ሴራ – የሶዶ ክስታኔ ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓት

ሴራ ወይም በጎርደና ሴራ የሶዶ ክስታኔ ቤተ ጉራጌ ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓት ነው። በሶዶ ክስታኔ በጎርደና ሴራ ጥልቅ የሆኑ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ያሉት ሲሆን ከ800 ዓመት በፊት ማህበረሰቡ ይዳኝበት የነበረና አሁንም ድረስ ተጠብቆ የቆየ ባሕላዊ የሸንጎ ሥርዓት መሆኑን ከምስራቅ ጉራጌ ዞን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። የሶዶ ክስታኔ ጉራጌ ሕዝብ ሥራ ወዳድና ታታሪ ሕዝብ ነው ይህ ሕዝብ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የወንጀልና የፍትሐ-ብሔር ሕግ ባልነበረበት ራሱን በራሱ የሚተዳደርበት ሕግና ደንብ የጎርደና ሴራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የሶዶ ክስታኔ ማህበረሰብ በማህበራዊ ኑሮ በኢኮኖሚያዊ በፖለቲካው የሚያስከትላቸው ችግሮች በመመርመር የኑሮ ቀውስ እንዳይገጥመው በለቅሶ፣ በሰርግ፣ በድንበር ጤናማ ኑሮ እንዳይኖረው የሚከለክለው ሁሉ ባወጣው ባሕላዊ መተዳደሪያ ደንብ መመሪያ መሰረት ሲጠቀምበት ቆይቷል፡፡ማህበረሰቡ አሁንም ድረስ ከዘመናዊ የወንጀል ሕግ ጋር በማይጋጭ መልኩ በጎርደና ሴራ ባሕላዊ መተዳደሪያ ደንብ ይተዳደራል፤ በዚህ ውስጥ ነፍስ ከማጥፋት ወንጀል ጀምሮ ስርቆትና አካል ማጉደልንም ጨምሮ የሚይበት ሁኔታ መኖሩን መረጃው ያሳያል።

ባሕላዊ ግጭት አፈታት ሥርዓት እንደ ሶዶ ክስታኔ እጅግ የሚደነቅ ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮችን በማየትና በማስታረቁ ትልቅ ሚና የሚጫወት እንዲሁም ለዘመናዊ ዳኝነቱም እገዛ እንደሚያደርግ የባለጉዳዮችን መጉላላትን እንደሚቀንስ ይታመናል። ይህ ብቻም ሳይሆን ትልቁ ጠቀሜታው እርቁ እውነተኛ እርቅ እንዲሆን ቂም በቀል ሳይያዝ በነፃነት የሚፈፀምበት መሆኑ ነው። በተለይም ከነፍስ ማጥፋት ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ወንጀሎችን በሰላማዊና የማህበረሰቡን ማህበራዊ ግንኙነት በማያሻክር መልኩ እንዲከናወን በማድረግ ረገድ የሴራ ሸንጎ ሚና የላቀ እንደሆነም ይጠቀሳል፡፡

በጎርደና የነፍስ ማጥፋት ወንጀል ፍርድ የሚሰጠው በሀገር ሸንጎ ሲሆን ውሳኔው የሚፀናው ደግሞ በወማኖ የሴራ ሽማግሌዎች ነው። በሀገር ሸንጎ የነፍስ ማጥፋት ወንጀል የሚዳኘው ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ቅደም ተከተል መያዝ ይጠበቅበታል። ወንጀል ፈፃሚው በተለያየ ምክንያት ሰው ሊገድል ይችላል፤ አስቦበትና ሆን ብሎ አልያም በስህተት ሊገድል ቢችልም በሴራ ሸንጎ በዝርዝር ተፈትሾ የሚታይበትና ተበዳይም ሆነ በዳይ ፍትሕ እንዲያገኝ የሚያደረግበት ሁኔታ ነው ያለው።

ወንጀል የፈፀመው ወይም ነፍስ ያጠፋው ግለሰብ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ አካባቢውን ለቆ ቤተሰቡን ሰብስቦ ይሰደዳል። ከቆይታ በኋላ ሽማግሌዎች እርቅ እንዲፈፀም ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ልጃገረድ፣ ወጣት ወንድ እና ሌሎች የገዳይ ቤተሰብ ተሰብስበው ወደ ሟች ቤት ሽማግሌዎች ይዘው ሄደው ይለምናሉ። እነዚህ ገዳይን ወክለው የተገኙ ሽማግሌዎች የፈጣሪን ስም በማንሳት የሟች ቤተሰብ ‹‹ይቅር ለእግዚአብሔር›› እንዲሉ ይማፀናሉ። ከሁለት ከሶስት ጊዜ ልመና በኋላ የሟች ቤተሰቦች ሽምግልና ይቀበላሉ፡፡

ይሁንና የሟች ቤተሰቦች እርቁን እሺ የማይሉ ከሆነ ልጃገረድና ወጣት ወንድ ላይ ቀንበር ተጭኖ ከሽማግሌዎቹ ጋር እንዲሄዱ ይደረጋል። ይህ የሚደረገውም ልመናው ከፍ ያለ መሆኑን ለማመላከት ነው። ከዚህ ሁሉ ምልልስ በኋላ የሟች ቤተሰብ የእርቅ ሥነ-ሥርዓት ከተቀበሉ ወጪ ዘርዝረው እንዲያቀርቡ ቀጠሮ ይያዛል። በቀጠሮው ቀን የገዳይ ቤተሰቦች እና ሽማግሌዎች ብሩን ይዘው የሚቀርቡ ሲሆን፣ ሙሉ እርቅ ለሚፈፀምበት ቀን ደግሞ ሌላ ቀጠሮ ይዘው ይለያያሉ።

በዚህ ቀን በሀገር ሸንጎ ላይ ጉማ ወይንም ካሳ ወይፈን፣ ጊደር፣ አልባሳትና ሌሎችም ቁሳቁስ ይዘው ይመጣሉ። እነዚህ እርቅ የሚያስፈፅሙ ዳኞች በሁለቱም በኩል በገዳይም በሟችም በኩል ይቀመጣሉ። ከዚህ በኋላ በሟች ቤት ድግስ ተዘጋጅቶ ሁሉም በእርቅ የተሳተፉ አካላት በእለቱ ይገኛሉ። ጥቁር በግ ተዘጋጅቶ ገዳይ እራሱ እንዲያርድ ይደረጋል። በበጉ አንጀት የሁለቱ (በገዳይና በሟች ቤተሰብ) አውራ ጣት ላይ ይታሰርና መሀላ እንዲፈፅሙ ይደረጋል። አንጀቱ መሀል ላይ እንዲቆረጥ ይደረጋል። ይህ የሚደረገው ሁለቱ ባለጉዳዮች ቃላቸውን ማጠፍ እንደሌለባቸው ለማመልከት ነው።

ከእርቁ በኋላ ማር፣ ጠላ፣ ቅቤ፣ ቦርዴ እና አስፈላጊ የሆኑ መጠጦች ይቀርባሉ፤ የሟች ቤተሰብ እና የገዳይ ቤተሰብ አንድ ላይ ተሰብስበው ከተቀመጡ በኋላ የተጣለው ጉማ /ካሳ/ ገዳይ ለሟች ቤተሰብ ይሰጣል። በመቀጠልም ሽማግሌዎች መርቀው ገዳይና ሟች በቀረበው ማዕድ እንዲጎራረሱና ቅቤም እንዲቀቡ ይደረጋል። በማግስቱ በገዳይ ቤት በሚዘጋጅ ድግስ ላይ ሁሉም እንዲሳተፉ ይደረግና ከሟችና ከገዳይ ቤተሰቦች ሽማግሌዎች በመምረጥ እርቁን የፀና ለማድረግ ወደ ወማኖ የሴራ ሽማግሌዎች ለመውሰድ ቀጠሮ ይዘው ይለያያሉ።

በቀጠሮው እለትም የተመረጡ ሽማግሌዎች፣ ገዳይና የሟች ቤተሰቦች በጋራ ወደ ወማኖ ሽማግሌ ሄደው ጉዳዩን በዝርዝር ካስረዱ በኋላ መስተካከል ያለበትን እንዲያስተካክሉ፤ ባለበት የሚፀናውም ባለበት እንዲፀና ተደርጎ እርቁ የፀና እንዲሆን ይደረጋል። የወማኖ ሴራ አስፈፃሚዎች በደቡብ ሶዶ ወረዳ የሚገኙ ሲሆን በጎሳ ገንዛደም ይባላሉ።

