ዋጋ እያስከፈሉን የሚገኙት። አገራችን በላጭ ሀሳብ ያስፈልጋታል። በበላጭ ሀሳብ አገራችንን መምራት ልምድ ማድረግ ይኖርብናል። በላጭ ሀሳብ በሌለበትና ተነጋግሮ መግባባት በማይችል አገርና ሕዝብ ውስጥ ነውጥ እንጂ ለውጥ የለም። መገፋፋት እንጂ መተቃቀፍ አይታሰብም። መነጋገር እኮ ዘመናዊነት ነው፤ ዘመናዊነትን መዝገበ ቃል ላይ ብትፈልጉት፣ ከብዙ ዝርዝሮች ውስጥ ተነጋግሮ መግባባት የሚል መልስ ይሰጣችኋል።
እንደ ዜጋ ዘመናዊነታችንን ተነጋግሮ በመግባባት ውስጥ ልንፈልገው ይገባል። እንደ አገር ዘመናዊነታችንን በውይይት መጀመር ይኖርብናል። ባለመነጋገር ከዘመናዊነት ርቀን የሰነበትንባቸው እነዛ በርካታ ዓመታት አስተምረውናል ብዬ አስባለሁ። ባለመነጋገር ሰላማችንን፣ አንድነታችንን ነጥቀውን አለያይተውን ነበር። አሁን ግን መከራ ይበቃናል፤ በጠብመንጃ ሳይሆን በውይይት፣ በመለያየት ሳይሆን በመቀራረብ ሰላም ማምጣት መልመድ ይኖርብናል። የዓለም ስልጣኔ በመነጋገር ውስጥ የቆመ ነው። ወደ አፍሪካ ስንመጣ ግን ይሄ እውነት ጎልቶ አይታይም። በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊ ሕይወታችን ባጠቃላይ በእያንዳንዱ የሕይወት እንቅስቃሴያችን ላይ የውይይት ስልጣኔ አይስተዋልም። ለብዙ ነገር ሰልተን ለመነጋገር ሲሆን ግን የከሸፍን ነን። አፍሪካን ዋጋ እያስከፈላት ካለው ነገር ውስጥ አንዱና ዋነኛው ይሄ ነው ብዬ አስባለሁ። ወደ እኛ አገር ስንመጣ ደግሞ የከፋ ሆኖ እናገኘዋለን። ያለፉት ሃምሳ አመታት ካለመነጋገር ጦርና ጎራዴ የተማዘዝንባቸው ሆነው ያለፉ ነበሩ። በቀላል ነገር ብዙ ነገሮችን ያጣንባቸው ጊዜያቶች ነበሩ።
እንደ አያቴ ጥበበኛ ሴት አላውቅም፤ በሕይወቴ ሁሉ የምታስገርመኝ ሴት ናት። ምድር ላይ ዘጠና ስድስት አመት ስትኖር ሁሌ የምትለው አንድ ነገር ነበር “መተው ነገሬን ከተተው..›› እንደ አያቴ የመተውን ጥበብ ያስተማረኝ ማንም የለም። በአያቴ ነፍስ ውስጥ፣ በአያቴ ሴትነት ውስጥ በእርጅናዋ ውስጥ ሳይቀር አፍርቶና ጎምርቶ ያገኘሁት አንድ ታላቅ ጥበብ ቢኖር የመተው ጥበብ ነው። የአያቴ እውነት ይሄ ብቻ አይደለም እውነተኛ አሸናፊነት የት እንዳለ የምታውቅ ሴት ነበረች። እውነተኛ አሸናፊነት በመተውና በመቻል ውስጥ ነው ያለው ብላኛለች። በትዕግስትና በይቅርታ ውስጥ ነው ያለው ብላ ነግራኝ ታውቃለች። ይሄንንም እውነት ስታስረግጥልኝ “መቻል ምን ይከፋል ሆድ ካገር ይሰፋል፤” ስትል አውግታኛለች። እኔና እናንተ ይሄን እውነት አናውቀውም። አያቴ ይቺን ምድር እስከተሰናበተችበት ጊዜ ድረስ በመተው ጥበቧ ለዘጠና ስድስት አመታት ከሰው ልጅ ሁሉ ጋር በመስማማት ኖራለች። የአያቴ እውነት.. እምነት ያስደንቀኛል። የጠፋችውን ኢትዮጵያ በእሷ ነፍስ ውስጥ፣ በእሷ ሴትነት ውስጥ አያታለሁ። የአያቴ እውነት አሁን ላለነው ለእኛ መልካም እውቀት ሆኖ ስላገኘሁት አካፈልኳችሁ።
