በሰው ልጅ የዘመናት ታሪክ ውስጥ ብዙ ኩነቶች ይሄዳሉ ይመጣሉ። ሁሉም ባይሆኑም በሰው ልጅ ቁጥጥር ስር ሆነው የሚያልፉ ናቸው። ሆኖም አንድነትና መተባበርን ባህል ላደረገ ማህበረሰብ የትኛውም ችግር ከአቅሙ በላይ አይሆንበትም። በዘመናት የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከሰው ልጅ አቅም በላይ ሆነው ያለፉ ችግሮች ሁሉ በአንድነትና በተባበረ ክንድ ስላልተመከቱ ነው። አንዳንድ ጊዜ በዚህ ረገድ የሚከሰቱ የመከራ ፍሬዎች ጣፋጭ ናቸው።
የጥፍጥናቸው ጣዕም ሀገርና ህዝብ ላይ ሲያርፍ ደግሞ ትርጉማቸው ሌላ ይሆናል። ልክ እንደ እኛና እንደተጓዝንበት የህዳሴ ተስፋችን ሁሉም እንግልቶች ፍሬ ከማፍራታቸው በፊት መራራ ናቸው። ድካም ፍሬ ሲያፈራ፣ እንግልት ዋጋ ሲያወጣ መከራችንን እንደ አለፈ ውሀ እንረሳዋለን። የዓባይ መንገድም እንዲሁ ነው፤ ትናንት በሃሳብ ተጠንስሶ ዛሬ ለብርሃን እስኪበቃ ያለው ውጣ ውረድ ግዙፍ ነው፤ ሆኖም አባይ በትንሳኤው ያንን ሁሉ አስረሳን።
የህዝቦች አንድነት ማጣት ትንሹን ችግር ትልቅ የማድረግ ሀይል አለው። ከዛሬ መቶ ሀያ አምስት አመት በፊት ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ ወራሪውን ጣሊያንን ድል መተው ስማቸውን በወርቅ ቀለም የጻፉበት ታሪክ ነበር። በሌሎችም በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያስመዘገብናቸው ድሎች የአንድነታችን ውጤቶች ሆነው ያለፉ ናቸው። ልክ እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም የአሁኑ ትውልድ የጥንቱን የአባቶቹን የአልሸነፍ ባይነት ባህል በአባይ ላይ ደግሞታል።
ታላላቅ ነገሮች ሁሉ በእችላለው መንፈስ የተሰሩ እንደመሆናቸው፤ እችላለው ብሎ ለተነሳ ሀገርና ህዝብ የማይቻል ነገር የለም። ታላቁ የህዳሴ ግድብም በኢትዮጵያዊያን የእንችላለን መንፈስ ተጀምሮ በእንችላለን መንፈስ እንሆ ለብርሀን በቃ፤ይህ ታሪካዊ የህዝቦች የጋራ ቅርስ ድካማችንን ወደ እልልታ የቀየረ የኢትዮጵያውያን የተስፋ ምልክት ነው።
አባይ ለዚህኛው ትውልድ የተጋድሎ፣ የመስዋዕት የአርበኝነት ጥግ ነው። ስለ አባይ እያሰቡ ኖረው እያሰቡ የሞቱ አባቶች ነበሩን። ስለ አባይ እያሰቡ ተወልደው፣ እያሰቡ ያረጁ ብዙ ናቸው። ዛሬ ግን በዚህኛው ትውልድ አባይ ከወንዝነት ወደ ግድብነት ከግድብነትም ወደ ሀይል ማመንጫነት ተሸጋገረ። አባይ ወንዝ ብቻ አይደለም፤ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ታሪካችን፣ አርማችን መታወቂያችንም ጭምር ነው። በላባችን ወዝ የቆመ፣ በአጥንትና በደማችን የገነባነው የማንነታችን ወጋግራ ነው።
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በብዙ ልዩነት ውስጥ አንድነትን ያስተማረን፣ በብዙ መለያየት መካከል መተሳሰብን ያሳየን፣ ፍቅርን መተሳሰብን የሰጠን በትውልድ መካከል የተሰመረ በኩራችን ነው። የህዳሴ ግድባችንን በተመለከተ እንዲህ ነው የሚሰማኝ። ይሄ የአብሮነት ስሜት እስከመጨረሻው አብሮን እንደሚዘልቅ ጥርጥር የለኝም። የመጨረሻውን ሳቅ እስክንስቅ ድረስ ከአባይ ጋር ወደ ፊት እንሄዳለን።
ምክንያቱም በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ አባይ በዝቶና ተትረፍርፎ አለ። በብዙ ድህነት፣ በብዙ ችግር ውስጥ ሆነን የተሻለ ነገን ለማየት ስንል ቦንድ የገዛን እልፎች ነን። በትምህርት ቤት፣ በስራ ቦታ፣ በሰፈር፣ በቀበሌ ለአባይ ግድብ ድምጻችንን ያሰማን ሞልተናል። መጪው ትውልድ በኩራትና በሞገስ ሲያስታውሳችሁ ይኖራል።
