ሚዛን በማኅበረሰባችን ዘንድ ነጋዴውን ከሸማቹ፣ ባለሱቁን ከደንበኛው የሚያግባባ..የሚያስማማ መተማመኛ ነው። ገበያ ወይም ሱቅ ሄዳችሁ የገዛችሁት ስኳር ልክ መሆኑን ለማረጋገጥ ሚዛን ትጠቀማላችሁ፤ ግራሙና የገዛችሁት ዕቃ እኩል ሲሆን ያኔ እውነት በሆነ መንገድ ገንዘባችሁን ከፍላችሁ ዕቃችሁን ትወስዳላችሁ። ያኔ ከሸጠላችሁ ሰው ጋር ትግባባላችሁ፤ ምክንያቱም በመካከላችሁ ሚዛኑ አለና። ግን ደግሞ ወይ ግራሙ ወይ የገዛችሁት ዕቃ ወደ አንድ ጎን አጋድሎ ከሁለት ለአንዳችሁ ካደላ በመካከላችሁ መተማመን የለም ማለት ነው። ነገ ላይ ከዚያ ሰውዬ ዕቃ አትገዙም። ነጋዴውም ለእናንተ ለመሸጥ ፍቃደኛ አይደለም።
ይህን እውነት ወደ ሕይወት ስናመጣው እንዲህ ይሆናል፤ ሕይወት የብዙ አስተሳሰቦች ጥርቅም ናት፤ በዙሪያችን በርካታ እይታ በርካታ አመለካከት ያላቸው ሰዎች አሉ፤ ከነሱ ጋር ነው የምንኖረው በዚህ የጋራ ሕይወታችን ውስጥ የኔ አስተሳሰብ ሌላውን እንዳይጎዳ የሌላውም አመለካከት እኔን እንዳይጎዳኝ ሆነን በመቻቻል መኖር አለብን። ልክ እንደሚዛኑ ሁሉ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ለሌሎች የሚሆን ሚዛናዊ እውነት ሊኖረን ይገባል።
ስንኖር ራስ ወዳድ በሆነ የእኔነት ስሜት ወደራሳችን ብቻ የምናተኩር ከሆነ የሌሎች ፍቅርና አብሮነት እየራቀን ይመጣል። የሌሎች ፍቅርና አብሮነት ራቀን ማለት በሕይወት ለመኖር አቅምና ጉልበት አይኖረንም። በመካከላችን መለያየትና መገፋፋት ይፈጠራል። ይሄ እንዳይሆን ልክ እንደሚዛኑ ሁላችንንም የሚያስማማ የጋራ ሀሳብ፣ የጋራ እውነት ያስፈልገናል። እናም ሚዛናዊ እይታ ለአገር እድገት ከፍተኛ ሚና አለው።
በአሁኑ ሰዓት አገራችን ኢትዮጵያ የተቸገረችበት አንዱና ትልቁ ነገር ሁሉን አቃፊ የሆነ ሚዛናዊ እይታ አለመኖር ነው። እይታችንም ሆነ አስተሳሰባችን አንድን ወገን ብቻ የሚጠቅም፣ ለአንድ ወገን ብቻ የሚወግን የተወሰነ ነው። ይህ የተንሸዋረረ እይታ ይባላል። እይታችን ካልጠራ፣ አስተሳሰባችን ከወገንተኝነት ካልጸዳ ከግለሰባዊነት ባለፈ የምናመጣው ማህበራዊ ለውጥ የለም። ለውጥ መልካም ልብ፣ መልካም ነፍስ ይፈልጋል። ብዙዎቻችን የቆምነውም በሌሎች ድጋፍ ነው። አሁን ያለንበት ቦታ ለመቆማችን ብዙዎች ዋጋ ከፍለዋል። ራሳችንን ችለን የቆምን ይመስለናል እንጂ ለብቻችን የገነባነው አንዳች ሕይወት የለንም። በዚህ ዓለም ላይ ካለሌሎች እገዛ፣ ካለሌሎች ፍቅር ራሱን ችሎ የቆመ ማንም የለም።
በሕይወት ለመኖር አንዳችን ለአንዳችን እናስፈልጋለን። የብቻ ሀሳብ፣ የብቻ ኃይል አገር አያቆምም። ብዙዎቻችን ግን ይሄን እውነት አናውቀውም በአስተሳሰባችን፣ በንግግራችን፣ በማኅበራዊ ሕይወታችን ሌሎችን እንዳገለልን፣ ሌሎችን እንዳስቀየምን ነው። በፍቅርና በአብሮነት ለመኖር በመካከላችን የሀቅ ሚዛን ያስፈልጋል። ቅዱስ አስተሳሰብ፣ ቅዱስ እይታ ግድ ይለናል። መዝኖ ሲሰጠን ካለምንም ቅሬታ ባለሱቁን እንዳመንነው ሁሉ በማኅበራዊ ሕይወታችንም መተማመን አለብን።
ካለምንም ፍራቻና ጥርጣሬ እርስ በርስ መጠጋጋት አለብን። ጊዜአችንን ሊጠቅሙንና አገር ሊቀይሩ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ማሳለፍ አለብን። አሁን ላይ እየሆንን ያለነው ነገር ለእኛ የሚመጥን አይደለም። ዓለምን አሰልጥነን ፊተኛ አድርገናል፣ በእኛ ቀደምትነት ፊተኝነትን ያገኙ የውጭ አገራት እኛን ለማስማማት መሀከላችን እስኪገቡ መጠበቅ አይኖርብንም። ለአገራችን ስንል የመለያየትን ግድግዳ ማፍረስ አለብን።
እዚህ ምድር ላይ ለዘላለም አንኖርም። ነገን የማናውቅ እኛ፣ በትንታ የምናልፍ እኛ ይሄን ያክል እርስ በርስ መጨካከንና መጎዳዳት የለብንም። ምናልባትም ከሃምሳና ከመቶ አመት በኋላ እዚህ ምድር ላይ በሕይወት የለንም። አሁን እንኳን ብዙ እያሰቡ፣ ብዙ እያለሙ ከአጠገባችን በሕይወት የሌሉ ብዙ ናቸው። መኖር እየፈለጉ ያልኖሩ፣ ነገን ለማየት እየጓጉ ያላዩ ብዙ ወዳጆች ብዙ ቤተሰቦች አሉን..ታዲያ ስለምን እንባላለን? ስለምን ክፉና ጨካኝ እንሆናለን?
መልካምነት እኮ ክፍያ የለውም። ጥሩነት እኮ ለማንም በነፃ የምንሰጠው አምላካዊ ስጦታ ነው። አልገባንም እንጂ አሁን ላይ ዋጋ እየከፈልንባቸው ያሉ ነገሮች ሁሉ የማይጠቅሙን ናቸው። የከፍታ ስፍራ መስለውን እየሄድንባቸው ያሉ ጎዳናዎች ሁሉ የሚጥሉን ናቸው። ብዙዎቻችን ሕይወትን ውስብስብ በሆነ መንገድ የምንመራ ነን። ካልተጨነቅን፣ ካልተጠበብን ካልወጣንና ካልወረድን መሽቶ የሚነጋ የማይመስለን ብዙዎች ነን። ካልዋሸን፣ ካላጭበረበርን የምንኖር የማይመስለን ሞልተናል።
ሕይወት እንዲህ አይደለም..ምኞትና ድርጊታችን ስላልተገናኘ አብዛኛው ነገራችን ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ነው። መልካም ሕይወት በገንዘብ ብቻ የሚመጣ የሚመስለን አለን። የምንፈልገውን ነገር ሁሉ በጭንቀታችን በኩል የምናገኝ የሚመስለን ሞልተናል። ካለመልካም ሀሳብ የሚሆን ምንም የለም። መኖር የምንጀምረው ለሌሎች በቆምን፣ ለሌሎች መጨነቅ በጀመርን ማግስት ነው።
እስኪ ለአንድ አፍታ ለሌሎች መልካም በመሆን በሕይወታችን ውስጥ የሚመጣውን ለውጥ እንመልከት። እስኪ ለአንድ ጊዜ በመነጋገርና በመወያየት የምናመጣውን አገራዊ በረከት እናስብ። እስኪ ለአንድ ቀን ከነበርንበት እንውጣና በሚዛናዊ አስተሳሰብ ውስጥ ራሳችንን እናግኘው። ያኔ ካለድካም ካለውጣ ውረድ መኖር እንጀምራለን። ያ ጊዜ የአገራችን እረፍት፣ የትውልዱም ትንሳኤ ነው እላለሁ። ያኔ በሕይወታችን መጥቶ የማያውቅ ሰላምና መረጋጋት የእኛ ይሆናል። ያኔ ሕይወትን እንደ አዲስ ማየት ትጀምራላችሁ።
ይሄ ብቻ አይደለም ሚዛናዊ አስተሳሰብ ከዛሬ የተሻለ ብሩህ ነገን የሚፈጥር የኃይል ክምችት ነው። ከግለሰብ ወደ ማኅበረሰብ፣ ከማኅበረሰብ ወደ አገር የሚፈስ የለውጥ ኃይል ነው። አሁን ላይ እየሞትን ያለነው፣ ከስኬት ርቀን የቆምነው፣ ከድህነት መውጣት አቅቶን የምንሰቃየው በማይጠቅሙን ነገሮች ላይ ጊዜአችንን ስለምናጠፋ ነው። ለሌሎች ተስፋን በመስጠት፣ ለሌሎች ቅንና አዛኝ በመሆን ቀናችንን ብንጀምር ተዐምራት ይፈጠሩልን ነበር።
ለሌሎች የስኬት ምንጭ በመሆን፣ በየሆስፒታሉ የታመሙትን፣ በየእስር ቤቱ የታሰሩተን በመጠየቅ ሕይወታችንን ውብ ማድረግ እንችላለን። ካለን ላይ በማካፈል፣ በላቀ ምክረ ሃሳብ ችግሮቻችንን በመፍታት ለአገራችን አስፈላጊዎች መሆን እንችላለን። ይሄ ብቻ አይደለም በመልካም ሃሳብ ውስጥ መገኘት ብዙ ዕድሜ የሚያኖር እንደሆነም በሳይንቲስቶች ተረጋግጧል። ዕድሜአቸው ከመቶ አመት በላይ በሆኑ ወንድና ሴቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው ከሆነ ሁሉም አዛውንቶች በሕይወታቸው ውስጥ ለሌሎች መልካም ሥራን ያደረጉ ሆነው እንደተገኙ ተነግሯል።
ሀሳባችሁ ስኬታማ መሆን ከሆነ በመጀመሪያ ለሌሎች የስኬት ምክንያት ሁኑ። ሀሳባችሁ ከሌሎች የተሻለ ሰው መሆን ከሆነ ሌሎች የተሻሉ እንዲሆኑ መንገድ ጥረጉላቸው። በንግዳችሁ ትርፋማ መሆን ከሆነ ሌሎች በንግዳቸው ትርፋማ እንዲሆኑ አግዟቸው። በሕይወታችሁ፣ በኑሯችሁ እንዲሁም በትዳራችሁ ደስተኛ መሆን ከሆነ ደግሞ ከሁሉ በፊት እንዲሆንላችሁ የምትፈልጉትን ለሌሎች አድርጉ። ህልማችን ለአገርና ለትውልዱ ውለታ መዋል ከሆነ ተነጋግሮ መግባባት ያሻናል።
በዚህ ውስጥ ነው ስኬት ያለው…በዚህ ውስጥ ነው ስልጣኔ ያለው። የሚያስፈልገንን ከማወቃችን በፊት በመጀመሪያ ሌሎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንወቅ። የምንፈልገውን ለማግኘት ከመነሳታችን በፊት ሌሎች የሚፈልጉትን እንዲያገኙ መሰላል መሆን ይጠበቅብናል። የእኛ የሁላችን ስኬት የሌሎችን ስኬትና ደስታ ታኮ የሚመጣ ነው። የአገር እድገትና ብልጽግና የእኛን ሚዛናዊ እይታ፣ ሚዛናዊ ሀሳብ የሚፈልግ ነው። የእኛን አንድነትና እርቅ የሚሻ ነው። ለዚህም ነው ቀደም ብዬ የሚጠቅመን እያለ ወደማይጠቅመን የምንሄድ ነን ያልኩት።
የሚያስፈልገን ነገር አጠገባችን ነው ያለው..ሩቅ መሄድ አይጠበቅብንም። እኛ ከተስማማን፣ እኛ አንድ ከሆንን በረከቶቻችን ሁሉ ከአጠገባችን የሚፈልቁ ሆነው እናገኛቸዋለን። ሁሉም ነገር ለሌሎች በሆንነው ልክ የሚሆንልን ነው። ክፋታችንና ተንኮላችን ነገን እንዳናይ ከማድረግ ባለፈ የሚሰጠን ጥቅም የለም። አባቶቻችን እኮ ያስተማሩን ፍቅርን ነው። ይቅርባይነትን ነው።
እነርሱ አይደለም በጎረቤታቸውና በወንድሞቻቸው ላይ ሊጨክኑ ቀርቶ አገር ሊወር፣ ታሪክ ሊበርዝ የመጣውን የጣሊያን ወታደር እንኳን ማርከው በመግደል ፈንታ ውሃና ምግብ ሰጥተው በመልካም ስፍራ በማስጠለል ሕክምና የሚሰጡ ነበሩ። እኛ ከየት መጣን? እኛ የማነን? የምኒልክ የአብዲሳ አጋ አይደለን..ከዘርዐደረስ አብራክ የወጣን አይደለን? ስለምን በዚህ ልክ ክፉዎች ሆነን? አላውቅም..ስልጥንና ስይጥንና ከሆነብን ቆይቷል። መማር መደንቆር ከሆነብን ሰንብቷል። ትልቁንና ይቅር ባዩን እኛን ለትውልድ ማስተላለፍ እንጂ በገዳይነትና በጭካኔ ሌሎች እንዲያውቁን ማድረግ የለብንም።
መኖራችን ዋስትና የሚያገኘው ለሌሎች በምንሞተው ሞት ልክ ነው። ሕይወታችን ትርጉም የሚኖረው የሌሎችን ህመም በታመምነው ልክ ነው። የዚህ ዓለም መልካም ነገሮች ሁሉ በበጎ ሥራ ውስጥ የተደበቁ ናቸው። የሚያኖረን ፍቅር ነው የሚያኖረን የጋራ ሥርዓት ነው። ብዙዎቻችን በሕይወት የተደረገልንን መልካም ነገር አናይም። በሕይወት ውስጥ በረከት ሊያስገኙልን የሚችሉ ነገሮች በነፃ የምናገኛቸው ነገሮች እንደሆኑ ብዙዎቻችን አናውቅም። ገንዘብ ካላወጣን፣ ካለፋን ካልደከምን ጥሩ ነገር የምናገኝ የማይመስለን ሞልተናል እውነቱ ግን ይሄ አይደለም የደስታችን አጥቢያ ያለው ልባችን ውስጥ ነው። ለሌሎች በምንሰጠው ፍቅርና ክብር ልክ፣ ከሌሎች በምንቀበለው መልካም ምላሽ ልክ ጎዳናችን ይቀናል።
ሕይወታችንን፣ አካባቢያችንን ባጠቃላይ ዓለምን የምናይበትን የአስተሳሰብ ሚዛናችንን ማስተካከል ግድ ይለናል። የእይታ ሚዛናችን ሳይስተካከል የምናደርገው ጉዞ ገደል ነው የሚከተን። አሁን ላይ እዛም እዚም የምናያቸው ነውጦች፣ ሞቶች፣ መፈናቀሎች እይታቸው በተዛባ ግለሰቦች የተፈጠሩ ናቸው። ሰውነትን ባልተረዱ፣ ፈጣሪን በማይፈሩ፣ ፍቅርን በማያውቁ ጥቂት ግለሰቦች የሚፈጸም ነው።
ወደዚህ ዓለም ነፍስ እንድናጠፋ አልመጣንም። በሚያስደንቅ ፍቅር የሌሎችን ሞት እንድንሞት፣ የሌሎችን ስቃይ እንድንሰቃይ ነው ሰው የሆንነው። ወደዚህ ምድር ደም ለማፍሰስ አልመጣንም…የሌሎችን እንባ እንድናብስ፣ የሌሎችን ሲቃ እንድንገታ እንጂ። እንድንራራ፣ እንድንምር እንጂ ለጭካኔ አልተፈጠርንም። እንድንመርቅ..እንድናስደስት እንጂ እንድናሳዝን ሰው አልሆንም። የብዙዎቻችን የአስተሳሰብ ሚዛን በተዛባበት ሰሞን ላይ ነን። ወደ ብልጽግና እየገሰገስን፣ ወደ ልማት፣ ወደ ለውጥ እየሄድን ወደ ኋላ የምናይ ብዙዎች ነን። ኢትዮጵያ ክብሬ ናት፣ ደሜ..ማዕረጌ ብለን በአደባባይ መስክረን ዞረን ለኀዘኗ ምክንያት የምንሆን እንዲህም ነን።
