የኢትዮጵያዊነት ትርጉም ፍቺ ቅኔና ወርቁ ረቂቅ ነው። ኢትዮጵያውያንም አገራቸውን የሚወዱ፣ አገራቸው ተሻሽላና አድጋ ማየት የሚፈልጉ፣ ይህንንም ከልብ የሚመኙና ለዚያም የሚታገሉ ናቸው። ይህ ማለት ግን በዘርና በጎሳ ልክፍት የተለከፉ ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ ኢትዮጵያዊነት አቋም ያላቸው የሉም ማለት አይደለም፤ እንዳሉ አይካድም።
ይሁንና ‹‹ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያዊነቱን አይተውም እንደሚባለው›› እውነተኛ ኢትዮጵያውያንም መቼም ቢሆን ለአገራቸው ያላቸው ፍቅርና አክብሮት የሚለወጥ አይደለም። እድገቷን እንጂ ዝቅታዋን፣ ደስታዋን እንጂ ኀዘኗን፣ ክብራን እንጂ ውርደቷን ፈጽሞ የሚመኙም አይደሉም።
ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ያላቸው ፍቅር በቃላት ብቻ የማይገለጽ ስለመሆኑ የቀደሙ ታሪኮችም ሆኑ የእስካሁን ክንዋኔዎች ምስክር ናቸው። ኢትዮጵያውያንም የአገራችን ጉዳይ ሲነሣ ደመ ቁጡዎች፣ አትንኩን ባዮችና ኮስታሮች መሆናቸው የአደባባይ ሃቅ ነው።
አገሩ ሲደፈር ‹‹እንዴት ተደርጎ›› የማይል ኢትዮጵያዊ ይኖራል ተብሎም ፈጽሞ አይታሰብም። ኢትዮጵያውያንም አገራቸውን የነኩባቸው እለት ትንታግና አይነኬ አራስ ነብር እንደሚመስሉ፣ በአገራቸው ለመጣ ሞትን እንደ ሰርግ እንደሚቆጥሩም የሩቅ ሳይሆን የቅርብ ሁነቶች በቂ ምስክር ናቸው።
በየዘመናቱ የተነሱ ጠላቶቿን በሕዝቦቿ አንድነትና የጋራ ክንድ እያሳፈረች ዘመናትን የተሻገረችውና ለጥቁሮች የነፃነት ምልክት የሆነችው ኢትዮጵያም እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ቢሆን ግን ጠላቶቿ አላንቀላፉም። በውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ጠላቶቿ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊና መስተጋብሯን ለማናጋት ረጃጅም እጆቻቸውን ዘርግተውባታል።
አንዳንዶቹም ሉዓላዊነቷን በመዳፈር ነፍስ እንዳላወቀ ሕፃን ልጅ በሞግዚት አስተዳደር የማስተዳደርና የመጠበቅ ህልማቸውን ለማሳካት ማእቀብ ከማወጅ፣ ረቂቅ ሕግ ከመቀመር አንስቶ በየጊዜው ሴራቸውን እየቀያየሩ መከሰት ተይይዘውታል።
እንደ ትናንቱ ሁሉ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፈተና እንዲቀል የሁላችንም አበርክቶ የግድ ይላል። ወቅቱም የኢትዮጵያን ችግሮች የመሸሽ ሳይሆን የማሸሽ ተጋድሎን ይጠይቃል። ኢትዮጵያም በአገራዊ የአንድነት አስተሳስብና የፍቅር ውል ኪዳን የተሳሰሩና የታነጹ ልጆቿን ከመቼውም ጊዜ በላይ ትሻለች።፡
በእርግጥ ‹‹ማን ነው ኢትዮጵያን አገሩን የሚወድ? እጁን ያውጣ›› ቢባል ሁሉም እጁን ያወጣል። ‹‹ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን የሚፈልግስ?›› ተብሎ ቢጠየቅ፤ አሁንም ሁሉም የአገሩን ሰላም እንደሚፈልግ ይናገራል። አበው ‹‹ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” ይሉናል። ይህንን የሚሉን ‹‹ቃል›› ምን ያህል ከባድ እንደሆነና፤ ከወለዱትም ልጅ በላይ ሊጠብቁት የሚገባ መሆኑን ሲያስገነዝቡን ነው።
‹‹አገሬን እወዳለሁ›› ስንል ግን የእለት ተእለት ተግባራችንም ይህንኑ ቃላችን የሚያስታውስና የሚያስመ ሰክር ሊሆን ይገባዋል። አገሩን የሚወድ በአገሩ ጉዳይ ዳር ተመልካች አይሆንም። አገሩን የሚወድ የአገሩን ጥቅም ያስከብራል፡፡
አገሩን የሚወድ ለአገሩ ዘብ ይቆማል። አገሩን የሚወድ ፍላጎቱን ከአገሩ ፍላጎት አያስበልጥም። በአጠቃላይ አገሩን የሚወድ ማንኛውም ዜጋ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ መስጠት ያለበት ለአገሩ ህልውና መሆኑ የሚያከርክር አይደለም።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት በመቆም ሰንደቋን ከፍ አድርገው ወደ ታላቅነት ክብሯ የሚመልሱ አገር ወዳድ ልጆች ያስፈልጋታል። የጠላቶቿን ዓላማ ለማምከን ጀርባቸውን ሳይሆን ግንባራቸውን የሚሰጡ ልጆችን ትሻለች።
አሁን ላይ እናት አገር ኢትዮጵያ እየተጣራች ነው። እድገቷም ውድቀቷም በእኛ በልጆቿ እጅ ላይ ነውና አቤት አለሁልሽ እንበላት። ለኢትዮጵያ ያለናት እኛው ነን። ለእኛም ያለችን እሷ ናት። ስንኖርላት ታኖረናለች። ስንዋደቅላት ታቆመናለች። ስንበረታላት ትበረታለች። ትጠነክራለች።
አሁን ላይ እናት አገር ኢትዮጵያ እየተጣራች ነው። ነገዋን ማሳመር የምንችለው ልጆቿ ብቻ ነንና አቤት እንበላት። ምሬቷን በሀሴት እንቀይርላት። መከፋቷን በደስታ እንለውጥላት። ዝቅታዋን ለሚመኙ ከፍታዋን እናሳይላት። ወዛን ከሚነጥቁ ውበቷንም ከሚሰርቁ እንታደጋት።
ኢትዮጵያ አይናችን ናት። አይናችንን አናስደፍር። በአይን አይቀለድም። ኢትዮጵያ የምትፈልገን ትክክለኛ ጊዜ ላይ ነን። አስተማማኝ ምርኩዝ እንሁናት። ኢትዮጵያ ካለ እኔና እናንተ አትበረታም። በነጻነት መቆም ከፈለግን በያለንበት ኢትዮጵያን አንጣላት። በኢትዮጵያ ለመጣ ምንም ነገር ወደ ኋላ አንበል። በክብሯ ሲመጡ በስብዕናችን እንደመጡ እናስብ። እርሷን የነካ አይናችንን እንደነካ እንወቅ።
ኢትዮጵያ ወድቃ እኛ እንደማንቆም፣ እኛ የምንከበረው በእሷ ተከብሮ መቆየት ውስጥ መሆኑን፣ እሷ ጎድሎባት እኛ እንደማይሞላልን፣ እሷ ዝቅ ብላ እኛ እንደማንገዝፍ፣ እሷ እያዘነች እኛ እንደማንደሰት፣ እሷን ረስተን እኛ እንደማንታወስ፣ ጠንቅቀን መገንዘብ ይኖርብናል።
ዛሬ ላይ የደረሰነው በአገራችን አትምጡብን ብለን በአንድነት በተፋለምነው እልህ አስጨራሽ ትግል ውጤት ነው። ትናንት ግን ዛሬ አይደለም። ወቅቱም በትናንት ተጋድሎ ተኩራርተን ሩጫችንን የምንገታበት አይደለም። ይልቁንስ የቅብብሎሽ ሩጫችንን ለማፍጠን ተጨማሪ ጥረት ግድ የሚልበት ነው። እዚህ ላይ ሩጫን ማቋረጥ ለተሸናፊነት ይዳርጋል።
እናም ትንሽዋ ተግባር ወይም ትንሽዋ የእሳት ፍም እንኳ የራሷን ተጽእኖ ታሳርፋለችና በጀመረነው ትንፋሽ የማይሰጥ ሩጫ ሌሎችን በረጅም ርቀት ለመቅደም ፈጣን የአሯሯጥ ማስተካከያ ማድረግ ይኖርብናል። በዚህ አገርን የመጠበቅ ተጋድሎም ‹‹ከእኔ የሚጠይቀውን ሁሉ ለማድረግ እጓጓለሁ፤ ዝግጁም ነኝ» የሚል ዜጋ የግድ ይላል።
ከፍታችንን ለማዝለቅ የነበርንበትን የኋሊት እያስታወስን፣ ከምናደንቀው ተምረን የቆሞ ቀርነት ታሪካችንንም አውግዘን በሌላ አነጋገር ከስኬታችንም ከጉድለታችንም እውቀት ቀስመን ወደፊት መሮጥ ይኖርብናል። ይህን ፍልሚያ አሸንፎ መውጣት ካለብን ጅማሪያችን እንዲህ ካሉ ተግባራት መሆን ይገባዋል። የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ መገንባት የምንችለው ይህም ሲሆን ነው ።
ከፊታችን እጅግ ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል። ዛሬ ላይ በጋራ የፈነጠቀናትን የእድገት ጭላንጭል ወደ ተንቆጠቆጠ ደመራ ለማሸጋገር እልህ አስጨራሽ ትግሉ ከፊታችን ተደቅኗል። ፍልሚያ በድል መወጣት ካለብን ደግሞ ቆሞ ቀርነት ማስወግድ የግድ ይላል።
ዓለም ላይ ጣፋጩን ስኬት የሚያጣጥሙም የሚጀምሩ ሳይሆኑ የሚጨርሱ ናቸው። መጀመርም ይልቅ መጨረስ ትጋት ይጠይቃል። በመጀመራችን ብቻ ሳይሆን ስለመጨረሳችንም እርግጠኞች ልንሆን ይገባል። ኢትዮጵያን የማስከበሩ ተጋድሎ በፍፃሜ እንጂ በጅማሬ ብቻ አይመጣም።
ፈለግንም አልፈለግን በወቅታዊው ፈተና መፈተናችን አይቀርም። ይሁንና ቆሞ ከመሞት እየዳሁ መኖር ያዋጣል። እናም በምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም የሚበጀንን በውል እየለየን የጀመርነውን የህልውና ጉዞ መቀጠል ይኖርብናል።
ፈተናዎቻችን የጥንካሬአችን ማሳያ ማድረግ ይኖርብናል። ከፈተናችን መጠንከር ይልቅ የእምነታችን መላላት በቁም ይጨርሰናል። ማመን ያለብን አንድ እውነት ቢኖር የጠላት ክንድ መቼም አያሸንፈንም። ብንወድቅም እየተነሳን ብንሞትም እየተተካካን አገራችንን ማስቀጠል የግድ ይለናል።
በተራመድን ቁጥር የአገራችን ክብር የምናስቀጥል በመሆኑ በፍፁም ለሚያቆሙን መቆም የለብንም። መንቀሳቀስ ለምንፈልገው ነገር ቅርብ ያደርገናልና ተራምደን ለመድረስ እንጂ ቆመን ለማልቀስ እጅ አንስጥ። በማይቆም ጥረት ውስጥ ስንኖር ደግሞ ለማይቀር ድል እንታጫለን።
‹‹What Goes Around Comes Around›› እንደሚባለው፣ የምናጭደውም ከዘራነው ውጪ አይሆንም። ሽንፈታችን የሚፀናው ፍልሚያ ለማቆም ስንቆም ነው። ድላችን ሁሉ ትግላችንን መሰረት ያደርጋል። ስኬታችንም የጽናታችን ውጤት ነው።
ለብሔራዊ ጥቅም መከበር በተለይም በ no more ም ሆነ ኤች አር 6600 እንዲሁም ኤስ 3199 የተሰኙ ረቂቅ ሕጎችን እንዳይፀድቁ ለማድረግ ያስመለከትነውና እያስመለከትን የምንገኘውን ተጋድሎ በማስቀጠል ነገ ቀና ብለን ለመኖር ዛሬ ላይ ኢትዮጵያን ከሚያስጎነብሷት እንጠብቃት። ይህን ስናደርግ ኢትዮጵያን የተበተቡ ሰንሰለቶች ይበጣጠሳሉ። የተቆለለባት የሴራ ተራራ ይናዳል። የጨለማውን ዘመን አልፋ ብርሃን በአናት አገራቸው ጸዳል ላይ ያበራል።
በጽናታችን ከጸናን ውጤት አይርቀንም። በየሚሆነው ሁሉ ያንገዳግደን ይሆን እንጂ አይጥለንም። ባለመሰልቸት ከታገልን የፈለግነውን ከማግኘት የሚያቆመን ሃይል አይኖርም። አገራችን ኢትዮጵያን አቤት እንበላት። አቤት አለሁልሽ ሰንላት ጠላቶቿን ሁሉ ታሸንፋለች። ዳግምም ታብባለች።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 /2014