ሁሌም በማለዳ የሰፈራችን ሰዎች የሚቀሰቅሰው ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ነው። በጠዋቱ ተነስቶ ይጮሃል። በጠዋቱ የጀመረውን ጩኸቱን የሚያቆመው ሲተኛ ብቻ ነው ። ከጩኸቱ ብዛት ልቡ ፈንድቶ አለመሞቱ እያለ ሁሉም የሰፋራችን ሰው በሃዘን ከንፈሩን ይመጣል። ደረቱንም ይደቃል።
ትንሽ የታሪክ እና ፖለቲካ ቀለም የነካው ሰው ይልቃል አዲሴ የሚናገረውን ንግግር የወፈፌ ንግግር ነው ብሎ አያልፈውም። ሐረግ በሐረግ እየተነተነ ይመለከተዋል እንጂ። የሰፈራችን መሪዎች እና ተፎካካሪ ቡድኖች የይልቃል አዲሴን ነቆራ ስለሚጠሉ ይልቃል አዲሴን በፊታቸው ካዩ እንዳይሰድባቸው በማሰብ ፊታቸውን አዙረው መሄድን ይመርጣሉ።
አንድ ቀን የእድራችን መሪ የሆነውን አቶ መሐመድ ይልማ የሰፈራችን ሰላም እና እድገት በማስመልከት እንዲሁም የእድራችንን ወርሃዊ ስብሰባ ለማካሄድ በማሰብ ከገበያው መካከል ባለው ትልቅ ዋርካ ስር ሕዝቡን ሰበሰበ። ተሰብሳቢዎችም ከዋርካው ስር ለዘመናት ከማይጠፉት ድንጋዮች ላይ አቧራቸውን በቅጠል እያራገፉ ተቀመጡ። በዚህ ጊዜ ስብሰባውን ለመታደም ማን ቢመጣ ጥሩ ነው ፤ ይልቃል አዲሴ !። ይልቃል አዲሴ መሐመድ ይልማን ፊት ለፊት አገኘው። መሐመድ ይልማ የእድሩን ወርሃዊ ስብሰባ አቋርጦ አይሄድ ነገር ችግር ነው። የይልቃል አዲሴን ስድብ እና ነቆራ እያዳመጠ አይቀመጥ ነገር ችግር ነው። ሕዝብን ሰብስቦ ምንም ሳይሉ መበተን ችግር ስለሆነበት እየተሸማቀቀም ቢሆን ስብሰባውን አስጀመረ። የፈሩት ይደርሳል፤ የጠሉት ይወርሳል ማለት ይሄ አይደል።
እንደተለመደው አቶ መሐመድ የእኛን ሰፈር ሰው የሚደልልባቸውን ቃላት ተጠቅሞ ጎሳችን በቋንቋው እንዲማር፣ እንዲዳኝ ብሎ ሲጀምር ይልቃል አዲሴ በጩኸት ንግግሩን አቋረጠው። ሁሉም የእድሩ አባላት ፊታቸውን ወደ ይልቃል አዲሴ አዞሩ። ይልቃል ንግግሩን እንዲህ ብሎ ጀመረ፤ ብልህን ሰው ለማሞኘት መሞከር ትርፉ ትዝብት ነው። ዛሬም እንደዚህ ቀደሙ ጉራህን ቸርችረህ ልትሄድ ነው። አልፈቅድልህም ! ጉራውን ተወውና የእድሩ እና የሰፈራችን ሰው ምንድን ነው የሚፈልገው ብለህ ጠይቅ ። መጀመሪያ አንተ እና ጓደኞችህ ሕዝቡን ተረዱት። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሕዝብ የተቸገረው በልቶ ማደር ነው። ብሄር፣ ጎሳ ወዘተ ምናምን አያስፈልገውም። ከምግብ እና ከምግብ ውጭ ሌላ ምንም አትበሉን። በልተን ስለምናድርበት ስልት እና ብልሃት ብቻ አቅጣጫ ጠቁሙን። በረሃብ ልናልቅ ነው !
