የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር እና ተዋቂ ጸሃፊ የነበረው ቤንጃሚን ዲዝራኤሊ እንደተናገረው አለም የምትገዛው ተራ ሰው እንደሚያስብው የስልጣን ወንበር በተቆናጠጡት ሰዎች አይደለም። አለም የምትገዛ ባለስልጣናትን በሚቆጣጠሩት እና የአገዛዝ ፍልስፍና ወይም ርዕዮተ አለሙን በሚቀርጹ ከትዕይንቱ በስተጀርባ ባሉ ሰዎች ነው ።ይህን አባባል ስመለከት አይተ ጭሬ ልድፋው መሰረትኩት ያለውን መንግስት ያስታውሰኛል።
በህዝብ ላይ በፈጸመው ግፍ ከስልጣኑ የተባራረው የአይተ ጭሬ ልድፋው ከመጋረጃ ጀርባ በሚያሽከረክሩት የጥፋት ሹፌሮቹ ተገፋፍቶ ከሃገራችን ህግና አሰራር ውጭ መንግስት መሰረትኩ አለ። መሰረትኩት ያለው መንግስትም በእነሚስተር ቶማስ እርዳታ ካልተደረገለት እና በእነ ደባልቄ አሸብር እንዲሁም በእነሱሌማን አወል ፈቃድ እርዳታ ማመላለሻ ኮሊደር ካልተፈቀደለት እንደ መንግስት ይቅርና እንደ ህዝብ መኖር አይችልም ። ያለጨው በርበሬ ያለሞፈር በሬ ማለት ይህ አይደል?
የአይተ ጭሬ ልድፋው መንግስት የኢኮኖሚ አማራጮችን ከመመልከት ይልቅ እርዳታን በመጠባባቅ መንግስት ነኝ የሚል የአለማችን ብቸኛው መንግስት ነው። ጂኒየስ ቡክ ኦፍ ሪኮርድስ እስከ ዛሬ እንዴት እንዳልመዘገበው ይገርመኛል ።በነገራችን ላይ የአይተ ጭሬ ልድፋው መንግስት በእርዳታ ላይ የተንጠለጠለ የአለማችን ብቸኛው መንግስት ሆኖ ሳለ ጂኒየስ ቡክ ኦፍ ሪኮርድስ አለመመዝገቡ ጂኒየስ ቡክን በራሱ በጂኒስ ቡክ ላይ ሊያስያመዘገበው ይገባዋል ባይ ነኝ ።በአስቸኳይ ጂኒየስ ቡክ ኦፍ ሪኮርድስ የማይመዘግበው ከሆነ የውጭ እርዳታ አሰባስብንም ቢሆን ጂኒየስ ቡክ ኦፍ ርኮርደስን ጨምሮ የሚመዘግብ ሌላ ተቋም በአገራችን ማቋቋማችን የማይቀር ነው።
በጠራራ ጸሃይ ህንጻ በመሸጥ የምትታወቀው ዮዲት እንዲህ ሆኖ መንግስት መሆን ከተቻለ እኔንም ከስራዬ አባሩኝ እና ለእኔም እርዳታ እንዲሰጠኝ ተመቻችቶልኝ ዘመድ አዝማዶቼን አሰባስቤ መንግስት ልመሰርት ማለቷን ሰማን። ለአምባገነኖች እና የግብዞች መልካም ተሞክሮ ማለት ይህ አይደል!
በአዲስ አበባ እና በሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች የጠፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና የተሰወሩ ዩኒቨርሲቲ ህንጻዎች የት እንደገቡ ሳይታወቁ የውሃ ሽታ የሆኑት ብቻቸውን ሳይሆን አይተ ጭሬ ልድፋው እና ግብረ አበሮቹን ለአመታት በቂ ሁኔታ ከሚያስተዳደር ገንዘብ ፣ ሃሽሽ፣ ውስኪ እና ከመሳሰሉት ነገሮች ጋር ይመስለኛል።ቢሆን ነው እንጂ የአይተ ጭሬ ልድፍው እና ግብረ አበሮቻቸው ረሃብ ተከሰተበት ተብሎ ሰዎች በግፍ ከሚሰደዱበት አካባቢ እነሱ ውስኪ ከቁርጥ እያማረጡ መኮምኮማቸው።
የሆነው ሆኖ ውስኪን በህንጻ፤ ተራራን ከእህል ጋር ቀላቅለው የሰረቁት ግብዞች ለራሳቸው «ወዲ እከሌ ወዲ እከሌ» እያሉ ቅጽል ስም እየሰጡ በሰረቁት ንብረት ማፈር ሲገባቸው የሰፈራቸውን ሰዎች እኛ ሰፈር ውስጥ መኖር ካልቻልክ አደጋ ተጋርጦብሃል ሲሉ ሰበኩ ። ለጦርነትም መለመሉ ። መከራ የተፈረደበት ህዝብም እውነት መስሎት ወዲ እከሌ በህይወት የማይኖር ከሆነ የእኛ ሰፈር ህዝብ እንደህዝብ መኖር አይችልም ሲል ለራሱ ነገረ ።
ፈረስ ጥሎ ይደነግጣል፤ በቅሎ ጥሎ ይረግጣል እንዲሉ አይተ ጭሬ ልድፋው እና ግብረ አበሮቹ ለበርካታ አመታት ከስንት እና ስንት ክፍቶቻቸው እና ሃጢያታቸው ጋር ተሸክሞ በፈለጉት የአለም ሀገራት አንቀባሮ ያኖረን ህዝብ ሊያመሰግኑት ሲገባቸው ከመሃል አገር ከጠፋው ኮንዶሚኒየም እና የዩኒቨርሲቲ ህንጻ ጋር የሰረቁትን ውስኪ ከሃሺሽ ጋር ቀላቅለው እየማጉ ጥጋባቸው አላስችል ብሎአቸው የራስ አሉላን ልጅ ከአውሬ የሚጠብቃትን እና የሚንከባከባትን ባለቤቷን ጥላ እንደምትረግጠው በቅሎ ሆኑበት ።ክፉኛም ጎዱት።
ይበጃል ያሉት ኩል አይን አጠፋ እንዲሉ፤ ለራስ አሉላ ልጅ ይበጃል የተባለው አይተ ጭሬ ልድፋው የሰፈሩን ሰው በረሃብ አለንጋ እያስገረፈው ይገኛል ። ጦርነቱን አቁማችሁ ህዝቡን በርሃብ አለንጋ ከመገረፍ የማታድኑት ለምንድን ነው? ተብሎ የተጠየቀው አይተ ጭሬ ልዳፈው «ህዝቡን በርሃብ አለንጋ አታስገርፉት የምትሉ ከእኛ ውጭ ህዝቡ መቼ ጠግቦ ያውቃል? የሚኖረው በሴፍትኔት አይድል እንዴ? ሲሉ ይሞግታሉ። ታዲያ በሴፍትኔት የሚኖርን ህዝብ ራሱን በምግብ እንዲችል በማድረግ ፋንታ ስለምን ለጦርነት ታሰልፉታላችሁ? ተብለው ሲጠየቁ ዋይ ! ህዝቡን ለጦርነት አሰልፈን አገርን ካላበጣበጥን እንደፈለግን የምንሆንበት ገንዘብ ማን ይሰጠናል? ሲል ጥያቄን በጥያቄ መመለስ ይቀናቸዋል። ይበጃል ያሉት ኩል አይን አጠፋ የሚባለው እንደዚህ አይነት አጋጣሚ አይደል ።
አይተ ጭሬ ልድፋው በእርዳታ ላይ የተመሰረተ መንግስት መመስረቱ ብቻ አይደለም የሚገርመው፤ እርዳታ ሊገባባቸው የሚችሉ ቀዳዳዎችን ሁሉ በራሱ መድፍ እና ታንክ ጥርቅም አድርጎ መዝጋቱ ነው ። እርዳታ የሚገባባቸውን መንገዶች በራሱ መድፍ እና ታንክ ጠርቅሞ እየዘጋ ስልምን እርዳታ የሚያመላለሱ ካሚዮሎች (ተሽከርካሪዎች) እንዳይገቡ ይከላከላል ብሎ እሪታውን ያቀልጠዋል ።
ገድሎ በአለቃዬ፤ ከሰሰ በጠበቃዬ እንዲሉ፤ አይተ ጭሬ ልዳፈው ራሱ በራሱ ችግር ፈጥሮ አገርን ካወከ በኋላ ምግብ እና እርዳታ አልደርሰኝ ብሎ ከመጋረጃ ጀርባ እንደፈለጉ ለሚያዝዙት ምዕራባዊያን ድረሱልኝ ይላል። የሚገርመው ምንም ምን የአልሚ ምግብ አይነቶችን ለሰፈሩ መቅረብ እንዳለበት እንኳን የሚመርጠው አይተ ጭሬ ልድፋው እንጂ ረጂ ድርጅቶች አለመሆናቸው ነው ።ይህን ተከትሎ የአለም የዕርዳታ ድርጅቶች ምን አይነት አልሚ ምግብ በብዛት ይቅረብላችሁ ብለው በጠየቁ ጊዜ አይተ ጭሬ ልዳፋው ምን ቢል ጥሩ ነው ዋይ! ለእኛ የምንፈልገው አልሚ ምግብ በአንደኛ ደረጃ ሀሺሽ ፣ ውስኪ እና ጫት ነው ።በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የጦር መሳሪያ ነው። የእኛ ሰፈር ሰው እንደሆነ እርሃቡን ለትግል በርሃ ከገባን ጊዜ ጀምሮ አላምደነዋል ።ስለዚህ ምንም ምግብ አያስፈለገውም ። ማሽላ እና በቆሎ ከሆነ በሚቀጥለው የመኸር ወቅት ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ከአመረቱት ከአጎራባች ክልልች በምናውቀው ዘዴ እንሰርቃለን! ሃሳብ አይግባችሁ ብሎ አረፈው ።
አይተ ጭሬ ከበፊትም ጀምሮ አለምን የሚያስገርም ንግግር በማድረግ ይታወቃል ።ለምሳሌ «ደብል ዲጂት» የኢኮኖሚ እድገት ፣ በአፍሪካ በእድገት ጎዳና ላይ ያለች ብቸኛ አገር ወዘተ የሚል ጉራ መታወቂያው ነው ።አሁንም ይህ አመሉ አለቅ ብሎት በአንድ በኩል በአስቸኳይ እርዳታ ያስፈልገኛል ።እርዳታው ባስቸኳይ ካልደረሰ እኔ እና የሰፈር ሰዎች ልናልቅ እያለ ለአገኘው ሁሉ ይጮሃል። በሌላ በኩል ራሽያ በዩክሬን ላይ እያደረገች ያለውን ጦርነት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት አለማውገዙ ስላበሳጨኝ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ልጀምር እችላለሁ ሲል ተደመጠ ።እማማ ሁሉ አገርሽ ትለብሰው የላት ትከናነበው አማራት ያሉት እንደዚህ አይነቱን አይደል።
