ከብልጽግና 1ኛ ጉባኤ በኋላ በተዘጋጁ ሕዝባዊ መድረኮች ያለልዩነት ዳር እስከ ዳር ጮክ ብለው የተደመጡ እሮሮዎች ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ናቸው ። የደህንነትና የጸጥታ ጉዳይ ፤ ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ፤ በመንግስት መዋቅር የተንሰራፋው ብልሹ አሰራርና የገነገነ ሙስና ፤ የመልካም አስተዳደር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ፣ የፍትሐዊነትና የእኩልነት ጥያቄዎች ይገኙበታል ።
እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች ፣ እሮሮዎችና ብሶቶች የተፈጠሩት በጊዜ መፍትሔ ስላላገኙ ነው ። አዎ ! ገና በጥያቄ ፣ በጥቆማና አስተያየት ደረጃ እያሉ በጊዜ ቢፈቱ ኑሮ ዛሬ ላይ ወደ ዋይታና ሙሾነት ባልተቀየሩ። ለዚህ ነው የአገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ሰሞኑን በተሰናዳ የትውውቅ መድረክ ላይ ፤… የሕዝብ ለቅሶና ዋይታ መርገብ ብቻ ሳይሆን መቆም አለበት ።…ያሉት ።
በአንዳንድ መድረኮች ከእሮሮነትም አልፈው ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ያዘሉ ነበሩ ። በነገራችን ላይ ቀያይ ያበሩም ናቸው ። ይህ ችግሮች ለአመታት ተባብሰው ተባብሰው አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ገሀድ ያወጣል ። ለመፍትሔ የሚደረጉ ጥረቶች ይሄን የሚመጥኑ ካልሆኑ ደግሞ ከዚህ በላይ ተባብሰው መጀመሪያ የደህንነትና የጸጥታ ችግር በማስከተል የህልውና ስጋት እንደሚሆኑ አያጠያይቅም ።
እነዚህ እሮሮዎቹ የአንድ ሰሞን ብሶትና ምሬት የወለዳቸው አይደሉም ። ቢያንስ ከአጼው ፣ ከደርግና ከኢህአዴግ ሲንከባለሉ የመጡ ናቸው ። ሆኖም ባለዕዳዎች ይህ ትውልድ ፣ ይቺ ሀገርና ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ናቸው ። ዕዳው እንደ የእሳት አሎሎ አንዱ ለአንዱ ሲወረውር ሲወረውር እዚህ ላይ ደርሷል ። ከዚህ በኋላ ግን በእኛ ማለፍ አለበት ። ለነገው ትውልድ፣ ለነገዋ ኢትዮጵያና ለነገው ፓርቲ ልንወረውረው አይገባም ። በእኛ ማለፍና ቀን መውጣት አለበት ። ይህ ግን ስለተመኘን ብቻ አይሆንም ። ከዘመቻ ፣ እሳት ከማጥፋትና ከሆይ ሆይ አሰራር ወጥተን ፤ በተሳካ የቀዶ ጥገና ትክክለኝነት(precision) ልክ በጽኑ ሕሙማን ክፍሎች የሚገኙ ሕመሞቻችንን ማከም አለብን ።
ስለሆነም የፊዚክስ ሊቁ አልበርት አነስታይን ” ችግሩን በፈጠረው አስተሳሰብ ፤ ችግሩን መፍታት አይቻልም ። ” እንዳለው ፤ በታላቁ መፅሐፍ የማቲዎስ ወንጌል 9 ÷ 17 ላይም እንዲህ እንደተባለው ፤ ” በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም ። ቢደረግ ግን፣ አቁማዳው ይፈነዳል፣ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል ። ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፣ ሁለቱም ይጠባበቃሉ ።”። በሀገራችን የተካሄደው ለውጥ እንጂ አብዮት ስላልሆነ ፤ ዛሬ ተባብሰው እሮሮና ብሶት የሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎችን በጊዜ ያልመለሰው መዋቅርም ሆነ ተቋም ከሞላ ጎዳል ዛሬም በቦታው እንዳለ ነው ።
