በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የአገራችን ሕዝብ በኑሮ ውድነት ሲያማርር ይሰማል። በተለይ የመንግሥት ሰራተኞችን ጨምሮ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ‹‹ኑሮ ከብዶናል›› የሚል ሮሮ ያሰማሉ።
የኑሮው ሁኔታ በዚህ መልኩ እየናረ በመጣበት በዚህ ወቅት፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በድንገት ደሞዝ ሲቋረጥ ደግሞ ችግሩ ምን ያህል የከፋ እንደሚሆን መገመት ከባድ አይደለም። ወትሮም ቢሆን በኑሮ ውድነት እየተቸገረ ያለው የመንግሥት ተቀጣሪ ሠራተኛ ደሞዝ ሲቋረጥበት ለከፋ ችግር መዳረጉ ምስክር የሚያሻው አይደለም።
ይህን ማንሳታችን ያለምክንያት አይደለም። በአፋር ክልል ዱብቲ ከተማ በተገኘንበት ወቅት ሰብሰብ ብለው አቤቱታቸውን ያሰሙንን የዱብቲ ከተማ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ሰራተኞች ቅሬታ ልናካፍላችሁ ስለወደድን ነው።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ላለፉት ሶስት ዓመታት ደሞዝ ስላልተከፈላቸው ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል። ለሶስት ዓመት ደሞዝ አልተከፈለም የሚል መረጃ ሲደርስ፤ ለማመን ከበድ የሚል በመሆኑ እንዴት ሊሆን ቻለ? በማለት ቅሬታቸውን በማዳመጥ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግረናል።
የዱብቲ ከተማ የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት በብዙ ችግሮች የተተበተበ ተቋም እንደሆነ ሰራተኞቹ ያማርራሉ። የዚህ ተቋም ችግር ወደኋላ ብዙ ዓመታትን ይጓዛል። ተቋሙ እንደሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከመንግሥት በጀት አይመደብለትም። እንዲተዳደር የተደረገው ከሕብረተሰቡ በሚሰበስበው የቆጣሪ ክፍያ ነው። ይህ መሆኑ ባልከፋ፤ ነገር ግን ተቋሙ ከሕብረተሰቡ የሚሰበስበው ገንዘብ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሲመጣ የተቋሙ ሰራተኞችም ለችግር ተዳረጉ።
የዱብቲ ከተማ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት 28 ሰራተኞች አሉት። ከእነዚህ ውስጥ 13ቱ ሰራተኞች ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ባለፉት ሶስት ዓመታት ደሞዝ ስላልተከፈላቸው ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን፤ ጥቂቶቹ ደግሞ አላግባብ ከስራ በመባረራቸው አቤት በማለት የዝግጅት ክፍሉ አቤቱታቸውን እንዲያስተናግድ ጠይቀዋል።
ሠራተኞቹ እንደሚሉት የዱብቲ ውሃ አቅርቦት ቀስ በቀስ እየተበላሸ በመሄዱ ሕብረተሰቡ ውሃን በአግባቡ አያገኝም። ውሃዋም በምትመጣበት ወቅት ሃይል ስለሌላት በቧንቧ ወደ ላይ መውጣት አትችልም። በዚህ የተነሳ አብዛኛው ነዋሪ መስመሩን እየቆረጠ ከዋናው መስመር እየቀጠለ መጠቀምን ዋነኛ አማራጭ እያደረገ ይገኛል።
