በአሁኑ ወቅት በፌስቡኩ መንደር መልካም እና ገንቢ እሳቤዎች የሚንሸራሸሩበትን ያህል በብዙ መልኩ የስነ ስርዓትና የስነ ምግባር ዝቅጠት ጎልቶና ተደጋግሞ ይታያል። በርካቶችም ጥላቻንና ስሜታዊነትን የሚሰብኩበት፤ ጦርነት የሚቀሰቅሱበት፤ ግለሰብን፣ ህዝብና አገርን የሚዘልፉና የሚያፈርሱ መልእክቶችን የሚያስተላልፉበት ሲሆን እያስተዋልን እንገኛለን፡፡ መንደሩም «ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት» በሚል የህግ ሽፋን ድብቅ አላማ ባነገቡ እና መርዛም ብዕር በጨበጡ ፀሃፍት ተወሯል፡፡
እኔ እንደታዘበኩት የእነዚህ መርዛም ፀሃፍት የአንድነት መገለጫ ብዙ ነው። ጥላቻ እንጂ ፍቅር አያውቁም። ሞት እንጂ ህይወትን አይመርጡም።ጥፋት እንጂ ልማት ዓላማቸው አይደለም። ከማዳን ለመቅበር ይቸኩላሉ። አዕእምሯቸው በመንደር ማንነት የታጠረ ነው።አያስቡም።አይጨነቁም። አበጥሮ ከማጣራት በሩቁና በግርድፉ መፈረጅ ይቀላቸዋል። አንድን ክስተት በርዝውና ከልሰው እንዳልሆነ ያሰፍራሉ። የድብቅብቆሽ ዓለምን እየፈጠሩ የጠራውን ከደፈረሰው፣ የፀዳውን ካደፈው ይደባልቃሉ።
በስሜተኛነትና በወገንተኛነት የተበከሉ በመሆናቸው የጠራውንና የነጣውን እውነት ከጎደፈ የግል አስተያየት ጋር አጋብተው ያቀርቡታል።እውነትን በውሸት ይለውሳሉ። ያታልላሉ፡፡ ማሰብ መጨነቅን፣ማበጠር ማጣራትን አያውቁም።የሚዘሩት ጥላቻ፣ የሚያቆሙት ሐውልት፣ የሚያፈርሱት ምልክት፣ የሚጽፉት ክታብ፣ የሚያበጁት ገደብ፣ የሚቆፍሩት ጉድጓድ እጅጉን አስፈሪ ነው፡፡
አብዛኞቹ ፍርሃትንና ስጋትን በማሰራጨት ህዝብን ምቾትና እንቅልፍ ማሳጣት ዓላማቸው ያደረጉ የጥፋት ጥቅመኞች ናቸው። በኢትዮጵያ እኩልነት ዴሞክራሲ ነፃነትና ፍትህ እንዲሰፍን ፍላጎት የላቸውም።በአገሪቱ የተጀመረው ሁለንተናዊ ለውጥ ቀጣይ እንዳይሆን የሚችሉትን ሁሉ ያዋጣሉ፡፡
በህዝብ ስቃይ የሚንፈነድቁ የእነዚህ ፀሃፍት የጥፋት ተግባር መነሾ የሚቀዳውም ጥልቅ ከሆነው የግል ጠብና ቂማቸው ነው። በዚህ የተስፋ ቢስነት ጥላቻና ቂም የተዋቀሩ እንደመሆናቸውም በመርዛማ ብዕራቸው የሚረጩት መርዝ አደገኛነት አይረዱትም።
ከሁሉ በላይ አንድ የሚያደርጋቸው መገለጫም የተቃራኒ ምኞት ሰለባ መሆናቸው ነው። እነዚህ ፀሃፍት ከየራሳቸው ምኞት ውጭ የሚያዩት የለም። ከአስደሳቹ ይልቅ የሚያስለቅስውን መራጮች ናቸው። አምጠው የወለዱት ክፋት ለማሳደግ የሚሞክሩ፤ ክፋታቸው ተመልሶ እነሱን እንደሚያቃጥል እንኳን በቅጡ የማይገነዘቡ ድኩማን ናቸው።
የሆነውንም፤ያልሆነውም፤ ቢያውቁትም ሆነ ባያውቁት የመጣላቸውን ሁሉ መዘርገፍ ምርጫቸው ነው። የማሳወቅ እንጂ የማወቅ አምሮት የላቸውም። ለማስተማር መማር እንደሚያስፈልግ የዘነጉ፤ ለማሳወቅ ማወቅ ግድ እንደሚል የማይረዱ ናቸው።
ከመገንባት ይልቅ ማፍረስ ይቀናቸዋል። ከመፍጠር ይልቅ አቃቂር ማውጣት ምርጫቸው ነው። የተሻለ ካስተዋሉም ለማኮሰስ ወይም ለማሳነስ ይጣጣራሉ። በጎሳ ምሽጉ ውስጥ የገቡ በመሆናቸው አንድነት ውስጥ ልዩነትን ለማጉላት ይማማላሉ። አእምሮአቸው ውስጥ ባስቀመጡት ምስል በጅምላ ይጠላሉ፤ ይንቃሉ፤ ይሰድባሉ፤ ያዋርዳሉ።