ስለሆነም ለሕዝብ እሮሮዎች የዳረጉ መዋቅሮችንና ተቋማትን ተሸክሞ የማያዳግም መፍትሔ መስጠት አይቻልምና በጥንቃቄ እንደገና ሊፈተሹና ዳግም ሊወለዱ ይገባል ። ማሻሻያዎች በሙላት እየተፈጸሙና እየተመሩ መሆኑን እርግጠኛ መሆን ያሻል ። ለውጡን ተከትሎ የተደረጉ ዙሪያ መለስ ማሻሻያዎች በሀገሪቱ ላይ ተደቅነው የነበሩ የህልውና አደጋዎች እንዲያባሩ ቢያደርጉም ዘላቂና ወጥ መፍትሔ ግን ማምጣት አልቻሉም ። ከችግሮቻችን ስፋትና ጥልቀት አንጻር በአንድ ጀምበር የሚፈቱ ባይሆንም በሚፈለገው ፍጥነትና ጥራት ግን እየሄዱ አይደለም ።
ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ ቢደረግም የዋጋ ግሽበቱን፣ የኑሮ ውድነቱንና ስራ አጥነቱን ከግስጋሴ ሲገታ አልተመለከትንም ። መከላከያን ጨምሮ በአጠቃላይ የጸጥታ መዋቅሩ ማሻሻያ ያደረግን ቢሆንም የዜጎች በሰላም ወጥቶ የመግባትም ሆነ የደህንነትና የጸጥታ ችግሮች ገና ሙሉ በሙሉ አልተቀረፉም ። በሀገሪቱ የተደቀነው የህልውና አደጋም ተቀለበሰ እንጂ ሙሉ በሙሉ አልተወገደም ።
ዴሞክራሲን ፣ ፍትሕን ፣ እኩልነትን ፣ መልካም አስተዳደርን የሚያሰፍኑ የአሰራርና የአደረጃጀት ማሻሻያዎች ቢደረጉም ዛሬም ሕዝብን ያማረሩ ችግሮች እንዳሉ ናቸው ። ሰከን ብሎ ወደራስ ማየት የሚጠይቅ ፈታኝ ጊዜ ላይ ነን ። ውሳኔዎቻችንና እርምጃዎቻችን ይሄን የሚመጥኑ መሆን አለባቸው ። ጣት መቀሳሰሩን ፣ መወነጃጀሉን ፣ ችግር መገፋፋቱን ትቶ በቅንነትና በቁርጠኝነት በአንድነትና በቅንጀት መስራትን ግድ ይላል ።
ሌላው በመድረኮቹ ጮክ ብለው የተደመጡ እሮሮዎች የአንድ ብሔር ወይም ሀይማኖት አልያም ፖለቲካ ፓርቲ እሮሮ ሳይሆኑ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ በአንድነት ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል ። ገዢው ፓርቲም ሆነ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት በበለጠ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት መዋቅሩንና ተቋማቱን ሊፈትሽ ይገባል ። ገዢው ፓርቲ ከስህተት አዙሪት ወጥቶ በምሳሌ በመምራት ሕዝብን ከጎኑ ማሰለፍ ይጠበቅበታል ።
በሕዝባዊ መድረኮች ካስተዋልነውና ልብ ካልነው የብልጽግና አመራሮች ከብሔር አጥር ለመውጣት ተንጠልጥለው ተመልክተናል ። በሒደት ሙሉ በሙሉ ይወጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን ። የማንነትና የብሔር ፖለቲካ ጥደው እያንተከተኩ አይደለም ብልጽግና አንካሳውን ልማታዊ መንግስት እውን ማድረግ እንደማይቻል ባለፉት 27 አረጋግጠናል ።
የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሀመድ እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ፤ የአፋር ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ኤሌማ አቡበከር በሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ፤ የቢኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እና የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ በአሶሳ፤ የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል በባህርዳር ፤ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ፤ ወዘተረፈ አወያይነት የተካሄዱ ውይይቶች የአማራው ችግር የኦሮሞውም