እርዳታን ተማምኖ መንግስት እመሰርታለሁ ብሎ ማሰብ በሀገር ላይ የሚያስከትለውን የከፋ ጉዳት ተመልክተናል። ሃገራችንን ለማበጣበጥ የሚፈልጉ ሃይሎችም ይሄን እንዴት ሲጠቀሙበት እንደነበር ተመልክተናል። የውጪውስ መቼም የውጭ ነው ፤ እኔን የገረመኝ በአገራችን ተወልደው ያደጉ በአገሪቱ አሉ የሚባል ስልጣን የተሰጣቸው ግለሰቦች በአገሪቱ ሰላም እንዳይኖር ሲጥሩ ስመለከት ነው ።
በቀደም ዕለት የማማ ሁሉን ላንች ልጅ አቶ መርዳሳ ኢብሳ የተባለው ባለስልጣን ከአይተ ጭሬ ልድፋው ካስነሳው ጦርነት ጋር ተያይዞ በአገራችን የተፈጠረውን ያለመረጋጋት ቀዳዳ ተጠቅሞ አገር ለማስበጥበጥ በማሰብ ያለፈው ወር የጊዎርጊስ ዕለት ከአራት ኪሎ ቤተ መንግስት እስከ ምኒሊክ አደባባይ ባለው አስፋልት ድንጋይ በመደርደር ከፍተኛ ጩኸት እና ግጭት በመፍጠር የአገሪቱን ሰለማ ለማወክ ሲሯሯጥ ነበር። ይህን ተከትሎ የፌደራል ፖሊስ ጽጥታውን ለማስጠብቅ አስቦ ሁከት በተፈጠበት አካባቢ ተገኘ ። ፖሊስም ለምን የአገሪቱን ሰላም ትበጠብጣላችሁ? ብሎ መንገዱን በድንጋይ የዘጉ ሰዎችን ማወያያት ጀመረ። ወዲያውኑ ለምን መንገድ እንደዘጉ ለመናገር በርካታ ሰዎች እጃቸውን እንደ ጭራሮ አንጨርፍፈው አወጡ። አቤት ፍጥነት ! ፖሊስም በየተራ እንዲናገሩ እድል ሰጠ።
አይን ነሽ፤ ጥርስ ነሽ ሳይል ሁከት ፈጣሪዎችን በቆመጥ ሲዠልጥ የሚታወቀው ፌዴራል ፖሊስ ያለወትሮው ሁከት የፈጠሩትን አካላት እያወያየ እንዳለ ያዩት እማማ አረጋሽ ሰዎችን ሰብስቦ እያነገረ ያለው የፌዴራል እንባ ጠባቂ ወይስ የፌዴራል ፖሊስ ሲሉ ባለቤታቸውን አቶ ደሰለኝን ጠየቁ ።አቶ ደሳለኝም የጊዎርጊስ፤ የጊወርጊስ የፈዴራል ፖሊስ ላለመደባደብ መሃላ መግባቱን አልሰማሽም ሲሉ ለባለቤታቸው መለሱ።
መንገድ ከዘጉት አንዱ ለምን መንገድ እንደዘጋ ለፖሊስ ምክንያቱን ሲናገር ምን ቢል ጥሩ ነው ! እውነት ለመናገር በአጼ ኃይለ ስላሴ ላይ የተፈጸመው መፈንቀለ መንግስት በታሪክ ሳነብ እጅግ በጣም ይገርመኛል ። የአሁኑ ትውልድ ደግሞ መፈንቀለ መንግስት እንዴት እንደሚካሄድ ተሞክሮ የለውም። ስለሆነም መፈንቅለ መንግስት እንዴት ማድረግ እንደሚቻል በተግባር የተደገፈ ትምህርት መስጠት ስለሚያስፈልገው በአጼ ሃይለስላሴ ላይ የተፈጸመው መፈንቀለ መንግስት ሲካሄድ ትእይንቱ እንደገና ይደገምልን ብሎ አረፈው ።ፖሊስም የአመጸኛውን ሰውዬ ወደ ኦነግ ሸኔ እንዲቀላቀል ምክር ቢጤ ሊሰጠው አስቦ ኦነግ ሸኔን ከተቀላቀለ በቀጣይ ህግን ለማስከበር በሚኖረው ግዳጅ ላይ ስራ ያበዛብኛል ብሎ አሰበ ። ወደ ቂሊንጦ እንዳይወስደውም ታራሚዎችን እንደሚበጠብጥበት አሰበ ።በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ የተጋባው ፖሊስ የውጭ ወታደር ልቀጥር እፈልጋለሁ ላለችው ዩክሬን መልምሎ ወደ ዩክሬን እንደላከው ሰማን።