ወገቡን እከክ እያደረገ ይልቃል ንግግሩን ቀጠለ፤ ከመቶ አመታት ወዲህ ሰፈራችንን ባስተዳደሩ አባቶቻችን የተጀመረ እና አሁን ላይ ያሉ የእኛ ሰፈር መሪዎች እንደጥሩ ነገር ተቀብለው የሚያስሄዱት አንድ ነገር አለ። ይህም ምንድን ነው፤ ሰፈራችን ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሰፈራችን ባህል፣ ወግ፣ ሃይማኖት፣ አስተሳሰብ፣ ስነ ልቦና ወዘተ በመነሳት ፖሊሲዎችን እና እስትራቴጂዎችን ከመቅረጽ ይልቅ በባህል፣ ወግ፣ ሃይማኖት፣ አስተሳሰብ፣ ስነ ልቦና ወዘተ ምንም የማንመሳሰላቸው የአውሮፓ እና የኤዥያ አገራትን የፖለቲካ ፍልስፍናን መስመር በመስመር በመኮረጅ ወይም ቀድቶ በማምጣት ለአገራችን ህግ ማድረግ ይቀናቸዋል ። ለምሳሌ የ1923ቱ ህገ መንግስት ከጃፓን የተቀዳ እንደሆነ ይታወቃል። የ1960ዎቹ ተማሪዎቹ የትግል መርህ እና ስትራቴጂዎች የተቀዱት የኮሚኒስት ፍልስፍና መነሻ ማህጸን ከሆነችው ራሺያ ነው።
የ1960ዎቹ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ወግ ጠራቂዎች አንዳቸውም የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግር መነሻ ምንድን ነው? የሚለውን አልተረዱም። ፋብሪካ የሌላትን አገር በምናባቸው ከበለጸጉ አገራት ጋር በማስተካከል «ላባደር እና ወዛደር» የሚሉ ቃላትን በመተንተን ወግ ይጠርቁ ነበር። አሰሪ እና ሰራተኛ በሌላባት አገር ለወዛደር እና ለላባደር መብት እንታገላለን አሉን። በሌለ ነገር እየተነታረኩ ጊዜአቸውን ማባከናቸው አልቆጭ ብሎአቸው እርስ በርስ በመገዳደል የአገሪቱን የሰው ኃይል እና ንብረት ማጥፋት ስራዬ ብለው ተያያዙት። ይሄም እስካሁን አገሪቱ ለገባችበት ምስቅልቅል ዋናው ምክንያት ሆኖ እናገኘዋለን።
በንጉሱ ዘመንም ሆነ እስከዛሬ ድረስ በአገሪቱ በሚገኙ ቢሮዎች አርሶ አደሮች ተቀጥረው ሲሰሩ ታይቶም፤ ተሰምቶም አይታወቅም። በንጉሱ እና በደርግ ዘመን እንኳን አርሶ አደር የሚሰራበት ቢሮ ሊኖረን ይቅርና የተማሩት አካላት እንኳን የሚሰሩባቸው ቢሮዎች ባለመኖራቸው የዳኝነት ስነ ስርዓት እንኳን የሚካሄደው በዛፍ ጥላ ነበር። እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የ1960ዎቹ ትውልድ ከምዕራባዊያን የሰሙትን ቋንቋ በቀጥታ ገልብጠው ወደ አገራችን በማምጣት ስሙን የማይጽፍን አርሶ አደር በቢሮ እንደሚሰራ አድርጎ ለራሳቸው በመንገር ለአርሶ አደሩ ቢሮክራሲ የሚል ታርጋ ለጠፉለት። በቢሮክራሲ ስምም መሬቱን ነጠቁ። ከእርስቱም አፈናቀሉት። የማይችሉትን ፖለቲካ እያነኮሩ የጭቁኑን የአርሶ አደር ልጆችን ሜዳ ላይ በተኑ።
በአገራችን የፖለቲካ ማሳ ውስጥ የበቀሉ አረሞዎች ከምዕራባዊያን ቃላትን እየተዋሱ አገርን የማተራመስ ዛራቸው አርጅቶ ከመቃብር አፍፍ ላይ ሲደርስ ተመልከተን እፎይ ልንል ነው ብለን ስናሰብ አሁን ላይ ደግሞ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠል በሚል ሌላ አጀንዳ በማምጣት ለሺህ ዘመናት አብሮ እና ተካበብሮ የኖረን ሕዝብ ለማባላት ላይ ታች ሲኳትኑ እያየን ነው። ከእነኚህም መካከል አንዱ አቶ መሐመድ ይልማ ነው።
የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የብሔር ፖለቲካ አራማጆችም እንደ ላባደሩ እና ወዛደሩ እንዲሁም ቢሮክራሲ የሚባሉት የፖለቲካ ፋሽኖች መጥፋታቸው የማይቀር ነው። እነኚህ ፖለቲከኞች መርከብ ውስጥ የተደበቁ አይጦች አይነት ናቸው። መርከብ ውስጥ ተደብቀው የሚራቡ አይጦች መርከቡ በሰመጠ ጊዜ መውጣታቸው የማይቀር ነው።
ይልቃል ንግሩን ቀጠለ፤ ኢትዮጵያ የቃል ኪዳን ምድር መሆኗን የዘነጉ በብሔር ስም እየነገዱ ኢትዮጵያን በብሔር ስም ሊበታትኗት የሚራኮቱ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ወግ ጠራቂዎች ስመለከት፤ ሰማይ እንደሚታየው ቅርብ መስሎአቸው ሊመቱት ድንጋይ ሽቅብ እንደሚወረውሩ ህጻናት ይመስሉኛል። መቼም የማይሆን ምኞት!