አሁን ላለችው ኢትዮጵያ የአያቴ ጥበብ ያስፈልጋታል። አሁን ላለነው ትውልዶች የአያቴ እውነት ያስፈልገናል። አያቴ በመተው ውስጥ ከዘጠኝ አስርት አመታት በላይ በኩራትና በልዕልና ተራምዳለች። ሁላችንም ወደ መተው እንመለስ። ወደ ሆደ ሰፊነት፣ ወደ ሰምቶ መቻል እንመለስ። በትዕግስት፣ በይቅርታ ወደማሸነፍ እንሸጋገር። በውይይት ወደመርታት እንምጣ። ሳንግባባ የምንሄድባቸው መንገዶች ሩቅ አያደርሱንም። ሳንስማማ በልዩነት የምንራመድባቸው ጎዳናዎች አይባርኩንም። የምንመኛትን ኢትዮጵያ አንደርስባትም። ልንፈጥረው የምናስበውን ትውልድ አንታደገውም። ብንሄድ ብንሄድ ወደ ረፍታችን አንደርስም። የትንሳኤአችንን ጥጉን አናገኘውም። በመሆኑም ላሰብናቸው አገራዊ በጎ ሀሳቦች ሰላም ያስፈልገናል። አገራዊ መግባባት ግድ ይለናል። ሀሳቦቻችንን ካልገታናቸው ወይም ደግሞ በሌላ አስታራቂ እውነት ካልቀየርናቸው አደገኛ ነው የሚሆኑብን። ብዙ አገራት የፈረሱት፣ ብዙ ትውልዶች የመከኑት በሀሳብ ነው። እንደዚሁም ደግሞ በጋራና በመተማመን ሀሳብ ያተረፉ በርካታ አገራት አሉ። ለእኛም የሚያስፈልገን በጋራ ሀሳብ ወደፊት መሄድ ነው።
አገራችን በአሁኑ ሰዓት ወደ ከፍታ እርምጃ ላይ ናት፤ እርምጃዋ ይፈጥን ዘንድ ሁሉን አቀፍ ምክክር ያስፈልጋታል። ትላንት ላይ ለጦርነት ምክንያት የሆኑ የመለያየት ሀሳቦች በውይይት መፈታት ለአገራችን እርምጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ከታች እስከላይ ባለው አገራዊ መዋቅር ለነውጥና ለሰላም መደፍረስ መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮች እየተለዩ እልባት ቢሰጥባቸው እጅግ ዋጋ ያለው ነገር ነው። የውስጥና የውጭ ፖለቲካዊም ሆኑ ማህበራዊ ችግሮቻችን በጋራ ውይይት የሰላም ፀሀይ ቢወጣባቸው በብዙ እናተርፋለን ባይ ነኝ። እኛ እየኖርን ያለነው በድሮ ባህል ነው፤ ትላንትና ለጦርነት መንስኤ የሆኑ ችግሮቻችንን ዛሬም ለጦርነት እየተጠቀምንባቸው እንገኛለን። ተወያይቶ ከመስማማት ይልቅ ጎራ ወደመፍጠር መሄድ ይቀናናል። ትላንትናዎቻችን በዚህ ደረጃ የተቃኙ ነበሩ፤ እናም ልምዶቻችንን መቀየር ይኖርብናል። ዋጋ ያስከፈሉንን ትላንትናዎች ዛሬ ላይ መድገም አይኖርብንም። ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ ናት ብለን ስንናገር በምክንያት መሆን አለበት። ምክንያቱም ለውጥ ብዙ ገጾች አሉት፤ የሁሉም ገጾች ማረፊያ ግን የሀሳብ የበላይነት ነው። የሀሳብ የበላይነት ደግሞ ተነጋግሮ በመስማማት የሚመጣ የስልጣኔ ከፍታ ነው። ለውጥ በሀሳብ የበላይነት ካልመጣ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል።