የአስተሳሰብ ሚዛን መዛባት ለአገርም ሆነ ለትውልድ የከፋ አደጋ አለው። እንዲህ ዓይነት ማንነት ለራስ ብቻ ከማሰብ ባለፈ ለሌሎች ግድ የለውም። በየቦታው ጥላቻና መለያየትን የሚሰብክ ነው። በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚዘራ ነው። ዋሽቶ ከማስታረቅ ይልቅ ዋሽቶ የሚያጣላ ነው። ባልሆነና ባልተደረገ ነገር ላይ የውሸት ማስረጃ እያቀረበ ሕዝብ የሚያባላ ነው። የአስተሳሰብ ሚዛን መዛባት ፍሬኑ እንደተበጠሰ መኪና ነው። ልንራመድ እንችላለን ወዴት እንደምንሄድ ግን አናውቅም።
ፍሬኑ የተበጠሰ መኪና ምን ጥቅም አለው? ጋራዥ ገብቶ በባለሙያ እስካልተስተካከለ ድረስ አደጋ ከመፍጠር የዘለለ ጥቅም የለውም። ፍሬናችን አስተሳሰባችን ነው…አስተሳሰባችን ሁሉ ነገራችን ነው። ትናንታችን ዛሬአችን ነጋችን ሳይቀር የተገነባው በአስተሳሰባችን ላይ ነው። በአስተሳሰባችን ላይ እክል ካለ በሕይወታችን፣ በኑሯችን በአጠቃላይ በእንቅስቃሴአችን ላይ ችግር አለ ማለት ነው።
አሁኑኑ መስተካከል ይኖርብናል። አሁኑኑ ወደ ሰላም ወደ አንድነት መመለስ ይኖርብናል። አላማችን አንድ አገር፣ አንድ ሕዝብ ከሆነ ሚዛናዊ አስተሳሰብ ያስፈልገናል። ይሄ ብቻ አይደለም ሚዛናዊነት የዘመናዊነት መገለጫም ነው። ሚዛናዊነት የእውቀት፣ የጥንካሬ ከሁሉ በላይ የሰውነት መገለጫ ነው።
እስኪ ራሳችንን እንፈትሽ..ምን ዓይነት ሰዎች ነን? ምንድነው የምናስበው? ለአገርና ሕዝብ የሚሆን ምን ጥሩ ነገር አለን? ምርጥነታችን ያለው በዚህ ጥያቄዎቻችን ውስጥ ነው። አንድ ነገር ሁሌም አስታውሱ ሀሳባችን ያለበት ቦታ እኛ አለን። ስሜት እንዲገዛችሁ አትፍቀዱ…ለራሳችንም ሆነ ለሌላው አስፈላጊ ሆነን ለመቆም እንሞክር። የምናምነውን እውነት እንኑር..ተነጋግሮ መስማማትን የሕይወታችን መርህ እናድርግ።
ሕይወትን በእውነትና በምክንያት መኖር አንዱና ዋነኛው የሚዛናዊ ጭንቅላት መገለጫ ነው። አገርን በመነጋገርና በመስማማት መምራት ሰላምና ብልጽግና ከሚፈጥራቸው መንገዶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው። እንዲህ ስንሆን ልዩዎች ነን፣ እንዲህ ስንሆን ዛሬም ነገም ሁሌም አስፈላጊዎች እንሆናለን። ሁላችንንም በሚያስማማ መልኩ ምርጥነት ለሌሎች መትረፍ፣ ለሌሎች መወገን ነው። በራስ እውነት ሌሎችን ማኖር መቻል እንዲህም ነው።
ምርጥ ሰዎች ምርጥ ነገር የሚያቡ ናቸው። በየትኛውም እውቀት በየትኛውም መመዘኛ ብታዩት ምርጥነት ከዚህ የዘለለ ትርጉም የለውም። ነገ ለምትፈጠረው ኢትዮጵያ በሚዛናዊነት የተቃኘ ሁሉን አቃፊ አስተሳሰብ ያስፈልገናል። የሁላችን የጋራ ቤት የሆነችውን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት ከአሮጌነት እንውጣ እያልኩ አበቃለሁ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2014