የዛሬው የዘመን እንግዳችን ወታደርና ደራሲ ወጣት ነው። የተወለደው ምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ውሃ ገልጥ ቀበሌ ውስጥ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ውሃ ገልጥ እና አውጃ በተባሉ ትምህርት ቤቶች ተከታትሏል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በሞጣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማረው። ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ በግብርና ትምህርት ክፍል በእንስሳት እርባታ ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። ይሁንና በተመረቀበት የትምህርት ዘርፍ ሥራ ማግኘት ባለመቻሉ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድሮ በማለፍ ሠራዊቱን ተቀላቀለ።
ላለፉት 11 ዓመታት በእግረኛ ክፍል ውስጥ ተመድቦ አገሩን በማገልገል ላይ ይገኛል። ከዚሁ ጎን ለጎን የሥነ-ጽሑፍ ተሰጥኦውን በማሳደግ አንድ የግጥም መድብልና አንድ ልብ ወለድ መጽሐፎችን ለንባብ አብቅቷል። በሕወሓት ሠራዊት ጥቃት የደረሰበትን የሰሜን ዕዝ ግፍ የሚያትተውን ‹‹የተከዳው የሰሜን ዕዝ›› የተሰኘውን አዲሱን መጽሐፍ ደግሞ በዛሬው ዕለት በይፋ ያስመርቃል። በዚህ መጽሐፍና በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከመጽሐፉ ደራሲ ሃምሳአለቃ ጋሻዬ ጤናው ጋር ቆይታ አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ሠራዊቱን የተቀላቀልክበትን አጋጣሚ አስታውሰንና ውይይታችንን እንጀምር?
ሃምሳለቃ ጋሻዬ፡– ገና የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁም አየር ኃይል ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድሬ በአብራሪነት ለመሰልጠን አልፌ ነበር። ግን ልጅነት ስለነበር ይከብደኛል በሚል ስጋት በሙያው ሳልቀጥል ቀረሁ። ከዩኒቨርሲቲ በተመረቅሁበት ወቅት ደግሞ በተማርኩበት ዘርፍ ሥራ አልነበረም። እንደአጋጣሚ መከላከያ ማስታወቂያ ሲያወጣ እኔ እንደአንድ የሙያ ዘርፍ ቆጥሬው ነው የተወዳደርኩት። ያም ቢሆን ሙያውን እወደው ነበር፤ በሂደት ደግሞ ለተቋሙም ሆነ ለሙያው ያለኝ ፍቅር እየጨመረ መጣ። በመሠረቱ እኔ ግብርና ትምህርት ክፍል የገባሁት በፍላጎቴ አልነበረም። ትምህርቱንም እስከምጨርሰው ድረስ ደስተኛ አልነበርኩም ነበር። በተለይ ለሥነ-ጽሑፍ ከፍተኛ ፍቅር ስለነበረኝ ሶሻል ትምህርት ዘርፍ ውስጥ የመግባት ፍላጎት ነበረኝ።
በወቅቱ እንዲያውም በርካታ ግጥሞችና መጣጥፎችን እፅፍ ነበር። የሚገርምሽ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ጀምሮ ነው የመፃፍ ክህሎቴ እያደገ የመጣው። የምፅፋቸውን ግጥሞች የወላጆች ቀን ሲከበር በማንበብ ከፍተኛ እውቅና እና ሽልማት አግኝቼ ነበር። ዩኒቨርሲቲ ከገባሁም በኋላ በሥነጽሑፍ ክበብ ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ ከሚያደርጉ ተማሪዎች አንዱ ነበርኩ። የምማረው ግብርና ቢሆንም ሙሉ ትኩረቴን አደርግ የነበረው በኪነ-ጥበባዊ ሥራዎች ላይ ስለነበር እኔ ብቻ ሳልሆን መላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ያለመክሊትህ ነው የምትማረው ይሉኝ ነበር። ሠራዊቱንም ከተቀላቀልኩኝ በኋላ በርካታ ጽሑፎችን ጽፌያለሁ፤ መሠረታዊ የጋዜጠኝነት ስልጠና ወስጄ የመከላከያ ሪፖርተር ሆኜ ሠርቻለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ተሰጥኦና ዝንባሌ ለሥነ-ጽሑፍ ከሆነ ታዲያ በሚዲያ ተቋማት ላይ መሥራት አይቀልህም ነበር?
