ሰንፔር

ለመጀመሪያ ጊዜ መንግሥት ከሚሉት መሥሪያ ቤት ገባሁ። የምሠራበት መሥሪያ ቤት ዓመታዊ እቅዱን በተሳካ አፈጻጸም መከወኑን አስመልክቶ ለተዝናኖት ለሁለት ቀን ከከተማ ወጣ ልንል ሆነ። በደብረዘይት ውበታም ሃይቆች ላይ ቅዳሜና እሁድን ከአናት እስከትቢያቸው አስካካሁባቸው። ቅዳሜ እለት በእለታት ውስጥ የተሰካ ማስተዛዘኛ ካርድ ይመስለኛል። የሆነ ሞገስ አለው.. ሲመጣና ሊመጣ ሲል።

ደብረዘይት እንደቅዳሜ እለት የሆነ መንፈስ አላት.. እንደስሟ ጌታ የተመላለሰባትን የመጽሀፍ ቅዱሷን ትመስለኛለች። በዓመት ለብዙኛ ጊዜ ተመላልሼባት የማትታክተኝ የከንፈር ወዳጄን ናት..፡፡

12 ግድም እግርና ሃሳቤን ተከትዬ አካባቢውን ለመቃኘት ከተያዘልኝ መኝታ ክፍል ወጣሁ። ጽልመት ሊሰፍርበት ያደፈጠበት እለተ ቅዳሜ እሁድን ሊተካ በሽምግልና ያፋሽካል። በነፋሻው የሃይቅ ዳር ለምለም የሚሽኮረምሙ ዘንጣፋ እጽዋቶችን ከሠፈሩባቸው ንቦችና ነፍሳቶች ጋር እየቃኘሁ ለግማሽ ሰዓት ድረስ ተጓዝኩ። እንደበቃኝ ሳውቅ አቅጣጫ ቀይሬ ወደሆነ መንገድ ላይ ተሳፈርኩ።

ቀደም ሲል ወደአፌ አስገብቼ የማላምጠውን የማስቲካ ልባስ በአውራ ጣቴና በሌባ ጣቴ እያድበለበልኩ መልሼ ወደአፌ እከተዋለው። እንደልጅ ቂልነት ሰፍሮብኝ በተሳፈርኩበት መንገድ ርቄ ሄድኩ። ትንሽ እንዳዘገምኩ ከሪዞርቱ መሀል ሰፈር ደረስኩ። በካርድ የሚያገለግሉ የገንዘብ ማሽኖችን ጨምሮ በተለያየ ቀለም የተዋቡ ለመንፈስ ተሀድሶን የሚሰጡ ቅርጻቅርጾችን አየሁ። የራት ሰዓት እየቀረበ ስለነበር ለእራት ከወጡ ከአንዳንድ የመሥሪያ ቤት ሠራተኞች ጋር ተላተምኩ። የሆነ መቆሚያ እስካገኝ አልፌአቸው ሄድኩ። ከፊት ለፊቴ ኮምፒውተር ላይ ያፈጠጠች ቅላቷን ያጎላ ዩኒፎርም የለበሰች ቀይ ሴት የተሰየመችበት አንድ ባዶ ክፍል አየሁ።

እንግዳ መቀበያ ክፍል እንደሆነ መግቢያው በር ላይ በተቀመጠ ደማቅ ጽሁፍ አረጋገጥኩ። ባልባሌ ከምዞር እስከራት ሰዓት ድረስ እንድታዘልቀኝ በዛውም የጉዞዬ ማብቂያ እንድትሆን ፈልጌ ዘው አልኩባት፡፡

እጅግ ሥርዓት በተላበሰ ወግ ለዛውም ከፈገግታ ጋር ‹ጤና ይስጥልኝ እባኮዎ ምን ልርዳዎ? አለችኝ። እባክዎ የምባለው እንዲህ ባሉ ቦታዎች እንደዚች ባሉ ቆነጃጅት ነው። ነገ የሌላቸው እንዲህ ያሉ ማጎንበሶች ያሳቅቁኛል..ቀኔን ነው የሚያበላሹብኝ። ለእኔ አይነቱ እንቡጥ ብላቴና አይደለም ዘገር ይዘው በጉንባሴ ለሚሄዱትም ቢሆን ይሸክኩኛል፡፡

