
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬንን ጦርነት እንዲያስቆሙ የሁለት ሳምንታት ቀነ ገደብ እንደሰጡ ተናግረዋል። ፑቲን ጦርነቱን ማቆም ይፈልጋሉ ወይ ተብለው የተጠየቁት ፕሬዚዳንት ትራምፕ “እሱን ልነግራችሁ አልችልም። ነገር ግን በሁለት ሳምንት ውስጥ ታውቁታላችሁ” ብለዋል። በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ፑቲን ከእኛ ጋር ነው ወይስ አይደለም የሚለውን እናውቃለን” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የሀገራቸው ቀጣይ ርምጃ በሩሲያ ምላሽና ድርጊት ላይ እንደሚወሰን ገልጸዋል፡፡
ሩሲያ ሰሞኑን በዩክሬን ላይ ከባድ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ክፉኛ እንደተበሳጩ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡ ትራምፕ በሩሲያ ድርጊት ደስተኛ እንዳልሆኑ ገልጸው፤ ጠንከር ባለ እና ባልተለመደ ተግሳጽ ፑቲንን “ምን ነካው? ብዙ ሰዎችን እየገደለ ነው” ብለዋል። ኃይለ ቃላትን ተጠቅመውም ወርፈዋቸዋል፡፡
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በአንድ ሌሊት ከተፈጸሙት ጥቃቶች ሁሉ ከፍተኛው ነው በተባለውና ሩሲያ 367 ያህል ድሮኖችንና ሚሳኤሎችን ተጠቅማ በፈጸመችው ያለፈው እሁድ ጥቃት፣ በጥቂቱ 13 ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች እንደቆሰሉ ተዘግቧል። የዩክሬን አየር ኃይል ሩሲያ 298 ድሮኖችንና 69 ሚሳኢሎችን መተኮሷንና ከእነዚህም ውስጥ 266 ድሮኖችንና 45 ሚሳኢሎችን ማክሸፉን አስታውቋል፡፡
ትራምፕ ከሩሲያ ጥቃት በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “ፑቲንን ለረጅም ጊዜ አውቀዋለሁ፤ እንግባባለን፤ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ሮኬቶችን ወደ ከተሞች እያስወነጨፈ ሰዎችን እየገደለ ነው። በጭራሽ የምወደው ነገር አይደለም” ማለታቸው ይታወሳል። አክለውም “የተወሰኑ ግዛቶችን ብቻ ሳይሆን መላዋን ዩክሬንን መጠቅለል እንደሚፈልግ ሁልጊዜም እናገር ነበር። ምናልባትም ይህ ትክክል ሊሆን እንደሚችል ማሳያ ነው። ነገር ግን ይህንን ካደረገ ሩሲያን ወደ ውድቀት ይመራታል” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ “ሩሲያ የወሰደችው የአየር ድብደባ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ትንታኔ የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ ፑቲን እና ሩሲያ መርጠው. . . ጦርነቱን ለመቀጠል እና ነብስ ለማጥፋት የሚያደርጉት ነው” በማለት ጥቃቱን ኮንነዋል።
ዘለንስኪ አክለውም ሩሲያ ከድርጊቷ እንድትቆጠብ የአሜሪካ ጫና አስፈላጊ እንደሆነ በአፅንዖት መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ያለ አሜሪካ ጠንካራ ግፊት ይህ የሩሲያ አሰቃቂ ጥፋት ሊቆም አይችልም፡፡ የአሜሪካና የሌላው ዓለም ዝምታ ፑቲንን እያበረታታ ነው፡፡ ማዕቀቦች በትክክል ያስፈልጋሉ” ብለዋል፡፡
አሜሪካ በሩሲያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ለማክበድ እያሰቡ እንደሆነ ተጠይቀው የነበሩት ትራምፕ “በርግጠኝነት!” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የዩክሬን አውሮፓውያን አጋሮች በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ቢያዘጋጁም አሜሪካ በበኩሏ የሰላም ድርድሮችን ለማሳለጥ እንደምትሞክር እና ይህ ፍሬያማ ካልሆነ ራሷን ከአሸማጋይነት ሚናዋ እንደምታስወጣ ስትናገር ቆይታለች።
