የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮዎች ውሻን በሚያሳብድ በሽታ እየሞቱ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
ብርቅዬ እንስሳቱን ውሻን ከሚያሳብድ በሽታ ለመከላከል ክትባት እየተሰጠ መሆኑን ደግሞ የአማራ ክልል አካባቢ ደን እና የዱር እንሰሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ከሚገኙ ብርቅየ የዱር እንስሳት መካከል የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮዎች ይጠቀሳሉ፡፡
የኢትዮጵ ቀይ ቀበሮዎች በአማራ ክልል በሚገኙ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ፣በቦረና ሳይንት ‹‹ወረ ሂመኑ ብሄራዊ ፓርክ››፣በመንዝ ጓሳ እና በአቡነ ዮሴፍ የማህበረሰብ ጥብቅ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ በደላንታ ዳውንት አንዳንድ አካባቢዎችም አልፎ አልፎ እንደሚገኙ ከአማራ ክልል አካባቢ ደን እና የዱር እንሰሳት ጥበቃ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
በባለሥልጣኑ የዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለስልጣን አቶ አብርሃም ማርየ እንደተናገሩት በነዚህ አካባቢዎች ከ2 መቶ በላይ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ የቀይ ቀበሮ ዝርያዎች አሉ፡፡
እንደ ባለስልጣኑ ገለፃ ብርቅየ የዱር እንስሳቱን ውሻን ከሚያሳብድ በሽታ ለመከላከል የሚያስችል ክትባት እየተሰጠ ነው፡፡
ሰዎች የዕርሻና የግጦሽ ቦታወችን ለማስፋት በጥብቅ ቦታወች እና በፓርኮች ዙሪያ በሚያደርጉት ጣልቃ ገብነቶች የዱር አራዊቱ የመኖርያ ቦታ ስጋት ላይ ከመውደቁ ባሻገር ቀይ ቀበሮዎቹ በበሽታው እየተለከፉ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ባሳለፍነው ጥቅምት ወር በአቡነ ዮሴፍ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ በሽታው የሞቱ የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮዎች መገኘታቸውም ተገልጧል፡፡ የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስም ባለሥልጣኑ የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ ፕሮጀክት ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር በሁሉም የቀይ ቀበሮ መገኛ ቦታዎች ክትባት እየሰጠ ነው፡፡
አብዛኛዎቹ ቀይ ቀበሮዎች ክትባቱን እንዲያገኙ ለማድረግ ውሻን በሚያሳብድ በሽታ መድሃኒት የበለፀገ ስጋ በማቅረብ እንዲመገቡ የማድረግ ስራ የክትባቱ አንድ አካል ነው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በመንዝ ጓሳ ማህበረሰብ ጥብቅ ደን አራት የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮዎች ሞተው ተገኝተዋል፡፡ ለህልፈት የዳረጋቸው ናሙና ወደ እንግሊዝ ተልኮ ‹‹ካናዲስ ዲስትምፕተር ››የተባለ በሽታ መሆኑ መረጋገጡን አቶ አብርሃም አስረድተዋል፡፡
አብመድ እንደዘገበው ክትባቱ እስከያዝነው ህዳር ወር መጨረሻ ይቆያል፡፡