ስለዚህ አገራዊ ለውጣችን በመነጋገር ተጀምሮ በሀሳብ የበላይነት እንዲጠናቀቅ የሁላችንም ድርሻ ነው። መንግስት ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ የለም። ጥቂት ሰዎች ብቻ ነደው የሚፈጥሩት እሳት የለም። በእሳቱ ለመሞቅ ሁላችንም ነዳጅ መሆን አለብን። እሳቱ ለውጥ ነው..ለውጥ ደግሞ በጋራ የሚመጣ የአብሮነት ሀይል ነው። የለውጥ መጀመሪያ መነጋገር ነው። የመነጋገር መጀመሪያ ደግሞ በሀሳብ የበላይነት ለመስማማት መዘጋጀት ነው። ይሄ ሁሉ ባልሆነበት ሜዳ ላይ የሚመጣ አገራዊም ሆነ ግለሰባዊ መሻሻል የለም። አሁናዊ ችግሮቻችንን በመነጋገር ካልፈታናቸው ሌላ በምንም አንፈታቸውም። ሲወቅስና ሲተች፣ ሲረግምና፣ ሲያንቋሽሽ የኖረ አእምሯችንን ለአዲስ ለውጥ ማሰልጠን ይኖርብናል። በጥላቻና በመገፋፋት የቆመ አካላችንን አብሮነትን ማልመድ ግድ ይለናል። ሌሎችን ባለማዳመጥ ዘመናትን የተሻገረውን ሰውነታችንን ማደስ ይኖርብናል። በራሱ ፍቅር የወደቀ እኛነታችንን ሌሎችን ማፍቀር እንዲለምድ በማድረግ ለውጣችንን እንጀምር።
ሆድ ከአገር ይሰፋል፤ አዎ ለተጠቀመበት ሆድ ከአገር ሰፊ ነው። ብዙ ነገር ይተዋል፤ ብዙ ነገር ይችላል። ችግራችን የመቻል፣ የመሸነፍ ጥበብ የለንም። ችግራችን ሳንገዳደል፣ ሳንወቃቀስ መዋደድ እንዳለብን አለማወቃችን ነው። አሸንፈን የበላይ ለመሆን ስለምንሞክር በመግባባት ውስጥ ያለውን የሰላም ስፍራ አልደረስንበትም። አያቴ በሕይወቷ ውስጥ ምንም ነገር ይከሰት በመተው የምትጽናና ሴት ነበረች። በመተው ማሸነፍ ደስታው ምን ያክል ይሆን? በመርሳት ከፍ ማለት ሰላሙ እስከ የት ይሆን? የዚህ ጥያቄ መልስ እያንዳንዳችን ውስጥ አለ፤ ነገር ግን አናውቀውም። ድረሱበት ስልም አደራ እላችኋለሁ። ለምንድነው በመነጋገር መግባባት ያቃተን? ለምንድነው መታረቅ ያቃተን? ለምንድነው መተቃቀፍ ያቃተን? ከፍ ብዬ እንዳልኳችሁ እኚህ ጥያቄዎች በድሀ አገር ላይ ብዙ መልሶች አሏቸው።
እኛ አገር አብዛኞቹ ችግሮች ትላንት ወለድ ናቸው። በታሪክ የምንጣላ ብዙዎች ነን። ባልኖርንበትና በማናውቀው ትላንትና ውስጥ ገብተን በሰማንውና ባደመጥነው በጥቂት ግለሰቦች የውሸት ትርክት አይጥና ድመት የሆንን ብዙ ነን። ሰው እንዴት በማያውቀው ትላንት ይጣላል? የሆነው ሆኖ ላጣሉንም..እያጣሉን ላሉ ነገሮችም በመነጋገር ሰላም እናውርድ። ከሌላው ጋር ለመግባባት መጀመሪያ ከራሳችን ጋር መግባባት ይኖርብናል። ከራሱ ጋር የተግባባ ከሌላው ጋር ለመግባባት አይቸግረውም። የብዙዎቻችን ችግር ከራሳችን ጋር ሳንግባባ ከሌሎች ጋር ለመግባባት በጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጣችን ነው። ከፈረሱ ጋሪው እየቀደመ ለዘመናት በከሰረ ፖለቲካ ውስጥ ነበርን። የከሰረ ፖለቲካ የከሰረ አገርና ትውልድ ከመፍጠር ባለፈ ጥቅም እንደሌለው ብዙ ቦታ አይተናል። መጀመሪያ ከራሳችን ጋር እንስማማ። መጀመሪያ የሀሳባችንን ፍሬ እንመዝን፣ መጀመሪያ አገርና ሕዝብ ይቅደሙ፤ ያኔ ሁሉም መልካም ይሆናል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 /2014