አሳር በሌው ሕልመኛ፤
“ከሕዝቤ መካከል ዘጠና ዘጠኝ ከመቶ ያህሉ በተለያዩ የሃይማኖት ጥላ ውስጥ የተጠለሉ ናቸው” በማለት ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሕዝብ ጭምር አንድ ፐርሰንት ብቻ ገድፋና በእስታትስቲክ መረጃ አስደግፋ “ስሙልኝ፤ እወቁልኝ” ለምትለው አገሬ የሃይማኖት ጉዳይ ቀላል ግምት ሊሰጠው የሚገባ አይደለም። መሠረታዊው እውነታ ይህንን ቢመስልም አንኳን በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 11 ሥር፡-
1. መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው።
2. መንግሥታዊ ሃይማኖት አይኖርም።
3. መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም። ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም።
ተብለው የተዘረዘሩት ሦስት ሁነኛ ንዑሳን አንቀጽ እንደምን ሲተገበሩ እንደኖሩና እየተተገበሩ እንዳሉ ቆም ብለን ማሰቡና ማሰላሰሉ አይከፋም። በአንቀጹ ውስጥ የተጠቃቀሱት ቃላት በርግጡ “እስትንፋስ ኖሯቸው ይንቀሳቀሳሉ፤ ወይንስ የተሰደረው በድናቸው ብቻ ነው?” የሚለው ሞጋች ጥያቄም በጥሞና መመርመር ያለበት ይመስለናል።
አገሬ ድፍረት አግኝታና ጨክና እስከ ዛሬ ያጓጓዛትን ሕገ መንግሥት እንደ ሌሎቹ ጉዳዮቿ ፈጥና “ተሃድሶ” የምታካሂድበት ከሆነ እኛን ልጆቿን ለሚያስቆዝሙንና ለሚያቋስሉን በርካታ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች “አቤት” ማለት ስለምንፈልግ ዕድል እንዳትነፍገን አደራ እንላለን። የወገቧን መቀነት በአግባቡ ሸብ አድርጋና “የእንዳትረሺን ቀብዳችን” ግድ ብሏት ቀጠሮውን እንድታፋጥንልን ጭምር አደራ እንላለን።
ለማንኛውም፡- “በእምነቴ ጉዳይ የጸናሁ ሃይማኖተኛ ነኝ” እያለ “ለሚመካውና ለሚኩራራው” ወገን በአገራዊ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ ብቻ ብዕራችን እንዲያመር ወይንም እንዲያተኩር ማድረጉ እጅግም ፋይዳ የሚኖረው አይመስለንም። ይልቅስ ይህ ሕዝብ የሃይማኖቴ መመሪያዎች ከሚላቸው ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አስተማሪና መካሪ የሆኑ ታሪኮችን ጣል ጣል ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን ባለፈው አንድ ጽሑፌ ውስጥ ሃሳቡን ፈንጠቅ አድርጌ ማለፌ አይዘነጋም።
በመሆኑም ለዛሬው ጽሑፍ ማዋዣነት እንዲረዳ ከቅዱሳት መጻሕፍት ታሪኮች ውስጥ አንድን ባለታሪክ በማስታወስ ከአገራችን ወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር አገናዝበን ጥቂት ዳሰሳ ለማድረግ እንሞክራለን። ተጠቃሹ ባለታሪክ ዮሴፍ በመባል ይታወቃል። ታሪኩ የሚገኘውም በመጽሐፍ ቅዱስ የዘፍጥረት ክፍል ከምዕራፍ 37 – 50 ሲሆን፤ በቅዱስ ቁርዓን ውስጥ ዩስፍ እየተባለ በሱራ (ምዕራፍ) 12 (surat Yusuf (prophet) Joseph XII) ውስጥ በ111 (አያህስ) ቁጥሮች ታሪኩ ተጠቅሶ እናነባለን።