የወማኖ ሴራ

የዞኑ መረጃ እንዳመለከተው፤ የወማኖ ሴራ ‘ራጋ ‘እና ‘ጌፈቼ ሤራ’ የተባሉ ሌላ ሁለት መጠሪያ ስሞች ያሉት ሲሆን ዎማኖ የሚለው ስም የሀገር ሽማግሌዎች የወሰኑት ውሳኔ በትክክል ከጐርደና ሤራ ጋር የተጣጣመ መሆኑን የሚመለከቱ ባሕላዊ ዳኞች ይወክላል። በተለይም የጉዳት ካሳ፣ የወጪ መተኪያና ማካካሻን ለዕርቅ ሥርዓቱ መደረግ ያላባቸውን ባሕላዊ ሥርዓቶች በተመለከተ በትክክል መወሰናቸውን ይከታተላል ወይም ያረጋግጣል። በይበልጥ ደግሞ እውነቱ እንዲወጣና ዕርቁም በዚያው መሠረት መካሄዱን ለማረጋገጥ ጥረት ይደረጋል። በተጨማሪም በአንድ ቤተሰብ ላይ ወይም በአንድ አካባቢ የተከሰተን መከራና ክፉ ነገር ያመጣው ምን እንደሆነ ሚስጥሩን ገልፀው ያወጣሉ፡፡

የዎማኖ ሽማግሌዎች ለአንድ ጉዳይ ማስረጃ ፍለጋ አይሄዱም፤ የሀገር ሽማግሌዎች ባቀረቡት ማስረጃ መነሻነት ውሳኔያቸውን ያስተላልፋሉ። ዎማኖ ከግለሰብ ጉዳዮች አልፎ አሳሳቢ የሆኑ የጋራ ችግሮችን እንደ ሰብል ውድመት፣ የተፈጥሮ አደጋ መቅሰፍት፣ በአንድ አካባቢ የሰዎችም ሆነ የእንስሳት በብዛት ማለቅ ወይም ሌሎች ለየት ያሉ ክስተቶችን ይመለከታል፤ እንዲሁም የአካባቢውን ቀደም ያለ ታሪክ ይመረምራል፤ ይህን አስመልክቶም የሀገር ሽማግሌዎች በጉዳዩ ምን እንዳሉ ይፈትሻል። ይህ የኋላ ታሪክ የማወቁ ጉዳይ ምን ዓይነት ባሕላዊ ሥርዓት ይደረግ የሚለውን ለመለየትና በመጨረሻም (ኬርታ) እንዲካሄድ እስከ መወሰን ድረስ ሊኬድ ይችላል፣

የዎማኖ ሤራ የሚሰጠው (በገንዛደም) ጥብ (ጐሳ) ብቻ ሲሆን አመላመሉም ከገንዛደም ስድስት ሰዎች ይመረጣሉ፤ ከተመረጡት ሰዎች በዕድሜ መብሰል በሂደት የፍርድ ሂደቱን ተግባር ይረከባሉ። ሆኖም በአንድ ጊዜ የሚካሄድ ርክክብ አይኖርም። አንድ የዎማኖ አባል ይህን አገልግሎት የሚሰጠው የግብርና ሥራውን ጐን ለጐን እየሰራ መሆኑም መረጃው ይጠቁማል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዎማኖ በኬላ ከተማ በሚካኤል ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ በየወሩ የሚካሄድ መሆኑን የሚያመለክተው የዞኑ መረጃ፤ ማንኛውም ሰው ከየትኛውም ጐሳ፣ ፆታ፣ ሃይማኖት ይምጣ ችሎቱን የመከታተል መብት ያለው መሆኑ ያስረዳል። በዚህ ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓት ላይ የቀረበ ማንኛውም ተከራካሪ አካል ውሳኔውንም የሚቀበል ግዴታ አለበት፤ ተፈፃሚም እንደሚሆን ነው የሚያስገነበው። ዎማኖ የሚጀመረው በምርቃት ሲሆን ይህም የሚቀርቡት ጉዳዮች ያለ ምንም አድልኦ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ለማከናወን እንዲቻል ነው።

ጌፈቸን

ጌፈቸን ማለት በሶዶ ክስታኔ ትርጉሙ ይግባኝ ነው አንድ የሳቡኘት አባል በሳቡኘቱ የተወሰነበትን ማንኛውም ቅጣት ያለ አግባብ ነው ወይም ፍርድ ጎሎብኛል የሚል ከሆነ ቅጣቱ እንዲነሳለት በተጨማሪ ለበላይ የሀገር ሸንጎ ሽማግሌ ጌፈቸን (ይግባኝ) ሊል የሚችልበት ሥርዓት መኖሩን መረጃው ያመለክታል። ያቀረበው የጌፈቸን አቤቱታ በሸንጎ ተመርምሮ ወይም ይሻሻልለታል፤ አልያም ደግሞ ሙሉ በሙሉ ሊሰረዝለት የሚችልበት ሁኔታ አለ። ይህ ካልሆነ ደግሞ በሳቡኘት ደረጃ የተሰጠው የቅጣት ውሳኔ ሽንጎው ሊያጸናበት ይችላል።

