ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ያሻሻለችው ሕገመንግሥት ደቡብ ኮሪያን “ጠላት ሀገር” የሚል ብያኔ ሰጥቷታል።
የሰሜን ኮሪያ ፓርላማ ለሁለት ቀናት መክሮበት ተሻሽሏል የተባለው ሕገመንግሥት ጎረቤት ደቡብ ኮሪያን በጠላት መፈረጁ የኮሪያ ልሳነ ምድርን ውጥረት የሚያባብስ መሆኑ ተነግሯል።
ፒዮንግያንግ በሀገራቱ ድንበር የሚገኝ መንገድን ካወደመች ከሁለት ቀናት በኋላ ነው ሴኡልን በሕገመንግሥቷ በጠላትነት መፈረጇን ያስታወቀችው።
ብሄራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ (ኬሲኤንኤ) ሁለቱን ሀገራት በሚያገናኘው መንገድና የባቡር መስመር መውደሙ ሕገመንግሥቱን እንደማክበር የሚቆጠር ነው ብሎታል። ሕገመንግሥቱ ሴኡልን በጠላትነት መፈረጁን በመጥቀስ። የደቡብ ኮሪያ የውህደት ሚኒስቴር የፒዮንግያንግን ፍረጃ ለአንድነት እና ውህደት የማይበጅ ነው በሚል ተቃውሞታል።
የደቡብ ኮሪያ መንግሥት በፒዮንግያንግ ሊፈጸም ለሚችል ጸብ አጫሪ ድርጊት ፈጣንና ከባድ የአጻፋ ምላሽ ይሰጣል ሲልም አስጠንቅቋል ብሏል አሶሼትድ ፕሬስ በዘገባው።
ተንታኞች ኪም ጆንግ ኡን ደቡብ ኮሪያን በውጭ ጠላትነት መፈረጃቸው የኒዩክሌር መሣሪያዎችን ለመጠቀም ሕጋዊ ድጋፍ ለማግኘት በማሰብ ሊሆን እንደሚችል ያነሳሉ።
ከአሜሪካ ጋር በደቡብ ኮሪያ በኩል ሳይሆን በቀጥታ ለመደራደርም ሴኡልን “ጠላት ሀገር” አድርገው መበየንን መርጠው ሊሆን ይችላል የሚሉ አሉ።
ሴኡል ግን ርምጃው የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር ከዚህ ቀደም የወሰዳቸው ሰላማዊ የውህደት ጥረቶችን ያለመፈለግና ጦርነትን አጥብቆ የመሻት ማሳያ ነው ብላዋለች።
የኪም አስተዳደር ባለፉት ወራት የሁለቱን ኮሪያዎች ውህደት የሚያመላክቱ ሀውልቶች እና የሀገራቱን ግንኙነት ለማሻሻል የተቋቋሙ ተቋማት እንዲፈርሱ ማድረጉ ይታወሳል።
ወጣቱ መሪ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ የመልሶ መዋሃድ ፖሊሲው እንዲሰረዝ ማዘዛቸውም አይዘነጋም።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም