ቀዳሚ መንደርደሪያ፤
ግፈኞች ለበደል የሚፈጥኑት ሟች መሆናቸውን ስለማያስቡ ብቻም አይደለም። ሟችነታቸው ባይጠፋቸውም የግፋቸውን ጥም ለማርካት ሲሉ በደላቸውን እንደ ውሃ ስለሚጎነጩ ለፀፀት ጊዜ አይኖራቸውም። የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጡራን የሚለየው በጋራ በጸደቀ ሕግ መመራቱ ብቻ ሳይሆን በህሊና ዳኝነትና አመዛዛኝነት ጭምር ራሱን ስለሚገዛ ነው። ክፉና ደጉን ለይቶ ራሱን ለመግራትም ሆነ ለመምራት ፈጣሪ የተለየ ዕውቀት አድሎታል። እውነታው ይህ ቢሆንም ሰብዓዊ ፍጡር በአብዛኛው ነገን የሚናፍቀው «ስኬት» በማለት ከሚያልመው «ጫፍ» ላይ ለመድረስ እንጂ ከአፈር ጋር የሚዳበል ሟች መሆኑን ለማሰላሰልና ለማሰብ እጅግም ሲተጋ አይስተዋልም። የሩጫውን ልጓም እየገታም ቆም ብሎ ተሰባሪ መሆኑን ለመፈተሽ ጊዜ አይሰጥም።
ደራሲ ማሞ ውድነህ በአንድ መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ እንዲህ የሚል ሃሳብ አስፍረዋል፡-«አንዳንዶች… ከትቢያ እየተነሱ ለታላቅ ኃላፊነት ከደረሱ በኋላ የማሰብና የማስተዋል ብርታታቸው እየደከመ [እንደ ዘለዓለም ነዋሪ ራሳቸውን እየቆጠሩ]፣ የሰው ዘር እልቂትና የአገር ውድመት የየዕለቱ ደስታቸው እየሆነ…ሥራቸው ወጥመድ…ፍጻሜያቸው አሰቃቂ ሆኖ ያለፉ ብዙዎች ናቸው።» በማለት ከገለጹ በኋላ፤ አንድ የአገራችንን መራር ታሪክ በማስታወስ እንዲህ ጽፈዋል።
«…ያለ ርህራሄ ተደበደቡ። በተገኘው መሣሪያ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ተፈጁ። ቤት እየተዘጋባቸው ተቃጠሉ። በተወለዱበት አገራቸው፣ በአደሩበት አልዋሉም። በዋሉበት አላደሩም። በሀብታቸው አላዘዙበትም። የበደሉት ነገር አልነበረም… የፍርድ መሻት ጩኸታቸውም መልስ አላገኘም።…ፀጋ ከአገሪቱ መሬት ተገፈፈ…ቀኑም ሌሊቱም አንድ ነበር። ይህን ሁሉ ግፍ ያስፈጸሙት….» እያሉ ይቀጥላሉ።
ደራሲው «ይህንን ሁሉ ግፍ ያስፈጸሙት…» በማለት የሚወቅሱትን አካል ማንነት በሚገባ ገልጸውታል። ስለማን እንደሚናገሩ ባናውቅ ኖሮ ይህንን በእንጥልጥል የተተወ ድርጊት በቀጥታ የምናመሳስለው ከአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ስለመሆኑ አስረግጦ መናገር ይቻላል። ለመሆኑ ከላይ ከተዘረዘሩት አሰቃቂ ሁኔታዎች ዛሬ በዐይናችን ፊት ያልተፈጸመ ምን ነገር አለ? እንዲያውም ባይከፋ? ለማንኛውም ነፍሰ ሄሩ አንጋፋው ደራሲያችን በመጽሐፋቸው ውስጥ የተረኩት የፋሽስቶቹ መሪ የቬኒቶ ሞሶሎኒ ወራሪዎች በአገራችን የፈጸሙትን ግፍ ነበር። ለነገሩ የሩቁን ታሪክ ወደ ኋላ ዞረን ለመመልከት ምን አታከተን። የእኛዎቹ አሸባሪ ጉዶች የፈጸሟቸውና እየፈጸሟቸው ያሉት የክፋት ጥግ ግፎች ከዚህ በምን ይለያሉ። ደግሞስ ባይበልጡ!
ይህ ጸሐፊ «ልጄ ሆይ እንደምትኖር ሆነህ ሥራ፤ እንደምትሞት ሆነህ ኑር» የሚለውን ልብ ጠለቅ የጠቢብ ምክር ለመስማት የታደለው ገና በታዳጊነት ዕድሜው ላይ እያለ ነበር። ዓመታት ያላደበዘዙት ይህ ድንቅ አባባል ዛሬም ሆነ በወደፊት ቀሪ ሕይወቱ በፍጹም ወይቦ ወይንም ነትቦ ሊጠፋ እንዳይችል ሆኖ በአእምሮው ውስጥ ታትሞ ቀርቷል።
አገሬን በየዘመናቱ የገጠሟት የውስጥ ችግሮች በሙሉ መንስዔያቸው በአግባቡ ቢጠና ውጤቱ የሚመራን እንደ ዘለዓለማዊ ነዋሪ ቁምነገር ሠርተው፤ እንደ ሟች ደግሞ በህልፈት ሊሰናበቱ መቻላቸውን ማሰብ የማይፈልጉ ጨካኞች በሚፈጥሯቸው ችግሮች ምክንያት እንደሆነ በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል።
በተለይም እየኖርንበት ባለነው በዚህ የዕለት ጀንበራችን እየተፈጸሙ ያሉ መከራዎቻችንና አበሳዎቻችን የሚመነጩትና የሚረጩት እንደ «ቋሚ ነዋሪ» በራሳቸው ዙፋን ላይ በነገሡ ዜጎችና ሹመኞች አማካይነት መሆኑ ምስክር አያስፈልገውም። «ግፈኛ የሠይጣን መልዕክተኛ» መባሉስ ስለዚሁም አይደል።
አገሬን ሌሎች እንደምን ይገልጧታል?
«ግምገማ» የአገሪቱ ቋሚ ባህል እስኪመስል ድረስ መሠረቱ የተተከለው እጅግ ጠልቆ ነው። መገማገሙ ባይከፋም ከመጯጯኹ በኋላ የተገማገሙበት ጉዳይ ፍሬ አልባ፤ የተገመገመው ግለሰብም ቂመኛ ከመሆን ውጪ አንዳችም ትርፍ ስለማስገኘቱ «አትርፈንበታል» የሚሉት ይነግሩን ካልሆነ በስተቀር እኛ የታዘብነው ውጤቱ «የደመና ክምር» ሆኖ ሲበንና ሲበን ነው።
ለነገሩ ዓላማ ያለው ግምገማና ለማቅናት የሚደረግ መፈታተሽ ሁሉ እርባና ቢስ ነው ብሎ መጠቅለል እንዳልሆነም አጽንኦት ሰጥቶ ማስታወስ ያስፈልጋል። የመደበኛ የሥራ ውጤት በሥራ መሪ እንደሚገመገም፣ የፖለቲከኞች ስምሪትም (ብዙ ጊዜ «ለጥሎ ማለፍ» ሽኩቻ ጥሩ ሜዳ መሆኑ ሳይዘነጋ)፤ «ምን ሠርተህ/ሽ ከረምክ/ሽ፣ ምንስ ልትከውን/ልትከውኚ ጨከንክ/ሽ እንደሚባባሉ የሹሞችን ፊት አይተው የሚያድሩት ሚዲያዎቻችን ዕለት በዕለት ግብሩን ሳይሆን ቃሉን ሳያሰሙን ጀንበር ጠብታ አትመሽም።
ለማንኛውም አሰልችቶን ኖሮ እያሰለቸን ያለውን «የግምገማ ባህል» በወፍ በረር ግምገማ ከገመገምነው ዘንዳ ወደ መነሻ ሃሳባችን አቅንተን እንደተለመደው «መስሚያ ጆሮ» ይኖራቸው ከሆነ «ለሚመለከተው ሁሉ!» በማለት ትዝብታችንን እንዘረግፋለን።
ለመሆኑ አቻ አገራት አገሬን ይገምግሙና ሪፖርቱን ይግለጡልን ብንል የግምገማቸው ውጤት ምን ሊሆን ይቻላል? ከትናንት ይልቅ ዛሬ በዚህ ጉዳይ ላይ ቀልብያችንና ነፍሳችንን ሰብሰብ አድርግን «እህ» ብለን ብናደምጣቸው አንዳች ቁምነገር አናገኝም ይሆን?
የግምገማውን ውጤት ከመተንበያችን አስቀድሞ የዚህን ጸሐፊ አንድ መራራ ገጠመኝ ማስታወሱ ቦታው ሳይሆን እንደማይቀር በመገመት በአጭሩ እንዲህ እናስታውስ። ይህ ጸሐፊ ከጥቂት ዓመታት በፊት ታላቅ የተሰኘ ስልጠና ለመሳተፍ «የበቃሁና የነቃሁ ነኝ» በሚል አንድ አገር ተገኝቶ ነበር። ከስልጠናው መርሃ ግብሮች መካከል አንዱ እያንዳንዱ ሰልጣኝ በስልጠናው መስጫ ኢንስቲትዩት አካባቢ በሚገኙ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች እየተገኘ ስለ አገሩ የማስተዋወቂያ ንግግር እንዲያደርግ ይጠበቅበት ነበር።
ይህ ጸሐፊም በተመደበበት ት/ቤት ተገኝቶ ስለ አገሩ ስለ ኢትዮጵያ መሠረታዊ ናቸው የሚላቸውን ማሞካሻዎችና «መኩሪያ ባህሎች» በመዘርዘር ከተረከ በኋላ ተማሪዎቹ ጥያቄ ካላቸው እንዲጠይቁ ዕድል ሰጣቸው። «ጥያቄ ያለው?» ብሎ ገና ቃላት ከአፉ ከማውጣቱ እነዚያ ታዳጊ ወጣቶች ለጥያቄ እጃቸውን እንደ ችቦ በመቀሰር ቅድሚያ ለማግኘት ተሸቀዳደሙ።
የመጀመሪያው ተማሪ፡- «ለምን ጦርነት ወዳድ ሆናችሁ?» በማለት የጥያቄ ቋጥኝ ወርውሮ ራሱን መቀመጫው ላይ ወረወረ። ሁለተኛው ተማሪ ቀጠለ፡- «እንዴት ርሃብን ለማሸነፍ አቃታችሁ?» እርሱ በፈገግታ ተጠያቂው ፊቱን አጨፍግጎ «የተወነጨፈበት የዳዊት ጠጠር» በብዙ ጎሊያዶች ፊት እንዳይዘርረው በመስጋት ውስጡን ብርድ ብርድ እንዳለው በጠያቂዎቹ ተከታታይ የጥያቄ ማዕበል ወረደበት። «ለምን አትሰለጥኑም?» የከፋው ጥያቄ ይህ ነበር። እነዚህ ለናሙናነት የተመረጡት ጥያቄዎች ለጊዜው ስለሚበቁ በተከታዩ ክስተት ማጠቃለል ይበጅ ይመስለናል።
ለካንስ እነዚያ ገና «ነፍስ ለማወቅ ድክ ድክ የሚሉት ታዳጊዎች» ጥያቄው ተመጥኖና ተቀነባብሮ የተሰጣቸው በመምህራኖቻቸው አማካይነት ነበር። «እንዳያልፉት የለም…» አለ በረኸኛው አዝማሪ፤ እንኳንም አለፈ እንጂ ያንን ቀን ይህ ጸሐፊ በፍጹም አይዘነጋውም። እንኳን ሊዘነጋው ቀርቶ ትዝ ባለው ቁጥር እነዚያ ትንታግ ነበልባል ልጆች በመራር ትዝታ ግዘፍ ነስተው ብቅ ጥልቅ እያሉ እንደሚያባንኑት የሚገልጸው በኑዛዜ ያህል ነው። መቼም «ምን መልስ ሰጠሃቸው?» ብሎ አንባቢው ሌላ ሙግት ውስጥ እንደማይገባ በማመን ወደ ሌላው ጉዳይ እንሸጋገር።
ዛሬ «ታናናሽም» ይሁኑ «ታላላቅ» የምናላቸው ሉዓላዊ አገራት ጓደኛቸውን ኢትዮጵያን የግመገማ ጥያቄ እንዲጠይቋት ቢፈቀድላቸው ከታዳጊዎቹ ሕፃናት የተለየ ምን ጥያቄ ሊጠይቁ ይችላሉ ብለን እንጠረጥራለን? የጸሐፊው መልስ ልዩነት አይኖረውም የሚል ነው። «መቼ ነው ከርሃብ ባርነት ነፃ የምትወጡት? ለምን በመወያየት አታምኑም? ለምን እርስ በእርስ ትጠፋፋላችሁ? ለምን ግትርነታችሁን አታስወግዱም? ለምን ጦራችሁን ወደ ማረሻ አትለውጡም? ለምን እርዳታ በቃንን አታውቁም?» ይህቺ ምስኪን ገመምተኛ አገር ሌላም ብዙ ብዙ ጥያቄዎችን ልትጠየቅ እንደምትችል ብንገምትም ቁስሎቿን ላለመደነቋቆል ስንል በዚሁ እናቁም።
እንደ ጸሐፊው እምነት ለሁሉም ጥያቄዎች ሊሰጥ የሚገባው አጠቃላይና «ማስተር» መልስ የሚከተለው ቢሆን ከክርክር ብቻም ሳይሆን ከራሳችን የሽንገላ ቅንብርም የሚታደገን ይመስላል። እውነት ነው! የችግሮቻችን ዋናው ምክንያት «እንደሚኖሩ ሆነው የሚሠሩ፤ እንደሚሞቱ ሆነው የሚኖሩ ሹማምንት ስላጣን፣ ህሊና አደር ፖለቲከኞች ስለጠፉብን፣ ታማኝ ነጋዴዎች እንደ ሸቀጦቻቸው ስለተወደዱብን፣ ሆደ ባሻ ምሁራን የሩቅ ተመልካቾች ስለሆኑብን፣ መከራ የተሸከመው ሕዝብ በተስፋ መቁረጥ ስለተሞላ፣ ሥራ ጠልነት ባህላችን ስለሆነ፣ ሁሉም አውቃለሁ እንጂ ልወቅ ለማለት ልቡን ስላደነደነ ወዘተ.» የሚሉትን ሃሳቦች ፈነጣጥቆና እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደሩ ከሁሉም የተሻለ መልስ ነው።
መቼም ራሳችንን ለማየት «ህሊናችንና ድርጊታችን የዐይንና የቅንድብን» ጉርብትና ቢያስታውሰንም ሰከን ብለን እንደ አገርና ባለ አገሮች አቋማችንን ብንፈትሽ እውነታው ከላይ ከተዘረዘሩት መልሶች ውጪ ይሆናል ተብሎ አይገመትም። እስከ መቼ በአፍቅሮተ ራስ እንደናወዝን እንኑር? እስከ መቼስ ከችግር ጋር ተላምደንና ተዳብለን ዕድሜያችንን እንፍጅ? እኮ እስከ መቼ ለመደጋገፍ ሳይሆን ለመጠፋፋት አመጽን በደቦ ስንፈጽም እንኖራለን። ዘመን ሲነጉድ እኛ ግን በዚያው በተቀመጥንበት ቦታ ማጎላጀጁ ምን ረባን፤ ምን ጠቀመን። እስከ መቼስ «ሃሳብ እሹሩሩን» እንደ ብሔራዊ መዝሙራችን እያንጎራጎርን ዕድሜያችንን እንገፋለን? በዚሁ በእኛው ዕድሜና በእኛው ጀንበር በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያልተፈጸመ የግፍ ዓይነት ይኖራል? እኛ ያልሞከርነው ወይንም ያልተሞካከርንበት የእኩይ ድርጊትስ ይኖር ይሆን?»
መታወቂያ ግብሩን ያዋሰን አያ ሰይጣን እርሱ ከተካነበት ክፋት በተሻለ ሁኔታ ስንለማመድ ቢያየን ምን ይለን ይሆን፡- «እናንት ብርቱ ባሪያዎቼ እነሆ ወደ አዘጋጀሁላችሁ ስፍራ ተሰብሰቡ» ሳይለን ይቀራል። ርሃብ ሰለቸን፣ ሞት መረረን፣ መጠፋፋት አንገሸገሸን፣ መዘላለፍ እጅ እጅ አለን፣ ተንኮልና ሴራ አጥወለወለን። ስለዚህ እንደ አገርና እንደ ዜጎች ጨክነን ልንፈወስበት ለምንችለው ለዚህ መርህ አጥብቀን እንገዛ፡- «እንደምንኖር ሆነን እንሥራ፤ እንደምንሞት ሆነን እንኑር።» ይሄው ነው። ሰላም ይሁን!!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2014