ይህ እንዳይሆን በተደጋጋሚ ለተቋሙ ሃላፊ እና ከዚያ በላይ ላሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሃላፊዎች ችግሩ እንዲስተካከል ቢጠይቁም ሰሚ ማጣታቸውን ይናገራሉ። በኋላም የተቋሙ ገቢ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጣ። ይህ ደግሞ ተቋሙ ገንዘብ መክፈል እስከሚያቅተው ድረስ ለችግር እንዲዳረግ አድርጎታል።
የድርጅቱ ሰራተኞች እንደሚሉት ለዚህ ዋነኛው ችግር ተቋሙ በራሱ እንዲተዳደር መደረጉ አይደለም። ተቋሙን የሚከታተለው አካል ባለመኖሩ የአንድ ሰው ሀብት እስኪመስል ድረስ ፈላጭ ቆራጩና ሰራተኞችንም እንደፈለገ የሚያደርገው ሥራ አስኪያጅ በመኖሩ ነው።
ባለፉት ሶስት ዓመታት ከድርጅቱ ሰራተኞች ውስጥ አብዛኞቹ ደሞዛቸው ተቋርጧል። ሆኖም ከድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ጋር ባላቸው ግንኙነት ደሞዝ የሚያገኙ ሰራተኞች ሊኖሩ እንደሚችሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ። ከነዚህ 28 ሰራተኞች ውስጥ ቅሬታ ያቀረቡት 13 ሰራተኞች ናቸው። እነዚህ ሰራተኞች አቤቱታቸውን ለወረዳው ፍርድ ቤት ቅሬታ በማቅረባቸው ፍርድ ቤቱ የሰራተኞቹ ደሞዝ እንዲከፈላቸው ትዕዛዝ ይሰጣል። ነገር ግን ደሞዝ የሚከፍላቸው አልተገኘም። ከዚያ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታቸውን ያቀርባሉ።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም የሰራተኞቹ ቅሬታ ተገቢ በመሆኑ በአስቸኳይ ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ይጠይቃሉ። የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተግባራዊ የሚያደርግ አካል ግን አልተገኘም። በመጨረሻ ግን ከብዙ ጥረት በኋላ ከ2010 በጀት ዓመት የስድስት ወር እንዲከፈላቸው ይደረጋል። ከዚህ ውጭ ግን ገንዘብ ስለሌለን ለጊዜው መክፈል አንችልም የሚል ምላሽ ይሰጣቸዋል።
የከተማው የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ ልክ እንደ ግል ንብረታቸው ለሚፈልጉት ደሞዝ ሲከፍሉና ለማይፈልጉት ሲነሱ እንደኖሩ ነው ሰራተኞቹ የሚናገሩት። በዚህ የተነሳ ምክትል ስራ አስኪያጁም ጭምር አጠቃላይ ስለፋይናንስ አሰራሩም ሆነ ስለስራው ምንም አይነት መረጃ እንዳይኖራቸው በመደረጋቸው እርሳቸውም ደሞዝ ካልተከፈላቸው ሰራተኞች አንዱ ሆነዋል።
የወረዳው ፍርድ ቤት ለሰራተኞቹ ደሞዝ እንዲከፈል ውሳኔ በማስተላለፉ ግን የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ስራ አስኪያጁ ለዱብቲ ከተማ አስተዳደር እና በየደረጃው ለሚገኙ ተቋማት እንዲሁም ለክልሉ መንግሥት በግልባጭ ፍርድ ቤቱ ስራ አላሰራንም በሚል ከዚህ ድርጊቱ እንዲታቀብ ደብዳቤ ጽፈዋል።
የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ከሥራ ያገዳቸው ሰራተኞችም አሉ። ከእነዚህም መካከል ቅሬታ ያቀረቡት ከ30 ዓበላይ በድርጅቱ በጥበቃ ሰራተኝነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ተመስገን የማታው አንዱ ናቸው። አቶ ተመስገን ግንቦት 1 ቀን 2013 ዓ.