በእናተ ነፍስ ውስጥ የአባቶቻችሁ ነፍስ እንደሚያርፉ ስነግራችሁ ከልቤ ነው። በእናንተ ዛሬ ውስጥ ተስፋ ያጡ በርካታ ትናንቶች ፍሬ እንዳፈሩ ስነግራችሁ በታላቅ እውነት ነው። አባይ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ የተሳለ ህብረ ብሄራዊ አሻራ ነው። በደስታና በሀዘን ያጌጡ፣ በውጣ ውረድ የተፈተኑ አስራ አንድ አመታትን ከአባይ ጋር አሳልፈናል። ከአፋችን ላይ ሳይጠፋ፣ ከልባችን ሳይሰወር እንሆ በብርሀን ሊያጥለቀልቀን አንድ ብሎ ከአንድ ጀመረ፤ ቀሪ ተርባይኖቹ ወደ ስራ ሲገቡ ሙሉ ብርሃን ይሆነናል።
አባይ ለእኛ ተስፋ ብቻ ሳይሆን መለያየታችንን ሊሽር በመካከላችን ለእርቅ የገባ ሽማግሌ ነው የሚመስለኝ። በብዙ ነገር ተለያይተን በአባይ ጉዳይ ግን አንድ ነን። ተኮራርፈን እንኳን ስለ አባይ አንድ ላይ የምንቆም ህዝቦች ነን። አባይ አስታራቂያችን ነው። አባይ ሽማግሌአችን ነው። አባይ የአንድነታችን ሙሴ ነው። ለዚህም ነው አባይ ከወንዝነት ባለፈ ብዙ ነገራችን ነው ያልኩት። ዛሬ ብቻ አይደለም ከአባይ ጋር ብዙ ነገዎች አሉን። ብዙ ቀናት፣ ብዙ ዘላለማት፣ እልፍ አዕላፍ አመቶች ከአባይ ጋር ይጠብቁናል።
እርሱ በአባቶቻችን ልብ ውስጥ የነበረ ባለ ብዙ ውበት፣ ባለ ብዙ ቁንጅና ባለቤት ነው። ከዚያኛው ትውልድ የተረከብነው የአባቶቻችን የአደራ ሰነድ ነው። ውሀ ብቻ አይደለም ከእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ የሚፈስ የቁጭት እንባ ነው። በእያንዳንዳችን ነፍስ ውስጥ ያለ የህላዊ ደም እንዲህም ነው። አባይ እያንዳንዳችንን ነው። የእያንዳንዳችን መልክ፣ የእያንዳንዳችን ውጣ ውረድ ማስታወሻ ነው። በአባይ ውስጥ እኛ አለን። አባይ ሲነሳ እኛ ሁላችንም እንነሳለን። አባይ የመቶ ሀያ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ወዘና ነው። የሰማኒያ ብሄር ብሄረሰብ ቀለም ነው። ባህላችን፣ ታሪካችን ነው።
ለዘመናት ከደጃችን እየፈለቀ የእትብቱ ማደሪያ የሆነውን ቀዬ ግን ውሀ እያስጠማ ባዕድ ሀገራትን ሲያረሰርስ የኖረበት ዘመን አልፎ፤ ዛሬ ላይ በአስራ አንድ ዓመት ጉዞው ዛሬ ላይ እንደተመኘነው ብርሀንን መስጠት ጀምሯል። እኛ ም፡-
“አባይ ተሞሸረ..እኛም እልል አልን…
በተባበረ ከንድ ትንሳኤውን አየን..”
በማለት ነገን እያሰብን የህልማችን ፍጻሜ የሆነውን የግድቡን መጠናቀቅ እያሰብን በተስፋ ቆመናል። ከሳቅን ከእንግዲህ ነው…ከበረታን…ከደመቅን ከእንግዲህ ነው። ከጊዮን ማዶ ሊስቁ ያሉ በርካታ ፊቶች ይታዩኛል። ከጥቁር ህዝቦች አብራክ ስር ተስፋ ያወገገው ጸዳል ይታየኛል። ሀዘን የረሳቸው…የሚፍነከነኩ ጸዐዳ ልቦች ፈገግ ብለው ይታዩኛል። ዘለዓለማዊ ፈገግታ…። አባይ እናመሰግናለን..አንተ ኩሩ ህዝብ ክብር ይግባህ።
በአንድ ልብ፣ በአንድ ሀሳብ ስለ አባይ እያዜምን አስር አመታትን ተጉዘናል። በነዚህ አስር አመታት ውስጥ ብዙ ነገር አይተናል..ስለ አባይ ተገፍተናል፣ ጫና ደርሶብናል። የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ ከተስፋችን ሊያደናቅፉን የሚሞክሩ ነበሩ። በአንድ ላይ ሆነን ሁሉን አልፈነዋል። ከሌለን ላይ እየሰጠን፣ ካለን ላይ እየቀነስን፣ ከድሀ እና መቀነት በተሰጠ አምስትና አስር ሳንቲም እንሆ ለአይናችን ከናፈቀን ማለዳ ላይ ደረስን።
ከእንግዲህም በአባይ ጉዳይ ላይ የሚያቆመን የለም። አባይ ብሄራዊ መዝሙራችን ነው። ተኝተን በተነሳን ቁጥር፣ በኖርናት በእያንዳንዷ ንጋት ልክ የምናስበው የመኖራችን ዋስትና ነው። ጥንት አባቶቻችን በአድዋ ላይ እንዳስመዘገቡት ድል ሁሉ እኛም የዚህ ዘመን ትውልዶች አባይን ገድበን መጪውን ትውልድ ከድህነት የማውጣት ጀብደኝነት በእያንዳንዳችን ውስጥ አለ። በዚህ አንቆምም እንደ አባይ ያሉ ሌሎች ግድቦችንም በመገደብ ለሀገራችንና ለህዝባችን ውለታ የምንውልበት ጊዜ ላይ ነን። የድካማችንን ፍሬ የምንበላበት ብሩህ ጊዜ እየመጣ ነው። ሰላም!
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2014