
አዲስ አበባ፡- ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ተደራሽነትና አካታችነትን በማስፋት ሁሉም ዜጎች የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሠራ መሆኑን የኩባያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ገለጹ፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በትናትናው ዕለት 130ኛ ዓመት ክብረ-በዓሉን ምክንያት በማድረግ ባዘጋጀው ጨዋታ እድለኛ ለሆኑ ደንበኞች ሽልማት የመስጠትና እጣ የማውጣት መርሃግብር አከናውኗል፡፡
ሥራ አስፈጻሚዋ በመርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ላይ ነው፡፡ በዲጂታል ኢትዮጵያ ውስጥ መሠረተ ልማትም ይገኝበታል፡፡ የዲጂታል ተደራሽነት አካታችነትን በማስፋት ሁሉም ዜጎች የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሠራ ነው፡፡ለእድለኛ ደንበኞች በሚሰጠው ሽልማትም የዲጂታል የኑሮ ዘይቤና ባሕል የመገንባት ሂደት አካል ነው ብለዋል፡፡
ኩባንያው የኢንተርኔት ተደራሽነትን ከማስፋት ባለፈ ኑሮን ቀለል ማድረግ፣ ፋይናንስና ሌሎች አገልግሎቶችን አካታች ማድረግንም እየሠራ መሆኑን አመላክተው፤ በቴሌ ብር ሱፐር አፕ የቀረበውን ዘመን ገበያ ጨምሮ ሌሎችም በርካታ አገልግሎቶች ሕይወትን ዘመናዊና ቀላል የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮ ቴሎኮም የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ከማቅረብ ባለፈ በዜጎች ሕይወት ውስጥ ትርጉም ያለውና ችግር ፈቺ የሆኑ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉም ዜጎች የእዚህ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋልት የመስጠትና እጣ የማውጣት መርሃግብር አከናውኗል፡፡
የሚሰጡ ሽልማቶችም ከሽልማትነት ባለፈ ዘመናዊ የኑሮ ዘይቤን የማሳደግ ሥራ አካል መሆናቸው አንስተው፤ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቶችን ስንጠቀም የበርካታ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን አገልግሎቶችን ማግኘት የምንችልበት እድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
ዲጂታል የኑሮ ዘይቤን መገንባት ደግሞ በኢትዮ ቴሌኮም ብቻ እውን ስለማይሆን የሁላችንንም ትብብር ይፈልጋል ብለዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም 130ኛ ዓመት ክብረ-በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከመስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለደንበኞች ባዘጋጀው የኢትዮ 130 ሜጋ ፕሮሞ እና ኢትዮ 131 ላኪ ስሎት ሽልማት መርሃ ግብር የተለያዩ ሽማቶችን ሲሰጥ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፤ በትናንትናው ዕለት ሁለት ዘመናዊ የቢ.ዋይ.ዲ የኤሌክትሪክ መኪኖች እና አራት ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጆችን) ለዕድለኞች ሸልሟል፡፡
በተጨማሪም የሁለት ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መኪኖችንና የአምስት ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን እጣ የማውጣት መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡
የሽልማት መርሃ ግብሩ እስከ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ የተገለጸ ሲሆን፤ ደንበኞች እድላቸውን በመሞከር ሁለት ዘመናዊ መኪኖችን ጨምሮ በየቀኑ እና በየሳምንቱ የልዩ ልዩ ሽልማቶች ባለዕድል መሆን እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም