እንደምን አላችሁልኝ ውድ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አንባቢዎች!! እንደተለመደው በዛሬው መጣጥፌ አንድ ሀሳብ ልሰንዝርና እናንተም በነፃው ሀሳብ አምድ ላይ ተወያዩበት:: ልክ እንደ ተፈጥሮ ሁሉ ሕዝቦችም ከተፈጥሮኖ ከታሪክ የሚመንጭ አንድነትና ልዩነት አላቸው:: ሕዝቦች ሁሉ በሕዝብነታቸው አንድ ናቸው::
በእርግጥ አንድ ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ በተፈጥሮውና በቆዳ ቀለሙ በታሪክ ሂደት ውስጥ በተፈጠረው ዳር ድንበር፣ ባሕል፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ ሥነ ልቦናዊ አመለካከት ኢኮኖሚያዊ እድገት ቢለያዩም ሕዝብን ሕዝብ የሚያሰኙ የወል ባሕሪያቶችን ይጋራሉ:: ስለዚህ ሕዝቦች በአንድነታቸው ውስጥ ልዩነት በልዩነታቸው ውስጥ አንድነት አላቸው:: በመሆኑም በዛሬው ዓለም ትልቁ የሕዝቦች መታወቂያ አገር ነው:: መታወቂያቸው ከሁሉም በላይ ስለሆነ ከራሳቸው ይልቅ፣ ብዙዎቹ አገራቸውን ይወዳሉ::
በአንድ በኩል አንድነት በሌላ በኩል ደግሞ ልዩነት መኖሩ ይታወቃል:: እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የምንኖርባት አፍሪቃ ከምድር ጠቅላላ ስፋት ስድስት በመቶውን፤ ከመሬቷ ደግሞ ወደ ሃያ ተኩል በመቶውን የምትሸፍን በመሆኑ፣ በገጸ ምድር ስፋትና በሕዝብ ቁጥር ከእስያ ቀጥላ ሁለተኛ መደብን የያዘች አህጉር ነች። በአሰፋፈራችን ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ የምንገኝ የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤት አገር ያለን በመሆናችን ነፃነታችንን ጠብቀን የኖርን ሕዝቦች፤ አገራችንም ኢትዮጵያ ናት::
በሕዝብ ብዛትም ከአፍሪካ ሁለተኛ ስንሆን፣ በቆዳ ስፋት ከሃምሳ አራት አገሮች አስረኛ ደረጃ ላይ ነን:: በዲፕሎማሲያዊ ስልጣኔያችን ለመላው ዓለም በተጨባጭ ካሳየን፣ ከመቶ ዓመታት በላይ የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳለን ታሪካችን ያረጋገጥን ብቸኛ አፍሪቃዊት አገር ነን።
አብዛኞዎቹ የአፍሪቃ አገሮች ቢሆኑም በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረጅም ዕድሜ ከስድሣ ዓመት በላይ አያልፍም። ኢትዮጵያ ግን ከኢጣሊያና ከፈረንሣይ ከአሜሪካ (USA) እና ከእንግሊዝ ከሩሲያና ከጀርመንን ከመሳሰሉ (ከስድስት አገራት) ጋር ከመቶ ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደነበራት ታሪክ ምስክር ነው::
ዛሬ ላይ ግን ክብሯን በማይመጥን ደረጃ የፀረ ሽብር የክፉ ቀን አጋሯ አሜሪካ ውለታዋን እረስታ አውሮፓንና ሸሪኮቿን አስተባብራ በውስጥ ጉዳያችንና በሉአላዊነታን ላይ ዘመቻ ትከፍትብናለች ብሎ ማንም ያሰበም ሆነ የጠረጠረ አልነበረም:: ግን እውነት ስለ መሆኑ በታሪክ ፊት ቆመን እንመሰክራለን::
አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሽንጧን ገትራ አውሮፓን በ«ተባበሩኝ» እየተማፀነች የከፈተችብን የሚዲያ ዘመቻ ሳይበቃ የHR 6600 ረቂቅ ሕግ በምክር ቤቷ ለማፅደቅ እየተንጎራደች በማስፈራራት ላይ ትገኛለች::
በሌላ በኩል ለስልጣንና ለገንዘብ ሲሉ የገዛ ሐገራቸውንና ሕዝባቸውን አሳልፈው በሸጡ ሐገር ከሐዲ ባንዳዎች አማካኝነት አሜሪካ የHR 6600 እረቂቅ ሕግ እንድታፀድቅ ድጋፍ እየሰጡ ይገኛሉ:፡ በተለይም የሕወሓት ጁንታ ቡድንና ሸኔ የአንበሳውን ድርሻ ሲወስዱ ሆድ አደር ምሁራኖችና ፅንፈኛ ብሔርተኞች ታሪክ ይቅር የማይለው የአገር ክሕደት በነጩ ቤተመንግሥት ፊት ለፊት ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ቆመው የኢትዮጵያን መንግሥት ሲያወግዙ ማየት እጅግ ያሳፍራል።
እንደ አገር የምናስብ ከሆነ ኢትዮጵያ ይህን ጉዳይ ችላ ብላ በቀላሉ የምታልፈው አይመስለኝም:: ኮስተር ብላ በሳል ምሁራኖቻችን ሰብስባ የHR 6600 ትክክለኛ የአሜሪካንን ክስ እና የውስጥና የውጭ ፖሊሲዋን የተከፋይ ሎቢስቶችን ሴራ ጭምር ብትንትን አድርጋ አስጠንታ ዘላቂ መፍትሔ በማግኘት ለዓለሙ ኅብረተሰብ ማጋለጥ ይኖርባታል::
እስከዚያው እንደ ዜጋ የሚመስለንን ሐሳብ ለሕዝባችን ማንሸራሸርና ግንዛቤ ማስጨበጥ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነትና ግዴታም ጭምር በመሆኑ ያለንን ገንቢ ሀሳብ በነፃው አምድ ላይ እናዋጣ:: በዚህም «ለመሆኑ አሜሪካናም ሆነች ሸሪኮቿ የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የእኛ የእርስ በእርስ አለመስማማት ልባቸው ውልቅ እስከሚል አሳስቧቸው ነው?» የሚለውን ጥያቄ አብረን እንመልሰው።
እንደእኔ ግንዛቤ ከሆነ ግን መልሱ አይደለም ነው። ላለፉት ረጅም ዘመን በታሪክ እንዳየነው ብዙዎቹ ጦርነቶች የተካሔዱት የነዳጅ ዘይት ባስነሳው ውዝግብ ሳቢያ ነበር:: የእነዚህ ጦርነቶች ምክንያትም፣ ታሪክ ሆኖ ቢያልፍም፤ አሁን ዓለም ያለችበትን ሁኔታ አዳዲስ ጥናቶች እንደሚያስረዱን በሚቀጥለው መቶ አመታት አብዛኛዎቹ ጦርነቶች የሚካሂዱት የውሀ ፖለቲካ በሚያስነሳው ውዝግብ ሊሆን እንደሚችል የመስኩ ባለሞያዎች ሰሚ አጡ እንጂ መወትወት ከጀመሩ ውለው አድረዋል::
ውሀ እንደ ሰብዓዊ መብት የመኖርና ያለመኖር ሕልውና ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት ቢናገሩም፤ ከሳሃራ በታች ያሉት አገሮች የአንድ ሰው አማካይ የነብስ ወከፍ የውሀ አጠቃቀም ከ10 እስከ 20 ሌትር ብቻ ሲሆን፣ በአውሮፓ የሚኖር አንድ ሰው 200 ሌትር ውሀ በነፍስ ወከፍ እንደሚጠቀምም በጥናት አረጋግጠዋል:: በዚህ የተነሳ የወደፊቱ ዓለም በተፈጥሮ ሀብታችን ላይ አንድ ነገር እያሰላሰለ መሆኑን ብዙ ምልክቶች እያየን ነው።
ኢትዮጵያ አባይን ጨምሮ ሰባት ታላላቅ ወንዝ ያላት የውሀ ሀብታም አገር አንዷ ስትሆን፤ 85 በመቶ የሚሆን በግብርና የሚተዳደር ሕዝቧ በወንዞቹ አማካኝነት የእርሻ መሬቶቿን አልምታ እራሱን ለመመገብ እንዳትችል ግን በምስቅልቅል የክልል ፖለቲካና የትርክት ታሪክ እየታመስን ገበሬው በመስኖ የበቀለ እሸት ቆርጦ እንዳይበላ በምግብ እራሱን እንዳይችል በዘር ፖለቲካ ሰንሰለት አስረን በኑሮ ውድነት ስንቀጣው ኃያላን አገሮች ደግሞ በምግብ እራሳችንን እንዳንችል በወንዞቻችን እንዳንጠቀም በሰብዓዊ መብት ሰበብ አስገዳጅ ማዕቀቦችን እያረቀቁ ያስፈራሩናል::
ይሄን እንደ ዜጋ ስናስበው ያሳዝናል። በእርግጥ በእኛም በኩል ያሉብንን ስህተቶች መንግሥት በቶሎ ማረም ባለመቻሉ ሕዝባችን በኑሮ ውድነት እየደረሰበት ካለበት መከራ በተጨማሪ የመንግሥትን ባለስልጣን ሙሰኛና ሌቦችን መቋቋም እንዳቃተው ብሶቱን አደባባይ ላይ አውጥቶ ዘርግፎታል። መንግሥትም ድርጊቱ በሾሟቸው ባለስልጣኖች እንደሚፈፀም አምኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ፊት ለፊት በፓርላማቸው ላይ ፍረዱኝ ሲሉ ተደ ምጠዋል::
ነገር ግን እስካሁን የሚወሰዱት እርምጃዎች ከቁጣ ባለፈ ፀረ ሙስና ኮሚሽኑ በአንድም ባለስልጣን በራፍ ድርሽ አላለም:: የክልሎችን ሳናነሳ የአዲስ አበባ ከተማን ብቻ ለናሙና ብንወስድ እንኳን በአፍሪካ ከሚገኙና ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ካለባቸው 15 ከተሞች መካከል በቀዳሚነት መቀመጧን ቢዝነስ ኢንሳይደር አፍሪካ የተባለ ድረገጽ በወጣው መረጃ ነግሮናል። በዚህም ድረገጹ ባወጣው አሀዛዊ የኑሮ ውድነት መለኪያ መሠረት አዲስ አበባ በ58 ነጥብ 92 በአንደኛ ደረጃ ተቀምጣለች። ሕዝቡም ይሄን ይናገራል። ለዚህም እንደ ሕዝብ የገጠመንን ውጫውም ሆነ ውስጣዊ ፈተና ለመሻገር፤ እንደ መንግሥት ሕዝብ ላይ የተጫነውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ለማንሳት ተናብበው መንቀሳቀስ ተገቢ መሆኑን ያምናል።
ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
አዲስ ዘመን መጋቢት 23 ቀን 2014 ዓ.ም