የስልጢውም፤ የአፋር ችግር የሱማሌውም ፤ የሱማሌው ችግር የአፋሩም ፤ የቤኒሻንጉል ችግር የትግራዋዩም ፤ የኦሮሞው ችግር የአማራውም ፤ የሀረሪው ችግር የአማራውም ፤ የጋምቤላው ችግር የደቡብ ምዕራቡም ፤ የሲዳማው ችግር የደቡቡም ፤ መሆናቸውን ያስገነዘቡ ነበሩ ። የአንዱ ኢትዮጵያዊ ፈተና የሁሉም መሆናቸውን የሚያሳዩ ተምሳሌታዊ መድረኮች ነበሩ ማለት ይቻላል ። ለታይታና ለይምሰል የተተወኑ ድራማዎች እንዳልሆኑ ስለምናም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እናበረታታለን ።
ሁለት አስር አመታትን ያስቆጠረው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት የዜጋውን ኑሮ በብርቱ እየፈተነው ፤ ከኢኮኖሚያዊ ችግርነት ወደ ለየለት ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስነት እንዳይባባስ እያሰጋ ይገኛል ። በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ ኢኮኖሚው ለቀደሙት 27 አመታት የአንድ ቡድንና የጭፍራው መጠቀሚያ በመሆኑ በተከሰተው ኢፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ አሻጥር፣ ጦርነትና አለመረጋጋት እንዲሁም የራሽያ ዩክሬን ጦርነት በአናቱ ተከልሶበት ኑሮው አልቀመስ ብሏል ።
የውጭ ምንዛሬ እጥረት ፤ የተራዘመ የግብይት ሰንሰለት ፤ ከገበሬ ማሳና ከጉልት እስከ ጅምላ አከፋፋይ የተሰገሰገ ደላላ ፤ በግብይት ሰንሰለቱ የተንሰራፋው ስርዓት አልበኝነት ፤ ዋጋን በአድማ መወሰን ፤ ምርትን በመደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠር ፤ የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም፤ የኑሮ ውድነቱን ለመከላከል በመንግስት ዘንድ ወጥ የሆነ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አለመኖር ፤ የሎጅስቲክስ አገልግሎቱ ቀልጣፋ አለመሆን ፤ ወደብ አልባ በመሆናችን በየአመቱ ለወደብ ኪራይ ቢሊዮኖችን የምናወጣ እና ስለመብቱ የሚቆረቆርና የሚጠይቅ ሸማች አለመፈጠሩ እንደ ዚምባብዌና ቬኒዞላ ባይሆንም በሰዓታት ልዩነት ለሚተኮስ የዋጋ ግሽበት እንዲዳረግ መግፍኤ ሆኗል።
በየፍጆታ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ግሽበት በሌሎች ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ግሽበትንና የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ይገኛል ። በዚህ ሳቢያ በመዋቅራዊና በተቋማዊ ችግር የተነሳ ጽኑ ታማሚ ሆኖ ለኖረው ኢኮኖሚ ሌላ ራስ ምታት ሆኖበታል። የለውጡ መንግስት ባለፉት ሶስት አመታት የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አኃዝ ለማውረድ ያደረገው ጥረት ውጤት አለማስገኘቱን አምኖ የአዲሱ መንግስት ቀዳሚ ተግባርም ይሄን ማስተካከል እንደሆነ ቃል ቢገባም በሚፈለገው ፍጥነትና ቅንጅት እየሄደ አይደለም ።
እንደ አማርኛው ሪፖርተር ሀተታ ከሆነ፤ በየወሩ የሚስተዋልበት የዋጋ ግሽበት እየተንከባለለ መጥቶ በወርኃ የካቲት በተለይም በምግብ ነክ ኢንዴክስ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል ። በአገሪቱ የተመረጡ 119 የገበያ ቦታዎችን መሠረት አድርጎ በቀረበው የየካቲት ወር 2014 ዓ.ም የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር በ41ነጥብ9 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ። በተለይም በእህሎች ዋጋ ላይ በአብዛኛው ጭማሪ እንደታየ የማዕከላዊ ስታስቲክስ አገልግሎት ሪፖርት ያመለክታል።
የዋጋ ንረቱን ለመቋቋም የሚያስችል ወርኃዊም ሆነ ዕለታዊ የገቢ ጭማሪ ላላገኘው ብዙኃኑ የኅብረተሰብ ክፍል በየወሩ እየተጋፈጠው ያለው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለምላሹ ካልተጋበት ፣ በቀጣይ የሚመጣው ቀውስ ከፍተኛ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢኮኖሚና የፖሊሲ አማካሪ ባለሙያዎች አስረድተዋል ። የኢኮኖሚ ጉዳዮች ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ ፣ ምንም እንኳን በሚመለከተው የመንግሥት ተቋም በየወሩ ይፋ የሚደረገው የዋጋ ግሽበት አኃዝ ሁሉንም የሚያስማማ ባይሆንም ፣ የተለያዩ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጫናዎችን እያስተናገደ ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እስካሁንም የዋጋ ንረቱ በ30 እና 40 በመቶ መቆየቱ የሚያስገርም ነው ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል።
ከሁሉም በፊት መታየት ከሚገባቸው ነገሮች ውስጥ የዋጋ ንረት እንዴት ነው እየተሰላ የሚገኘው የሚለው መሠረታዊ ነገር ነው ያሉት አቶ ዋሲሁን ፣ 300 እና ከዚያ በላይ ሸቀጦች አንድ ላይ ተወስደው ጤፍም ሆነ ድንብላል፣ ስንዴ ሆነ ዱባ በአንድ ምድብ ተጨፍልቀው ሲሰሉ የሚገኘው ቁጥር መሬት ላይ ካለው እውነተኛ የዋጋ ንረት ጋር የማይስተካከል ዝቅተኛ ቁጥር ሊያስገኝ ይችላል ብለዋል።
ነገር ግን ስንዴ ፣ ጤፍ ፣ ገብስ ፣ ዘይት፣ ስኳርና መሰል አስፈላጊ አሥር የሚደርሱ ግብዓቶች ተሰልተው የዋጋ ንረቱ ቢሠራ በአማካይ የሚገኘው ቁጥር 100 ፐርሰንት ሊገባ ይችላል ሲሉ አስረድተዋል። በሌሎች አገሮች የዋጋ ንረትን ከቦታ ቦታ ለየብቻው እንደሚቀርብ የገለጹት የኢኮኖሚ ባለሙያው ፣ አዲስ አበባና ምንጃር ላይ አንድ ነዋሪ ለቤት ኪራይ እኩል ወጪ እንደማያወጣ ቢታወቅም ወርኃዊ የስታትስቲክስ ሪፖርት ሲቀርብ ግን መረጃው በመላው ኢትዮጵያ ተብሎ ሲቀርብ ይስተዋላል ብለዋል ።
በአጠቃላይ የዋጋ ንረትን በተመለከተ በእያንዳንዱ ክልል በየራሱ ተሠርቶለት የአገሪቱንም አማካይ ማስቀመጥ ፣ በቦታዎቹ ሊስተካከል የሚገባውን ጉዳይ ለማስተካከል ያስችላል ያሉት የኢኮኖሚ ተንታኙ ፣ ቁጥሮች ላይ ያለው ውዝግብ መታረቅ አለበት ብለዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (State of Emeregency) የሚያስፈልገበት ደረጃ ላይ ይገኛል ፤ የሚሉት አቶ ዋሲሁን ፣ ይህም የኢኮኖሚ መረጋጋት ከሌለ ፖለቲካዊ መረጋጋት ስለማይመጣ ነው ሲሉ ያክላሉ ። ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን አጥቶ መታገስና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶችን አጥቶ መታገስ እኩል አይደለም። በመሆኑም መንግሥት በዚህ ወቅት ከኢኮኖሚው የቀደመ አጀንዳ ሊኖረው አይችልም ብለዋል ።
የኢኮኖሚ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሁኑኑ !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2014 ዓ.ም