ለንግግሯ ምላሽ አንድ ጥፊ ባልሳትና እዛ ጊቢ ውስጥ ለሚሆነው ለየትኛውም ነገር ራሴን ማዘጋጀት ፈልጌ ነበር። ግን አላደረኩትም፡፡

ማታ ግን ያልታወቀበት የውበት መፍለቂያ ነው። ትንሽ ጨለማ ውስጥ ጥቂት ብርሃን ምን ማለት እንደሆነ ያን ቀን ነው የተረዳሁት። ለእሷም በደነቃት ሁኔታ በጨለማውና በጣሪያው ላይ ብርሃን መሃል ምን እንደምትመስል በማሰብ በዝምታ ብዙ ሰዓታትን ፈጀሁ፡፡

ከቅድሙ ፈገግታና ሳቅ አንዳች ሳታጎድል ‹እባኮ ምን ልርዳዎ› ስትለኝ ከዝምታዬ ጋር ነበርኩ። አማርኛዋን አስተካክላ እስክታናግረኝ በዝምታ ቀጣኋት። ጨለማና ብርሃን ተሳስመው በስመታቸው የነደፉት አንዳች ቀለም ከቀይ መልኳ ስር ሲንፎለፎል አያለሁ። አንድ ሰዓት ጨለማ ላይ ብርሃን ተንጠፍጥፎ ከዛ ጉደኛ ውበት ሌላ ምን ውብ ነገር ሊሠራ ይችላል? አንገቷ ላይ በትንሽ ጨርቅ የተሠራ የሪዞርቱን አርማ ሸብ አድርጋለች። ጣቶቿ የኮምፒውተሩን ቁልፍ ሲጠበጥቡ ይሰሙኛል…በሞዛርት ዘመን ላይ ያለሁ መሰለኝ። ሞዛርት እንደዚች ሴት በጣቶቹ ምት ውብ ዜማን ሲፈጥር ተመሳሰለብኝ። ከሴት የሆነ ሁሉ ለምን ውብ ሆነ? ይቺ ሴት ወንድ ብትሆን ይሄ ሁሉ ዜማ የት ይኖር ነበር? እኔስ በሃሳቤ ጥንተ ሞዛርት ስር ስለምእወድቅ ነበር?

ዜማ ወደሚፈጥሩት ጣቶቿ አተኮርኩ..ሌጣቸውን ናቸው አንዳች ፈርጥን አላሰሩም። ወደመልኳ አሻቀብኩ…ብርሃንና ጨለማ ሻሞ ያሉበት ንጋት መሳይ ጽንሰ ጎህ እድል ፈንታዬ ነበር፡፡

ሥራዋ መለማመጥንም ስለሚጨምር ‹ይቅርታ ጌታዬ ምን ልርዳዎ?› ስትል ከቅድሙ በባሰ አመረረችኝ። በዝምታዬ እሰነብታለሁ ብዬ ነበር..ጌታዬ በምትለው ቅጽል ማስመሰል እንዲህ ስል አፌን ፈታሁ.. ‹እስኪ ረጋ በይ ላንቺም ለሃሳብሽም ቦታ ምረጪ። ውድና ብርቅ ቃላቶችሽን ክብር ለማይገባው ለማንም ወንበዴ እያባከንሽ ነው..› ማለቴን አስታውሳለው..

ያ በጨለማና ብርሃን ስመት የተፈጠረ መልኳ ጥይምይም አለ። ጨለማ ማለት የብርሃን ጥላ..የውጋግ ኮቴ እንደሆነ ሳውቅና ቀጥዬ ምን ማለት እንዳለብኝ ሳስብ እሷ በመናገር ላይ ነበረች፡፡

‹ይቅርታ..ይሄ ሥራ ቦታ ነው..ልረዳዎት ዝግጁ ብሆንም ለመረዳት ፍቃደኛ አልሆኑም› የሚለው ንግግሯ ጆሮዬ ሰተት አለ። ከዛ በፊት የተናገረችውን ለማድመጥ ጊዜን ወደኋላ መመለስ አሰኝቶኝ ነበር፡፡

‹ከኔ በኋላ የሚመጡ ክብርና ሙገሳ የሚሹ ብዙ እንግዶች አሉብሽ ቃላቶችሽን ቆጥቢ እያልኩሽ ነው› በማለት ቁጣዋን ለማለዘብ ሞከርኩ። ለንግግሬ ምላሽ ፈገግታን የጠበኩ ቢሆንም አልፈገገችልኝም። ኮምፒውተሯ ላይ አተኩራ በዜማ ፈጣሪ ጣቶቿ አበሳዬን አየሁ፡፡