ከመንቀፍም ባለፈ ለወደፊት የሚሻሻልበትን ምክር መስጠት ምርጫቸው አይደለም። በማንኛውም ርእሰ ጉዳይ ወይም አጀንዳ ላይ ማጠቃለያ ለመስጠት ይቸኩላሉ። ማጠቃለያቸውም ከስሜት የመነጨ እንጂ ትክክለኛ አመክኒዮን መሰረት አድርጎ የሚቀመር አይደለም።
ሊኖራቸው ቢገባም ራሳቸውን የመውቀስ ባህል የላቸውም። ሁልጊዜ ትክክል መሆን ስለሚፈልጉ ስህተትን መቀበል እሬት እሬት ይላቸዋል። ስህተትን መቀበል ቀርቶ ከነአካቴው ስህተቱ አይታያቸውም።ስህተትን ከመቀበል ይልቅ ወደ ሌሎች ለማላከክ የሚሽቀዳደሙ ናቸው።
ህዝብ ተረጋግቶ እንዳይኖር የተሳሳተ ዓላማቸውን በሰው አእምሮ ውስጥ የሚያሰርፁት እነዚህ በሶሻል ሚድያው የፈሰሱ የፌስቡክ ፀሃፍት ሌላ የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር አብዛኞቹ ማንነታቸውን በፎቶ አለመግለፃቸው ነው። እነ ስሙ ሌላ መልኩ ሌላ ናቸው።
ምንም እንኳን ትክክለኛ ፎቶአቸውን በማስቀመጥ ማንነታቸውን ሳይድበቁ መርዝ የሚረጩት ቁጥር በርካታ ቢሆን አብዛኞቹ ግን ማንነታቸውን አያሳውቁም።ፎቶአቸውን አያስቀምጡም። አንዳንዶችም የግለሰቦችንና የድርጅቶችን ተመሳሳይ ስም ይጠቀማሉ። ይህ መሆኑም ያሻቸውን በፈለጉት መንገድ ለማስተላለፍ ከለላን ሰጥቷቸዋል። የሚያከብሩት ሕግ፣ የሚፈሩት ኃይል እንዳይኖር አድርጓቸዋል።
ማንነታቸውን ደብቀው ራሳቸውን በተለያየ ማንነት የሚያስተዋውቁ እነዚህ ስመ ብዙ መርዛማ ፀሃፍት፤ በዚህ ጭንብል ተሸፍነው ወተቱን አጥቁረው፤ ማሩን አምርረው ይቀርባሉ። ሰዎችን ከሰዋዊ ክብራቸው ዝቅ ያደርጋሉ። ያዋርዳሉ። «ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ»እንደሚባለው በመሰል የወረደ ተግባር በርካቶችን መርዘዋል፣ እየመረዙም ናቸው፡፡
በጣም የሚያሳዝነውና ሚያስገርመው ደግሞ ፀሃፍቶቹ በርካታ መርዝ አከፋፋይ ማለትም ሼር አድራጊዎች አሏቸው። ከመንቀፍ ይልቅ ጎበዝ! በርታ! የሚሏቸውና መርዙን መውደዳቸውን‹‹ላይክ›› በማድረግ የሚገልፁ ተከታዮቻቸው ቁጥርም በርካታ ነው።
ይሁንና በእነዚህ መርዛም ብዕር የጨበጡ ፀሃፍትና አከፋፋዮቻቸው በርካታ ንፁሃን እየተጉዱ ነው።ብሄር፣ ፆታና ቦታ በመቀየር የግጭት ድግስ የሚደግሱ ግጭት በመቀስቀስና ብጥብጥ በማንገስ የህዝብ መፈናቀልና ስቃይን እያባባሱት ይገኛሉ።
በተለይ የፀሃፍቶቹን ድብቅ ዓላማ ያልተረዱ ንፁሃን ወገኖች ሳያጣሩ በሚሰጡት አፀፋ ህዝቦች ወደ ግጭት ሲያመሩና ሲተናኮሱ እያስተዋልንም እንገኛለን። በአሁኑ ወቅትም መርዝ የሚያሰራጩ ፀሃፍቶቹ ቁጥርም ሆነ በእነርሱ ተግባር የሚደርሱ ጥፋቶች እየጨመሩ እንጂ እየቀነሰ አይደለም። ይህ እስከሆነም ጠንሳሾቹ ሳይውል ሳያድር ከመንደሩ ሊሸሹ የሚችሉበት መፍትሄ መቀየስ የነገ ሳይሆን የዛሬ ተግባር ሊሆን የግድ እንደሚል ማሰብ ይኖርብናል።