መገን/መገንታ

እነዚህ መገን እና መገንታ የተሰኙት ቃላት የመማጸኛ ወይም አንዳንዴ የማውገዣ ቃላት ናቸው። እነዚህ ቃላት በክስታኔ/ጉራጌ ማህበረሰብ ውስጥ በሰፊው የሚሰራባቸው መሆኑን የዞኑ መረጃ ያሳያል። መገን/መገንታ ጥሬ ትርጉማቸው ለምሳሌ በእግዜር መገን ፤ በሳቡኘት መገን፣ በሀገር መገን፤ በእገሌ መገን፤ ትርጉማቸውም በእግዜር አማጽናለሁ ወዘተ እንደ ማለት መሆኑን ያስረዳል። ይህ ማለት አንድ የሳቡኘት አባል ጎረቤቱ ወይም ሌላ አባል በደል ቢያደርስበት በቤተክርስቲያን ሕዝብ በተሰበሰበበት ቆሞ ስም ጠርቶ እገሌ እንዲህ ያለ በደል አድርሶብኛል ሲል በእግዜር መገን ፤ በሳቡኘት መገን፤ በሀገር መገን፤ በእገሌ መገን…ወዘተ ብሎ የሳቡኘት ወይም የሀገር ሸንጎው አይቶ ፍርዱን እንዲሰጠው በቃል የሚጠይቅ መሆኑንም ነው የሚያብራራው።

የእነዚህና ሌሎችም ጥንታዊ እሴቶች ባለቤት የሆነው የሶዶ ክስታኔ ሕዝብ በተለይም በባሕላዊው የሴራ ሥርዓት መንግሥት ባልነበረበት ወቅትም አካባቢና ሀገርን በማስተዳደር ለፍትሕ መስፈን አወንታዊ ሚና የተጫወተ ስለመሆኑ መረጃው ያመለክታል። ይህንን የሚያመላክቱ ሰነዶች አሁንም ድረስ ተሰንደው በብሔረሰቡ ሽማግሌዎች ዘንድ የተቀመጡ መሆናቸውን ይጠቁማል። ለምሳሌ ከካሳ ጋር ተያይዞ ከአንድ የሰውነት ክፍል ጣትን ብንመለከት ለሁሉም ጣቶች እኩል ካሳ እንደማይከፈልና ለጌጥ ተብለው የተለዩት በተለየ መልኩ ክፍያ እንደሚፈፀም ጠቅሶ፤ ይህ ባሕላዊ መተዳደሪያ ደንብ ከአስራ ስድስት ትውልድ በፊት ጀምሮ ሕዝቡ አምኖበት የሚተዳደርበት መሆኑን ያብራራል፡፡

በርካታ የብሔረሰቡ ተወላጆች ይህንን ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓት አክብረው የሚጠቀሙበት መሆኑን፤ ከዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት ጎን ለጎን ለአካባቢም ሆነ ለሀገር ሰላም መስፈን የማይናቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል። ሆኖም የብሔረሰብ ሸንጎ ምክር ቤት ከዚህ ሴራ መጽደቅ በኋላ የወማኖ ሴራ በተቋም ደረጃ ተቋቁሞና ከሚሰጠውም ትልቅ ሀገራዊና ማሕበረሰባዊ ግልጋሎት በማየት ከመንግሥት ጋር በመሆን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ መሥራት ያስፈልጋል። ለዚህም የሙያው ባለቤቶች ሰብስቦ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል።

በሌላ በኩል የጎርደና ሴራ የሶዶ ማህበረሰቡ ባሕል ታሪክና ቋንቋው ለማሳደግና ለመንከባከብ ብሎም ለማስተዋወቅ አጥፊዎች ለማረም የሚፈጠሩ ግጭቶችንና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የማይተካ ሚና እንዳላቸው አጠያያቂ አይደለም። በመሆኑም በተለይ የማህበረሰቡ ተወላጅ የሆኑ አዳዲስ ትውልዶች ሊጠቀምበትና እንዲሁም ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ የድርሻውን ሊወጡ ይገባል ባይ ነን፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም

Recommended For You