ዓለማችን በታላቅ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች። የኃያላን ጉትቻ ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ እንደ እንዝርት እየሾረ ነው። በዚህ የክረት መጠን ከቀጠለ ተበጠሶ ጥፋት የማያስከትልበት ምንም ምክንያት የለም። የታላላቆቹ አገራት ፍጥጫ የኃይል ሚዛኑን ወደ አንደኛው ወገን እንዲያዘነብል የሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ትግል ውጤት ነው። ጉዳዩ በዝሆኖቹ ፍትጊያ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። እያንዳንዱን አህጉርም ሆነ አገር በየደረጃው የገፈቱ ቀማሽ የሚያደርግ ነው።
የዚህ ፍጥጫ ውጤት ሳይውል ሳያድር አውሮፓውያኑን በቁጣ ማዕበል እየጎበኘ ነው። «ሩሲያ ለምን ዩክሬንን ወረረች» በሚል የማዕቀብ ናዳ በሞስኮ ላይ ያዥጎደጎዱት እነ አሜሪካና ምዕራባውያን በለኮሱት እሳት መለብለብ ጀምረዋል። ምልክቱ ስፔን ላይ እየታየ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ጦርነቱን ተከትሎ በተወሰዱ ማዕቀቦች የተበሳጨችው ሞስኮ የነዳጅ ምርቶቿን እቀባ ተከትሎ እየተፈጠረ ባለ የኢኮኖሚ ጫና ነው።
ይህ ያልተገመተ ቀውስ የስንዴና የተለያዩ የምግብ ሸቀጦች ከሩሲያ በሚያስገቡት አገራት ላይ ጭምር ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረ ያለ ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ላይ አገራት ግጭቱን ተከትሎ በተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ተጎጂ መሆናቸው እንደማይቀር ተንታኞች እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።
ወደ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ስንመጣ ደግሞ አሁንም የዘይት፣ በተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች፣ ሲሚንቶ እና ብረት … መናር ማኅበረሰቡ ላይ ጫና እየፈጠረ ይገኛል። የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች መናር ሥራ አጥነትን እየፈጠረ ከመሆኑም በላይ የኅብረተሰቡና የባለሀብቱን እጅ እንዲያጥር እያደረገው ይገኛል። ከሰሞኑ እንኳን ከፋብሪካ በ400 ብር አካባቢ የሚወጣ ሲሚንቶ ገበያ ላይ እስከ 1 ሺ ብር ይቸበቸባል።
ነጋዴዎች የዘይትና ሸቀጣሸቀጥ ምርቶችን እንደሚደብቁና ለምጣኔ ሀብት ንረቱ ምክንያት እንደሆኑ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለመሆኑ ለዚህ ምክንያት «የዓለም አቀፍ ወቅታዊ ግጭት ጫና» ወይስ «የስግብግብ ነጋዴዎችና ደላሎች አሻጥር» ነው? የመንግሥት ተቆጣጣሪና አስፈፃሚ አካላት ሚናስ እጅን ወደ አሻጥሩ ያስገባ ወይስ የሰበሰበ የሚለውና ሌሎችስ?
ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ኢትዮጵያውያን በብዙ ተፈትነናል። የኮሮና ወረርሽኝ፣ በአገር ውስጥ በተፈጠሩ ሽብርተኛና ተላላኪ ቡድኖች በሚፈጠር ቀውስ፣ የዓለም ኃያል አገራት የኃይል ሚዛን ለውጥ መጓተትና የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ድርቅ የፈጠረው የምጣኔ ሀብት ጫና ደግሞ እየፈተኑን ካሉ ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ይህ ሁሉ ጫና እያለብን ደግሞ ስግብግብ ነጋዴዎችና ከእነርሱ ጋር የሚያብሩ ደላሎች የገበያ ሥርዓቱ እንዳይረጋጋ በማድረግ ሁኔታውን «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንዲሆን እያደረጉት ይገኛሉ።
አሁን አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የደላሎች ሚና አለቅጥ እየተለጠጠና መስመሩን እየሳተ ይመስላል። እጃቸው ከመርዘሙ የተነሳ የገበያ ሥርዓቱን በምን መልኩ መሄድ እንዳለበት እስከመወሰን እየደረሱ ይገኛሉ። ሃይ ባይ ከማጣታቸውም በላይ የሴራ መረባቸውን እስከ ከፍተኛ መንግሥት አመራሮች ድረስ ዘርግተው ኅብረተሰቡን ቅርቃር ውስጥ እየከተቱት ነው።
ከእነዚህ ማፊያዎች ሴራ ጋር የአገር ውስጥ መረጋጋት መጥፋት እና ከዓለም አቀፍ ቀውሱ ጋር ሲደመር ሁኔታውን ከድጡ ወደ ማጡ እየወሰደው ይገኛል። መንግሥት አርቴፊሻል የኑሮ ውድነት በሚፈጥሩ ነጋዴና ደላሎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ በተደጋጋሚ ሲናገር ብንሰማም ቅሉ ግን እንደ ችግሩ ስፋት እርምጃው በዚያኑ ልክ ፈጣንና መፍትሄ አ ምጪ እንደሆነ አይሰማንም።
የገበያ ሰንሰለት ውስጥ አምራች፣ አከፋፋይና ሸማች በጤናማ ሥርዓት መገበያየት ሲገባው ሳይሠሩ መበልፀግ የሚሹ ጎረምሶች በድለላ ሰበብ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ላይ በመግባት የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ያደርጋሉ። በሸቀጣሸቀጥ ላይ ብቻ ሳይሆን በቤት ኪራይ፣ በተለያዩ ቁሳቁሶችና መሰል ምርቶች ላይ እጃቸውን በመስደድ ዜጎች እንዲማረሩና በመንግሥት እምነት እንዳያድርባቸው ያደርጋሉ። የተለያዩ የግል ፍላጎቶቻቸውን በዚሁ በዘረጉት መረብ ውስጥ ለማሳካት ሲጋጋጡ ይታያሉ።
ችግሩን ይበልጥ አስከፊ ያደረገው ደግሞ በቁጥጥርና ሕግ ማስከበር ሥርዓት ውስጥ ያሉ የመንግሥት አካላት እጃቸው እንዳለበት አንዳንድ መረጃዎች ማሳየታቸው ነው። እነዚህን አደራ በል አመራሮች መንግሥት በአፋጣኝ እርምጃ ወስዶ እጃቸውን ከሴራ ውስጥ እንዲያወጡና ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ ካልቻለ ጉዳቱ ከምንም ነገር በላይ የከፋ እንደሚሆን አያጠራጥርም።
ሕገወጥ ደላሎች ለምጣኔ ሀብት ቀውሱ ምክንያት የሚሆኑት በዚህ መልኩ ነው። የመጀመሪያው የተዛባ መረጃ በማኅበረሰቡ ውስጥ በመንዛት መረጋጋት እንዳይፈጠር ማድረግ፣ ምርቶች ከገበያ ውስጥ እንዲጠፉ ማሴር፣ ይህንን ተከትሎ ተገቢ ያልሆነ የትርፍ ህዳግ ነጋዴው እንዲሰበስብና ከዚያም የራሳቸውን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ። በዚህ ድርጊታቸው ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ዜጎች በቀጥታ ተጎጂ ከመሆናቸውም በላይ የዋጋ ግሽበቱ እንዲጨምር ምክንያት ይሆናሉ።
መንግሥት በሕገወጥ ደላሎችና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ተባባሪዎች ላይ እወስዳለሁ ያለው እርምጃ ተገቢ ቢሆንም ፈጣንና ከመቼውም ጊዜ በተለየ ርብርም የሚጠይቅ እንደሆነ እናምናለን። ነገር ግን ለጊዜው የሕዝብን ስሜት ለማረጋጋት ከሆነ ዘላቂ ለውጥ እንደማይመጣ መገንዘብ ይኖርብናል። ይህንን የምንልበት ምክንያት አሁን አሁን እየባሰ ከመጣው የዘይት፣ ስኳርና መሰል ሸቀጣ ሸቀጦች ውጪ ለዓመታት እየተንከባለለ የመጣው የሲሚንቶ እና የብረታ ብረት ምርት ላይ የሚፈጠረው አለመረጋጋት እንደ መነሻ አድርገን ነው።
መንግሥት ለበርካታ ጊዜያት የሲሚንቶ ምርት ላይ የሚፈጠር የሕገ ወጥ ደላሎችን ሴራ ለመበጣጠስ ጥረት እያደረገ መሆኑ ቢነገርም በተቃራኒው ግን «ከሄድ መለስ» ውጪ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት አልቻለም። ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው ኮንትራክተሮች እንዳረጋገጡት ቸርቻሪዎች ዘንድ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ እስከ 1000 ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል።
ለምግብነት ከሚውሉት ሸቀጣ ሸቀጦች ውጪ እንኳን የሲሚንቶ ዋጋ ንረቱ ገሃድ የወጣ ነው። የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር ለንረቱ እንደ ዋንኛ ምክንያት ሕገወጥ ደላሎች መሆናቸውን አረጋግጧል። መንግሥትም በተደጋጋሚ ይህን ቃል ሲናገር ተደምጧል። ለመሆኑ የእነዚህን ሕገወጥ ደላሎች መረብ መበጣጠስ ያልተቻለበት ምክንያት ምን ይሆን?
ከተለያዩ መረጃዎች እንደምንሰማው እዚህም እዚያም በሕግ አስከባሪዎች አማካኝነት እየተወሰዱ የሚገኙ እርምጃዎች ጭርሱኑ ሕገወጥነቱ ስር እንዳይሰድ ለማድረግ ሚና እንዳላቸው እናምናለን። ይሁን እንጂ ስር ነቀል እርምጃ ወስዶ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ግን ዜጎች ከየትኛውም ጊዜ በተለየ ይሻሉ።
መንግሥት በደህንነት ቢሮ አማካኝነት ትክክለኛውን መረጃ ለመሰብሰብ መዋቅር መዘርጋትና የሕገወጥ ደላሎችን መረብ ለመበጠስ እንደሚችል እናምናለን። የደህንነት ክንፉ በቂ የመረጃ ምንጭ የሆኑ አካላት በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉት ይታወቃል። ይህ ከሆነ «ስር የሰደደውን የሕገወጥ ደላሎች እጅ» ለማነቅ ለመንግሥት ያን ያክል ከባድ አይሆንም ማለት ነው።
ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠረው የአገር ውስጥ አለመረጋጋት፣ የዓለም የኃይል ሚዛን ለመቀየር የሚደረግ ፍጥጫ፣ ድርቅ እና በወረርሽኝ ምክንያት የተፈጠረው የምጣኔ ሀብት ቀውስ በተጨማሪ «ከድጡ ወደ ማጡ» እንዲሄድ በሴራ የሚሠሩትን ሕገወጥ ደላሎች ፈተና እንዳይሆኑ መንግሥት መፍትሄ እንዲያበጅላቸው እንጠይቃለን። ምክንያቱም ግርግር ለሌባ ያመቻልና!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2014