ሃምሳአለቃ ጋሻዬ፡- ሁሉም ሰው በተጠራበት መክሊት ውስጥ ይሠራል ብዬ አላስብም። እኔም ምንም እንኳን ለሥነ-ጽሑፍና ለኪነ-ጥበብ ፍቅርና ዝንባሌ ቢኖረኝም ውትድርናንም በጣም የምወደውና የማከብረው ሙያ ነው። ደግሞም በሠራዊቱ ውስጥ የማገልገል ዕድሉን በማግኘቴ ራሴን እንደዕድለኛ ነው የምቆጥረው። ወታደር በመሆኔ ከምንም በላይ ነው የምኮራው። በተለይም ባለፈው አንድ አመት ተኩል ውስጥ መከላከያ በጣም የተከበረበት፤ የሠራዊቱ ዋጋ በሚገባው ልክ ዋጋ ያገኘበት ጊዜ ላይ ወታደር እንደመሆን ሌላ መታደል ያለ ያለ አይመስለኝም። እንዳልሽው የሚዲያ ተቋማት ውስጥ ብሆን የሥነ-ጽሑፍ ፍላጎቴን የበለጠ የማረከበት ዕድል አገኝ ነበር፤ ግን ደግሞ ሠራዊቱ ውስጥ ሆኜም ይህንን ዝንባሌዬን የማስተናግድበት ዕድል አላጣሁም። እንዲያውም የበለጠ ተሰጥኦዬን የማዳብርበት አጋጣሚ ነው ያገኘሁት።
መከላከያ ከገባሁ በኋላ በተለይ ከሁለት ዓመታት በፊት ጦርነት ስላልነበር ብዙ ጊዜ ስለነበር በርካታ ጽሑፎችን እፅፍ ነበር። በጣም ደስ የሚለው ነገር ደግሞ መከላከያ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ተሰጥኦ ይስተናገዳል። አቅሙና ፍላጎቱ ካለሽ የምታሳዪባቸው ዕድሎች አሉ። ጫካ ውስጥ ሳይቀር ሆኜ አነብና እፅፍ ነበር። በነገራችን ላይ ዛሬ ከሚመረቀው ‹‹የተከዳው ሰሜን ዕዝ›› መጽሐፌ በፊት ‹‹ውሸታም›› የምትል አንድ የግጥም መድብልና ‹‹ኢትዮጵያ ትሙት›› የሚል ልብወለድ መጽሐፍ ለንባብ አብቅቻለሁ። አዲሱ መጽሐፌ ሙሉ ለሙሉ በጁንታው ጥቃት በደረሰበት የሰሜን ዕዝ ላይ ያጠነጠነ እውነተኛ ታሪክ የሆነ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ ከጥቅምት 24 እስከ ታኅሣሥ 9 ቀን 2013 ዓ.ም የነበረውን ሁኔታ ነው የሚሸፍነው። ይህም ማለት የመጀመሪያው የሰሜን ዕዝ ጥቃት ከተፈፀመበት ጦርነቱ አልቆ ተመልሰን የተደራጀንበትን ጊዜ ነው የሚዳስሰው። ይህም ቅፅ አንድ ነው፤ ከዚያ በኋላ ያለውን ታሪክ አያካትትም።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ታሪክ ለመፃፍ የተለየ ምክንያት ነበረህ? እንዴትስ ፃፍከው?
ሃምሳለቃ ጋሻዬ፡– በነገራችን ላይ እኔ ራሴ ከታፈኑት የሰሜን ዕዝ አባላት አንዱ ነበርኩኝ። የፃፍኩትም በራሴና በጓዶቼ ላይ የደረሰውን፤ በዓይኔ የተመለከትኩትን፤ የኖርኩትንና የሰማሁትን እውነተኛ ታሪክ ነው። እኔ 20ኛ ክፍለጦር ሆኜ አዲግራት ነሐሴ ወር ላይ በ2012 ዓ.ም ነው የተመደብኩት። ሁለት ወር ሳልቆይ ነው ይህ ጥቃት የተፈፀመው። ጥቃቱ በተፈፀመበት ወቅት ከታፈኑ ሠራዊት መካከል ነበርኩኝ። ለ25 ቀናት በአፈና እና በስቃይ ውስጥ ነበርኩኝ። እኔ ደግሞ በፊትም ቢሆን ከቦታ ቦታ ስንቀሳቀስ ማስታወሻ መፃፍ እወድ ነበር። የተለያዩ ነገሮች ይገጥሙሻል።
ይሄ ነገር ሲከሰትም እያንዳንዱን ነገር ቦታውንና ጊዜውን ሳይቀር በመጥቀስ ወደ መፃፍ ነው የሄድኩት። በመጀመሪያ ላይ በርግጥ ጥቃቱ በዚህ ልክ ይፈፀማል፤ ጦርነቱም ይሰፋል ብዬ አልጠበኩም ነበር። ሆኖም እያንዳንዷን ክስተት እፅፍ ነበር። ዕለት ዕለት ግን ነገሮች እየባሱ ሄዱ። እኔም መፃፌን ቀጠልኩኝ። ጓደኞቼም እያንዳንዱን ክስተት እንድፅፍ ይገፋፉኝና ይደግፉኝ ነበር። የምፅፈውም በስልኬ ስለነበር፤ ስልኬ እንዳይወሰድብኝ ሁሉም ጓዶቼ ተከላክለውልኝ ነበር።
የሚገርምሽ ይህች ታሪካዊ ስልክ አራት ጊዜ ከመቀማት ድናለች። እነሱ ቢያውቁ ኖሮ አይደለም ሞባይል እስኪሪብቶና ደብተር እንኳን ሳይቀር ነው የሚቀሙት። ምክንያቱም በየቀኑ ነበር እንፈተሽ የነበረው። በአፈና የቆየንባቸው እያንዳንዱ ቀናት የአመት ያህል የሚረዝምበት ሁኔታ ነበር ያሳለፍነው። በጣም ብዙ ስቃይ ነበር ያደርሱብን። በጓደኞቼ ድጋፍ ተደብቄ እፅፋለሁ፤ በድብቅ ፎቶ እናነሳም ነበር። እነዚህን ፎቶዎች በመጽሐፌ ውስጥ አካትቼያቸዋለሁ።
እንደዕድል ሆኖ ቀድመው ከተያዙ የሠራዊቱ አባላት አንዱ ስለነበርኩ አብዛኛው ሠራዊት ጫካ እያደረ እኔና ጥቂት ጓዶቼ ቤት ውስጥ የማደር ዕድሉ ገጥሞን ነበር። ልብስ ተሸፋፍኜ ነበር የምፅፈው። ያም ሆኖ ግን በከፍተኛ ደረጃ በርሃብ እንድንሰቃይ ያደርጉን ነበር። በርሃብ ብዛት የሞቱ ጓደኞቼም አሉ። ምክንያቱም በአራት ቀን የሚያመጡልን አንድ ዳቦ ነው፤ ውሃ ማግኘት አይቻልም ነበር። በዚያ ላይ በጣም ብዙ ሠራዊት ነው ያለው። ደግሞም እጅ ላለመስጠት በርካታ ቀናት በጦርነት ውስጥ ስለቆየን ብዙ ተጎድተን ነበር።
ምግብ የጠየቁ ልጆች ዓይናችን እያየ ገድለዋቸዋል። ከዚያ በተቃራኒ ደግሞ ለእኛ የሚያለቅሱ፤ አፍነው ሲወስዱን የሚከራከሩልን ፤ ለእኛ ሲሉ የተገደሉ የክልሉ ተወላጅ የሠራዊቱ አባላትና ሲቪል ሰዎች ነበሩ። በዚህ አጋጣሚ ግን የትግራይ ተወላጅ የነበሩ ሁሉም አባላት ሠራዊቱን እንደከዱ ተደርጎ በሚቀርበው ሃሳብ እኔ አልስማማም። አንዳንድ የክልሉ ተወላጅ አባላት ከእኛ ሳይለዩ ስለእውነት ሲሉ የሞቱ እና ክቡር መስዋትነት የከፈሉ አሉ። ለእኛ የሚያለቅሱ እናቶችም ነበሩ። እነዚህን ነገሮች ስመለከት ወዲያውኑ የሚቀናኝ ማስታወሻዬ ላይ ማስፈር ነበር።
እንደሚታወቀው ደግሞ ትግራይ ውስጥ በጣም በርካታ ካምፕ ነው ያለው። ክልሉ በሙሉ ካምፕ ነው ማለት ይቻላል። በየካምፑ ብዙ ግፎች ተፈፅመዋል። ሠራዊቱ አንድ ላይ ስለተሰበሰበ በየካምፑ የተፈፀመውን ነገር የመስማት ዕድሉ ነበረኝ። የትኛው ካምፕ ላይ ምን እንደተፈፀመ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ለእኔ በጣም ቀላል ነበር። ከበደሉ ባሻገር የተደረጉ በጎ ተግባራትንም የማየት አጋጣሚው ነበረኝ። ከተጨፈጨፈውና ከተገደለው ባሻገር ጥቂት የማይባል ሠራዊት በሕይወት መትረፍ ችለዋል።
ይህ እንዲሆን ደግሞ በጣም በርካታ የትግራይ ተወላጆች አስተዋፅኦ ነበራቸው። የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻው ሳይቀር ግማሹ ሲተኩስብን ሌላው ይከላከልንን ነበር። ሲቪሉ ማህበረሰብ ራሱ የተከፋፈለ ነበር። የተወሰነው እነሱን ሲደግፍ፤ ሌላው በእኛ በኩል ሆኖ የሚዋጋ አለ፤ መሃል ላይ ቆሞ ግራ የተጋባና የተደናገጠ ሕዝብ ነበር። እነዚህ ሁሉ ነገሮች እውነተኛ ታሪክ ስለሆኑ በሁሉም ፈርጅ ያለውን ለማካተት ሞክሬያለሁኝ።
አዲስ ዘመን፡- ብዙጊዜ ባለው ሂደት ታሪክ በአፍ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ በቆየ እውነታ ላይ ተመርክዞ ነው፤ ይህም ደግሞ ታሪኩ በራሶ ተዛብቶ የሚቀርበበት ሁኔታ እንደፈጠረ ይታመናል፤ ከዚህ አኳያ አንተ ራስህ የታሪኩ አካል ሆነህ መፃፋህ ምንዓይነት ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለህ ታምናለህ?
ሃምሳአለቃ ጋሻዬ፡- እንደሚታወቀው ይህንን መጽሐፍ የፃፍኩት በሕይወትና በሞት መካከል ሆኜ ነው። በመሆኑም እውነታውን ለሕዝብ ለማድረስ እንጂ እንዲህ በሕይወት ተርፈን በመፃፍ ደረጃ ለማሳተም እበቃለሁ ብዬ አልነበረም። ብዙዎቻችን ያጋጠመንን ችግር ለሕዝብ የሚያደርስ ሰው እንዲተርፍ ፈጣሪን እንማፀን ነበር። ምክንያቱም ያሳለፍነው ጊዜ በጣም ከባድ ነበር። ብዙዎቻችንም ከዚያ ሁሉ ስቃይ እንወጣለን ብለንም አናስብም ነበር። ግን እኛም በሕይወት ተርፈን የደረሰብንን በመጽሐፍ ለማሳተም መቻሌ ራሴን እንደዕድለኛ ነው የምቆጥረው።
ከዚያ ባለፈ ግን እንዳልኩሽ የሆነውን ሁሉ አንድ በአንድ ሳልጨምር ሳልቀንስ ነው የፃፍኩት። በተቻለ መጠን በጣም ሚዛናዊ ለመሆን ሞክሬያለሁ። በተለይ ወታደር እንደመሆኔ የወታደር ወኔና ስሜታዊነት በመውጣት ለመፃፍ ጥረት አድርጌያለሁ። ምክንያቱም በውጊያ መንፈስ የምፅፈው ከሆነ ሚዛናዊ ላልሆን እችላለሁ የሚል ስጋት ስለነበረኝ በተቻለ መጠን ከወታደራዊ ስነልቦናዬ ለመላቀቅና ገለልተኛ ለመሆን ሞክሬያለሁ። በተለይ ደግሞ እኔ ራሴ የዚህ አካልና የታሪኩ ትክክለኛ ምንጭ በመሆኔ እውነታው ቀጥታ እንዲደርስ ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም በስማ በለው ከሚፃፈው ይልቅ የችግሩ ሰለባ የነበርኩት እኔ መፃፌ የበለጠ ተቀባይነት ይኖረዋል ብዬ ነው የምገነዘበው።
ከዚያ ባለፈ ሕዝቡ ይህንን መጽሐፍ እንዴት ይቀበለዋል? የሚለውን ነገር ለአንባቢ መተው ነው የሚሻለው። እኔ ግን በዚህ መጽሐፍ የተነሳ ምንም ነገር ቢመጣ አይቆጨኝም። እንዳልሽው ብዙ ሰዎች አስተያየት እየሰጡኝ ነው ያሉት። አንዳንዶቹ በሽፋኑ ብቻ ላይ በመሞርኮዝ ‹‹ከዚህ ቀደም በተዛባ ታሪክ መጣላታችን አልበቃ ብሎ አንተ ደግሞ ይህንን መጥፎ ታሪክ መፃፍ ቀጣዩ ትውልድ ላይ መጥፎ ጠባሳ ትጥላለህ›› የሚሉኝ አሉ። እኔ ግን በእውነተኛ ታሪክ ላይ ከተፃፈ የምንጣላበት ምክንያት አለ ብዬ አላምንም።
እውተኛ ታሪክ ሊያጣላን አይገባም። እንዲያውም ቀጣዩ ትውልድ ከዚህ ታሪክ ብዙ የሚማርበት ነው የሚሆነው። እንዲያውም በትክክለኛ አዕምሮ ለሚያስብ ሰው የተጣሉ ሰዎችን የሚያስታርቅ መጽሐፍ ነው። እኔም በዚያ ልክ ይሆናል ብዬ ነው የምጠብቀው። እኛ የኖርበት ስለሆነ ምንም ላይመስለን ይችል ይሆናል፤ በሩቅ ሆኖ ለሚያየው ሰው ግን ሲያነበው የከፈልነው ዋጋ ምን ያህል ከባድ እንደነበር የሚገነዘበው።
ይሁንና በእኛ አገር ታሪክ ሲፃፍ አንድ ፈረንጅ የፃፈውን እንደማጣቀሻ አድርጎ ካልተፃፈ በስተቀር ለመቀበል የሚቸገሩ ብዙ ሰዎች አሉ። እኔ ግን በዚህ ስለማላምን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ምንም ዓይነት ማጣቀሻ አልተጠቀምኩም። ሆን ብዬ ነው ያደረኩት። እኔ በሕይወት እያለሁ ያየሁትንና የኖርኩት ሰው ሌላ ማጣቀሻ መጽሐፍም ዋቢ የሚሆን ፈረንጅ አያስፈልገኝም። ይህ መጽሐፍ ራሱ ሌሎች ለመፃፍ መነሻና ማሻቀሻ የሚሆን ነው። ለምርምር ሥራ ጭምር የሚጠቅም ነው። ምክንያቱም በእኛ ላይ ብሎም በአገር ላይ የተፈፀመው ክህደት ለትውልዶች ታሪክ ሆኖ የሚቆይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የዚህ መጽሐፍ ርዕስ በሠራዊቱ ላይ ከደረሰው ጉዳት አንፃር ምን ያህል ይሸከመዋል ብለህ ታምናለህ?
ሃምሳለቃ ጋሻዬ፡– በነገራችን ላይ በዚህ መጽሐፍ ርዕስን በሚመለከት ከአንዳንድ ሰዎች ጋር በጣም ተጨቃጭቀናል። እኔ ግን መቶ በመቶ አምኜበት ይመጥነዋል ብዬ ነው ያስቀመጥኩት። እንዳልኩሽ የሚያጠነጥነው የአንድ ወር ጊዜ እንደመሆኑ በዚያ ጊዜ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሊገለፅ የሚችለው በክህደት ብቻ ስለሆነ ነው ርዕሱን የተካደው ሰሜን ዕዝ ብዬ የሰየምኩት። ምክንያቱም እኛ ትግራይ ውስጥ ስንኖር የማኅበረሰቡ አካል ሆነን ነው የኖርነው። እኔ ራሴ ለቦታው አዲስ ብሆንም የፊተኛውን መጽሐፌን ሸጬ ባገኘሁት ገቢ ለተማሪዎች ስጦታ ሰጥቼ ነበር።
በተለይ አዲግራት አካባቢ ለሚኖሩ 200 ለሚሆኑ ሕፃናት ቢያንስ ለአንድ ዓመት የሚሆን የጽሕፈት መሣሪያ ለመስጠት ጥቅምት 17 ጀምረን አቅደን መንቀሳቀስ በጀመርንበት በሳምንቱ ነው ጥቃት ያደረሱብን። ከዚያ በፊት ደግሞ አምበጣ መጣና ያንን ለማባረርና የደረሰውን ሰብል በማጨድ ከአርሶ አደሩ እኩል ነበር የደከምነው። ያን ሁሉ ዋጋ እየከፈለ ለነበረው ያ ድንቅ ሠራዊት ላይ በምትኩ በሌሊት ጥይት ነው የዘነበበት። በተለይ እኔ በዋነኝነት እኔ ስለነበርኩኝ የእርዳታውን ሥራ የማስተባብረው ሙሉ ትኩረቴን እዚያ ላይ አድርጌ ስለነበር እንዲህ ዓይነት አሰቃቂ ግፍ ይፈፀምብናል ብዬ አላሰብኩም ነበር። ምንአልባት ለዚህ ተግባር ሌላ ቃል ስለሌለው እንጂ ‹‹ክህደት›› ከሚለው በላይ ብገልፀው ደስ ባለኝ ነበር።
ብዙ ሰዎች እንደሚሉት በሠራዊቱ ላይ የተፈፀመው ድርጊት በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው። ምንአልባት ቢኖርም እንኳን የእኛን ያክል ይሆናል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም የእኛ ሠራዊት ትግራይ ውስጥ 23 ዓመት ሲኖር ከእናትና አባት በላይ ማኅበረሰቡን ቀርቦ ነው የኖረው። ወልዶ የልጅ ልጅ ሁሉ ያየ አለ። በየትኛውም ዓለም ካለ ሠራዊት በላይ ከሕዝብ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ነበረን። ይህ በመሆኑም የየትኛው አገር ሠራዊት ቢካድ ህመሙን የኛን ያህል አይሆንም። ምንአልባት ከዚያ በኋላ የሆነውን ነገር በቅፅ ሁለት ሲፃፍ ይሄ ርዕስ ላይቀጥል ይችላል። ለዚህም ነው ይህንን መጽሐፍ አጠቃላይ የጦርነቱን ሂደት የሚያካትት አድርጎ መወሰድ የሌለበት።
አዲስ ዘመን፡- አንተ እንደገለፅከው ከኅብረተሰቡ ጋር ያን ያህል ቅርበት ኖሯችሁ ሳለ ስለጥቃቱ እንዴት ቀድማችሁ ፍንጭ ማግኘት አልቻላችሁም?
ሃምሳአለቃ ጋሻዬ፡- ይሄ ጉዳይ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው። እኔ እስከሚገባኝ እና እዚህ መጽሐፍ ላይም እንዳሰፈርኩት ከጥቅምት 24 በፊት በግልፅም፤ በሰውርም የሚደረግ ነገር ነበር። ለምሳሌ በቴሌቪዥን ልዩ ኃይላቸውን አሰልፈው ሲፎክሩ ያሳዩን ነበር፤ ፕሮፖጋንዳቸውም ከባድ ነበር። በመሠረቱ እኛ ነሐሴ ወር ላይ ወደ ትግራይ ስንገባ በጣም ከባድ ስቃይ ነው ያሳለፍነው። ከዚያ በፊት እኔ ባድመ ላይ ተመድቤ ስለነበር ትግራይን በደንብ አውቀዋለሁኝ። እንዳልኩሽ ከማኅበረሰቡም ጋር የተለየ ቅርበት ነበረን። ከዚህ አንፃር የሕወሓት ሰዎች በግልፅ የሚያሳዩን ነገር ነበር።
ያንን ነገር እየታየን ቀደም ብሎ ጥንቃቄ ማድረግ አልተቻለም? ብለሽ ከጠየቅሽ ግን ትክክለኛውን ምላሽ ልሰጥሽ አልችልም። ምክንያቱም ከእኔ አቅም በላይ ነው። ግን ደግሞ ከኅብረተሰቡ የተለያዩ ጥቆማዎችን ይሰጡን ነበር። ደግሞም የትኛው ወታደር ከአንዱ ካምፕ ወደሌላው ካምፕ ለመሄድ መሣሪያ ይዞ መውጣት አይችልም። ሁሉም ነገር በእነሱ ቁጥጥር ውስጥ ነበር።
የትኛውም የሠራዊቱ መኪና ከካምፕ ሲወጣ መሣሪያ ይዞ መውጣት አይችልም። መኪናው ራሱ መውጣት የሚችለው በእነሱ ፍቃድ ብቻ ነበር። በተጨማሪም የእኛን የወታደር ልጆች ሳይቀር ያሰለጥኗቸው ነበር። የትግራይ ተወላጆች የሆኑ አባላት በሙሉ ከሌላው ሠራዊት ተነጥለው እዚያው ካምፕ ውስጥ ስብሰባ ያደርጉ ነበር። መጽሐፍ ውስጥ እደገለፅኩትም አንዳንዶቹ በቀልድ አስመስለው አንዳንድ ፍንጮችን ይጠቁሙን ነበር።
ለአብነት ያህል የቤተሰብ ፍቃድ ስንጠይቅ ‹‹ምንፍቃድ አስጠየቀህ? መከላከያን ማፍረሳችን ስለማይቀር ያኔ ጠቅልለህ ትሄዳለህ›› ይሉን ነበር። የደመወዝ ጉዳይ ሲናነሳ ደግሞ ‹‹አይደለም የደመወዝ ጉዳይ ልታነሳ ትጥቅ መፍታትም አለ›› የሚል ሃሳብ ያነሳሉ። አየሽ ይህንን ያክል ነበር የሚነግሩን! ፤ ግን ደግሞ ወታደር እንደመሆናችን ትዕዛዝና መመሪያ ትጠብቂያለሽ። ይህ አሠራር በመኖሩ ማንም ሰው የሚናገረውን ሰምተን እርምጃ መውሰድ አንችልም ነበር። ግን ይህ ጥያቄ የእኛም ስለነበር መጽሐፉ ውስጥም የተካተተው በጥያቄ ነው። በተለይ እነሱ ያንን ያክል ዝግጅት ሲያደርጉ ለምን ምላሽ መስጠት አልተቻለም? የሚለው ነገር አሁንም ለእኔም ሆነ ለሌላው ምላሽ ያላገኘ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡-ጥቃቱ ካደረሰው ጉዳት ባሻገር ግን ሕዝቡን በአንድነት የአገሩን ህልውና ለማስቀጠል እንዲነሳ ከማድረግ አኳያ የነበረው ፋይዳ እንዴት ይገለፃል?