በእርግጥ የሰው ልጅ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ እንዲሁም መረጃን የማግኘት መብቱ እንዳለው አያከራክርም፡፡ በዲሞክራሲያዊ አገር መሰል መብቶች መገደብ እንደሌለባቸውም ሁላችንንም ያስማማል፡፡ በአገር ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ምክንያታዊና ተጨባጭ በሆነ መልኩ የሚሰጡ ገንቢ ሃሳቦችና በመንግስት አሰራር ላይ በሚታዩ ድክመቶች ዙሪያ የሚሰጡ አስተያየቶችና ትችቶች መበራከታቸውም የሚጠላ አይደለም፡፡ አስተማሪና ለለውጥ መነሾ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጥርጥር የለውም፡፡
ይሁንና በሰንካላ አስተሳሰብና በተንኮል በህዝቦች መካከል መርዝ መርጨትን እንደመብት ወይም ሃሳብን በነፃነት እንደመግለፅ መመልከት ነገ እንባና ደም ወለዱን ጨምሮ እንደሚያስከፍል መገንዘብ የግድ ነው፡፡ መሰል አካሄድም ሳይውል ሳያድርም በቃ ሊባል እንደሚገባው በእጅጉ መተማመመን ይኖርብናል።
የፌስቡኩን መንደር የወረሩትን መርዝ የሚረጩት ብዕረኞች ዓላማ ለማክሸፍ ደግሞ ቀዳሚው የተጠቃሚው ሃላፊነት ነው። ከሁሉ ቀድሞም ለፀሃፍቶቹ ድጋፍ መቸር የአእምሮንና የኅሊናን መዳከም ወይም ጭራሹኑ አለመኖር እንደሚያመላክት መረዳት ይገባል።
እንደ ፀሃፍቶቹ ላለመጥበብና በራስ የአስተሳሰብ ሳጥን ብቻ ላለመታጠርም ጥበብ ያለው ማንበብን መልመድ ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ጥበብ የሌለው ማንበብ ትክክለኛና የተመጣጠነ አስተሳሰብ እንዲሁም አስተዋይ አዕምሮን አይገነባምና ነው።
የፀሃፍቶቹ ዓላማ ህዝብንና አገርን ምቾት እንቅልፍ ማሳጣት መሆኑን ከመገንዝብ ስህተታቸውን አይቶ ከማለፍ ይልቅም «ስህተቱን ነው ፣ ቀጣፊ ናችሁ» ማለትና በተጨባጭ ምክንያት ብሎም ማስረጃ መሟገትን ልምድ ማድረግም ያስፈልጋል።
መርዛም ብዕረኞችም ቢሆን አንድን ክስተት በርዝውና ከልሰው የጠራውን ከደፈረሰው፣ የፀዳውን ከአደፈው መደባለቃቸውና፤ መልዕክታቸው በብዙ ሰዎች ስለ ተደገፈ እውነት አይሆንምና ሁልጊዜም ቢሆን ምክንያትን ማስቀደም፣ መረጃዎችን እየመረጡ ለመጠቀምና መመርመር ሊያስቡ ይገባል።
የፌስቡኩን መንደር የወረሩትን መርዝ የሚረጩት ብዕረኞች ዓላማ ለማክሸፍ መንግሥትም ቢሆን ኃላፊነቱ ግዙፍ ነው፡፡ በርካታ አገራት አፍሪካዊቷ ግብፅን ጨምሮ በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግ አውጥተዋል። እኛም በተደጋጋሚ የቀውሱ ገፈጥ ቀማሽ በመሆናችን በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ያለውን የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ በአግባቡ መጠቀም፤ ካልሆነም አጠናክሮ ማውጣት ይገባል። ይህ ሲሆን ነው የማህበራዊ ሚዲያው መርዘኞች ዘላቂ ማርከሻ የሚያገኙት፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2014 ዓ.ም