ም የስንብት ደብዳቤ ደርሷቸዋል። ለዚህ የቀረበው ምክንያት ደግሞ በአንድ በኩል ተቋሙ የበጀት እጥረት ስላጋጠመው የሚል ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ እርሳቸውም ምንም አይነት ስራ ሳይሰሩ ወራት ስለተቆጠሩ እና በጽህፈት ቤቱ ላይ የሰራተኛ ደሞዝ ውዝፍ የሆነበት ምክንያት በማይሰሩ ሰራተኞች የተነሳ በመሆኑ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ነገር ግን ከዚያ በፊት ስራ ላይ ላለመገኘታቸው የተሰጣቸው ማስጠንቀቂያም ሆነ ቅጣት እንደሌለ አቶ ተመስገን ይናገራሉ። አቶ ተመስገን እንደሚሉት፤ እርሳቸው ይህንን ያህል ካገለገሉበት ተቋም ‹‹እንዴት ቢያንስ ያለጡረታ እባረራለሁ›› በሚል ወደ ጡረታ ሚኒስቴር ይሄዳሉ። እዚያ ሲሄዱ የተሰጣቸው ምላሽ ግን ‹‹አናውቃችሁም›› የሚል ነው። ምክንያቱም ይህ ተቋም የጡረታ ገንዘብ አስቆርጦ አያውቅም።
ነገር ግን በአገራችን እያንዳንዱ የግል ድርጅት ጭምር የማሕበራዊ ዋስትና አገልግሎት መስጠት እንዳለበት በአዋጅ ተደንግጓል። የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታን የተመለከተ አዋጅ ቁጥር 715/03 ላይ በግልጽ እንደሰፈረው፤ እያንዳንዱ የግል ድርጅት የሠራተኞች የጡረታ መዋጮ ከደመወዛቸው ቀንሶና የራሱን መዋጮ ጨምሮ ለሰራተኛው የወር ደሞዝ ለሠራተኞች ከተከፈለበት ቀን አንስቶ በ 30 ቀናት ውስጥ የመክፈል ግዴታ አለበት።
ከሠራተኞቹ ደመወዝ ሊቀነስ የሚገባውን መዋጮ ሣይቀንስ የቀረ የግል ድርጅት ክፍያውን ራሱ ለመፈፀም ሃላፊነቱን ይወስዳል። ኤጀንሲው ወይም ውክልና የተሠጠው አካል ተገቢውን የጡረታ መዋጮ ለጡረታ ፈንድ ገቢ ሣያደርግ ከ 3 ወር በላይ የቆየ የግል ድርጅትን በባንክ ካለው ሂሣብ ላይ ተቀንሶ ገቢ እንዲሆን የማስደረግ ሥልጣን ይኖረዋል።
በአዋጁ እንደተጠቀሰው አንድ የግል ድርጅት ሠራተኛ ከ 10 ዓመት ያላነሰና 20 ዓመት ያልሞላ አገልግሎት ፈፅሞ በራሱ ፈቃድ ስራውን ከለቀቀ ወይም ከ 20 አመት ያነስ አገልግሎት ፈፅሞ በአዋጁ ከተጠቀሱት ውጪ በሆነ ምክንያት ከስራ ከተሠናበት የአሠሪውን ድርሻ ሣይጨምር ሠራተኛው ራሱ ባዋጣው መጠን ብቻ የጡረታ መዋጮ ይመለስለታል።
አቶ ተመስገንም ለአገልግሎታቸው ካሳ እንዲከፈላቸው ለዱብቲ ከተማ ፍርድ ቤት ያቀረቡት ቅሬታ ሲታይ ቆይቶ በመጨረሻም 32 ሺህ ብር እንዲከፈላቸው ይፈረድላቸዋል። ነገር ግን ጽህፈት ቤቱ ገንዘብ የለውምና ‹‹ልንከፍሎት አንችልም›› የሚል ምላሽ ያገኛሉ። ከዚያ ወደ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይሄዳሉ። ፍርድ ቤቱም የወረዳው ፍርድ ቤት ውሳኔ ትክክል በመሆኑ እንዲከፈላቸው ውሳኔን ያፀናል። ሆኖም አሁንም ሰሚ አላገኙም። በመጨረሻ ግን ከብዙ ድካም በኋላ 16 ሺህ ብር ይሰጣቸዋል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሳ አብዶ ላሌ እንደሚሉት የዱብቲ የውሃ ፍሳሽ አገልግሎት ሰራተኞች ጉዳይ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱም አቅም በላይ ነው። ሰራተኞቹ የሚያቀርቡት ቅሬታ ትክክል ሆኖ እያለ ምላሽ የሚሰጥ አካል የለም። ጉዳዩ እንዲፈታ እና ለሰራተኞቹ ገንዘባቸው እንዲከፈል ለማድረግ ብንሞክርም ተቋሙ በአካውንቱ ምንም ገንዘብ የለውም። ከዚህም ውጭ የራሱ ህንጻም የለውም። ስለዚህ አስቸጋሪ ነው ይላሉ።
‹‹ለሶስት ዓመታት አላሰናበቱኝ፤ ወይ ደሞዝ አልከፈሉኝ፤ እንዲሁ እየሄድኩ እመለሳለሁ›› ያሉን ደግሞ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በጽህፈት ቤቱ በጥበቃ ስራ ላይ እንደቆዩ የሚናገሩት አቶ ሃሰን ሀመዱ ሀሰን ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በድርጅቱ አብዛኛው ሠራተኛ እየሠራ አይደለም። ይህንን የሚከታተልም አካል የለም። አልፎ አልፎ ሠራተኞች ይገቡና ይወጣሉ። ከዚህ ውጭ ግን ምንም አይነት እንቅስቃሴ በተቋሙ ውስጥ የለም።
ሌላዋ የድርጅቱ ሰራተኛና ቅሬታ አቅራቢ ወይዘሮ አለሚቱ አሊ ትባላለች። የእለት ገቢ ሰብሳቢ ናት። ወይዘሮ አለሚቱ እንደምትለው ድርጅቱ ምንም አይነት የፋይናንስ አሰራር ሕግ አይከተልም። ቢል በአግባቡ አይሰበሰብም። ውሃም በአግባቡ ለሕብረተሰቡ ስለማይደርስ አብዛኛው ቆጣሪ ተቆርጦ ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ውሃን መጠቀም ጀምረዋል።
እነርሱም በድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አማካኝነት ከእያንዳንዱ ቤት 200 ብር እንዲሰበስቡ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት ገንዘቡን ሰብስበው ገቢ አድርገዋል። እሷን ጨምሮ በዚህ መልኩ ገንዘብ የሰበሰቡት አምስት የፋይናስ ሰራተኞች ሲሆኑ እርሷ በበኩሏ ብቻዋን 69 ሺህ ብር ሰብስባ ገቢ አድርጋለች። ከዚያ በኋላ ግን ገንዘቡ የት እንደገባ የምታውቀው ነገር የለም። ለሰራተኞች ደሞዝ እንዲከፈል የጽህፈት ቤቱ አካውንት ውስጥ የተገኘውም 69 ብር ብቻ ነው።
የመዝገብ ቤት ሰራተኛ መሆኗን የምትናገረው ሌላዋ ቅሬታ አቅራቢ ወይዘሮ ነኢማ ይማም በበኩሏ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ የተለያዩ መረጃዎችን ከመዝገብ ቤት በራሳቸው ፈቃድ ስለሚያወጡ ይህ ለምን ይሆናል የሚል ጥያቄ ስታቀርብ ከስራዋ እንድትባረር መደረጓን ትናገራለች። በዚህም መሰረት ከስራ በመባረሯ በአሁኑ ወቅት የምትተዳደረው እና ልጆቿን የምታሳድገው የጀበና ቡና እየሸጠች ነው ።
ወይዘሮ ነኢማ እንደምትለው እርሷም የተባረረችበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። ለምን እንደሆነ የሚገልፅ ደብዳቤ የላትም። ስንብት የተሰጣት ስራዋን በአግባቡ ስለማትሰራ በሚል ብቻ ነው ።
የድርጅቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ በድሩ መሃመድ ኢብራሂምም ቅሬታ ከሚያቀርቡ ሰራተኞች አንዱ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ጽህፈት ቤቱ በአጠቃላይ በአንድ ሰው ብቻ የሚመራ በመሆኑ እርሳቸው ስለድርጅቱ ለማወቅ አልቻሉም። ይህንን በተመለከተም በየደረጃው ለሚመለከታቸው አካላት ቢያሳውቁም ሰሚ አላገኙም። ከዚህም አልፎ ‹‹የድርጅቱ ስራአስኪያጅ በማስፈራራት ቅሬታ የምናቀርበውን ሰዎች ደሞዝ እንዳናገኝ በማድረግ ለችግር ዳርጎናል›› ይላሉ።
አቶ በድሩ ልክ እንደሌሎቹ ሰራተኞች ደሞዝ ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል። በዚህ የተነሳ ልጆቻቸውን ለማብላት ሲሉ የቤት እቃቸውን ጭምር እስከመሸጥ መድረሳቸውን በእንባ በታጀበ አንደበት ይገልጻሉ።
እነዚህ ሰራተኞች ከሚናሩት ቅሬታ በተጨማሪ ከፍርድ ቤት የተሰጣቸው ማስረጃዎቻቸውንም ይዘዋል። ነገር ግን እነሱ እንደሚሉት ጉዳዩ ከፍርድ ቤትም አቅም በላይ ነው። በዚህ የተነሳ ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮችም ተፈጻሚ የሚሆኑበት እድል የለም። በተለይ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ለማንም የሚታዘዙ ባለመሆኑ በግልጽ የትም ብትሄዱ ምንም አታመጡም የሚል ዛቻ እንደሚያቀርቡባቸው ይናገራሉ።
እነዚህን ቅሬታዎች በመያዝ የከተማዋ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑትን አቶ ወግሪስ አይቲአሶ አሊ ስለጉዳዩ ለማነጋገር ወደ ቢሯቸው አመራን። ቢሯቸው ስንደርስ በቅድሚያ የጠበቁን ክላሽ መሳሪያቸውን እንደታጠቁ ነበር። ‹‹እናንተ ማንናችሁ? ቅሬታ ይዛችሁ የምትመጡት እምባ ጠባቂ ወይስ ሰብአዊ መብት ናችሁ?›› በሚል መልስ ለመስጠት አንገራገሩ።
ነገር ግን ከእምባ ጠባቂም፣ ከሰብአዊ መብትም ሳንሆን የሚዲያ ባለሙያዎች መሆናችንን በመንገር እና ደውለንም ጉዳዩን እንዳስረዳናቸው በማስታወስ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ቢሰጡ ጉዳዩን ግልጽ ለማድረግ ስለሚጠቅም ነው በሚል መረጃ እንዲሰጡን በድጋሚ ጠየቅን። የማውቀው መረጃ ብለው ምላሽ ሰጡ።
እነዚህ ከላይ በዝርዝር ቅሬታ ያቀረቡ ሰራተኞችን ጠቅሰው ‹‹ የማይገቡና ስራ የማይወዱ ናቸው። ከዚህም ባሻገር ምክትል ስራ አስኪያጁ ጭምር ችግሩን መፍታት ሲገባው በየፍርድ ቤቱ ክስ ይሄዳል። ይህ ትክክል አይደለም።›› ካሉ በኋላ፤ የሰራተኞቹ ቅሬታ ተገቢ አለመሆኑን ተናገሩ።
ጽህፈት ቤቱ ምንም አይነት ገንዘብ እንደሌለውና የከተማዋ ነዋሪዎች ቆጣሪዎችን እየፈቱ ስላስቸገሩ በእያንዳንዱ ቤት ሁለት ሁለት መቶ ብር ለመሰብሰብ መገደዳቸውን ጠቆሙን። ይሁን እንጂ የተሰበሰበው ገንዘብ የት ሄደ በሚል በዝግጅት ክፍሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ለጥገና እና ለመሳሰሉ አገልግሎቶች ውሏል ከማለት ውጭ ትክክለኛውን መረጃ ሊሰጡን አልቻሉም።
በሌላም በኩል ደሞዝ ያልተከፈላቸው ሰራተኞች ጉዳይ ቀደም ሲል ከነበረው የወረዳ አስተዳደር ጊዜ ጀምሮ ሲንከባለል የመጣ መሆኑንና ከዚያ በኋላ የከተማ አስተዳደሩ ግን ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረጉን ተናገሩ። በዚህም መሰረት የስድስት ወር ደሞዝ መክፈሉንና አሁንም ቀሪውን ገንዘብ ለመክፈል በሚቀጥለው በጀት አመት ጥረት እንደሚያደርጉ ገለፁ።
በሌላ በኩል ጡረታን በተመለከተ ይህ ድርጅት የመንግሥት በጀት የተመደበለት ባለመሆኑና ከደንበኞች በሚሰበሰብ ገንዘብ የሚተዳደር በመሆኑ የጡረታ ገንዘብ እንዳልተቆረጠ ተናግረዋል። ይህ ግን ከመንግሥት አሰራር ጋር የሚጣረስ መሆኑን አምነዋል። ከዚህ ውጭ አብዛኛው ሰራተኞች በሰዓት የማይገቡና የዲሲፕሊን ችግር ያለባቸው እንደሆኑ ጠቁመዋል።
የዱብቲ ከተማ ከንቲባ አቶ መሃመድ አወል ሃሰን በበኩላቸው ይህ የሰራተኞች ቅሬታ ሶስት አመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ችግራቸው ቀደም ሲል ከነበረው የወረዳ አስተዳደር ጀምሮ ሲንከባለል የመጣ መሆኑን ጠቁመው፤ እርሳቸው ግን ላለፈው አንድ አመት ከስራቸው በመታገዳቸውና ወደስራ ከተመለሱ ገና ቀናትን ያስቆጠሩ በመሆኑ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ሆኖም የከተማ አስተዳደሩ በቂ ገንዘብ እና በጀት የሌለው በመሆኑ የእነዚህ ሰራተኞች ደሞዝ ለመክፈል የከተማ አስተዳደሩ አቅም እንደሌለውና ችግራቸው ሊፈታ የሚችለው ምናልባት በቀጣዩ በጀት አመት እንደሆነ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ከእያንዳንዱ ቤት የተሰበሰበው ሁለት መቶ ብር የት ገባ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ እሳቸው በቂ መረጃ እንደሌላቸውና እሳቸውም እንደከተማዋ ነዋሪ ገንዘቡን መክፈላቸውን ተናግረዋል። በከተማዋም በአጠቃይ አምስት ሺህ የሚሆን የውሃ ቆጣሪ መኖሩን የሚናገሩት አቶ መሃመድአወል፤ ነገር ግን አንዳንድ ነዋሪዎች አጥር ሲያስፋፉ ጭምር የውሃ መስመርን በመቁረጥ እና በህገወጥ መንገድ ቆጣሪን በመንቀል ተቋሙ ላይ ችግር መፍጠራቸውን ተናግረዋል። ስለዚህ በቀጣይ ይህንን ጉዳይ እንደሚያጣሩ ጠቁመዋል።
ከሰራተኞቹ የጡረታ ገንዘብ አለመቆረጥ ጋር በተያያዘ እርሳቸው በቂ መረጃ እንደሌላቸው የሚገልጹት፤ ከንቲባው ይህ በቀጥታ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ስራ አስኪያጅን እንደሚለመለከት ነው የተናገሩት። ሆኖም እርሳቸው የከተማዋ ከንቲባ እንደመሆናቸው ጉዳዩ እንደሚመከላቸው በተደጋጋሚ ላቀረብንላቸው ጥያቄ ብዙ ጊዜ እግድ ላይ በመቆየታቸው በቂ መረጃ እንደሌላቸው በመጠቆም ጉዳዩን እንደሚያጣሩ ገልፀዋል። ሆኖም የሰራተኞቹ ቅሬታ ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል።
እንግዲህ ከላይ እንዳነሳነው የዱብቲ ከተማ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ቅሬታ በሕግ አግባብ ሲታይ ትክክል እንደሆነ ሁሉም ያምናል። ነገር ግን መፍትሄ የሚሰጥ አካል አልተገኘም። እነዚህ ሰራተኞች አብዛኞቹ የቤተሰብ ሃላፊነት ያለባቸው ናቸው። በመሆኑም ሰራተኞቹ በዚህ መልኩ ደሞዝ ተከልክለው በመቆየታቸው ከእነሱም አልፎ ቤተሰቦቻቸው ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ገልፀዋል።
በአንጻሩ ፅህፈት ቤቱ ላይ የሚታዩ የሕግ ክፍተቶች እንዳሉም ሰራተኞቹም ሆኑ መረጃዎቹ ይጠቁማሉ። ምንም እንኳ ፅህፈት ቤቱ ከመንግሥት በጀት ባይመደብለትም በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ሃላፊዎች ይህንን አገልግሎት ሰጪ ተቋም ጠጋ ብለው የመመልከት ግዴታ አለባቸው። የሰራተኞቹን ችግር መፍታትም ይጠበቅባቸዋል።
ከዚህም ባሻገር የዱብቲ ከተማ ነዋሪዎች በውሃ እጥረት መቸገራውን ያማርራሉ። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም በስፍራው በነበረው ቆይታ በርካታ ነዋሪዎች በውሃ እጥረት እና አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ፈተና ላይ መውደቃቸውን ታዝቧል።
በመሆኑም እንዲህ የተወሳሰበ ችግር ውስጥ ያለውን ተቋም ጠጋ ብሎ መመልከት እና የሰራተኞችንም ሆነ የሕብረተሰቡን ችግር መፍታት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ ባለመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ይፈቱ ዘንድ ጥቆማችንን እናቀርባለን።
ወርቁ ማሩ
አዲስ ዘመን መጋቢት 28 /2014