ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓትን በኢትዮጵያ ውስጥ ለመዘርጋት የሚደረገው ጥረት ፈጣን እመርታ እያሳየ መሆኑን በርካታ መረጃዎች ያመለክታሉ። አብዛኛውን ጊዜ በአገራችን ዜጎች በተለያየ ተቋማት ውስጥ አገልግሎት ለማግኘት ሲሄዱ በአሰራር ሥርዓትና በአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍና ምሬት ውስጥ እንደሚገቡ ይነገራል። ይህ አይነት ችግር የሚፈጠረውም ወቅቱ የፈጠረውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ጊዜን፣ ጉልበትንና ገንዘብን በሚቆጥብ መልኩ ለደንበኞች አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ቁርጠኝነት፣ አቅምና እውቀት ማነስ እንደሆነ ይነገራል።
ምስጋና ለዘመኑ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ይግባና አሁን አሁን ዓለማችን ፈጣን ርቀት የማይገድበው ጉልበትና ጊዜን የማያባክን የአሰራር ሥርዓትን በመዘርጋት ላይ ትገኛለች። ይህ የአራተኛው ትውልድ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ዲጂታል ሥርዓት አያሌ ተግባራትን ለማከናወን እንዲቀል ጉልህ ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል። አገራት የኢኮኖሚ፣ ማሕበራዊና መሰል ዘርፎችን ከቴክኖሎጂና ዲጂታል ሥርዓት ጋር በማዋሃድ የበላይነትን ለመውሰድ ጥረት ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ይህ ነው የሚባል አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ባትችልም አሁን አሁን ግን ተስፋ ሰጪ ጥረቶች እየታዩ ይመስላሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው። መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠትና ማእከሎችን በመገንባት እንዲሁ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች በዲጂታል ሥርዓት እንዲመሩ በማድረግ የአራተኛውን ትውልድ የውድድር መንገድ ቀስ በቀስ እየተቀላቀለ ይመስላል። ለዚህ ማሳያ እንዲሆነን አሁን ላይ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሰጡ የዲጂታልና ኦላይን አገልግሎቶችን በምሳሌነት በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አምድ ላይ እናንሳ።
የኦላይን አገልግሎት
ዜጎች በተለያየ ምክንያት ወደ መንግሥት ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ይሄዳሉ። ይሁን እንጂ ፈጣንና ጊዜን የሚቆጥብ የአሰራር ሥርዓት ይፈትናቸዋል። አገራት ይሄን ችግር ለመቅረፍና ደንበኞችን ማእከል ያደረጉ አሰራር ሥርዓቶችን ይዘረጋሉ። ከዚህ ውስጥ የዲጂታል ክፍያ መንገድ አንዱ ነው። ይህ ሂደት አሁን ላይ በዓለማችን እጅግ ቀልጣፋና ተመራጭ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ መሰል ሥርዓት ለመዘርጋት ጥረቶች እተደረጉ እንደሚገኝ የዘርፉ አንቀሳቃሽ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ይፋ አድርጓል። ጥቂት ይሁኑ እንጂ ከዚህ ቀደምም የበይነ መረብን በመጠቀም ክፍያን ከመፈፀም ጀምሮ መሰል አግልግሎቶችን የሚሰጡ ተቋማት ነበሩ። አሁን ደግሞ ይሄን ሥርዓት በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አውቀናል።
ከእነዚህ ሙከራዎች መካከል የኢትዮጵያ መንግሥት የኦንላይን አገልግሎት ክፍያዎችን በዲጂታል አማራጭ እንዲፈፀሙ ሊያደርግ መሆኑን ነው። ለምሳሌ ያክል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ማስተር ካርድ የመንግሥት አገልግሎት የክፍያ ሥርዓትን ለማዘመን የሚያስችላቸውን ስምምነት በቅርቡ ተፈራርመው ነበር። ይሄ እርምጃ የዲጂታልና ኦላይን ሥርዓት በአገራችን የአገልግሎት ዘርፍ ላይ ወደፊት የሚኖራቸውን ድርሻ የሚያመላክት ይመስላል። ለመሆኑ “የኦላይን ክፍያዎችን በዲጂታል አማራጭ” ስንል ምን ማለታችን ነው። ለዚህ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መልስ ይኖረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የማስተር ካርድ የክፍያ አማራጭን ከኢ ሰርቪስ አገልግሎት ፖርታል ጋር በማቀናጀት ዜጎች ክፍያዎችን ኦንላይን እንዲፈፀሙ የሚያስችል ነው። ጉዳዩን ዘርዘር ባለ መንገድ የሚያስረዱት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ጥረታችን ኢትዮጵያን ከጥሬ ገንዘብ ህትመትና ስርጭት ወጪ ማላቀቅና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂያችን ተግባራዊ ማድረግ መሆኑን ይገልፃሉ። ከማስተር ካርድ ጋር የሚደረገው ትብብር ሁለገብ ዲጂታል የክፍያ መፍትሄዎችን በማቅረብ ዜጎች በማንኛውም የባንክ ካርድ ክፍያ እንዲፈፀሙ ያስችላቸዋል። የገቢ አሰባሰብን ለማሻሻል እና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል።
የማስተር ካርድ የምስራቅ አፍሪካ ሥራ አስኪያጅ ሸርያር አሊ ቀልጣፋ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ፈጠራ የታከለበት የዲጂታል የክፍያ አማራጮችን በመዘርጋት የኢትዮጰያ መንግሥትን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እንደሚደግፉ ነው የሚገልፁት።
ከውጭ አገራት ጭምር ባሉበት ቦታ ሆነው ለተጠቀሙት የመንግሥት አገልግሎት በማስተር ካርድ የክፍያ አማራጭ ክፍያዎችን ኦንላይን መክፈል ይችላሉ። በመጀመሪያው ዙር የትግበራ ምዕራፍ የኢትዮጵያ ሲቪል ማሕበራት ድርጅት አባላት ይህንን የክፍያ መተግበሪያ አማራጭ በመጠቀም ፍቃድ ለማውጣትና ለማደስ በማንኛውም የክፍያ ካርድ አይነት ክፍያ መፈፀም ይጀምራሉ። ይህንን አሰራር ለመተግበር ማስተር ካርድ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስምምነት ላይ የደረሱት በ2020 ሲሆን ይህም “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቲጂን” መሰረት በማድረግ ነው።
ከዚህ ስምምነት መረዳት የምንችለው የኢትዮጵያን የክፍያ ሥርዓት በዲጂታል ኦላይን በማስተሳሰር ከየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ ዜጎች አገልግሎቱን ያለምንም መጉላላት እንዲያገኙ እድል መፍጠሩን ነው።
ድንበር ተሻጋሪ ዲጂታል ሥርዓት
ከላይ ላነሳነው ርእሰ ጉዳይ ተጨማሪ አስረጂ ተግባር የሚሆነን ደግሞ በትራንስፖርቱ ዘርፍ የዲጂታል ሥርዓት ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር እየዘረጋች ያለው ቴክኖሎጂን ይመለከታል። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች በጎረቤት አገራት ወደብ ተጠቅማ እንደምታመጣ የሚታወቅ ነው። ይህ ተግባር ደግሞ በተለይ አሁን ላይ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የማይታገዝ ከሆነ ከጊዜ፣ ጉልበትና አላስፈላጊ ወጪ ጋር ተያይዞ ኪሳራዎች መፈጠራቸው አይቀርም።
በዚህ ዘርፍ ላይም የኢትዮጵያ መንግሥት መሻሻሎችን ለማምጣት ሳይንሳዊ መፍትሄን እየፈለገ ይገኛል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የዲጂታል ድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት ሥርዓት ለመገንባት መስማማታቸው ነው። ለመሆኑ “ድንበር ተሻጋሪ ዲጂታል ትራንስፖርት” ስንል ምን ማለታችን ይሆን? ሁለቱ አገራትስ በምን መልኩ ነው ይሄን ሥርዓት የዘረጉት?
ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የዲጂታል ድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ ሥርዓትን በትብብር ለመምራትና መረጃዎችን መጋራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ነው የተፈራረሙት። ይህ ስምምነትም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ እና ከዚህ ቀደም የነበረውን ኋላቀር የመረጃ አያያዝ በማዘመን ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚረዳ መገንዘብ ይቻላል። በተለይ ኢትዮጵያ አገልግሎቶችን በኦላይንና ዲጂታል ሥርዓት በመምራት በምታደርገው ጥረት ላይ አዲስ እሴት የሚጨምር ነው። በተለይ የሁለቱ አገራት የትራንስፖርት ስምምነት መረጃዎቹ ደህንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ እና በሕጋዊ አካሄዶች ለመከወን የሚያስችላቸው ነው። የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ በተመለከተ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ለመዘርጋት የተስማሙት ኢትዮጵያና ጅቡቲ የጭነት ትራንስፖርት ሥርዓታቸውን ለማሳለጥ ጠቀሜታ እንዳለው አምነውበታል።
ነዳጅና የኦላይን አገልግሎት
የነዳጅና ኢነርጂ ዘርፍ በዲጂታል ቴክኖሎጂ መመራት ካለበት ዘርፍ ውስጥ ቀዳሚው ነው። መንግሥትም ከፍተኛ ሀብት የሚያንቀሳቅሰውን ይህን ተቋም በቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ አሰራር ሥርዓት ለማገዝ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በቅርቡ ይፋ እየሆኑ ካሉት መረጃዎች መገንዘብ ይቻላል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ለዛሬው ርእሰ ጉዳያችን አስረጂ የሚሆነን ከሰሞኑ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን 46 አገልግሎቶቹን ኦንላይን ለመስጠት የሚያስችለውን ሥርዓት አስመርቆ ማስጀመሩ ነው።
የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያደረሰን መረጃ እንደሚያሳየው አገልግሎቶቹ ሙሉ ለሙሉ በሚኒስቴሩ የለሙ ሲሆን የኤሌክትሪክ ሥራዎች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መስጠት፣ እድሳት ማድረግ፣ ምትክ መስጠት፣ አዲስ ጊዜያዊና ቋሚ የኢነርጂ አገልግሎት ኩባንያ ፍቃድ መስጠት፣ ኦን ግሪድ የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ፣ ማመንጨትና ማከፋፈያ የሥራ ፍቃድ መስጠት፣ ንግድ ፍቃድ ማደስ እና ሌሎችንም የያዘ ነው። ተመርቀው ወደ ሥራ የገቡት አገልግሎቶች አጠቃላይ በኦንላይን የሚሰጡ የመንግሥት አገልግሎቶችን ብዛት ወደ 331 ከፍ አድርጎታል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ውስጥ ማነቆ የነበረውን የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር ችግር ለመቅረፍ ፀድቆ ወደ ሥራ ከገባው የትራንዛክሽን አዋጅ በተጨማሪ የተለያዩ ሕግና መመሪያዎች እየተዘጋጁ ይፋ አድርጓል። የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑን መስሪያቤቶቹ በማመን በትብብር የኦላይን ዲጂታል የአሰራር ሥርዓትን በጋራ መዘርጋት ችለዋል።
ይህ የዲጂታል ኦላይን ሥርዓት በመግቢያችን ላይ እንዳነሳነው በወረቀት ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች የሚያስቀር ሲሆን፤ በዲጂታል ሥርዓት በተደራጀ መልኩ መስጠታቸው የተቀላጠፈ አገልግሎት ለተገልጋዮች ለመስጠት ያስችላል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የለሙት አገልግሎቶች ሳይቆራረጡ ለአገልግሎት ፈላጊዎች አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግና በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግሥት ተቋማቶቹን በዲጂታል ሥርዓት ለማስተሳሰር የሚያደርገውን ጥረት ቀጥሎበት ልክ እንደ ሌሎቹ ሁሉ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ስድስት አገልግሎቶቹን በኦንላይን መስጠት መጀመሩን ይፋ የተደረጉ መረጃዎች ያመለክታሉ። እነዚህ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ውጤቶች በተመሳሳይ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የለሙ ሲሆን የፈሳሽ አገልግሎት ቦቴ ትክክለኛነት ማረጋገጫ፣ ድጋሚ ትክክለኛነት ማረጋገጫ፣ ምትክ ማረጋገጫ፣ ምትክ መለያ ቁጥር፣ የሚዛን ልኬት ትክክለኛነት ማረጋገጫና ምትክ ማረጋገጫ አገልግሎቶች ናቸው።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለ መኮንን የፈሳሽ ጭነት አገልግሎት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በቴክኖሎጂ ለመፍታት እና ፍትሃዊ ውድድር እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ።
አገልግሎቶቹ በኦንላይን መስጠታቸው ግልፅ፣ ቀልጣፋና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር እንዲኖርና ተገልጋዩ በከፈለበት ልክ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዜጎች የመንግሥት አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ ሁኔታ ባሉበት ሆነው እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። እስካሁን በ25 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት 282 የሚጠጉ አገልግሎቶች ለምተው በሥራ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚህ አመት 400 የመንግሥት አገልግሎቶችን ኦንላይን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። የለሙት ሥርዓቶች ሳይቆራረጡ ለማሕበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በመንግሥት የሚተዳደሩት ተቋማት ያደርጋሉ።
እንደ መውጫ
ከላይ በተለያዩ መረጃዎች ለመመልከት እንደሞከርነው መንግሥት አገልግሎት የሚሰጥባቸው ተቋማት ቀልጣፋ፣ ተአማኒና ጥራትን መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ነው። ይሁንና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዓለማችን በፈጣን ለውጥ ውስጥ ከመገኘቷ አንፃር ኢትዮጵያ ብዙ ርቀትን መጓዝ ይጠበቅባታል።
በተለይ የፈጠራ ባለሙያዎችን በማፍራት፣ ተቋማት ሳይንስና ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ አገልግሎቶችን በጥራት መስጠት የሚችሉበት ቁመና እንዲኖራቸው አድርጎ በመገንባት እንዲሁም ማሕበረሰቡ ለኦላይን ዲጂታል አገልግሎቶች ቀና አመለካከትና የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ አሁን ካለው በተሻለ የቴክኖሎጂ ልቀት አድማሱን ማስፋት ያስፈልጋል በማለት የዛሬውን ርእሰ ጉዳይ ማጠንጠኛ እዚህ ላይ እንቋጫለን ። ሰላም!
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መጋቢት 27 /2014