ዋናው ዮሴፍን ያስታወስንበት የመነሻ ምክንያታችን ከታሪኩ የተዋስነውንና ለዚህ ጽሑፍ በርዕስነት የተጠቀምንበትን ጉዳይ ለማብራራት ነው። ዮሴፍ የሕልም ስጦታ እንደነበረው በክርስቲያኖች፣ በሙስሊሞችና በአይሁዳዊያን ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በተመሳሳይ ይዘት ተተርኳል። ይህ የሕልም ስጦታው በአስራ አንዱ ወንድሞቹ አልተወደደለትም። አለመውደዳቸው ብቻም ሳይሆን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀኑበት ስለነበር እንኳን እንደ ታናሽ ወንድም ሊወዱትና ሊንከባከቡት ቀርቶ በበጎ ዐይን እንኳን ሊያዩት አልፈለጉም።
የጥላቻቸው የትኩሳቱ መጠን ከፍ ማለቱ በቅዱስ መጽሐፍቱ ውስጥ የተገለጠው እንዲህ ተብሎ ነው። “ወንድሞቹም ባዩት ጊዜ ጠሉት…እነርሱም እንደገና በብዙ ጠሉት…ይልቁንም ስለ ሕልሙ አብዝተው ጠሉት። ያ ባለ ሕልም ይኼው መጣ ኑ እንግዲህ እንግደለውና በአንድ ጉድጓድ ውስጥ እንጣለው። ክፉ አውሬም በላው እንላለን። ሕልሙም ይፈጸም እንደሆነ እናያለን።”
ታሪኩ እጅግ መመሰጥ ብቻም ሳይሆን የሰውን ልጅ የልብ ድንዳኔና ለሰይጣናዊ ድርጊቶችም ምን ያህል ጨካኝ እንደሆነ የሚያመለክት ነው። የመራር ጥላቻ የዕድገት ደረጃ በዮሴፍ ወንድሞች የተገለጸው እንደሚከተለው ነው። ከታሪኩ ውስጥ ነቅሰን እናመልክት፡- “ወንድሞቹ ጠሉት…እንደገና በብዙ ጠሉት…ይልቁንም አጥብቀው ጠሉት።” ጥላቻቸው ነፍስ ዘርቶ መተግበሩም እንዲህ ተገልጧል፡- “በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱን ቀሚሱን ገፈፉት፤ ወደ ጉድጓድም ውስጥ ጣሉት። ከጉድጓድ አውጥተውም በሀያ ብር ሸጡት። ገዢዎቹም ወደ ግብጽ ወሰዱት።” ሙሉውን ታሪክ ከቅዱሳት መጻሕፍቱ ውስጥ ማንበብ ይቻላል። ይህንን ታሪክ ከራሳችን ጉዳዮች ጋር እያዛመድን እንየው።
ሕልመኞቻችንን ያጨነገፉ ታሪካዊ ሾተላዮች፤
“ታላቋ እንግሊዝ” ራሷን “ታላቅ” አሰኝታ “ፀሐይ በግዛቶቿ ላይ እንደማትጠልቅ” ከመፎከሯ አስቀድሞና ገና “ጉተናዋ ጠንቶ” እንደ ሉዓላዊ አገር ከመሰባሰቧ አስቀድሞ ኢትዮጵያ ግን [የሃይማኖትና የፖለቲካው ሽኩቻው ሳይዘነጋ] ከነክብሯ እንደደመቀች ነበረች። እስፓኛዊው ፓየዝ “የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን ምሥጢር” በዐይኑ አይቶ፤ በጆሮው ሰምቶ ለመመስከር የመጣው በዚሁ ዓመት መሆኑን ልብ ይሏል።