ከሳምንት በፊት ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በሚያበቃበት ሁኔታ ላይ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከሁለት ሰዓታት በላይ የዘለቀ የስልክ ውይይት አድርገዋል። ከውይይቱ በኋላም ሁለቱም መሪዎች የስልክ ውይይታቸው ገንቢና መልካም እንደነበር በየፊናቸው ተናግረዋል፡፡ ሩሲያ እና ዩክሬን በአፋጣኝ የተኩስ አቁም ለማድረግ ንግግር እንደሚጀምሩም ፕሬዚዳንቱ ገልጸው ነበር፡፡ በተለይም ፕሬዚዳንት ፑቲን ሀገራቸው ለጦርነቱ ሰላማዊ አማራጭን እንደምትደግፍ እንዲሁም ከዩክሬን ጋር ለመሥራት እና ወደፊትም የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ መሆናቸውንም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ትራምፕ ከፑቲን ጋር ስለነበራቸው ውይይት ለፕሬዚዳንት ዘለንስኪ እና ለአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ገለጻ አድርገውላቸውላቸዋል፡፡ ዩክሬንና አጋሮቿም ትራምፕ በዩክሬን ሰላም ለማስፈን ለሚያደርጉት ጥረት አመስግነው፤ አሜሪካ ለጦርነቱ መፍትሔ ለመፈለግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስተዋጽኦ ማበርከቷን እንድትቀጥልም ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ቫቲካን ሩሲያና ዩክሬን የሚያደርጉትን ድርድር እንደምታስተናግድ መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡ የአሜሪካና የአውሮፓ መሪዎችም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ፲፬ኛ ቫቲካን የሩሲያ-ዩክሬን ድርድርን ለማስተናገድ ያላቸውን ዝግጁነት አድንቀው ነበር፡፡
ደም አፋሳሹን የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም እየተሞከሩ ያሉ ሰላማዊ አማራጮች እስካሁን ፍሬ ማፍራት አልቻሉም፡፡ ጦርነቱ እንዲያበቃ የተሞከሩ ጥረቶች ይህ ነው የሚባል የረባ ለውጥ አለማምጣታቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ሳያበሳጭ እንዳልቀረና ጦርነቱን ለማስቆም ሲያደርጉት የነበረውን ተሳትፎም ሊያቋርጡ ይችላሉ ተብሎ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ባለፈው ሳምንት ትራምፕና ፑቲን ያደረጉት የስልክ ውይይት አሜሪካ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ ሚናዋን እንደምትቀጥል ማሳያ ስለመሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡
የሰሞኑ የሩሲያ ጥቃት ደግሞ በፕሬዚዳንቶቹ የስልክ ውይይት ታይቶ የነበረውን ተስፋ ያጨለመና ትራምፕንም አበሳጭቶ ወደ ማዕቀብ ማስፈራሪያና የቀነ ገደብ ማስጠንቀቂያ እንዲያዘነብሉ አድርጓቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለሩሲያ ያስቀመጡት የሁለት ሳምንት ቀነ ገደብ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ትዕግስታቸው እየተሟጠጠ መሆኑን አመላካች ስለመሆኑ ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን አጋሮች ለሀገሪቱ በሚሰጧቸው የጦር መሳሪያዎች ላይ ጥለዋቸው የነበሩትን ገደቦች ማንሳታቸው ተገልጿል፡፡ የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሬድሪኽ ሜትስ ምዕራባውያን የዩክሬን አጋሮች ለሀገሪቱ በሚሰጧቸው መሣሪያዎች ዓይነትና የአጠቃቀም ገደብ ላይ ጥለዋቸው የቆዩትን ገደቦች እያነሱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ገደቦቹን ካነሱት ሀገራት መካከል ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካና ጀርመን እንደሚገኙበት ሜትስ ገልጸዋል፡፡
ሜትስ በርሊን ውስጥ በተከናወነ ኹነት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ዩክሬን በሩሲያ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ኢላማዎችን መምታት አትችልም ነበር፡፡ ከእዚህ በኋላ ግን ሩሲያ ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ ይዞታዎችን በመምታት ራሷን መከላከል ትችላለች” ብለዋል፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ድሚትሪይ ፔስኮቭ የዩክሬን አጋሮች ውሳኔ ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት የሚደረገውን ጥረት ፍጹም የሚጻረር ተግባር መሆኑን በአፅንዖት ተናግረዋል፡፡ “ውሳኔው የሚተገበር ከሆነ፣ ለጦርነቱ መፍትሔ ለመፈለግ የሚደረገውን ጥረት ፈፅሞ የሚያበላሽ ነው” ብለዋል፡፡
በአንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም