በዚች ሀገር የ”100”፣ የሦሥት ሺህም ሆነ የሰባት ሺህ ዓመት ዘመናዊ ሆነ ጥንታዊ የአገረ መንግሥት ታሪክ እንደ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መንግሥት እና እንደዚህ ሕዝብ በኃይለኛ የውቅያኖስ ማዕበል (ሱናሚ ) መካከል እንደምትቀዝፍ ታንኳ ከየአቅጣጫው የተላጋ ፣ የተናወጠ ፣ የተፈተነና መልሕቁን ለመጣል የተቸገረ የለም ማለት እችላለሁ ። ታሪካዊ ንጽጽሬ ላይ የዘመነ ጓዴነት /contemporaries/ ጥያቄ የሚያነሳ ካለ ደግሞ እንዲህ ላስተካክለው፡- ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በየትኛው አህጉር ያለ አገርና ሕዝብ እንደ ኢትዮጵያ የተፈተነ የለም። የመንም ፣ ሊቢያም ፣ ሶሪያምና ሶማሊያም ፣ ሌላም አገር ቢሆን ።
ለውጡ የባተበትን አራተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ይሄን ዘካሪ መጣጥፍ አራት ሻማዎችን ለኩሼ እያጠናቀርሁ እያለ እንኳ ፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በምስራቅ ሸዋ ፈንታሌ ወረዳ ቆርኬ አካባቢ በአካባቢ ሚሊሻና በፌደራል ፓሊስ አባላት ላይ አክራሪ ኃይሎች በፈጸሙት ጥቃት ለተገደሉ የሐዘን መግለጫ ያወጣ ሲሆን፤ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አድኖ ለሕግ ለማቅረብ የሚያደርገውን ጥረት ሕዝብ እንዲተባበረው ጠይቋል። እንዲሁም የአማራ ክልል ፤ የአማራን ሕዝብ እረፍት ለመንሳትና ከአጎራባች ክልሎች ጋር ለማጋጨት አክራሪ ኃይሎች በቅንጅት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን በመግለጽ ሕዝብ ከጎኑ እንዲሰለፍ ጥሪ አድርጓል ።
በአማራና በአፋር ክልሎች በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ የተነሳ ከ12 ሚሊየን በላይ ወገኖች ፤ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በተከሰተው ድርቅ የአርብቶ አደሩ የህልውና ዋስትና የሆኑ እንስሳት አልቀው በሚሊዮኖች የሚገመት ሕዝብ የዕለት ደራሽ እርዳታ ፈላጊ ሆነዋል። በአናቱ የቀደሙትንና ሰሞነኛዎችን ሳይጨምር እስከ አለፈው አመት በአገሪቱ 113 ማንነትን ኢላማ ያደረጉ ጭፍጨፋዎች ፣ ጥቃቶችና ግጭቶች በተቀናጀ አግባብ መፈጸማቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ያስታውሷል ።
በመላ አገሪቱ እየተስተዋለ ያለው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ሕዝቡን ክፉኛ እያማረረ ባለበት በዚህ ፈታኝ ሰዓት ፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ፤ የአሜሪካ ጥቂት የኮንግረስ አባላት ኤች አር 6600 እንዲሁም ኤስ 3199 የተሰኙ ረቂቅ ሕጎችን በማዘጋጀት እጅ አዙር የጭቆና ቀንበራቸውን ለመጫን እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው ፤ ዶ/ር ቴዎድሮስ ፣ አቡነ ማቲያስና በአገር ቤትም ሆነ በውጭ ያለው የሕወሓት ጭፍራ ይህ የማዕቀብ ሕግ እንዲጸድቅ በተናበበ መንገድ ጥረት እያደረገ ይገኛል ። (እዚህ ላይ ሕወሓት አቡነ ማቲያስን እንደፈለገ ቁጭ ብድግ የሚያደርጋቸው ፤ ከሲኖዶሱም ሆነ ከቤተክርስቲያኗ ቀኖና ውጭ ለዛውም በዓቢይ ጾም እንዲህ ያለ መግለጫ እንዲሰጡ የሚያደርጋቸው አንዳች ማስፈራሪያ ወይም (blackmail) ማድረጊያ ነገር ሳይዝባቸው አይቀርምና የሚመለከተው አካል ምርመራ ማድረግ ይገባዋል፤ የሚል ሀሳብ አለኝ) ።
ይሁንና ሁሉም ነገር ተስፋ አስቆራጭና ድቅድቅ ጨለማ ነው ማለት አይደለም ። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከክሽፈት ተርፎ በአንድ ተርባይን 375 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት መቻሉ በራሱ ትልቅ ስኬት ቢሆንም የቀጣናውን ጂኦፖለቲካ በመበወዝ የሚኖረው ሚና እጅግ ከፍ ያለ ነው ። በድህነታችንና በተመጽዋዕችነታችን ሳቢያ ፖለቲካዊ ብቻ የነበረውን ግማሽ የነጻነትና የሉዓላዊነት ታሪካችን ሙሉ የሚያደርግ የበጋ ስንዴ ልማት ሌላው ተስፋ የሚያሰንቅ ተግባር ነው ። 430ሺህ ሔክታር የበጋ ስንዴ ማምረት ባንችል ኖሮ በራሽያና በዩክሬን ጦርነት የተነሳ ጣራ የነካውን የስንዴ ዋጋ በምን ጎናችን እንችለው ነበር ። የቀድሞው የኢሳት ጋዜጠኛ ደረጀ ሀብተወልድ ይሄን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ ዘመኑን አበክሮ የዋጀና ትንቢታዊ ነው ይለዋል ። የዩክሬንና የራሽያ ጦርነት እንደሚቀሰቀስ ቀድመው ያወቁ ይመስል የበጋ ስንዴ በማስጀመራቸው ነው ውሳኔያቸውን ትንቢታዊ ነው ያለው ። ኩታ ገጠም ግብርና እና ሜካናይዜሽን ላይ እየተሠራ ያለው ሥራም ተስፋን የሚያለመልም ነው ። የአረንጓዴ አሻራውና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቱም የብሩህ ተስፋችን ቡቃያ ነው ።
አገራዊ ምክክር ለማድረግ መንግሥት ኮሚሽን በአዋጅ ማቋቋሙና ኮሚሽኖች በገለልተኛ አካል እንዲሰየሙ መደረጉ ፤ አካታች አገራዊ ምክክሩ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል ነው ። በማንነት በልዩነትና በጥላቻ የተጎነቆለውን ፖለቲካችንን እልባት የሚሰጥ ነው ። አገረ መንግሥቱን ከተቀለሰበት ድቡሽት አንስቶ በጽኑ መሠረት ላይ የሚያንጽ ነው። ትውልዶች ለዘመናት ሲያነሷቸው ሲታገሉላቸውና መስዋዕት ሲከፍሉላቸው የኖሩ ጥያቄዎችን በማያዳግም ሁኔታ የሚመልስ ነው ። አገራዊ ምክክሩ የጋራ አገር ፣ የጋራ ሕልም ፣ የጋራ ራዕይ ፣ የጋራ ሰንደቅ አላማ ፣ የጋራ ጀግና ፣ የጋራ ታሪክ ፣ ወዘተረፈ. እንዲኖረን የሚያግዝ ነው ። ገለልተኛነቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ከተመለሱና በቅንና ንጹሕ ሕሊና ከተመራ የትውልድ ተስፋና ለአገርም ወሳኝ መታጠፊያ/critical juncture/ ነው ። አገርን እንደ ንስር የሚያድስና በከፍታ የሚያበር ነው ።
