ሰላም! ልጆች እንዴት ናችሁ? ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ልጆችዬ ዛሬ ታላቅ የአገር ባለውለታ ስለሆኑት ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ላስተዋውቃችሁ ነው። ልጆች! ስለ እኚህ ታላቅ ሰው ምን ታውቃላችሁ? ፀሀፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ መጋቢት 5 ቀን 1904 ዓ.ም የዛሬ 107 አመት የተወለዱ ታላቅ የሀገር ባለውለተኛ ናቸው። በአቤቶ ኢያሱ ዘመን ወደዚህ ምድር የመጡት አክሊሉ የሰገሌ ጦርነት ጊዜ የ5 አመት ልጅ ነበሩ። አቤቶ ኢያሱ በዘመናቸው 5ቱን ደንቦች ባሻሻሉበት ዓመት የተወለዱት አክሊሉ የአማርኛ ትምህርታቸውን በራጉኤል ቤተክርስቲያን አጠናቅቀዋል።
ልጆችዬ ! አክሊሉ ሀብተወልድ የተወለዱት ከአዲስ አበባ 35 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በቢሾፍቱ ወረዳ ‹‹ደንቢ›› በተባለች ቀበሌ ነበር። የአክሊሉ የትውልድ ቦታ አሁን ድረስ ‹‹ ደንቢ›› ቀበሌ በሚል ይታወቃል። አክሊሉ የልጅነት ጊዜያቸውን ማለትም እስከ 7 አመታቸው ድረስ በቡረቃ ያደጉት በደንቢ ሜዳ በመቦረቅ ነበር ፤ ይህን ሜዳ ዛሬም ሕጻናት ይቦርቁበታል። የአክሊሉና የወንድሞቻቸው ታላቅ ወንድም አቶ መኮንን ሀብተወልድ፣ ጥቅምት 19 ቀን 1911ዓ.ም የ25ኛ አመት የልደት በአላቸውን በሚያከብሩበት እለት የጉምሩክ ዋና መስሪያ ቤት የሂሳብ ሹም ተብለው ተሾሙ። ወላጅ አባታቸው አለቃ ሀብተወልድ በሞት ከተለዩ 8 ወራት ሆኖአቸው ነበር።
መኮንን አዲሱን ስራቸውን እንደተረከቡ በመጀመሪያ ያለአባት ብቻቸውን ለሆኑት ለታናናሽ ወንድሞቻቸው ተጨነቁ። እነዚህም የታላቅ እህታቸው የወይዘሮ ደብሪቱ ልጅ መክብብ ዳምጠውና፣ ወንድማቸው አካለወርቅ ሀብተወልድ የ9 አመት ልጆች ሲሆኑ ትንሹ ወንድማቸው አክሊሉ ገና የ6 አመት ልጅ ነበር። መኮንን እነዚህን ትንንሽ ልጆች፤ አዲስ አበባ አምጥተው ለማስተማር ያስባሉ። ትልቁ ፈተና የነበረው ሀይለኛዋ እናታቸው ወይዘሮ ያደግድጉ ፍልፍሉ የመኮንን ሀሳብ ይቀበላሉ ወይ የሚለው ነበር። ወይዘሮ ያደግድጉ፣ ባለቤታቸው አለቃ ሀብተወልድ ሀብቴነህ ከሞቱባቸው በኋላ ልጆቻቸው በድቁና እንዲያገለግሉ ይፈልጉ ነበር።
ስለሚፈልጉም የራሳቸውን እርምጃ ወስደው ነበር። መኮንን ሀብተወልድ ይህን አልሰሙም። አዲሱ ስራቸውን ከተረከቡ ከ2ወር በኋላም እናታቸውን ወይዘሮ ያደግድጉን ለገና በአል እንኩዋን አደረሰሽ ለማለት ታህሳስ 28 ቀን1911 ዓ.ም ደንቢ ደረሱ። ነገር ግን ትንንሽ ወንድሞቻቸውን ሳያገኙ ቀሩ። የት ሄዱ ብለው ቢጠይቁ መክብብ ፣ አካለወርቅ፣ እና አክሊሉ ወደ እንጦጦ ራጉኤል ተወስደው እየተማሩ ናቸው የሚል መልስ ተሰጣቸው። መኮንን ፣ ደነገጡ። እናት ያደግድጉ ፍልፍሉ ፣ ልጆቻቸው የቤተክርስቲያን ሰው እንዲሆኑ ይፈልጋሉ።
መኮንን ደግሞ ልጆቹ አዲስ አበባ መጥተው ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ ይመኛሉ። መኮንን እናታቸውን አሸንፈው ወንድሞቻቸውን መውሰድ እንዳልቻሉ አወቁ፤ ለዚህም መላ ያመጡ ዘንድ የእመት ያደግድጉ የንስሀ አባት መምሬ ገብረዮሀንስን አማላጅነት ጠየቁ፤ እናት በቀላሉ የሚረቱ አልነበሩም። በኋላ ቆየት ብለው ትንሹን አክሊሉን ከራጉኤል መውሰድ ትችላላችሁ ብለው ፈቃደኝነታቸውን አሳዩ። መክብብና አካለወርቅ ግን ትጋት ስለሚታይባቸው እዚያው ይቅሩ ሲሉ እናት አቋማቸውን ገለጹ። መኮንን ሀብተወልድ፣ የወይዘሮ ያደግድጉ ፍቃድ ከተገኘ በኋላ አክሊሉን ለማምጣት ጥር 11ቀን 1911ዓ.ም በጥምቀት በአል እንጦጦ ራጉኤል ሄዱ።