ፖሊስ የአጼ ኃይለ ስላሴ መፈንቀለ መንግስት ትዕይንት ይደገምልን ባለው ልጅ ግብዝነት ተገርሞ ሳይጨርስ ሌላ ጎፈሬውን ያበጠረ ልጅ ከመቀመጫው ተነስቶ እኔ ለዚህ አመጽ የገፋፋኝ ጉዳይ የፓርላማው ሰዓት ስንት አመት ሙሉ ሳይንቀሳቀስ ስለተመለከትኩ በዚያ ተሰምቶኝ ነው አለ ።ፖሊሱም ቀበል አድርጎ ምን ለማለት ፈልገህ ነው ? ሲል ጎፈሬውን ልጅ ጠየቀው። ጎፈሬውም ልጅ አምና ምርጫ ስናደርግ የፓርላማው ሰዓት እንደሚንቀሳቀስ ተስፋ አድርጌ ነበር። ነገር ግን ይሄው ዘንድሮም ሰዓቱ እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ ባለበት እንደተቀመጠ ነው። ምንም ሲንቀሳቀስ አይታም። ስንት መንገድ እና አጥር በመዲናችን ብሎም በአገራችን ሲታደስ ለምን ሰዓቱ አይታደስም? ሲል ፖሊሱም ቅኔው ወዲያወኑ ገብቶት እውነትህን ነው የፓርላማው ሰዓት እንዲንቀሳቀስ ቢደረግ ኖሮማ የፌዴራል ፖሊስም ይህን ያህል ስራ አይበዛበትም ነበር ሲል ለጠያቂው ምላሽ ሰጠ። የሚገርመው በአንድ ሰልፍ በመርህ እና በአላማ ደረጃ ፍጹም አራምባ እና ቆቦ የሆኑ አመጸኞች የተሳተፉበት እና አብዛኛው አመጸኛ ደግሞ ምን እና ለምን እንዳመጸ አለማወቁ ነው።
ፈረስ ቢጠፋው ኮርቻውን ገልጦ አየ እንዲሉ እኛ ኢትዮጵያዊያን ችግራችን ምን እንደሆነ እያወቅን ለችግራችን ሁነኛ መፍትሄ ከመለግ ይልቅ በሰፈር በቡድን በቡድን እየተከፋፈለን መነታረክ ይቀናናል ።የእኛ ችግር በልቶ ማደር ነው። የእኛ ችግር ለብሶ ማደር ነው ።የእኛ ችግር ድህነት ነው። እንዲሉ መጀመሪያ ይሄንን ችግር እንደፖለቲከኛ ድህነትን ተጋፍጠን አንገብጋቢ የሆነውን እና መቅደም ያለበትን ችግር መፍታት ሲያቅተን የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ፣ መብት ወዘተ እያልን ስልጣናቸውን ማራዘም ይቀናናል ።ድንቄም ፖለቲካኛ ! ሰውን አባልታችሁ አስጨርሳችሁ ማንን ልትመሩ ነው ?
«ፈጅቶ ከሚያጠግበኝ እስኪበርድ ይራበኝ» እንዲሉ አሁን ላይ ለእኛ ኢትዮጵያዊያን የቸገረን የብሔር ብሔረሰቦች መብት ፣ እኩልነት ወዘተ እየተባለ ፖለቲከኞች ለጥቅማቸው የሚፈተፍቱት ነገር አይደለም። እኛ የቸገረን አይተ ጭሬ ልድፋው እና መሰሎቹ ለአመታት ሲከዝኑብን የኖሩት ድህነት ነው ።ስለዚህ ሁሉም ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ስለእውነት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስብ ከሆነ ድህነትን የምናሸንፍበትን መንገድ ያሳየን።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን መጋቢት 22 /2014