የብሔራዊ ምክክሩን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዓርብ በማኅበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት ታሪክ የሚቀይሩ ወርቃማ የለውጥ ዕድሎች ገጥመዋታል ። ፖለቲካችንን አንድ ደረጃ ወደፊት የሚያስፈነጥሩና ቀጣይ ዘመናችንን ብሩህ የሚያደርጉ አያሌ የለውጥ ችቦዎች ተለኩሰዋል። እነዚያ ለውጦች የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ፤ ቁጭት ። በቁጭት ተጠንስሰው ፣ በቁጭት ተካሂደው፣ በቁጭት ይጠናቀቃሉ ። አብዛኛውን ጊዜ የለውጥ ምዕራፎች በሚጀምሩበት ወቅት የምንሰንቃቸው የለውጥ ሐሳቦች ዳር ከመድረሳቸው በፊት ሲኮሰምኑ በተደጋጋሚ አይተናል ። በለውጥ በሂደት ወቅት ግባችንን ለማሳካት ከመተባበር ይልቅ በጥቃቅን ጉዳዮች እርስ በእርስ መጓተቱን ስለምናስቀድም በመጀመሪያ ያስጎመጅ የነበረው የለውጥ ፍሬ በመንገዱ መሐል ተጨናግፎ ይቀራሉ ።
መጨናገፋቸውን ልብ የምንለው ዘግይተን በመሆኑ ዕድሎቹ ካለፉ በኋላ እንደ አገር መልሰን እንቆጭባቸዋለን። እኛ የቀደመውን ትውልድ “ይሄንና ያንን ቢያደርግ ኖሮ” እያልን እንደምንወቅሰው ሁሉ፣ የቀደመው ትውልድም ከእሱ በፊት የነበረውን ትውልድ ሲኮንን ነበር። ከዚህ የታሪክ አዙሪት ለመውጣት እስካልወሰንን ድረስ ነገ የእኛም ዕጣ ካለፈው የተለየ አይሆንም ። ዛሬ በቸልታ የምናልፋቸው አጋጣሚዎች ተደምረው ነገ ላይ የልጅ ልጆቻችን እኛን የሚወቅሱበት ምክንያት ይሆናል ። ይህ እንዳይሆን ዛሬ እጃችን ላይ የሚገኙ የለውጥ ዕድሎችን ሁሉ አሟጥጠን ለመጠቀም መረባረብ አለብን ። ለዘመናት እየተንከባለሉ ዛሬ ላይ የደረሱ የፖለቲካ ፈተናዎቻችንን በጉልህ መቅረፍ የሚያስችለንና መጻዒ ዘመናችንን አዲስ መሠረት ላይ የማቆም አቅም ያለው ብሔራዊ የምክክር ሂደት ዛሬ በእጃችን ላይ ያለ ወርቃማ ዕድል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ይህን ወርቅ የሆነ አጋጣሚ የስንት ልፋት እና የስንት ታሪክ ሂደት ውጤት መሆኑን ዘንግተን እንደ ጠጠር ከቆጠርነው በቀላሉ ልናጣው እንችላለን ። በተቃራኒው እንደ ዕንቁ አክብረንና ተንከባክበን ከተጠቀምንበት ዋጋው ከፍ ያለና ታሪክ ቀያሪ ዕድል ይሆናል ። ልጆቻችንም “አባቶቻችን እንዲህ በማድረጋቸው አገራችን እዚህ ከፍታ ላይ ደረሰች” ብለው የሚያመሰግኑበትን አጋጣሚ ይፈጥራል ።
አካታች ብሔራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ሒደቱ ተቀባይነት ያለው ሆኖ መከናወን አለበት ። ይኸም የሚሆነው ሁላችንም የምክክር ሂደቱን በበላይነት የሚመራውን የምክክር ኮሚሽን በተለያዩ መንገዶች መደገፍ፣ ማትጋትና ማጽናት ስንችል ነው ። በዚህ ጉዳይ ዳር ቆሞ መገኘት በታሪክ ፊት የሚያስወቅስ ተግባር ነው። ሁሉም አካል በባለቤትነት ስሜት ለምክክር ሂደቱ አስተዋጽዖ በማድረግ ተሳትፎውን ያረጋግጣል እንጂ አንዱ ጋባዥ ሌላው ተጋባዥ እንደሆነ አድርጎ መቁጠር ከታሪክ ተጠያቂነት ነጻ አያደርግም ።