ጊዜ ፊቱን አዙሮላት “ጡንቻዋን በማፈርጠም” እንደ ሞገደኛ ኮርማ የሀገራትን የፖለቲካ በረት ካላመስኩ የምትለውና ምድሩም፣ አየሩም፣ ህዋውም ሆነ ጠፈሩን ሰብስቤ ከብብቴ ውስጥ ካላስገባሁ ብላ የምትፎገላው አሜሪካ ይሏት አገር ጁላይ 4 ቀን 1776 በአሥራ ሦስት እስቴቶች እንደ ሉዓላዊ አገር ተቆጥራ ከአራስ አልጋ ላይ ሳትነሳ በፊት ኢትዮጵያ ታሪኳን ለዓለም ትተርክ የነበረው ሺህ ዓመታት እያሰላች ነበር። ይህቺን ስመ ገናና ክብረ ትልቅ አገር ጓዳ ጎድጓዳዋን ፈትሾ በመጽሐፍ ለመሰነድ እንግሊዛዊው ጀምስ ብሩስ ባህር አቋርጦ ከደጃፋችን የደረሰውም “የያኒኪዎቹ አገረ አሜሪካ” ጡጦዋን ከአፏ ላይ ሳያስጥሏት በፊት ነበር።
የኢትዮጵያን የግዛትና የዜጎቿን የልብ አንድነት ለማጽናት ቴዎድሮስ የነገሡት ትልቅ ሕልም አርግዘው ቢሆንም ሕልማቸውን ለማጨንገፍ የተረባረቡት የራሳቸውና የቅርባቸው ሰዎች ነበሩ። የሕልማቸው ጭንገፋ የተጠናቀቀውም ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም ራሳቸውን በራሳቸው እጅ አጥፍተው ስለመሆኑ በሁሉም ዘንድ ይታወቃል። አፄ ዮሐንስም ቢሆኑ አገራቸው በደርቡሽ ወራሪዎች እጅ መውደቅ እንደሌለባት በማለም ለጦርት በዘመቱበት ከእነ ሕልማቸው መጋቢት 2 ቀን 1881 ዓ.ም እስትንፋሳቸው ጨልሞ፤ አንገታቸው በጠላቶቻቸው እጅ ተቆርጦ ታሪካቸው መደምደሙ አንዱ የታሪካችን ምዕራፍ ነው።
ከአፄ ምኒልክ ህልፈት በኋላ በኢያሱ፣ በዘውዲቱና በተፈሪ መኮንን መካከል የተፈጠረው ሽኩቻም ብዙ ባለ ሕልመኞችን እንዳሳጣን ታሪካችን አንገቱን ደፍቶ ይተርክልናል። አፄ ኃይለ ሥላሴ በዙፋናቸው ላይ ተደላድለው ከተቀመጡም በኋላ በተለያዩ የፖለቲካ ሴራዎች ምክንያት ለአገራቸው ታላላቅ ራእይ የነበራቸውን በርካታ አለኝታዎች አጥተናል። እነዚህ ባለ ሕልሞች ለህልፈት የበቁት ወግ ያለው የቀብር ሥነ ሥርዓት እንኳን ሳያገኙ ነበር።
ጸጋዬ ገብረ መድኅን በ1984 ዓ.ም ጽፎ ለመድረክ ባበቃው “ሀ ሁ ወይንም ፐ ፑ” ተውኔቱ ወስጥ ሁለት ገጸ ባሕርያትን በማናገር የሕልመኞቻችን ሾተላይ ምን እንደሆነ በግልጽ አሳይቶናል። ከቃለ ተውኔቱ ጥቂት ሃሳቦችን እናስታውስ፡-
“እናታችን ኢትዮጵያ ባሕላዊ ሾተላይ ናት መሰል። ዴሞክራሲን በስድሳ ስድስት ወልዳ በላች። አስቀድሞ በሃምሳ ሦስት አስጨንግፏታል። ብትወልድም ብትገላገለውም ለዘለቄታ አያደርግላትም። የማሕፀን መርገምት አለባት። የዴሞክራሲ ሾተላይ ናት – ኢትዮጵያ። በስድሳ ስድስትማ ወዲያው ማግስቱን መፈክር ተፈከረላት። “አብዮት ልጆቿን ትበላለች” ተባለላት። ተሸለለላት። የዴሞክራሲ ሾተላይ እናት፤ በላኤ ሰብነቷን መላው የዓለም ሕዝብ አስጠንቅሮ አወቀላት።”
“ዛሬስ? ዛሬማ…የሾተላይ ጥሪቷ ዳግመኛ እንዳያጓጓት …በመሃላ ተገዝታለች። የሕጻኑ እርግብግቢት ገና በአራሱ፣ በሾተላይ ዐይኖቿ ተወግቶ እንዳይፈርስ፣ ቃለ – መሃላዋ እንዳይረክስ፣ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዳይነግሥ፣ ጨቅላ ዴሞክራሲ አራስ ብሌኑ እንዳይፈስ…እናታችን በግዝት ተይዛለች”
