እውነት ነው የሀገራችን መገናኛ ብዙሃንና በውስጣቸው የሚሠሩ ጋዜጠኞች በርካታ ጭቆናዎቸን አልፈዋል። የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት ለስም ብቻ ቢደነግግም ከጎን በሚወጡ የሚታዩና የማይታዩ ህጎችና መመሪያዎች እንዲሁም ሚዲያውን ለማፈን በተቋቋሙ መስሪያ ቤቶች አማካኝነት በተግባር ሳይተረጎሙ ዓመታትን አስቆጥረዋል። መንግሥታዊ መረጃዎችን መንፈግ፣ እንደ እንጀራ ልጅና የጥፋት መልዕክተኛ አድርጎ መመልከት፣ ማዋከብ ማሠርና እንዲሰደዱ ጫና ማድረግ በግል መገኛ ብዙሃን ላይ ሲፈጸሙ ከነበሩ ጥቃቶችና ጫናዎች ዋነኞቹ እንደነበሩ በዘርፉ ተዋንያን፣ በዓለም አቀፍ ድርጅቶችና በለውጡ አመራሩ የተመሰከሩ እውነታዎች ናቸው።
የህዝብ መገናኛ ብዙሃንንም በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ መገደብ፣ የመንግሥት ቃል አቀባይ ብቻ ሆነው እንዲሠሩ ማድረግ፣ ያፈጠጡና ያገጠጡ እውነታዎችን ዓይናቸውን በጨው ታጥበው እንዲክዱ ወይም ዓይተው እንዳላዩ ሆነው እንዲያልፉ ማድረግ በአጠቃላይ ተዓማኒነታቸውን የሚንድ ሥራ እንዲሠሩ በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ጫና ይደረግባቸው እንደነበርም ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው። ከላይ በተጠቀሱት አፈናዎችና ጫናዎች ምክንያትም የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ቀጭጨውና ግርማ ሞገሳቸው ተገፎ የግል መገናኛ ብዙሃኑም ወደ መጥፋቱ ተቃርበው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
ባለፉት ዓመታት በተለይም ከምርጫ 97 ወዲህ በርካታ ጋዜጠኞች ለእስር ከመዳረጋቸውም በላይ ከሀገር የተሰደዱትም ቁጥር ቀላል አልነበረም። ይህም ሁኔታ የሀገራችንን ገጽታ ክፉኛ ከመጉዳቱም በላይ ጋዜጠኞችን በማዋከብና በማሰር ኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓትም ቆይቷል። በግሉም ሆነ በህዝብ ሚዲያዎች ላይ ሲደረጉ የነበሩ ጫናዎች በህብረተሰቡ ላይ የሃሳብ መታፈንና የመጨቆን ስሜት በመፍጠራቸው ብሎም የመንግሥትን ድክመት በነፃነት እየነቀሱ መተቸት ባለመቻሉ ሶሻል ሚዲያውን በአማራጭነት በመጠቀምና ወደውጭ አገር ተሰድደው የማሳራጫ ጣቢያ በማቋቋም ሃሳብንና ተቃውሞን መግለጽ እንደአማራጭ እንዲወሰድ አድርጓል።
ከዚህም ባለፈ በሀገሪቱ ለተነሱ ተቃውሞዎች እንደ አንድ አቀጣጣይ ፈንጅ በመሆንም ህዝቡን ለለውጥ አነሳስቷል። ከመገናኛ ብዙሃን ነፃነት አንጻር ዛሬ ላይ ያ ዘመን ነበር ሆኖ ቀርቷል በሚያስብል ሁኔታ ላይ እንገኛለን። የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት በሩ ያለምንም ተጽእኖ ብርግድ ብሎ ስለመከፈቱ ሁሉም የሚሰማማበት ጉዳይ ነውና። ሚዲያ ለማቋቋም የሚፈልግ ማንኛውም አካል ተፈላጊዎቹን መስፈርቶች ካሟላ በፍጥነት እየተስተናገደ መሆኑን በግሉ መገናኛ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት እየመሰከሩት ያለ ሀቅ ነው። መረጃ ለማግኘት ሲፈለግ ከሚደረግ እንቅፋት ውጪ ማንም የተሰማውንና ያመነበትን የሚጽፍበት ምቹ ዓውድም ዕውን ሆኗል።
በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜም ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የታሰረ ጋዜጠኛ የሌለባት አገር ስለመሆኗም በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሳይቀር የተመሰከረ እውነታ ሆኗል። የተገኘውን ነፃነት በመጠቀም የህዝብ መገናኛ ብዙሃን በሚፈለገው መጠን ባይሆንም ከከዚህ ቀደሙ በተሻለ ነፃነት እየሠሩና መንግሥትን ሳይቀር እየተቹ ያሉበት ሁኔታም ይበል የሚሰኝ ነው። ከዚህ ሁኔታ በመነሳትም መንግሥት ለመገናኛ ብዙሃን ነፃነት የሚጠበቅበትን ተወጥቷል ብለን መናገር እንችላለን። አሁን ኳሷ ሙሉ ለሙሉ በመገናኛ ብዙሃኑ እግር ስር እንደሆነችም አርግጠኛ እንሆናለን።
ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዲህ ምቹ ሆኖ ሳለ በኳስ አጠቃቀሙ ላይ ችግር እንዳለ ግን እየታየ ነው። በስመ ነፃነት የግለሰቦችንና የተቋማትን ስም ማጥፋት፣ ያለምንም የኃላፊነት ስሜት ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል ዘገባ ማስተላለፍ፣ የሐሰት መረጃዎችን መልቀቅ፣ ጎራ ለይቶ መፋለም፣ ህዝብን መከፋፈልና በስሜት የመነዳት ችግሮች በግል መገናኛ ብዙሃኑ ላይ በስፋት እየተስተዋሉ ነው። በክልሎች የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙሃንም አጠቃላዩን ህዝብና አገር አይቶ ከመሥራት ባለፈ የእርስ በእርስ መነቋቆርና ስሜት ማጦዝ ላይ ማተኮርን የመሳሰሉ አላስፈላጊ ግድፈቶች ሲፈጽሙ እየተስተዋለ ነው። የአንዳንዶቹ ሁኔታ በአንድ አገር ያሉ እስከማይመስልበት ደረጃ ተደርሷል።
አገራችን አሁን በተጨባጭ በመንታ መንገድ ላይ የቆመች አገር ናት። መከበባር መተሳሰብና መዋደዱን ከቻለንበትና ጠንክረን ከሠራን መዳረሻችን እጅግ አጓጊ አይ ይሄ አይበጀንም ብለን የነገር አጀንዳዎችን እየመዘዝን ከተናቆርንና ከተባላን ደግሞ ፍጻሜያችን እጅግ አደገኛ መሆኑ ግልጽ ነው። ለዚህ ደግሞ መገናኛ ብዙሃኑ ያላቸው ድርሻ የአንበሳውን ይይዛል።
ልዩነትን አጥብቦ ሰላምን ሰብኮና አንድነትን አምጥቶ ህዝባዊ አደራን መወጣት ወይም ደግሞ ጥላቻን አራግቦ አገርን ማፍረስ በመገናኛ ብዙሃኑ እጅ ላይ የወደቁ አማራጮች ናቸው። ሆኖም ሁሉ ቢፈቀድ ሁሉ አያዋጣምና ቅዱሱ ተግባር ፍቅርን መስበክ፣ መከባበርና ተቻችሎ መኖር ነው። በመሆኑም መገናኛ ብዙሃኑ በእግራቸው ስር ያለችውን ኳስ ለዚሁ ተግባር ያውሏት እንላለን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 7/2011