በመንግሥት በኩል እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ድረስ የተቋቋመው የምክክር ኮሚሽን በቅልጥፍና መሥራት እንዲችል አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም ። የክልል መስተዳድሮች ቀናነት፣ ባለቤትነትና ታሪካዊ ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ለኮሚሽኑ ሥራ አስፈላጊ የሆነውን ግብአት በማቅረብ ለሥራው ምቹ ሁኔታ ሊፈጥሩ ይገባል ። ተፎካካሪ ፓርቲዎች በውይይቱ እንደሚሳተፍ ብቻ ሳይሆን እንደ ሂደቱ ባለቤት ለሂደቱ ቅልጥፍናና ስኬት አስፈላጊውን ሁሉ እንድታደርጉ በትኅትና እጠይቃለሁ ። ምሁራን ኮሚሽኑ አስተያየትና ምክረ ሐሳባችሁን በሚፈልግበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በቅድሚያ ተነሣሽነት ፤ የሂደቱ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የታሪካዊ ጉዟችን እና የዘመን አሻራችን ለሆነው ምክክር አስተዋጽዖዋችሁ የላቀ እንዲሆን እማጸናለሁ ።
የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች አገር ስምምነትን በምትፈልግበት በዚህ ወቅት አማካይ ሆናችሁ ሁሉን የማስማማት አደራ አለባችሁና የመቀራረቢያውን መድረክ በማገዝ አገራዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ ከልብ በመነጨ ትኅትና እጠይቃለሁ ። የሁሉም ኃላፊትነት ተደምሮ የሚወድቀው በአገርና በሕዝብ ትከሻ ላይ ነው ። ሁላችንም ልዩነቶቻችንን አቻችለን በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ አለብን ። ሕዝብ ያላከበረው እና ሕዝብ ያልደገፈው እንቅስቃሴ ውጤቱ መና ነውና መላ ኢትዮጵያውያን ድጋፋችሁ ፣ ተሳትፏችሁ ፣ ክብራችሁና ጸሎታችሁ ከኮሚሽኑ እንዳይለይ ከታላቅ አክብሮት ጋር እጠይቃለሁ ሲሉ ዶ/ር ዐቢይ ጥሪ አድርገዋል ።
በዚህ መጣጥፍ መግቢያ ላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው አገራችን በታሪኳ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተለይ ለውጡ ከባተ ወዲህ ባሉት አራት ዓመታት የገጠማትን አይነት ፈተና በታሪኳ ገጥሟት አያውቅም። ለዚህ ነው እነዚህን ፈታኝ የለውጥ ዓመታት በንፋስ ሊጠፉ በተቃረቡና በሚስለመለሙ አራት ሻማዎች ወክዬ የዐቢይ አራት ሻማዎች ጭላንጭል ያልኋቸው ። ኮንፊሽየስ ፣ “ ሺህ ጊዜ ጨለማን ከመውቀስ አንድ ሻማ መለኮስ ይሻላል ።” እንዳለው፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩና የለውጥ ኃይሉ በዚህ ድቅድቅ ጨለማ ከአንድም ሁለት ሶስት አራት ሻማዎችን በመለኮስ የኮንፊሺየስን ምክረ ሀሳብ የሰሙ ይመስላል ። ያው ሻማዎቹን የዐቢይ ብላቸውም በውስጠ ታዋቂነት መላው የለውጥ ኃይል ፣ እኔ ፣ አንተ ፣ አንቺ አለን ። ሆኖም ከንፋሱ ጋር እየታገሉ በሚሰጡት የብርሃን ፀዳል ጨለማውን አሸንፈው ወገግ ማለታቸው ፤ በቁጥርም መበርከታቸው አይቀርም ። ጨለማውን ከመርገም የተለኮሱ ሻማዎች እንዳይጠፉ የዜግነት ግዴታችንን እንወጣ !!! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2014 ዓ.ም