ዛሬስ? እኛም የራሳችንን ዛሬ እንሞግት፤
ዛሬም እንደ ትናንቱ የኢትዮጵያ ሕልመኞች በሾተላይ እንዲወጉ ዐይነ ጥላቸውን ያሳረፉባቸው ብዙዎች ናቸው። የባዕዳን ቡዶች ብቻ ሳይሆኑ የራስ አንጋዳዎችም የሾተላዩ ወጊ ዐይኖች ናቸው። እንዲያውም የሾተላዩ ብርታት ከትናንት ይልቅ ዛሬ “በጅኒዎች” ርብርብ የጠነከረ ይመስላል። ባለ ሕልሞች የሚጠቁባቸው የጽንስ ማምከኛ ዘዴዎች አበዛዛቸው አጃኢብ ያሰኛል። ከዮሴፍ ታሪክ ጋር እንደገና መለስ ብለን ከዛሬያችን ጋር እናነጻጽር።
በዚህቺው እየሞቅናት ባለችው በእኛው ጀንበር ወንድም የወንድሙን ልብስ ሳይሆን ነፍሱን በደም ሲነክር አይሰቀጥጠውም። ብዙ ባለ ሕልሞች በጉድጓድ ውስጥ ተጥለው “በሻጭና ገዢ መካከል” ድርድር ሲደረግባቸው ማየት ብርቃችን አይደለም። የየዘመናቱ የሾተላይ ዐይነ ጥላ ለሞት ባይዳርገውም ዛሬም ድረስ ኮርኩዶ በእንፉቅቅ እንዲሄድ የተደረገው የአገሬ ዴሞክራሲ አልጋ ላይ ወድቆ እስትንፋሱ ጭል ጭል እያለ ያለው የተስፋ ጉሉኮስ እየተጋተ ይመስላል።
እውነቱን በድፍረት እንነጋገር ከተባለ የባለ ሕልሞችን ራእይ የሚያጨነግፉ በርካታ አገራዊ ሾተላዮች እንደከበቡን በድፍረት ገላልጠን ልንወያይ ይገባል። መልካም ሲታሰብና ሲታቀድ ኡኡታ! መልካም ሲሰራ ኡኡታ! አልፎም ተርፎ የአድማጩንና የአንባቢውን ስሜት ከፉኛ መጉዳት ብቻም ሳይሆን የተናጋሪውን/የጸሐፊውን የራሱን አንደበት የሚያቆሽሹ ቃላትን በንግግር ወይም በጽሑፍ በማመንጨት ጥቀርሻ ለመቀባት የሚተጉትና የሚያንጓጥጡ በርካታ ዜጎችን ማስተዋል ዛሬ ዛሬ እንግድነቱ ቀርቷል፤ አሸማቃቂነቱም ተዘንግቷል።
ባለ ሕልሞች ከእነ መልካም ሕልማቸው እየሞቱ እስከ መቼ አገራዊ እርማችንን እንደበላን እንኖራለን። እስከ መቼስ የገደሏቸውን ባለ ራእዮች የቀብር ሥርዓት በስላቅና በሃሜት በአደባባይ መሃል ሲቀበሩ እያስተዋልን “ዝም አይነቅዝም” በሚል ፍርሃት ታብተን “የሾተላይ” እጀ ሰብ ዜጎችን ድርጊት ታግሰን እንዘልቀዋለን። እስከ መቼስ በዐይነ ወጎች ድርጊት እንደተሳቀቅን እንኖራለን። ባለ ሕልሞችን አፈር እያለበስንስ እስከ መቼ መኖር ይቻላል። ስንቱ ባለ ሕልም የአገር ተስፋ አልቃሽ አጥቶ እምባውን እያዘራ ተቀብሯል? ምን ያህሉስ ሕልሙም እንቅልፉም ተነጥቆበት በአገሩ ላይ ባይተዋር ሆኗል? በሾተላይ ሴራ የተለከፈው የአገሬ ፖለቲካ የሚፈወሰው ምን በሚሉት መድኃኒት ይሆን? “ማሕበረሰብ አንቂ” የሚል የመሸሸጊያ ዐይነ ርግብ አጥልቀው ሕልም ያላቸውን ዜጎች አዋርደው ለመቅበር ቀን ከሌት የመቀበሪያ ጉድጓድ ሲምሱ ውለው የሚያድሩትንስ ማንና የትኛው ሕግ ይሆን መማሻ አካፋና ዶማቸውን ከእጃቸው ላይ አስጥሎ በፍትሕ መንበር ፊት የሚያቀርባቸው? ከወራት በፊት ባስነበብኩት የጽሑፍ ርእስ ልሰናበት፤ ኦ ዴሞክራሲ በስምህ ስንት ግፍ ተሰራ! ሰላም ይሁን!!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2014