አክሊሉም ከወንድሞቼ ከመክብብና ከአካለወርቅ ተለይቼ ከአንተ ጋር አልሄድም አላቸው። መክብብና አካለወርቅም አክሊል ከእኛ አይርቅም አሉ። መኮንን ፈተና ውስጥ ገቡ። ‹‹…እምዬ ያደግድጉ፣ ለአሁኑ የፈቀዱልኝ አክሊልን ብቻ እንድወስድ ነው። ሌሎቻችሁን ከ2ወር በኋላ እወስዳለሁ›› እያሉ ለማባበል ቢሞክሩም ከሄድን በአንድነት ከቀረንም በአንድነት ብለው ሶስቱም በአንድ ድምጽ ተባበሩ። አቶ መኮንንም ሶስቱንም ትተዋቸው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ። ከዚህ በኋላ፣ በሀብተ ወልድ ልጆች ዘንድ የተፈጠረውን ክስተት አምባሳደር ዘውዴ ረታ የቃና ዘገሊላ በአል ተአምር ሲሉ ይጠሩታል። ወይዘሮ ያደግድጉ፣ የዛን ሰሞን አንድ ህልም ያልማሉ። መኮንን ሀብተ ወልድ በክብር ልብስ አሸብርቀዋል። በወርቀ ዘቦ የተለጠፈ ካባም ደርበዋል። ባርኔጣ አድርገው ሶስቱን ወንድሞቻቸውን አስከትለዋል። እናት አሁንም በህልም አለም ውስጥ ናቸው። መኮንን ወንድማቸውን አስከትለው ትልቁን ቤተ-መንግስት እየዞሩ መሬት እየለኩ ይሰጣሉ።እመት ያደግድጉ ይህን ካለሙ በኋላ ህልም ፈቺ አላስፈለጋቸውም። የልጆቹ እድል በመኮንን እጅ መሆኑን ፈጣሪ እንደነገራቸው አመኑ። መኮንን ሀብተ-ወልድ ይህን ከሰሙ በኋላ ከደስታቸው ብዛት እንቅልፍ አጥተው አደሩ። መክብብ ፣ አካለ ወርቅና አክሊሉ ከታላቅ ወንድማቸው ቤት ለማደግ ቅዳሜ ጥር 24 ቀን 1911ዓ.ም ከእንጦጦ ራጉኤል ተነስተው በበቅሎ አዲስ አበባ ደረሱ።
ሰኞ መስከረም 20 ቀን 1912 ዓ.ም ሶስቱ የሀብተወልድ ልጆች በዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ጀመሩ። እነ አክሊሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ፈጽመው ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ፈረንጅ ሀገር እስከተላኩበት ድረስ ወንድማቸው ቤት በኖሩበት በ8 አመታት ውስጥ ‹‹ ምክር መስጫ›› የተባለ ፕሮግራም ይዘጋጅላቸው ነበር። በዚህ ፕሮግራም ላይ መኮንን ፣ በእነ አክሊሉ አእምሮ ውስጥ የሀገር መውደድ ስሜትና ሀገርን ወደ ስልጣኔ የማራመድ አደራ እንዲሰርጽ ያደርጉ ነበር። አክሊሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በግብጽ ሀገር በሚገኘው የፈረንሳይ ሊሴ ትምህርት ቤት ከተማሩ በኋላ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ ፓሪስ ሄዱ። በፓሪስ ዝነኛ በሆነው የሶርቦን ዩኒቨርሲቲ በህግ በኤል ኤል ቢ ተመረቁ።
አክሊሉ ሀብተወልድ ትምህርታቸውን ከተማሩ በኋላም ለሀገራቸው ብዙ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ጸሀፌ ትእዛዝ አክሊሉ፣ በባልደረቦቻቸው ሁልጊዜም ይመሰገናሉ። ሀገራቸው በታላቅ የእድገት ጎዳና ላይ ተራምዳ ማየትን ይናፍቃሉ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲመሰረት ያደረጉት ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ጸሀፌ- ትእዛዝ አክሊሉ ለ60 አመታት ያህል በኢጣሊያ ቅኝ ግዛት የነበረችውን ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በአለም ሸንጎ ላይ ለ7 አመታት ተሟግተዋል።ልጆች! ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ በጣም ታላቅ የአገር ባለሁለታ ናቸው አይደል?፤ልጆች! እናንተም አድጋችሁ አገራችሁን የምታስከብሩ፤ በተለያዩ የዓለም መድረክ አገራችሁን ወክላችሁ የምትቆሙ መሆን አለባችሁ። ለሁሉም ግን ጠንክሮ መማር አስፈላጊ ነው።
አብርሃም ተወልደ