በእርግጥ የዘውግ ፖለቲካ ፍቅርም፣ ሃይማኖትም ምንም አያውቅም። ሰዎችን ከሰውነት አውጥቶ እብድ የሚያደርግ እና አንዱን ከአንዱ በጥርጣሬ አስተያየት የሚያባላ በውስጡ አጋንቶች የሰፈሩበት የፖለቲካ መቆመሪያ ማሽን ነው። ይሁን እንጂ የቃል ኪዳኗን ምድር ኢትዮጵያን በብሔር ግጭት ለማጥፋት መሞከር ከቤርሙዳ ትርያንግል የገባችን መርከብ ለማውጣት እንደመሞከር ነው።
በዚህ ወቅት ሁሉም በዋርካው ስር የተገኘው ተሰብሳቢ ለወፈፌው ይልቃል አዲሴ አጨበጨበ። አቶ ሙሐመድ በጭንቀት አይኑ ፈጠጠ። «ሕዝብን በተፈጥሮው ተለዋዋጭ ነው ፤ ሕዝብን ለማሳመን ቀላል ቢሆንም በእምነቱ ማግኘት ግን በእጅጉ አዳጋች ነው።» የሚለውን የኒኮሎ ማኪያቬሊን ፍልስፍና አስታወሰ። በሕዝቡ የነበረውን ተቀባይነት ያጣው አቶ መሐመድ ይልቃል አዲሴን በጠባቂዎቹ ተደብድቦ እንዲባረር አዘዘ። ሕዝቡም እሱን የምትደበድቡት እኛን ጨርሳችሁ ነው ብሎ በአንድ ላይ ተነሳ። በዚህ ጊዜ አቶ መሐመድ ሕዝቡን መልሰው ማታለል ያዙ።
ሕዝቡም ይልቃል አዲሴ ንግግሩን ካላስጨረሳችሁት እኛ የእናንትን ዲስኩር ተቀምጠን አናደምጥም አለ። አቶ መሐመድም እየጨነቃቸውም ቢሆን ወፈፌው ይልቃልን እንዲናገር ፈቀዱ።
ይልቃል አዲሴ ሕዝቡ ያስገኘለትን እድል ለመጠቀም ጉሮሮውን ጠረግ ጠረግ እያደረገ ንግግሩን ቀጠለ። እንድናገር ሕዝብ ከፈቀደለኝ የእኛ ሰፈር ገዥዎች ሁለንተናዊ ባህሪ ከኒኮሎ ማኪያቬሊን አስተሳስብ ጋር እያገናኘሁ አብራራለሁ አለ። ከኒኮሎ ማኪያቬሊን ፍልስፍናዎች አንደኛው እና ብቸኛው የወደድኩለት «ገዥዎች አገዛዛቸውን መመስረት ያለባቸው በረቂቅ አይነት አሰራር ሳይሆን ታሪካዊ ሃቅን በመመርመር ነው ! » የሚለውን ነው። ስለእውነት ይህን የኒኮሎ ማኪያቬሊን ፍልስፍና የሚያዳምጥ አንድ ሰው ቢኖር ኖሮ የእኛ ሰፈር ከብሔር እና ከጎሳ ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ችግሮች አይኖሩም ነበር።
ይሁን እንጂ መሪውም፣ ተመሪውም እንዲሁም ተፎካካሪ ፓርቲዎችም እውነተኛውን የአገራቸውን ታሪክ ከመመርመር ይልቅ ሴራን እንደ ብልሃት ስለሚቆጥሩት በሚፈጠሩት ሴራ ረሃባችንን በአግባቡ እንዳናስበው እያደረጉን ነው። ይህ የማኪያቬሊን አስተሳሰብ ስለእውነት ሁሉም ወግ ጠራቂ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ በትክክል ተገንዝቦ የፖለቲካው መርህ ሊያደርገው ይገባል።
ነገር ግን መሪዎቻችን እና የማህበረሰብ አንቂዎቻችን እንደለጋስነት ራስን የሚጎዳ ነገር የሚለውን የማኪያቪሊን አስተሳሰብ ሳያላምጡ ጨልጠው የዋጡ ይመስለኛል። ይህን ስል በአመክንዮ እንጂ በግብዝነት አይደለም። ለምሳሌ አቶ ካሳሁን ጎይቶም የተባለው ሰው በተፈናቃይ አርሶ አደርነት ስም የሰፈራችንን መውጫ መግቢያ ግጥም አድርጎ እንዲያጥር ያደረጉት መሪዎቻችን እና ተፎካካሪዎቻቸው ናቸው። ምክንያቱም ተፈናቃይ የተባለው አርሶ አደር በስሙ ከወሰደው ግማሹን መሬት በጉቦ መልኩ ለእነሱ ስለሚሰጣቸው ነው።
