“ከአምስት ቀን በኋላ ሥራዬን እለቃለሁ” – አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) በ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሦስተኛና አራተኛ ጨዋታዎችን ባለፈው ቅዳሜና ማክሰኞ ከጊኒ ጋር አድርገው በሁለቱም ጨዋታዎች መሸነፋቸው ይታወቃል። በገለልተኛ ሜዳ ኮትዲቯር ላይ በተደረጉት ሁለቱ ጨዋታዎች ዋልያዎቹ 4ለ 1 እና 3ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸንፈው ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ዕድላቸውን አጥበበው ተመልሰዋል።

የዋልያዎቹ አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በወቅታዊ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ዙሪያ ትናንት በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት በሰጡት መግለጫ፣ “ከአምስት ቀን በኋላ ሥራዬን እለቃለሁ” በማለት ከዓመት በፊት የፈረሙት ውል መጪው ጥቅምት 23/2017 ዓ/ም እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።

አሠልጣኙ እየተመዘገበ ባለው ውጤት “እንደ አንድ ግለሰብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሲሸነፍ ምን ይሰማሃል?” ተብለው በጋዜጠኞች ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ፣ “ኢትዮጵያ ስትሸነፍ ከእናንተ የተለየ ስሜት አይኖረኝም። ከእናንተ በላይ ነው የምቆረቆረው። እኔ ተዋናይ ስለሆንኩ እናንተ ተዋንያን ላትሆኑ ትችላላችሁ፣ እኔ ደግሞ ከማንም በላይ እጎዳለሁ፣ ስሜቱ በጣም ከባድ ነው። የምንችለውን ያህል ነው ጥረት የምናደርገው። መታወቅ ያለበት ተጨባጭ አቅማችንን ማወቅ አለብን። አንዳንድ ጊዜ ስሜታዊ መሆን አያስፈልግም። ከጊኒ ጋር ተጨባጭ የአቅም ልዩነት አለን፣ እንደ ቡድን ጠንካራ ሀገር ነው። በተቻለ መጠን ያለውን ልዩነት አጥብበን ተፎካክረን ለመውጣት ጥረት አድርገናል። ያም ቢሆን የፍጥነት ልዩነት ይጎላል። በተለይ የመከላከሉ ላይ እና ኳስ ስናጣ የምናደርገው እንቅስቃሴ የለም። የምንጫወተው ኳስ ስናገኝ ብቻ ነው። ይህ በጣም መታረም ያለበት ሥራ የሚፈልግ ነገር ነው።” ብለዋል።

አሠልጣኙ በቀጣይ ከብሔራዊ ቡድን ጋር የሚኖራቸውን ቆይታ አስመልክቶ ሲናገሩም “ከአምስት ቀን በኋላ እለቃለሁ፣ ውሉ በሃያ ሦስት ነው የሚያልቀው ምን እንደሚያስጨንቃችሁ አላውቅም። ውሉ ሲጠናቀቅ እለቃለሁ” በማለት ተናግረዋል።

“የኢትዮጵያን ሽንፈት የዓለም ፍፃሜ አታድርጉት” በማለት የተናገሩት አሠልጣኝ ገብረመድህን፣ ቡድናቸው የሥነ ልቦና ችግር እንዳለበት ሲያስረዱ አንድ ግብ ሲያስተናግድ ሌላ ግብ በቀላሉ የማስተናገድ ችግሮች ሲያስረዱ “ተጫዋቾቻችን በየጨዋታው የተለያየ አቋም ማሳየት ትንሽ ችግር ፈጥሮብናል። በዚህ ላይ የሥነ ልቦና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል በአንድ ነገር ቶሎ የመርካት ነገር ይታይባቸዋል።” ብለዋል።

ከአጨዋወት ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄም “አቋሜን አልቀይርም፣ አሁንም ወደ ፊትም ቀጥተኛ አጨዋወት ነው የምጫወተው ፤ ከዚህ በኋላ ምን ያህል ጊዜ ሊኖረኝ ይችላል ? ባለኝ አጭር ጊዜም ቢሆን አልቀይርም ፤ ረጅም ጊዜ አልቆይም ፤ እኔ ባመንኩበት ነው የምቀጥለው። የአጨዋወታችን ስህተት ስለነበረ አይደለም በግልጽ ልዩነት ስላለን ነው የተሸነፍነው፣ ሲሉ አሠልጣኝ ገብረመድህን ገልፀዋል።

በ2025 አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዋልያዎቹ በሚገኙበት ምድብ ዴሞክራቲክ ኮንጎ በአራት ጨዋታ 12 ነጥብና ስድስት ግብ ይዛ ትመራለች። ጊኒ በስድስት ነጥብና አራት ግብ ሁለተኛ ላይ ስትገኝ፣ ታንዛኒያ በአራት ነጥብ ሁለት የግብ ክፍያ ይዛ ሦስተኛ ነች። ዋልያዎቹ በበኩላቸው አንድ ነጥብና ስምንት የግብ እዳ ይዘው የመጨረሻው ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ሂሳባዊ ስሌት መሠረት ዋልያዎቹ በሞሮኮ በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ያላቸው እድል ሙሉ በሙሉ ዝግ አይደለም። በቀሪዎቹ ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎች ዋልያዎቹ አሸንፈው ጊኒና ታንዛኒያ ሁለቱንም ከተሸነፉ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫው የመብቃት ጠባብ ተስፋ አላት። ዋልያዎቹ በቀጣይ የማጣሪያ ጨዋታዎች የምድቡን መሪ ዴሞክራቲክ ኮንጎንና ታንዛኒያን የሚገጥሙ ይሆናል።

ዋልያዎቹ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ያደረጉትን የመጀመሪያ ጨዋታ 4 ለ0 በሆነ ውጤት መሸነፋቸው የሚታወስ ሲሆን በሁለተኛው የማጣሪያ ጨዋታ ብቸኛውን ነጥብ ያገኙበትን ፍልሚያ ከታንዛኒያ ጋር 0 ለ 0 በማጠናቀቅ ነበር ማስመዝገብ የቻሉት።

ቦጋለ አበበ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You