ሃምሳለቃ ጋሻዬ፡-አንዳንድ ጊዜ አየሽ እንዲህ ያሉ ድንገተኛ ጥቃቶች በጣም በጣም ብዙ ጉዳት ይዘው በሚመጡበት ጊዜ ከችግሩ ባሻገር መልካም ነገርም ይዘው ይመጣሉ። በእርግጥ ጦርነት ባይመረጥም የራሱ ጠቀሜታም ነበረው። የማልክደው ነገር ይህ ጦርነት የብዙ ወገኖቻችንን ሕይወት ነጥቋል፤ የሠራዊቱን ሕይወት አመሰቃቅሏል፤ ልጅ ከወላጁ ተለይቷል፤ ቤተሰብ ተበትኗል፤ ሚስት ባሏን ያስገደለችበት፤ ልጅ አባቷን ክዳ አሳልፋ የሰጠችበት ለመቀበል የሚከብድ ሁኔታ ተፈጥሯል። እንዳልሽው ከለውጡ በፊት ሕዝቡና ሠራዊቱ ሆድና ጀርባ ነበር።
እንደአጋጣሚ ከለውጡ በፊት ጎንደር አካባቢ ነበርኩኝ፤ በወቅቱ ከነኮሎኔል ደመቀ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ አመፅ ሲቀሰቀስ ብዙ ጓዶቼን አጥቻለሁ። በጣም ከባድ ሁኔታዎችን አይተናል። ያ የሆነው ከዚህ ቀደም በነበረው ሥርዓት ነው። ሕወሓት ሕዝብና ሠራዊቱ እንዳይታረቅ አድርጎ ነበር ያጣላው። የዚህ ጦርነትም ውጤት ያ ነው። እንዳይታረቅ አድርጎ ያጣላውን ሠራዊት በገዛ እጁ በቀሰቀሰው ጦርነት እንዳይጣላ አድርጎ ሠራዊቱን ከሕዝብ ጋር አስታርቆታል ባይ ነኝ። ይህንን በአገርና በሠራዊት የተፈፀመ ክህደት ስትመለከቺ በቁጭት በኅብረት እንድትነሺ ነው የሚያደርግሽ። ብዙ ጉዳት ቢመጣብም ይህች አገር በሕዝቦቿ ኅብረት እንድትቀጥል አድርጓል።
በነገራችን ላይ እነሱ ሠራዊቱን ከሕዝቡ ጋር ብቻ ሳይሆን ተለያይቶ እንዲኖር ያደረጉት እርስበርሱ እንዳይጋባባ አድርገው ነበር የቀረፁት። በተለይ በጎሳ በመከፋፈል ሁሉም በየጎጡ እንዲቧደን በማድረግ ከሌላው ጋር ተስማምቶ እንዳይኖር ያልቆፈሩት ጉድጓድ የለም። ሲጀመር ምዝገባው ራሱ በጎሳ የተከፋፋለ ነበር። ይህንን ስልሽ አሁን ድረስ የትግራይ ተወላጆች ሆነው በኢትዮጵያዊነታቸው የሚኮሩና ከሁሉም ጋር በፍቅር መኖሩን የሚመርጡ የሠራዊቱ አባላት አልነበሩም ማለቴ አይደለም።
ከአመራር እስከ ተራ ወታደር ድረስ ከእኛ ጋር አብረው የተሰቃዩ አሉ። አብዛኛዎቹ እኛን ክደው ሲሄዱ ከእኛ ጋር የነበሩት ጥቂቶቹ ግን ብዙ ፍዳቸውን አይተዋል። ሠራዊቱ ግን ለመከፋፈል የተደረገውን ጥረት አልቀበልም ብሎ አንድ ሆነ፤ ይልቁንም ሊከፋፍሉት የመጡትን አሳፍሮ ነው የመለሳቸው። በተለይ ከጥቃቱ ቀን ጀምሮ እነሱ በጎሳ ከፋፍለነዋል፤ አይግባባም ብለው ያሰቡት ይህ ሠራዊት እንደአንድ ሕዝብ ሆኖ ነበር ሲታገላቸው የነበረው።
በአጠቃላይ ጥቃቱ ሠራዊታችንን በጣም ጎድቷል፤ በሌላ በኩል ግን ኅብረቱ የተጠናከረ ሠራዊት አድርጎታል። የእሱ ውጤትም ነው እንድናሸንፍ ያደረገን። እንደሥራቸው ቢሆንማ ኖሮ አይደለም ሠራዊቱ ኢትዮጵያ ራሱ እስከዛሬ አትሰነብትም ነበር። እንደአጀማመራቸውና እንደእነሱ እቅድ ቢሆን ኖሮ ከዚህ በከፋ ችግር ውስጥ በገባን ነበር።
አዲስ ዘመን፡- እንዲህ ዓይነቱ ነገር ለቀጣይ ምን አሰርተምሮ አልፏል ብለህ ታምናለህ?
ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ፡- በሠራዊቱ ላይ የተፈፀመው ይህ ድንገታዊ ጥቃት ከመጀመሪያው እንዲህ ይሆናል ብለን ባንጠብቅም ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ታላላቅ መንግሥታት ሳይቀር ነው የተሳተፉበት። በእኔ እምነት ኢትዮጵያ በዚህ ጦርነት ምክንያት የማይገባትን ዋጋ ከፍላለች። ይህንን ዋጋ የከፈለችው ደግሞ በራሷ ልጆች በጣም የሚያሳዝን እና የሚያስቆጭ ነው። ምክንያቱም እኛ ወታደሮች የአገራችን ሉዓላዊነት የምንጠብቀው ከውጭ ከመጣ ወራሪ ነው። አሁን እኛ እያደረግን ያለነው የህልውና ዘመቻ ነው።
ህልውና ከሉዓላዊነትም በላይ ከባድ ነው። ምክንያቱም የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው። የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ነው። ከሉዓላዊነትም በላይ የመጠቀ ነው። የእያንዳንዱን ቤት የሚያንኳኳም ነው። ይህ መሆኑ ነው የቆየንበትን ሁኔታ ከባድ ያደረገው። እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ለጦርነት አዲስ አይደለችም፤ ብርቋም አይደለም። እንዳካሄደችው ጦርነት ብዛት እስካሁን እንደአገር መቀጠሏ ራሱ አስገራሚነው። እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን፤ እነሱ ኢትዮጵያን አቆይተውልናል፤ እኛም እናስቀጥላታለን።
ሆኖም የተፈፀመው ክህደት በሕዝቦች መካከል የማያባራ ፀብ የሚፈጥር መርዝ ነው የሚሆንብን ብዬ እሰጋለሁ። በዚህ አጋጣሚ ግን ባንዳ የሆኑ ሰዎችን ለመመንጠር አስችሎናል። ከዚህ በኋላም ነገሮችን በጥንቃቄ ለመያዝ ትምህርት የሰጠ ነው ብዬ ነው የማምነው። በተጨማሪም ለአገሩ፣ ለሕዝቡ ለሰንደቅ ዓላማው ክብርና ፍቅር ያለው ሠራዊት እንዲፈጠር ያደርጋል።
እውነትን ብቻ ይዞ የሚሄድ፤ በትክክለኛ መንገድ ግዳጁን የሚወጣ ሠራዊት በደንብ እንዲፈተሽ ያደርጋል። ምክንያቱም በጦርነት ቀልድ የለም፤ ትንሽ ስህተት መሥራት ከፍተኛ ዋጋ ነው የሚያስከፍለው። እንዲህ ዓይነት መጽሐፍም የሚፃፈው እንድንማርበት ነው። ይህ ጦርነት የሠራዊቱን የቀድሞ ስም የቀየረም ጭምር ነው።
አዲስ ዘመን፡-ሠራዊቱ ዳግም ሪፎርም መደረጉ የኢትዮጵያዊነት ቁመና ያለው ተቋም ለመፍጠር ምን ፋይዳ ይኖረዋል?
ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ፡– እኔ መከላከያ ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ የአንድ ብሔር የበላይነት ጉዳይ ውስጥ ለውስጥ በደንብ ሲወራ የነበረ ነው። ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በደንብ ገንፍሎ በገሃድ የታየው የእርሱ ውጤት ነው። ከአዲስ አበባ ሄዶ ነው መገናኛ ኃላፊው የሰሜን ዕዝን የሬዲዮ ፕሮግራም ሲስተም የቀየረው፤ ይህ ሰው የትግራይ ተወላጅ ነው። አዲስ አበባ ሄዶ የአንድን ግዙፍ ዕዝ የሬዲዮ መገናኛ ሲስተምን ሲቀይር ማንም አላወቀም።
ይህም ውስጥ ለውስጥ ምን ያህል እንደሚሠሩ ነው። የሚገርምሽ ሰውየው ሲመጣ የእኛ ሠራዊት ሰንጋ ጥሎ በክብር ነበር የተቀበለው። እሱ ግን እንዲህ ላደረገለት ሠራዊት መሞቻውን ነው አዘጋጅቶለት የሄደው። ውጭ አገር ሱዳን ሰላም ማስከበር የሄዱ ጀነራሎች መጥተው ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል። በደንብ ስለሠሩበት፣ ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን ስለያዙ ነው ያደረጉትም።
በወቅቱ የነበረውን እኛ በግልጽ መናገር አንችልም ነበር። ውስጥ ለውስጥ ከምትመሳሰይው ሰው ጋር የምታወሪው ነበር። መከላከያ ውስጥ በፌዴራል ቋንቋ ብቻ ነው የሚሠራው። ነገር ግን አንድ እስታፍ በትግርኛ ብቻ ስብሰባ የሚደረግበት ነበር። በብዛት ዋና ክፍል፣ አስተዳደሩ፣ ስልጠና ክፍሉ፣ አዛዥነት ደረጃ ላይ ያሉ እነርሱ ነበሩ።
ሌላው ተዋጊ ነበር። አማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ አፋርኛ፣ ሱማሊኛ ወይም ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ በመካከላቸው አልነበረም። በሙሉ አንድ ብሔር ብቻ ነበሩ። የትምህርት ዕድል ሲሰጥ፣ ሰላም አስከባሪ የሚላከው በብሔር ተጠራርተው ነው። በአጠቃላይ በአንድ ብሔር የበላይነት ነው ይህንን ችግር ያመጣው።
ለውጡን ተከትሎ በተደረገው ሪፎርም በጣም ትልቅ ነገር ተደርጓል። በእኔ እምነት የመከላከያ ሠራዊት ሪፎርሙ ባይደረግ ኖሮ ጥቅምት 24 ቀን የሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ቤተ መንግሥትም ይደገም ነበር። ሪፎርም በመደረጉም ነው ኢትዮጵያን እንደአገር እንዲያስቀጥል የመከላከያ ሠራዊት እንዲቆይ የተደረገው። ከእዚያ በፊት እኮ የመምሪያ ኃላፊ፣ ክፍለ ጦር አዛዥ፣ ዕዝ አዛዥ የብሔር ምጥጥን ባይደረግ ኖሮ በአንድ ቀን ኢትዮጵያ ትፈርስ ነበር።
ግን ያም ሆኖ በደንብ ስለሠሩበት እና እስከ ታች ድረስ ለማስተካከል ብዙ ጊዜ ይጠይቅ ነበር። ምክንያቱም ሙያ ነው፣ መሪነት ነው። እየዳበረ የሚመጣ ነው፣ በትምህርት፣ በጊዜ ቆይታ የሚመጣ ነው። ማንንም አንስተሸ ጀኔራል ልታደርጊው አትችይም። ታች ያለው የሰለጠነና የበቃ ሰው ስላልነበር አምጥቶ ለመተካትም አስቸጋሪ ነበር። ሪፎርሙ ሠራዊቱ ላይ የደረሰውን ጥቃት፣ አገር እና መንግሥት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጥቃት በእጅጉ ቀንሷል። ያ ጥቃት በሰሜን ዕዝ እንዲደርስ ያደረገው ደግሞ በፊት ይሠሩበት የነበረው መረቡ በጣም ብዙ ጊዜ ይፈጅ ስለነበር ሠራዊቱ ሙሉ ለሙሉ እንዳይፈራርስ ሪፎርሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው።
አዲስ ዘመን፡- ዓለም አቀፍ መስፈርቱን ያሟላ ሠራዊት ለመፍጠር ስነ-ምግባሩ በምን መልኩ መቀረፅ ይገባዋል ብለህ ታምናለህ?
ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ፡– ወታደር ፖለቲካ፣ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ሃይማኖት፣ ብሔር አይመለከተውም። ሰው መብቴ ነው ብሎ የሚተገብራቸው አብዛኞቹ ነገሮች አይመለከቱትም። እርሱ የሚመለከተው ሕገ-መንግሥት ነው። ሕገ-መንግሥት ማለት ኢትዮጵያ የምትተዳደርበት፣ ሕዝብ የሚመራበት ነው። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከጎጥ ወይም ከዘረኝነት የፀዳ ሠራዊት ለመገንባት ሰፊ ጊዜ ያስፈልገዋል። አሁንም ሠራዊቱን ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖት፣ ከብሔር ጋር ያገናኙታል።
የአገሪቱ ፖለቲካ የታመመ ነው። በዚህ በታመመ ሂደት ጤናማ ሠራዊት ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ፖለቲካው፣ የሕዝቡ ኑሮ፣ ሰላምና ፀጥታው ሲስተካከል ነው ሠራዊቱ በአግባቡ ሊገነባ የሚችለው። ሰላም በሌለበት ሠራዊት ግንባታ የለም። አሁን ሠራዊት የምትገነባው ለጦርነት ነው። መሠረታዊ፣ ብቁ፣ በአስተሳሰቡ የበቃ፣ ሕገ-መንግሥቱን የሚጠብቅ፣ ለሰንደቅ ዓላማው የሚሞት፣ ለማንም ፖለቲካ ተላላኪ የማይሆን፣ በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በዘርና በጎጥ የማያምን ሠራዊት ለመገንባት ፖለቲካው መስተካከል አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ።
ሃምሳአለቃ ጋሻዬ፡- እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2014