ሌላው የእኛ ፖለቲከኞች የእውነት የማኪያቬሊን ተከታዮች ስለመሆናችሁ ማሳያው ደግሞ አሁን ላይ በእኛ ሰፈር ባለፋብሪካዎች ባለሰልጣናት እና ተፎካካሪዎች ናቸው። አስመጭ እና ላኪዎችም እነሱ ናቸው። እነኚህ አካላት ከራሳቸው ትርፍ ውጭ ሌላው ረሃብ ቅንጣት ያህል አያስጨንቃቸውም። የሰረቁት እንዳይታወቅባቸው ለመጡበት ጎሳ ተቆርቋሪ በመመሰል የጎሳ ግጭት ፈጥረው ድሃውን ያጫርሳሉ። ሌብነታቸውንም በጎሳዎች እልቂት ይደብቃሉ።
ባለስልጣናት አምባገነን ህሊናቸው የጎደፈ ከሆነ ለወንጀለኛ ጠበቃ እንደሚሆኑ እና ህሊናቸው ንጹህ ከሆነ ደግሞ ለወንጀሎች ቀጭ እንደሚሆኑ ይታወቃል። አሁን ላይ በእኛ ሰፈር ግን ማን አምባገነን ማን ንጹህ እንደሆነ መለየት አቅቶናል። ማን በማን እንደሚጠየቅ ግራው ግብቶናል! ከዚህ በፊት ገዥ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎችን አንዱ የአንዱን ችግር እየነቀሱ ያሳዩን ነበር። አሁን ግን የአንዳቸውን ወንጀል አንዳቸው ማጋለጥ ሲገባቸው አንዳቸው የአንዳቸውን ችግር ሲሸፋፈኑ ስንመለከት ባለትዳር ውሽማማቾችን ያስታውሱን ይዘዋል እያለ እየተናገረ እያለ በትምህርቱ ጎበዝ እንዲሆን አብሾ የተሰጠው ቀዥቃዣው ማስረሻ ዲባባ ማንም ሳይፈቅድለት ከተሰብሳቢዎች መካከል በመነሳት ለይልቃል አጨበጨበ። የራሱንም ንግግር ጀመረ።
ማስረሻ ዲባባ እንዲህ ሲል ጀመረ ፤ ኢትዮጵያን እናጥፋት በማለት ለሚታወቀው የኦስትሪያው ዲፕሎማት የሮማን ፕሮቻስኪ ሌጋሲ አስቀጣይ፤ ባልተጠራችሁበት አቤት ባይ ገዳይ አስገዳይ ጎሰኞች እኛን የቸገረን ነገር በልቶ ማደር ነው። ስለእውነት ለእኛ የምታስቡ ከሆነ እንዴት በልተን እንደምናድር በር ዘግታችሁ በደንብ ተወያዩ። ስትፈልጉም ተደባደቡ። ነገር ግን ለራሳችን በራሳችን ለችግራችን መፍትሄ ለማፈላለግ የምናደርገውን እሩጫ እናንተ በምትፈጥሩት የጎሳ ግጭት አታጨናግፉቡን ሲል በንዴት ጦፎ ተናገረ።
ሃጢያትና ትዕቢት ለእውር ህሊና ለመጀመሪያ ጊዜ ጣፋጭ ናቸው። ቆይተው ግን የሚያስከትሉት ጦስ ከኮሶም የሚመር ነው። አሁን ላይ በብሔር ስም ለመነገድ የምትሞክሩ በአገራችን የፖለቲካ ማሳ ውስጥ የበቀላችሁ እንክርደዶች፤ ዛሬ ላይ ራሳችሁን ስንዴ ስላስመሰላችሁ እንክርዳድነታችሁ ተደብቆ ይቀራል ማለት አይደለም። እንክርዳድ መሆናችሁ ሲታወቅ ሁሉም ይደፋችኋል።
ማስረሻ ንግግሩን ቀጥሎ መልካም ሰው ቢሞትም ቢኖርም ሊደርስበት የሚችል ጉዳት የለም። ጥሩ ነገር ለመስራት ሞክሩ። ጥሩ የሰራ በምድርም በሕዝብም ይወደዳል። በሰማይም ከፈጣሪው ዛሬ ፈረሰብኝ ፤ ነገ ፈረሰብኝ ብሎ ከማይጨነቅበት ዘላለማዊ የሆነ ማንም የማይነጥቀው ጽዱ እና ጽኑ ካርታና ፕላን ያለው እንዲሁም ግንባታው ያለቀለት ቦታ ይሰጠዋል ብሎ ወደ መቀመጫው ሲመለስ ሕዝቡም በጭብጨባ ተቀበለው።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2014