ራቴን አሳለፍኩ.. ስለእውነት ርቦኝ ስለነበር የራት ሰዓቴን በጉጉት ስጠብቅ ነበር። አጠገቤ ከእሷ ራቅ ለኔ ቀረብ ያሉ በሥርዓት ያልተደረደሩ ወረቀቶች ይታዩኛል። አተኮርኩበት..አይኔ ‹ሰንፔር› የሚል ስም ላይ አረፈ። ‹ሰንፔር እልፍ ነህ› ከስሙ ጎን አብሮ ስልክ ቁጥር እንዳለ ሳውቅ ደግሞ የበለጠ ረካሁ። የቀይዋን ሴት ዝምታ ተንተርሼ እንደቀልድ በሚመስል እብደት ስልኬን ከኪሴ አውጥቼ ቁጥሩን ስልኬ ላይ መዘገብኩት።

እንግዳ ተቀባይዋን ሴት የመጨረሻ በሆነ የአንድ ጊዜ እይታ ጋር ‹ደህና ያምሹ እመቤቴ› ስል አላግጨባት ወጣሁ። ግን ምን በደለችኝ? በክብርና በትህትና ስለተቀበለችኝ እንደዛ መሆን ነበረብኝ? ራሴን አትረባም እያልኩት ራት ወደሚበላበት አዳራሽ አዘገምኩ።

ሰንፔር ጋ ሳልደውል ሳምንታት አለፉ። የሆነ እለት ደወልኩ..አወራን ከሁለት ሳምንት የስልክ ማውራት በኋላ በአካል ለመገናኘት ብሄራዊ ቲያትር ቤትን መረጥን፡፡

ማክሰኞ ከሥራ መልስ 11 ሰዓት ላይ ብሄራዊ በር ላይ ቀድሜ ተገኘሁ። እለተ ማክሰኞ ብርሃናማ መልኩን በጸሀይ መግባት ተነጥቆ እከካም መስሏል። ጥላማ ጠይም መልኩን አስግጎ ወደእለተ ረቡዕ ያዘግማል..። ብሄራዊ የሰዎች መናኸሪያ ነው..። አዲስ አበባ ውስጥ ከመርካቶና ከመገናኛ እንዲሁም ከሜክሲኮ ቀጥሎ ብዙ ሰው የሚረግጠው ቦታ ነው። በዚህ የሰዎች ጋጋታ መሃል የማያውቁትን ሰው መጠበቅ ድካሙ ምን እንደሚመስል መገመት አይከብድም። ብቻ አንዲት ውብ ሴት እጠብቃለሁ.. በአእምሮዬና በልቤ የተሳለችን የጀምበር ጉማጅ። ከአራት ማዕዘን ፊት ውጪ ተክለ ቁመናዋን የማላውቃትን ሴት። ያለምክንያት የምትስቅን ነፍስ፡፡

ከቀጠሯችን አምስት ደቂቃ አልፏል..። ወዴት ማየት እንዳለብኝ ሳላውቅ ወደቀናኝ እገላመጣለሁ። ኮቴዋ ያማረ..በዳናዋ ላይ ሳር የሚያቆጠቁጥባት ሴት እጠብቃለሁ። ድንገት ስልኬ ጠራ..‹የቱጋ ነህ? የሚል ድምጽ ከስልኩ ጉያ ገዝፎ ከጀርባዬ ተሰማኝ። ወደ ኋላ ዞርኩ..የማውቀው ፊት፣ ከማውቀው ፈገግታው ጋር ዊልቸር ላይ ሆኖ በአንዲት ሴት እየተገፋ አየሁት፡፡

ልቤ ሲገፋትና ‹ክብረት? የሚል ጥሪ ስሰማ ባልተዛነፈ እኩሌታ ነበር፡፡

ከነዊልቸሯ አጠገቤ መጥታ ከፈገግታ ጋር እጇን ለሰላምታ ዘረጋችልኝ…

ጨበጥኳት..መዳፏም እንደመልኳና ሳቋ ነው..ለስላሳ። ዝም ብያለሁ..እንደዛ ስቦርቅ የነበርኩት ልጅ፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም

Recommended For You